ቅናትና ግልፍተኝነት የቀጠፈው ሕይወት

ገና የ24 ዓመት ወጣት ነው። የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ ወደ መሰናዶ የሚያስገባ ውጤት ስላልመጣለት የዲፕሎማ ትምህርትን በመማር ላይ ነበር። ነገር ግን ሕይወት ያን ያህል ቀላል አልነበረም። ቤተሰቦችም አቅም የሌላቸው በመሆኑ የተወለደበትን አማራ ክልል አዊ ዞን አስተዳደር ወጥቶ ኑሮውን ወደ አዲስ አበባ ለመኖር ወሰነ።

ሆኖም አዲስ አበባ መጥቶ መሥራት እና ኑሮን መጋፈጥ ቀላል ነገር አይደለም። በመሆኑም በ2014 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከዚህ በፊት አብሯቸው የተማሩ ተማሪዎችን በማፈላለግ ሥራውን ለመቀጠል ወሰነ። አንድን ሥራ ለመሥራት በሥራው ላይ ያለ እውቀት እና ክህሎት፣ የሥራ ልምድ የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር ሲሆን፤ ከዚህ ውጪ ግን ሰዎች በሚያውቋቸው ሰዎች አማካኝነት ከሙያቸው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የሥራ ዘርፍ ላይ ያሉ የሥራ ግንኙነቶች ሲኖሩ በቀላሉ ሥራ ማግኘት ያስችላል።

እንደ ክንዴ ላሉ ጠንካራ ትውውቅ እና ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሕይወትን ለመጀመር ምርጫው ያደረገው የጉልበት ሥራን መሥራት ነበር። ይህ ሥራ ከሰዎች ጋር ለመግባባት አቅምን ለማሳየት እና ያለውን ችሎታ እና ልምድ ቀጣሪው እንዲገነዘበው ለማድረግ የቀናት ጊዜን ብቻ የሚወስድ ሲሆን ክንዴ የመጀመሪያ ሥራውን ካገኘ በኋላ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተዘዋወረ ሠርቷል። ነገር ግን በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሕንጻዎችን ቀለም መቀባት፣ በግንባታ ሥራዎች ላይ መሳተፍ የሚሠራቸው ሥራዎች ናቸው። አንደኛው ፕሮጀክት ተጠናቆ ሌላኛው ሥራ ለማግኘት ብዙም አይቸገርም።

ታዲያ ክንዴ የሚኖርበት ቦታ እንደሚሠራበት ቦታ ይለያያል። ምክንያቱም ማምሸት በሚኖርበት ወቅት አምሽቶ ሥራውን ለመሥራት ሲል ሥራው አስኮ የሚያውለው ከሆነ የሚኖርበት ቦታ እጅግ ይራራቅ ስለነበር ወደ ሥራ ቦታው አካባቢ ጠጋ ብሎ ለመኖር ይሞክራል። እንዲሁም ሥራውን በቀየረ እና ሥራው ረጅም ወራትን ሊቆይ የሚችልበት ጥሩ ክፍያ እና የሥራ ሁኔታ ያለው ከሆነ ወደ አካባቢ ጠጋ ብሎ ይኖራል። ነገር ግን ክንዴ በባሕሪው ግልፍተኛ የሚባል እና በቶሎ የሚናደድ ዓይነት ሰው ስለሆነ ከብዙዎች ጋር ያጋጨዋል።

ክንዴ ለዚህ ሥራ አዲስ ባይሆንም፤ ለቦታው ግን አዲስ ነው። ሥራውን ሲቀላቀል ከአሠሪዎቹ ጋርም ሆነ ከሰዎች ጋር ለመግባባት ብዙም አልተቸገረም። ክንዴ ብቻውን የሚኖር በመሆኑ በቀኑ ውስጥ የምሳ ሰዓቱን የሚያሳልፈው በሥራ አካባቢው የሚገኝ ምግብ ቤት ከተመገበ በኋላ ርብቃ ጋር ጎራ በማለት ቡና ይጠጣል። ርብቃ ለቦታው አዲስ መሆኑን ስለተረዳች አዲስ የሆኑ ሰዎችን በፍጥነት ቦታውን እንዲላመዱት ታደርጋለች ።

ክንዴ ሥራውን ከጀመረ በኋላ በየዕለቱ ቡናም ሆነ ሻይ በሚጠጣበት ወቅት ከርብቃ ጋር በቀላሉ ሊግባባ ችሏል። ርብቃ ያላትን ሥራ ጥንካሬና ከሰዎች ጋር ያላትን በቶሎ መግባባት በተለየ ዓይን እንዲመለከታት አድርጎታል። በመሆኑም ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው ቁርሱን በልቶ እና ቡና ጠጥቶ ወደ ሥራው ይገባል።

አምሳሉ ዘነበ ወርቅ አካባቢ በሚገኝ ሕንጻ ላይ ረጅም ጊዜ ሥራ ዕድል አግኝቶ ሠርቷል። በአካባቢው የሕንጻ ግንባታ ላይ ረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑ፤ ርብቃን አስቀድሞ ያውቃታል። አምሳሉ የብዙዎች ዓይን ውስጥ የገባችውን ርብቃን አስቀድሞ ቢከጅላትም ይህ ነው የሚባል የእርስ በርስ ጠንካራ ትውውቅ ግን የላቸውም። አምሳሉ በባሕሪው ቁጡ እና በቶሎ የሚናደድ በመሆኑ አብረውት ካሉ ሰዎች ጋር ከሰላምታ የዘለለ ሰዓት የወሰደ ጨዋታ አይኖረውም።

ነገር ግን ርብቃ እና የሥራ ባልደረባው ከሥራ በኋላ ያላቸውን አዲስ ግንኙነት እና አብሮ መሆን በፍጹም ምቾት ነስቶታል። ነገር ግን በዓይኑ ከመከታተል የዘለለ እና አልፎ አልፎ ከርብቃ ጋር የነበረውን የቀድሞ ግንኙነት ለመመለስ ሙከራ ያደርግ ነበር። ርብቃ ደግሞ አዲሱን የሕንጻ ሠራተኛ ክንዴን ቦታውን እንዲለምደው ለማድረግ በሚመስል መልኩ የምታደርገው መስተንግዶ ያላቸው ግንኙነት እንዲጠነክር አድርጎታል።

የሕንጻውን ሥራ ለማከናወን ጠዋት ከሁለት ሰዓት በፊት ሥራ ቦታው ላይ ይገኛል። የጠዋት የመጀመሪያ ሥራው ርብቃ ጋር ቡና መጠጣት አብሯት ደቂቃዎችን ካሳለፈ በኋላ ሥራውን ይጀምራል። አምሳሉ ርብቃ እና ክንዴ ተግባብተው የፍቅር ግንኙነት ጀምረዋል የሚል እሳቤ ከሚያየው ነገር የተነሳ በውስጡ ቅናት እያደረ ነው። በዚህም ቅናት ቢጤ ጭሮበታል። ነገር ግን ይህ ነው የሚባል ቅርርብ ከክንዴ ጋር ስለሌለው ጉዳዩን ለማጣራት አልቻለም። ግን እንዲሁ በቅርብ ርቀት በመመልከት ሥራውን ይሠራል።

ጉዳዩን ለማረጋገጥ ከሰው መጠየቅም ባይጠበቅበትም የሚያየው ነገር ሁሉንም ነገር ግልጽ አድርጎለት ነበር። ታዲያ ይህንን ንዴቱን ለመወጣት አምሳሉ አዲስ ትውውቅ የመሠረተውን ጓደኛውን ብዙም ትኩረት ሊሰጠው አልፈለገም። ለሚጠይቀው ጥያቄም ሆነ አብረን እናሳልፍ ወዳጅነት ጥያቄ መልካም ምላሽ እየሰጠው አይደለም።

ሁለቱም የሥራ ባልደረቦች እርስ በርሳቸው በዓይነ ቁራኛ ይተያያሉ፤ በመሐከላቸው ይህ ነው የሚባል ችግር፣ ይህ ነው ተብሎ የሚገለጽ ተግባቦት ደግሞ የላቸውም። እየተሠራ የሚገኘው የሕንጻ ሥራ እየተጠናቀቀ በመሆኑ እንደሌላው ጊዜ ቀኑን ሙሉ በሥራ አያሳልፉም።

ታዲያ በአንዱ ቀን ያደሩ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በጠዋት ወደ ሥራው ያቀናው አምሳሉ ሥራ ቦታው ላይ ሌሎች ሠራተኞች እስከሚመጡ ድረስ ያደረ የሥራ አካባቢውን በማፅዳት እቃዎችን ለሌላ ሥራ ካዘጋጀ በኋላ ከሌሎች ሠራተኞች ጋር የዕለቱን ሥራቸውን ጀመሩ። ክንዴ እና አምሳሉ ያላቸው ባሕሪ ተመሳሳይ የሚባል ነው። ይህንንም በሥራ ላይ የሚኖረውን አለመግባባት የሥራ ባልደረቦቻቸው እና አለቆቻቸው ይረዱታል። ታዲያ በዚህ ቀን ይህ ነው የሚባል ግጭት አልያም በመሐከላቸው አለመግባባት ሳይፈጠር ሥራቸውን አጠናቀው ወደቤታቸው ለመሄድ ሲነሱ በመሐከላቸው በተፈጠረ ንግግር ከቃላት ልውውጥ ወደ እጅ መሰንዘር አመራ።

በሁለቱ ጎረምሶች መካከል በተፈጠረ ግብግብ ግን አስቀድሞ ነገር እንደፈለገ በሚያሳብቅ መልኩ ክንዴ በሆዱ ደብቆ የያዘውን ስለት በማውጣት አምሳሉ ሰውነት ላይ በተደጋጋሚ አሳረፈ። በደረሰበት ተደጋጋሚ መወጋትም አምሳሉ አቅም አጥቶ ወደቀ። መሬት ላይ የወደቀውን አምሳሉን ሲመለከት ወንጀል መሥራቱን የተመለከተው እብሪተኛው ክንዴ ከአካባቢው ለማምለጥ ጥረት ቢያደርግም በቦታው ግን በርካታ ሰዎች የሚገኙ በመሆናቸው ባሰሙት የጩኸት ድምፅ አምሳሉን ወደ ሕክምና ጥቃት አድራሹን ክንዴን ደግሞ ወደ አቅራቢያው ፖሊስ ጣቢያ ይዘውት ሄዱ። በአካባቢው የነበረው ሆስፒታል የመጀመሪያ ርዳታ እንዲያገኝ አለርት ሆስፒታል በቅርብ የሚገኝ ቢሆንም አምሳሉ ግን በተደጋጋሚ በደረሰበት ጉዳት ሆስፒታል ሳይደርስ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

የወንጀል ዝርዝር

ከሳሽ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ሲሆን ተከሳሽ ክንዴ ንብረት የኔታ እድሜው 24 አዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ሲሆኑ ተከሳሽ ሰው ለመግደል አስቦ በ9/3/2016 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 11 ሰዓት ሲሆን በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ ዘነበ ወርቅ ዘውዴ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ሟች አምሳሉ አገኘሁ በቢላዋ የግራ ጎኑን በመውጋት ሟች በደረቱና ሆዱ ላይ የውጊያ ጉዳት በማድረሳቸው ምክንያት በዕለቱ ርዳታ ለማግኘት በአቅራቢያው በሚገኘው ወደ አለርት ሆስፒታል እየሄደ እያለ ሕይወቱ አልፏል። በዚህም ተከሳሽ በፈጸመው ተራ የሰው መግደል ወንጀል ተከሷል። ይህም የሆነው በፖሊስ እና በሕዝብ ጥቆማ በተደረገ ትብብር ነው።

ወንጀሉ

በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ የተፈጸመ ነው ።

ማስረጃዎች

በሰነድ ማስረጃዎች የሟች የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክና ሜዲስን ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል የተላከ የምርመራ ውጤት ከትርጉም ጋር፣ በሥራ ቦታ የሚገኙ በአካባቢው ሁለቱን ሰዎች የሚያውቁ እና ሌሎች የቤተሰብ አባላት በጥቅሉ 5 የሰው ምስክር ማስረጃ፣ በገላጭ ማስረጃዎች የተወጋበት ቦታ ላይ የፈሰሰውን ደም የሚያሳዩ አምስት ፎቶግራፎች ተከሳሽ ሟችን የወጋበት በኤግዚቢትነት ተይዟል። ተከሳሽ ከ10 /03 /2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ይገኛል። በምርመራው ሂደት የተለያዩ መረጃዎችን ለበማጠናከር ሂደት ተጨማሪ የምርመራ ቀነ ቀጠሮ በመጠየቅ መረጃዎቹን አያይዟል።

 ውሳኔ

ተከሳሽ ክንዴ ንብረት ያኔት በተከሰሰበት ሰው መግደል ወንጀል ጉዳይ ክርክር ላይ የነበረና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ በ19/06/2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ክስና ማስረጃ ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ በ11 (በአስራ አንድ ዓመት) ጽኑ እስራት የቀጣ በማለት ውሳኔ አሳልፏል።

በሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You