የባሕርዳር ስታድየም ግንባታን ለማጠናቀቅ የተወሰደ ትልቅ ርምጃ

ባለፉት 15 ዓመታት የሀገሪቱን እግር ኳስ ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ግዙፍ ስታዲየሞች ግንባታ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ቢጀመሩም አንዳቸውም መጠናቀቅ አልቻሉም።

ለዓመታት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያስተናግድ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየምም ከሶስት ዓመት በፊት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ከማስተናገድ መታገዱን ተከትሎ እየታደሰ የሚገኝ ሲሆን ዛሬም ድረስ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት አልቻለም፡፡ በ2006 ዓ.ም ግንባታው በከፊል ሳይጠናቀቅ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን በማስተናገድ ወደ ሥራ የገባው የባሕርዳር ስታዲየም የብሔራዊ ቡድንና የክለቦች በርካታ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ሲያስተናግድ ቢቆይም የካፍ መመዘኛ መስፈርትን ሙሉ በሙሉ ባለማሟላቱ ከጥቅምት 2014 ዓ.ም አንስቶ ተመሳሳይ እገዳ ተጥሎበታል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የባሕርዳር ስታድየም ከታገደ ወዲህ የአፍሪካ ዋንጫና የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ለማድረግ ወደሌሎች ሀገራት ለመሰደድ ተገዷል። የባሕርዳር ስታድየም በካፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ ከታገደ ጀምሮ የክልሉ መንግሥት መሟላት ያለባቸውን መሰረተ ልማቶች ለማሟላት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በተደጋጋሚ ገልጿል። ያም ሆኖ ስታድየሙ አስፈላጊውን ዓለም አቀፍ መስፈርት አሟልቶ ሳይጠናቀቅ ዓመታት ተቆጥረዋል።

አሁን ግን የክልሉ መንግሥት ስታድየሙን በተቻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ ወይም አስፈላጊውን መስፈርት እንዲያሟላ ለማድረግ ተጨማሪ በጀት ከማፅደቅ በተጨማሪ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከነዚህም ሥራዎች መካከል በስታድየሙ 52 ሺ ዘመናዊ ወንበር ለመግጠም ተቋራጭ ተለይቶ ወደ ሥራ መገባቱን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከትናንት በስቲያ ይፋ ማድረጉን አሚኮ ዘግባል። ይህም ሳይጠናቀቅ ዓመታት እያስቆጠረ የሚገኘውን ስታድየም ለማጠናቀቅ የተወሰደ ትልቅ ርምጃ ሆኗል፡፡

የወንበር ገጠማ ሥራውን የሚያከናውነውም በሜድሮክ ኢትዮጵያ ሥር ያለ “አዲስ ጋዝ” የተሰኘ ንዑስ ተቋራጭ መሆኑ ተጠቁሟል። ለወንበር ገጠማው የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችም ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ መምጣታቸው ታውቋል፡፡ የሚገጠመው ወንበር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የዓለም አቀፉን እግር ኳስ ማኀበር (ፊፋ) የደረጃ መስፈርትን ያሟላ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።

የክልሉ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ለስታድየሙ ግንባታ ማጠናቀቂያ ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መፍቀዱ ይታወሳል። የስታድየሙ ግንባታ የቀሪ ሥራዎች ማጠናቀቂያ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት ተጠይቆ የነበረ ሲሆን ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ ነው የተፈቀደው። ከተፈቀደው ገንዘብ 400 ሚሊዮን ብር በሩብ ዓመቱ ሥራ ላይ መዋሉም ታውቋል።

የባሕር ዳር ስታድየም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ ቀሪ ግንባታውን የማጠናቀቅ ሥራ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ከዚህ ቀደም የተገለፀ ሲሆን፤ የማጠናቀቂያ ሥራዎችም ከዓመት በፊት መጀመራቸው ይታወቃል፡፡

የስታዲየሙ ሁለተኛ ዙር የግንባታ ሥራዎች ባለፈው ዓመት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በፈቀደው 700 ሚሊዮን ብር የተጀመረ ሲሆን፤ ቀሪው 300 ሚሊዮን ብር ደግሞ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ድጋፍ እንደሚሸፈን በወቅቱ ተገልፆ ነበር፡፡

በሁለተኛው ዙር የስታድየሙ ግንባታ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ጥራት ማሻሻያ፣ የእንግዳ መቀበያ ክፍል፣ መቀመጫ ወንበር መግጠም እና መሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

የማጠናቀቂያ ሥራው የፊፋ መመዘኛ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ የሚሠራ ሲሆን፤ ይህም ስታድየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ወደ ማስተናጋድ እንዲመለስ ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡የሁለተኛው ዙር ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You