የዘራፊዎቹ መጨረሻ

ጥርት ባለው የጥር ሰማይ ላይ ጨረቃ ባትኖርም ከዋክብት ግን ሞልተውታል። ሌሊቱን ለማድመቅ ሽሚያ ላይ ያሉ የሚመስሉት ከዋክብት ለመሬት እንዳላቸው ቅርበት ደመቅና ደብዘዝ ብለው ይታያሉ። ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 9፡30 ሰዓት ሲሆን በቀጠሮ ሰአታቸው የተገናኙት የተደራጀው የዘረፋ ቡድን አባላት ቤቱን ሰብረው ለመግባት አላንገራገሩም ነበር።

ከገና በዓል አስቀድሞ የዘረፋ እቅዳቸውን ያቀዱት የዘረፋ ቡድኑ አባላት ቤት ውስጥ የእንግዶች መብዛት እንቅፋት ሆኖባቸው አስራ አራት ቀናት ሙሉ በየእለቱ እየመጡ ምቹ ሁኔታን ሲጠባበቁ ነበር የሰነበቱት። ዛሬ በለስ እንደቀናቸው የተገነዘቡት የዘረፋ ቡድን አባላት ይዘውት የመጡት ሚኒባስ መኪና ውስጥ አረፍ ብለው ምቹ ሰአት እስኪደርስ ይጠባበቁ ጀመር።

ዘጠኝ ሰዓት ተኩል አካባቢ ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ቦሌ ሆምስ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ሚስተር ችንግ ሆንግ መኖሪያ ቤት ጊቢ ውስጥ ለመግባት ከመኪናቸው ወረዱ። ሽጉጥ፣ ዱላ እና ፌሮ ይዘው አጥር ዘለው በመግባት የጥበቃ ሠራተኛውን በማስፈራራት የግቢውን በር አስከፈቱት።

የጥበቃ ሠራተኛው በሩን እንደከፈተላቸው የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ አባላቸው ጋር በመሆን መኝታ ክፍል ውስጥ ከገቡ በኋላ ሽጉጥ እና ዱላ የግል ተበዳይን እና ሌላ ግለሰብን በማስፈራራት እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ መኖሪያ ቤቱን በመፈተሽ የግል ተበዳይ እና የሌሎች ጓደኞቹ የሆነ 410 ሺ ጥሬ ገንዘብ፣ የ 900 የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም የተለያየ ዋጋ ግምት ያላቸው የሞባይል ስልኮች ፣ላፕቶፕ እና ኮምፒውተሮች በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 632ሺ 100 ብር የሚያወጣ ንብረትና ጥሬ ገንዘብ በመውሰድ ከአካባቢው ይሰወራሉ።

የዘረፋው ቡድን አባላት

ወጣቶች ናቸው። እድሜያቸው የሃያዎቹን መጀመሪያ እምብዛም አይሻገሩም። አባይ አብርሃ፣ ኤፍሬም ገብረ ጊዮርጊስ፣ ኤፍሬም ክንፈ፣ ዮናታን ኤጀራ ይባላሉ። ወጣቶቹ በአቋራጭ የመክበር ህልም የያዙ ህልማቸውም ለመሳካት ያላቸውን ጉልበትም እውቀትም የሚጠቀሙ ወጣቶች ናቸው።

ወጣቶቹ ሰብሰብ ብለው ጫት የሚቅሙበት ቤት ውስጥ በመሆን የተለያዩ የዘረፋ ታሪኮች ያላቸውን ፊልሞች መመልከት ዋና ሥራቸው ነበር። በየእለቱ ከሚያዩት ፊልም ለእነሱ ዘረፋ የሚመጥን እቅድ ነድፈው በመንቀሳቀስ ተደጋጋሚ ዝርፊያን ሲፈፅሙ ሰንብተዋል።

ያገኙትን ገንዘብ ተከፋፍለው ነገሮች እስኪረሳሱ ድረስ ይደበቁና በሌላ እቅድ የሌላ ሰው ሀብትና ጥሪት መዝረፍ ሥራቸው ከሆነ ውሎ አድሯል። ያሁኑ ዘረፋ ደግሞ ከሌላ ጊዜው በተሻለ ገንዘብ ሊያስገኛቸው የሚችል መሆኑ በደንብ አስበውበት እንዲዘጋጁ አድርጓቸዋል።

በቂ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያዎች፤ የፖሊስ የደንብ ልብስ፤ የዘረፉትን እቃና እነሱን ጠቅልሎ መያዝ የሚችል ሚኒባስ መኪናም አዘጋጅተዋል። ሊዘርፉ ያሰቡት ቤት ላይ በቂ ጥናት ካደረጉ በኋላ ለዘረፋ ምቹ ቀን በመጠባበቅ አስራ አምስት ቀናትን አሳልፈዋል።

በርካታ ዝርፊያዎችን በመፈጸማቸው የተሻለ ገቢ ባለቤትም ሆነዋል። ይህ ሞራል የሰጣቸው ወጣቶች በአቋራጭ ለመክበር ለአሁኑ ዘረፋቸው የውጭ ሀገር ዜጋ ቤትን ኢላማ በማድረግ ወደ ተግባር ገቡ።

በዕለቱ በግምት ከሌሊቱ 9፡30 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ቦሌ ሆምስ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ለጊዜው ካልተያዙ ሌሎች ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ወደ ሚስተር ችንግ ሆንግ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ሽጉጥ፣ ዱላ እና ፌሮ ይዘው አጥር ዘለው በመግባት የጥበቃ ሠራተኛውን በማስፈራራት የግቢውን በር ካስከፈቱ በኋላ ወደ ውጪ እንዲወጣ አደረጉ።

ከዛ በኋላ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ ግብረአበራቸው ጋር በመሆን የአካባቢው ጥበቃዎች የሆኑትን 4 ግለሰቦች ወንጀል እየተፈፀመ እዚህ ምን ታደርጋላችሁ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ትሄዳላችሁ በማለት ሚኒ ባስ መኪና ውስጥ አንድ ላይ ሰብስበው አስገብተዋቸው ለጊዜው ያልተያዙ ሌሎች ግብረ አበሮቻቸውን ወደ ግቢው ውስጥ ያስገቧቸዋል።

በእለቱ ቤት ወስጥ የነበረች ግለሰብ ማንነታቸው እንዳይታወቅ እንድታጎነብስና ወደ ሚስተር ችንግ ሆንግ ዋና መኖሪያ ቤት እንድትወስዳቸው በማድረግ ሚስተር ችንግ ሆንግ መኝታ ክፍል ውስጥ ከገቡ በኋላ ሽጉጥ እና ዱላ የግል ተበዳይን እና ሌላ ግለሰብን በማስፈራራት እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ሚስተር ችንግ ሆንግ በዱላ እጁን በመምታት ጉዳት እንዲ ደርስበት አደረጉ።

ይህንን በማድረግ መኖሪያ ቤቱን በመፈተሽ የሚስተር ችንግ ሆንግ እና የሌሎች ጓደኞቹ የሆነ 410 ሺ ጥሬ ገንዘብ፣ የ900 የአሜሪካን ዶላር እንዲሁ የተለያየ የዋጋ ግምት ያላቸው የሞባይል ስልኮች ፣ላፕቶፕ እና ኮምፒውተሮች በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 632ሺ 100 ብር የሚያወጣ ንብረትና ጥሬ ገንዘብ በመውሰድ የወንጀል ተግባሩን ለመፈጸም በያዙት ያሪስ መኪና በ3ኛ ተከሳሽ አሽከርካሪነት ከአካባቢው ሲሰወሩ 4ኛ ተከሳሽ ካልተያዙት ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን የአካባቢው ጥበቃ የነበሩትን አምስት ግለሰቦችን በያዘው ሚኒባስ መኪና ጭኖ ወደ አቃቂ ቃሊቱ አቅጣጫ እያሽከረከረ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ ሲደርሱ ከመኪናው አስወርዷቸው ከአካባቢው ተሰወረ ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ልክ መረጃው እንደደረሰው ነበር ዘረፋ በተካሄደበት ቤት ተገኝቶ ምርመራ ማድረግ የጀመረው። ፖሊስ በምርመራው የዓይን ምስክሮችን፣ የካሜራ ላይ ማስረጃዎችንና አሻራን በማንሳት በቂ ማስረጃ ይሰበስባል። በማስረጃውም መሠረት ተጠርጣሪዎቹ 632 ሺ 100 ብር የሚያወጣ ንብረትና ጥሬ ገንዘብ ከግለሰብ መኖሪያ ቤት ገብተው በመውሰድ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የከባድ ውንብድና ወንጀል ጉዳያቸው እንዲታይ በማለት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቅርቧል።

የአቃቤ ሕግ ክስ

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የከባድ ውንብድና ወንጀል ጉዳያቸው እንዲታይ ያቀረበ ሲሆን 1ኛ አባይ አብርሃ፣ 2ኛ ኤፍሬም ገ/ጊዮርጊስ፣ 3ኛ ኤፍሬም ክንፈ፣ 4ኛ ዮናታን ኤጀራ የተባሉት ተከሳሾች ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 9፡30 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ቦሌ ሆምስ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ለጊዜው ካልተያዙ ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን የግል ተበዳይ ሚስተር ችንግ ሆንግ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ሽጉጥ፣ ዱላ እና ፌሮ ይዘው አጥር ዘለው በመግባት የጥበቃ ሠራተኛውን በማስፈራራት የግቢውን በር ካስከፈቱ በኋላ ወደ ውጭ እንዲወጣ አድርገዋል።

ከዛ በኋላ ለጊዜው ካልተያዘው የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ ግብረአበራቸው ጋር በመሆን የአካባቢው ጥበቃዎች የሆኑትን 4 ግለሰቦች ወንጀል እየተፈፀመ እዚህ ምን ታደርጋላችሁ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለምን አትሄዱም በማለት ሚኒ ባስ መኪና ውስጥ አንድ ላይ ሰብስበው አስገብተዋቸው ለጊዜው ያልተያዙ ሌሎች ግብረአበሮቻቸውን ወደ ግል ተበዳይ ግቢ ውስጥ በማስገባት የዐቃቤ ህግ ምስክር የሆነችውን ግለሰብ ማንነታቸው እንዳይታወቅ እንድታጎነብስና ወደ ግል ተበዳይ ዋና መኖሪያ ቤት እንድትወስዳቸው በማድረግ የግል ተበዳይ መኝታ ክፍል ውስጥ ከገቡ በኋላ ሽጉጥ እና ዱላ የግል ተበዳይን እና ሌላ ግለሰብን በማስፈራራት እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ የግል ተበዳይን በዱላ እጁን በመምታት ጉዳት እንዲደርስበት አ ደረጉ።

ይህንን በማድረግ መኖሪያ ቤቱን በመፈተሽ የግል ተበዳይ እና የሌሎች ጓደኞቹ የሆነ 410 ሺ ጥሬ ገንዘብ፣ የ900 የአሜሪካን ዶላር እንዲሁ የተለያየ የዋጋ ግምት ያላቸው የሞባይል ስልኮች ፣ላፕቶፕ እና ኮምፒውተሮች በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 632ሺ 100 ብር የሚያወጣ ንብረትና ጥሬ ገንዘብ በመውሰድ የወንጀል ተግባሩን ለመፈጸም በያዙት ያሪስ መኪና በ3ኛ ተከሳሽ አሽከርካሪነት ከአካባቢው ሲሰወሩ 4ኛ ተከሳሽ ካልተያዙት ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን የአካባቢው ጥበቃ የነበሩትን አምስት ግለሰቦችን በያዘው ሚኒባስ መኪና ጭኖ ወደ አቃቂ ቃሊቲ አቅጣጫ እያሽከረከረ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ ሲደርሱ ከመኪናው አስወርደዋቸው ከአካባቢው የተሰወሩ በመሆናቸው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/1/ለ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የወንጀል የተሳትፎ ደረጃቸው ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የከባድ ውንብድና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ሂደቱን ጠብቆ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ችሎት ያልቀረቡ በመሆኑ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን፤ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም በማለት ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግም የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ 4ቱም ተከሳሾች ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ አስረድቷል። ፍርድ ቤቱም እንዲከላከሉ በሰጣቸው ቀጠሮ መሰረት 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ቢያሰሙም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ሊያስተባብሉ ባለመቻላቸው ይከላከሉ በተባሉበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ሲባሉ 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት የታየ እንደመሆኑ መብቶቻቸው ታልፈው ክስ በቀረበባቸው የወንጀል ድንጋጌ ሥር የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል ፡፡

 ውሳኔ

 ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ላይ በእርከን 35 ስር በማሳረፍ በሌሉበት በ16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት፣ በ3ኛ ተከሳሽ ላይ በእርከን 32 ስር በማሳረፍ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት፣ በ4ኛ ተከሳሽ ላይ በእርከን 33 ስር በማሳረፍ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡና እንዲሁም ከሕዝባዊ መብቶቻቸው ለ3 ዓመት እንዲታገዱ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You