የሰውን ልብ ማሸነፍና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን!

እንዲህ በቀላሉ የሰውን ቀልብ መግዛትና ልቡን ማሸነፍ አይቻልም:: ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነው የሰውን ቀልብ አሸንፎ በጎረቤት፣ በሰፈር በማኅበረሰብና በሀገር ብሎም በአሕጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው መሆንም ቀላል አይደለም::

የሰውን ልብ አሸንፎ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው መሆን ትልቅ ጥረትና ልፋት ይጠይቃል:: ልፋትና ጥረቱ ደግሞ በጥበብና በብልሃት ሊታገዝ ይገባል:: ያኔ ነው ሰዎች በየራሳቸው መክሊት በሀገራቸው፣ በአሕጉራቸው ከፍ ሲል ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን የሚችሉት::

ሰዎች ከሰዎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት የሰውን ልብ ማሸነፍና መማረክ ትልቅ ችሎታ ይጠይቃል:: ይህን ችሎታ ሁሉም ሰው ይፈልገዋል:: ደስ የሚለው እንደማንኛውም ችሎታ የሰውን ልብ ማሸነፍ በሂደት ሊለመድና ሊዳብር የሚችል መሆኑ ነው:: የሀገር መሪዎች የሕዝብን ቀልብ፣ ልብና አዕምሮ ለማሸነፍና ለማቅለጥ ብዙ አይነት ጥበቦችን ይጠቀማሉ:: እኛም ሀገር ባንመራ ቤተሰብ እንመራለን:: ትዳር እንመራለን:: ድርጅት እንመራለን:: የምንሠራው ሥራ አይጠፋም:: ከብዙ ሰዎች ጋር እንገናኛለን:: ስለዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አለብን::

ታዲያ እንዴት ነው የሰዎችን ጫና ተቋቁመን፣ ልባቸውን አሸንፈን ለምንፈልገው ነገርና ለስኬታችን የምንጠቀምባቸው? በሥራችን፣ በቢዝነሳችን፣ በፍቅር ግንኙነታችን፣ በማንኛውም ጉዳይ እንዴት ነው ተፅዕኖ ፈጣሪ የምንሆነው? እነሆ መንገዶቹ፡-

1ኛ.ራስን መሆን

ሰዎች ራሱን የሆነን ሰው ይወዳሉ:: ልበ ሙሉ ሆኖ በራሱ መንገድ የሚጓዝና በራሱ መንገድ የሚወስንን ሰው መደገፍ ይፈልጋሉ:: ‹‹እርሱ እኮ ልበ ሙሉ ነው›› ይላሉ:: አብረው መሥራት ይመኛሉ:: ከእንዲህ አይነት ሰው ጋር መሆን ይመኛሉ:: መጀመሪያ አካባቢ ራስህ መሆን ስትጀምር፤ ከሰዎች መነጠል ስትጀምር ሰዎች ላይወዱህ ይችላሉ:: ላይቀበሉህ ይችላሉ:: ሊተቹህ ይችላሉ:: ነገር ግን በራስህ መንገድ ሄደህ የሆነ ለውጥ ማምጣት ስትጀምር የተቹህ ሰዎች አድናቂዎችህ ይሆናሉ:: አንተን መስማት ይጀምራሉ::

ራስን መሆን ማለት ከምናደንቃቸውና ከምንወዳቸው ሰዎች አለመኮረጅ ማለት አይደለም:: ከእነርሱ ጥሩ ጥሩውን መኮረጅ አለብን:: አንተም ከምታደንቀው ሰው የሆነ ነገር መውሰድ አለብህ:: ቻይናውያን ‹‹ስለመንገዱ ማወቅ ከፈለክ የሚመለሱትን ጠይቃቸው›› ይላሉ:: ካንተ የቀደሙና የተሻሉ ሰዎችን ትኮርጃለህ:: የምትኮርጀው ግን በራስህ መንገድ መሆን አለበት:: ማንም ሰው መቶ በመቶ ፍፁም አይሆንም:: ሁላችንም የብዙ ሰው ተፅዕኖ አለብን::

ያለተፅዕኖ ሕይወትህ ላይ የሆነ ቦታ መድረስ አትችልም:: ነገር ግን ተፅዕኖዎች፤ ከሰዎች የምትኮርጃቸው ነገሮች ራስህን ሊያሳጡህ አይገባም:: በራስህ መንገድ፣ በራስህ ማንነትና በራስህ ቅርፅ ኮርጅ:: ራስህን ሳታጣ ከሰዎች ብዙ ነገር ስረቅ:: በዛ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ራስህን ሁን:: ያኔ ነው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን የምትጀምረው::

2ኛ. ራስህ ላይ ሥራ

የሰዎችን ልብ መማረክና ማሸነፍ ከፈለክ መጀመሪያ ከውስጣዊ እስከ ውጫዊ መገለጫህና ማንነትህ ድረስ ራስህ ላይ መሥራት ይጠበቅብሃል:: በጣም የምናደንቃቸው፣ የምናከብራቸው፣ ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸውና የኔ ጀግና የምንላቸው ሰዎች ዝርክርክ አይደሉም:: ከአለባበሳቸው፣ አነጋገራቸው፣ ከአስተሳሰባቸው፣ ከሁኔታቸው ጀምሮ የሆነ የሚማርክ ነገር አላቸው:: ራሳቸው ላይ ሠርተዋል:: እንደውም ‹‹ምነው እነሱን በሆንኩ›› እንላለን::

እነዚህ ሰዎች ልክ እንደሸክላ ሠሪ ራሳቸው ላይ በየቀኑ ይጠበባሉ:: ራሳቸው ላይ በጣም ይሠራሉ:: ከኋላቸው እዚህ ያደረሳቸው የማይቆም ጥረት አለ:: በየቀኑ ለአዕምሯቸው ያነባሉ:: የሚጠቅማቸውን ይሰማሉ፤ ያያሉ:: ለጤናቸውና ለሰውነታቸው ስፖርት ይሠራሉ:: አመጋገባቸው የተስተካከለ ነው:: ጊዜያቸውን በአግባቡ ይጠቀማሉ:: ተራ ቦታ አይገኙም::

አየህ! አሁን ለደረሱበት የሚደነቅ ማንነት ትናንት የተለፋ ልፋት አለ:: እርሱን ነው መኮረጅ ያለብህ:: ራስህ ላይ መሥራት ማለት ከውስጣዊ እስከውጫዊ ማንነትህ ድረስ ለማደግ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ማድረግ ማለት ነው:: እነዚህ ሰዎች ያ ሁሉ ጥቃቅን ጥረታቸው ተጠራቅሞ ከፍ ማለት ሲጀምሩ ሰው ዓይን ውስጥ ይገባሉ:: ሰዎች በጣም ያደንቋቸዋል:: ስለነርሱ ማውራት ብቻ አዋቂ ያስብላል:: ጥረታቸው በጣም ትልቅ ስለሆነ እዛ ቦታ ላይ ሲደርሱ በእድል ሁሉ የደረሱ ይመስላል::

‹‹እርሱ እኮ እድለኛ ነው›› ይባላሉ:: ግን ከጀርባ በጣም ያላቡት ላብና የለፉት ልፋት አለ:: አንተም ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ከፈለክ፤ የሰዎችን ልብ መማረክ ከፈለክ ራስህ ላይ መሥራት አለብህ:: ሰዎች እንዲያከብሩህ ከፈለክ ራስህን አክብርና ወጥረህ ሥራ፤ ተቀየር:: ያኔ ነው የሰውን ልብ የሚያሸንፍ ማንነት የምትገነባው::

3ኛ. ስለምትሰጠው ብቻ አስብ

የሰዎችን ልብ የምታሸንፈው ሰጪ በመሆን ነው:: አየህ! የምትቀበለውን ነገር እያሰብክ፣ ስለምታገኘው ጥቅም እያሰብክ የምትሰጥ ከሆነ ጥቅመኛነትህ ጎልቶ ይወጣል:: በፍቅር ግንኙነት እንኳን ሴቶች የሆነ ጥቅም፤ የሆነ ነገር ፈልገህ እንደቀረብካቸው ሲያውቁ ካንተ መሸሽ ይጀምራሉ:: ስልክህን ማንሳት ያቆማሉ:: ዝም ይሉሃል:: ለምን? የሆነ ነገር ለማግኘት አስብህ እንደቀረብካቸው አውቀዋል::

በፍቅር ግንኙነት ብቻ አይደለም፤ በቢዝነስ፣ በሥራና በማንኛውም ግንኙነት ውስጥ ሰዎች ለሆነ ጥቅም እንደቀረብካቸው ካወቁ ይርቁሃል:: ቦታ አይሰጡህም::

ስለዚህ እንተ የምትሰጠው ለመቀበል ብለህ አይደለም:: መልካም ስለሆንክ ነው:: ሰጪ ስለሆንክ ነው:: በርግጥ የዚህ ዘመን ፍልስፍና ሰጥቶ መቀበል ሊሆን ቢችልም አንተ ግን ስለመስጠት አስብ:: እንደገበሬ አስብ:: ገበሬ ዘር ሲዘራ ገና የሰኔ ዝናብ ዘንቦ፣ ኮትኩቶ፣ አብቅሎ፣ አሳድጎ፣ አረም አርሞ የሆነ ቀን እንደሚያጭድ ያውቀዋል:: ስለዚህ ይታገሳል:: የሚያተኩረው መስጠቱ ላይ ነው:: መዝራቱና መኮትኮቱ ላይ ነው እንጂ እንደው መቼ ነው የማጭደው ብሎ አይጨነቅም:: ለዚህ ነው አንተም ሰጪ መሆን ያለብህ::

ሰዎች ካመኑህና ከወደዱህ እኮ ሁሉ ነገራቸውን አሳልፈው ይሰጡሃል:: ላንተ ልባቸውንና ሁሉ ነገራቸውን ያስገዛሉ:: የሰውን ልብ ልታሸንፍ የምትችለው ሰጪ በመሆን ነው:: ስለመቀበል እያሰላህ አትንቀሳቀስ:: ስለመቀበል እያሰብክ የምትፈፅመው ድርጊት ጥቅመኛነትህን አጉልቶ ያወጣዋል:: ይህ ሲባል ግን ራስህ ጎድተህ ራስህን ጥቀም ማለት አይደለም:: ግን ደግሞ የሰዎችን ልብ የሚያሽንፍ ሰው እነርሱ የሚፈልጉትን ነገር ያለስስት አውጥቶ ይሰጣል:: አየህ! በጣም ትልልቅ የቢዝነስ ሰዎች እውቀታቸውን፣ ችሎታቸውን፣ ጥበባቸውን አሟጠው የሆነ ሕዝብ ችግር ለመፍታት ጊዜያቸውን ይሰጣሉ:: ስለዚህ ትልቅ ችግር ይፈታሉ፤ ትልቅ ሀብት ይገነባሉ::

4ኛ. በእነርሱ መማረክ አለብህ

አንተ ባለህ ነገር ሰዎች እንዲቀበሉህ ማድረግ ከባድ ነው:: ቢቀበሉህ ራሱ ጊዜያዊ ነው:: ስለዚህ አንተ ባለህ ነገር ሳይሆን እነርሱ ባላቸው ነገር አንተ ከተማረክ፣ ከወደድካቸው፣ ከቀረብካቸው ነው ላንተ ትልቅ ቦታ የሚሰጡህ:: አንተ መቅደም አለብህ:: አየህ! ችግራቸውንና ሃሳባቸውን ከተረዳህላቸው ይረዱሃል፤ ላንተ ቦታ ይሰጡሃል:: አንተን ማክበር ይጀምራሉ::

ለምሳሌ አሰሪህ አብዝቶ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው? ፍቅረኛህ ትልቁ ጭንቀቷ ምንድን ነው? ደምበኞችህ በጣም የሚፈልጉት ነገር ምንድን ነው? ይህን ለመረዳትና ለማወቅ ሞክር:: ከቻልክ መፍትሔ አዘጋጅለት:: መፍትሔውን ባታውቀው ራሱ ችግራቸውን ስለተረዳህላቸው ብቻ ትልቅ ቦታ ይሰጡሃል:: ፖለቲከኞች እንዴት ነው በሕዝባቸው ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩት? በጣም ትኩስ የሚባለውን አጀንዳ፤ ትልቁን የማኅበረሰብ ሃሳብ ያነሱና ችግርህ ችግሬ ነው ይላሉ:: ሕዝብ ችግሩ ስለታወቀለት፤ ቁስሉ ስለተነካለት ልቡን አሳልፎ ይሰጣል:: ያምናቸዋል:: ይመርጣቸዋል፤ ይሾማቸዋል::

ስለዚህ እውነተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሰውን ልብ የሚማርኩት የዛን ሰው ችግር በመረዳት ነው እንጂ ስለራሳቸው አብዝተው በማውራትና ‹‹እኔ እኮ እንደዚህ አለኝ›› በማለት አይደለም:: ከዚህ አንፃር ሰዎች ላይ ፍላጎት ማሳየት መቻል አለብህ:: አጥብቀህ እነርሱን መፈለግ አለብህ:: ሰዎች ጠቃሚነታቸውን የማሳየት ትልቅ ፍላጎት አላቸው:: ጠቃሚ እንደሆኑ የሚያውቁት ደግሞ ችግራቸውን እንደምትረዳላቸው፣ ሃሳባቸውን እንደምታውቅላቸው ካወቁ ነው:: ስለዚህ ከቻልክ ልትቀርባቸው፤ ልባቸውን ልታሸንፍ ስለምትፈልጋቸው ሰዎች በሚገባ መረጃ ሰብስብ:: በደምብ እውቃቸው:: ያ ነው መማረክ ማለት ነው::

5ኛ. ሁሉም እንዲወድህ አትጠብቅ

አንድ ወጣት ልጅ ነው:: ትንሽ ሞኝነት ያጠቃዋል:: አባቱን ሄደና ‹‹አባዬ ሁሉም ሰው እኮ ይወደኛል›› አላቸው:: አባት መለሱ ‹‹ድሮስ ጅል የሆነን ሰው ማን የማይወደው ሰው አለ›› አሉት:: አየህ! በሕይወትህ ውስጥ ሞኝ ካልሆንክ፣ በሰዎች ፍላጎት የምትነዳ ካልሆንክ ሁሉም እኩል ሊወድህ አይችልም:: ይህን ማወቅ አለብህ:: ሁሉንም ስለማስደሰት መጨነቅ የለብህም:: የውድቀት መንገድ ሁሉንም ለማስደሰት መጣር ነው:: ግን ሰዎች እንዲያከብሩህ አንተ ራስህን አክብረው:: ሰዎች ባይወዱህ ራሱ ሊያከብሩህ ይገባል::

ያኔ ሲያከብሩህ ባይወዱህ ራሱ ሃሳብህን ያደምጡታል:: ጥሩ ነገር ስለምታወራ ያደምጡሃል:: ይቀበሉሃል:: አንዳንዴ አትወዳቸውም ግን ተፅዕኖ የሚፈጥሩብህ ሰዎች አሉ:: ትሰማቸዋለህ:: ባትወዳቸውም ሃሳባቸውን ታዳምጣለህ:: እነዚህ ሰዎች ሁሉም ሰው እንደማይወዳቸው ያውቃሉ:: ይረዳሉ:: ሁሉን ማስደሰት እንደማይችሉ ያውቁታል:: ነገር ግን ራሳቸው ላይ ይሠራሉ:: አንተም ራስህ ላይ ከሠራህ ሰዎች ባይወዱህ ራሱ ያከብሩሃል፤ ያደምጡሃል:: ስለዚህ ሁሉን ለማስደሰት አትጣር::

6ኛ. አክብሮትህን በተግባር አሳይ

ሰዎች የሚያከብራቸው ሰው ልባቸውን ያሸንፋል:: ኦፓራ ዊንፍሬይ እና ኤለን ሊጀነረስ በሕዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ናቸው:: የዚህ ትልቁ ምክንያት ፕሮግራማቸው፤ ሥራቸው ራሱ በተግባር ተመልካችን ያከበረ ነው:: ከሚጋብዙት እንግዳ ጀምሮ፣ አቀራረባቸው፣ የሚወራው ወሬ፣ የሚያነሱት ሃሳብ ተመልካችን በጣም ስለሚያከብር የሰዎችን ልብ በቀላሉ ያሸንፋሉ::

አንተም በፍቅር ግንኙነትህ፣ በሥራህ፣ በቢዝነስ፣ ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነትና በሌሎችም ጉዳዮች ከምትገናኛቸው ሰዎች ጋር አክብሮትህን በተግባር አሳያቸው:: ከእነርሱ ጋር ስታወራ ስልክህን ልታጠፋ ትችላለህ:: ስማቸውን በደምብ ጠንቅቀህ አውቀህ እየጠራህ ልታወራቸው ትችላለህ:: በጣም ልታደምጣቸው፤ ትኩረት ሰጥተህ ልትሰማቸውና አይንህን ሌላ ቦታ የማታደርግ ከሆነ የሆነ ክብር የሰጠሃቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል:: ሰዎች ደግሞ የሚያከብራቸውን ያከብራሉ:: ስለዚህ በቀላሉ እነርሱ ላይ ተፅዕኖ ትፈጥራለህ:: ለምን? ልባቸውን አሸንፈሃላ:: አክብረሃቸዋል፤ ትልቅ ቦታ ሰጥተሃቸዋል:: ስለዚህ ክብርን ለሰዎች በተግባር አሳያቸው:: ተፅዕኖ ትፈጥራለህ::

7ኛ. ብዙ አትናገር

ተፅዕኖ ፈጣሪ ማለት ብዙ ተናግሮ የሚያሳምን፣ ከባድ ምላስ ያለው ይመስለናል:: ግን ብዙ ስትናገር ብዙ ስህተት ነው የምትሠራው:: ረጅም ወሬ ካወራህ የሆነ ሰዓት ማሰብ ታቆማለህ:: ምክንያታዊ መሆን ታቆምና ስሜታዊ ትሆናለህ:: ድንገት ስትነቃ ‹‹ምን ሆኜ ነው የምቀባጥረው?›› ልትል ሁሉ ትችላለህ:: ስለዚህ ግልፅና አጠር ባለ መንገድ ሃሳብህን ማስረዳት መቻል አለብህ:: ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እንደዛ ናቸው::

ለቢዝነስ ወይ ለሥራህ በጣም ረዘም አድርገህ የምታወራ ከሆነ እነዛ ሰዎች ልታጭበረብራቸው ያሰብክ ሁሉ ሊመስላቸው ይችላል:: እውነተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ቃላቶቻቸውን ዝም ብለው አይበትኑም:: ለትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ሰዓት ነው የሚናገሩት:: አብዛኛውን ጊዜያቸውን በማድመጥ፤ ፍሬ ሃሳቡን ወደ ውስጣቸው በማስገባት ነው የሚያጠፉት:: ብዙ ስትናገር የቃላቶችህ ኃይል ራሱ ይቀንሳል::

ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች በጣም ቁጥብ ናቸው:: ተናጋሪ በበዛበት ዓለም፤ ብዙ አድማጭ የሚፈልግ በበዛበት ዓለም ላይ አዳማጭ መሆን ማለት በጣም ተፅዕኖ ፈጣሪ ያደርግሃል:: የሰዎችን ልብ እንድታሸንፍ ያደርግሃል:: እንደውም አንተ ብዙ ስለማትናገር በደምብ አስበህ የተናገርክ እለት ያንተ ሃሳብ እንደትልቅ አጀንዳ ይያዝልሃል:: ስለዚህ ብዙ አትናገር:: ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ቁጥብ ናቸውና!!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You