በኢትዮጵያ ከ30 በላይ የሚሆኑ ስፖርቶች በፌዴሬሽኖችና በማህበራት ተደራጅተው እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። እነዚህ የስፖርት አይነቶች የሚንቀሳቀሱት መንግሥት በሚመድብላቸው የድጎማ በጀት አማካኝነት ሲሆን ከጥቂት ስፖርተቶች ውጪ የራሳቸውን ገቢ አመንጭተው አቅም መፍጠር አልቻሉም። ይህም ስፖርቱን ለማሳደግ ትልቅ ችግር መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል።
ስፖርቱን ሕዝባዊ መሠረት ለማስያዝ በሚደረገው ጥረት መንግሥት ለነዚህ ስፖርቶች የሚመድበውን በጀት ቀስበቀስ እየቀነሰ ወደ ሂደቱ እንዲገቡ እየተሞከረ ይገኛል። በዚህም አብዛኞቹ የበጀት እጥረት እየገጠማቸው ነው። መንግሥት የፌዴሬሽኖችንና ማህበራትን ደረጃ በማውጣትና እንደየ ደረጃቸው የሚደርሳቸውን ዓመታዊ የድጎማ በጀት ወደ መስጠት ርምጃ ውስጥ ገብተዋል። ይህ ደግሞ እንደ ፓራሊምፒክ ያሉትን ውጤታማ ስፖርቶች እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱና በዓመት በቂ የሆኑ ውድድሮችን በሚፈለገው ልክ እንዳያካሂዱ አድርጓል። በተጨማሪም ልዩ ትኩረት የመስጠትና የአሳታፊነቱንም ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል።
የፓራሊምፒክ ስፖርት ወትሮውንም ብዙ ችግሮች ያሉበትና ትልቅ ድጋፍ የሚያሻ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ድጋፍና ክትትል አልተደረገለትም። በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለስፖርት ተቋማትና ማህበራት በተሰጠው ደረጃ መሠረት የፓራሊምፒክ ስፖርት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል። በተሰጠው ደረጃ መሠረትም በዓመት የተመደበለት የድጎማ በጀት 170 ሺ ብር ገደማ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም ልዩ ድጋፍና ክትትልን ለሚፈልገው የፓራሊምፒክ ስፖርት በቂ የውድድር እድልን ለመፍጠር የሚያስችል አይደለም። የተሰጠው ደረጃም ተገቢና ለስፖርቱ የሚመጥን አለመሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጊዮን ሰይፉ፣ ፓራስፖርት የአካል ጉዳተኞች ስፖርት እንደመሆኑ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠው ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹በስፖርቱ ላይ ያለው ችግር ሳይታይ ሶስተኛ ደረጃ ተሰጥቶት 170 ሺ ብር ዓመታዊ የድጎማ በጀት ተመድቧል።›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ለስፖርቱ የተሰጠው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን እንደሚያመለክት ጠቁመዋል።
ይህ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተፈጠረ የግንዛቤ ችግርና ለጽሕፈት ቤቱ የተመደቡ ሰዎች ለስፖርቱ የሚገባውን ጥቅም በአግባቡ በማስረዳት ስለማይሠሩ የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል። ፌዴሬሽን ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች በጎ ፈቃደኛ በመሆናቸው የጊዜ መጣበብና ሌሎች ችግሮች ተጨምሮበት ስፖርቱ ችግር ውስጥ እንዲገኝ ማድረጉንም ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ።
ፓራሊምፒክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት የሚያመጣ ስፖርት ቢሆንም፣ በሀገር ደረጃ ያለው የግንዛቤ መጠን በጣም ዝቅተኛ መሆኑ እነዚህን ችግሮች እንደፈጠረ ፕሬዚዳንቱ ያብራራሉ። የፓራሊምፒክ ኮሚቴው ሀብት ለመሰብሰብ 50 የሚደርሱ ድርጅቶችን ድጋፍ ቢጠይቅም ምላሽ የሰጠው አንድ ብቻ ነው። እስከ አሁን የግማሽ ዓመቱ በጀትም ያልተለቀቀለት ሲሆን ይሄም 80 ሺህ ብር ገደማ በመሆኑ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔና የኢትዮጵያ ቻምፒዮናን ማከናወን ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ ቻምፒዮናን ለማዘጋጀት ከ500 ሺ ብር በላይ የሚጠይቅ ሲሆን ገንዘቡ ትንሽ ስለሆነ የተጠቀሱትን ወጪዎች መሸፈን አይችልም። በነዚህና በሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
ኮሚቴውን ቀድሞ የሚመራው አካል አሁን እየመራ ላለው ኮሚቴ በቢሮ ደረጃ ምንም ነገር እንዳላስረከበ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ስፖርቱ ከተመሠረተ 20 ዓመት የሚጠጋ እድሜን ያስቆጠረ ቢሆንም የሚያስፈልጉት መሣሪያዎች እንኳን እንደሌሉት አክለዋል።
‹‹ሥራ እንዳይሠራ የሚደረጉ ጠለፋዎች መኖራቸው ችግሩን የከፋ አድርጓል። በዚህም የተነሳ ፌዴሬሽኑ እያደገ ሳይሆን እየሞተ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የተደራጀ ቢሮና የመሥሪያ መሣሪያዎችም የሌሉት መሆኑን ጠቁመዋል። ከስፖርታዊ ውድድር የሚገኝም ሆነ ከሌላ ድጋፍ ከሚያደርግ አካላት የሚገኝ ቋሚ ገቢ እንደሌለው ገልጸውም፤ በዚህ የተነሳ በወጣው ደረጃ መሠረት መንግሥት የሚበጅተው ገንዘብ ውድድሮችን ለማካሄድ፣ ሥልጠና ለመስጠትና ቢሮን ለማደራጀት የማይበቃ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዲገኝ አድርጎታል ይላሉ።
ይሄም በስፖርተኞቹ ላይ ከፍተኛ ተፅኖን ከማሳደሩም በላይ ክለብ በማቋቋም ሂደት ላይ እንቅፋት ሆናል። ከአካዳሚ ተመርቀው የሚወጡትን ስፖርተኞች ክለብ ተመስርቶ እንዲቀበላቸው በኮሚቴው በኩል የተደረጉ ጥረቶች ፍሬያማ መሆን አልቻሉም። ተቋማቱ የፓራሊምፒክ ክለቦችን እንዲያቋቁሙ ፍቃደኝነት አያሳዩም። ለዚህ ግማሹ የበጀት እጥረትን ሲያነሳ የተቀሩት ደግሞ ከጥቅም አንጻር ጥያቄ እንደሚያነሱም ተጠቅሷል።
ኮሚቴው በዓመት በሚመደበው የድጎማ በጀት፣ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ፣ አንድ ሀገር አቀፍ ውድድር ማካሄድ እና ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የወጣት ሴቶች ውድድርን ማካሄድ የሚኖርበት ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በበጀት ማነስ ምክንያት እነዚህን ተግባራ ማካሄድ ሳይችል ቀርቷል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም