የአፋር ክልል ‹‹የሰው ዘር መገኛ፤ የቱሪስት መስህቦች መዳረሻ፤ የበረሃ ገነት›› በመባል ይታወቃል። ክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ክምችት ካለባቸው የሀገሪቷ ክልሎች መካከል ተጠቃሹ መሆኑን ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። እንደ ጨው፣ ወርቅ፣ ኦፓል፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝና የመሳሰሉት ክልሉ በስፋት ይገኛሉ። በተለይም የክልሉ የጨው ምርት የኢትዮጵያን የጨው ፍላጎት 85 በመቶ እንደሚሸፍን ይታወቃል።
እነዚህ ሁሉ የማዕድን ሀብቶች በክልሉ ቢገኙም የማዕድን ሀብቶቹን በማልማት ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ብዙ ርቀት አልተሄደም። ከክልሉ ማእድንና የሥራ እድል ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ ማዕድናቱ የሚመረቱበት መንገድ ባሕላዊ መሆኑና የሕገወጥነት መስፋፋት ለዘርፉ ልማትና እድገት እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል። በክልሉ የማዕድን ሀብት ለማልማት ከተደራጁት አምራች ማኅበራት መካከል ጥቂቶቱ ብቻ እየሠሩ ያለበት ሁኔታም የማዕድን ልማቱን በተፈለገው ልክ የማከናወኑን ሥራ አስቸጋሪ አርጎት ቆይቷል።
የአፋር ክልል ማዕድንና የሥራ ዕድል ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዲሂሉ እንደተናገሩት፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት በክልሉ በማዕድን ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ አልተሠራም። አሁን ላይ ለማዕድን ልማቱ በተሰጠው ትኩረት በየጊዜው መሻሻሎች እየታዩ ናቸው።
በክልሉ ዘንድሮ (በ2016 በጀት ዓመት) ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ምክትል የቢሮ ሃላፊው ጠቅሰው፤ ይህም ከባለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል አመላክተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ ወርቅ፣ ጨው፣ ኦፓል፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝ፣ የኮንስትራክሽንና የተለያዩ ማዕድናት ይገኛሉ። እነዚህ በጥናት የተለዩ ሲሆን፣ በጥናት ያልተለዩ በርካታ ማዕድናትም በክልሉ ይገኛሉ። በጥናት ከተለዩት መካከል ኦፓል፣ ወርቅ፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝ (በጥቂቱ ቢሆን) እና ከፍተኛ የሆነ የቪንትራየትስ ክምችት መኖሩን ጠቅሰው፣ 85 በመቶ የኢትዮጵያ የጨው ፍላጎት የሚሸፈነው ከዚሁ ክልል መሆኑን አቶ ኢብራሂም አስታውቀዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ማዕድናትን ለመለየት በተመረጡ ሦስት ወረዳዎች (በዞን ሦስት፣ ዞን ሁለትና በዞን አራት) ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥናቱም በክልሉ ያሉ በውል ያልታወቁ የማዕድን ሀብቶችን በማወቅ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በክልሉ በተደረገው ጥናት መሠረት ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት መኖሩ ቢታወቅም፣ ከወርቅ ምርቱ ግን አጥጋቢ ውጤት አልተገኘም። ለዚህ እንደምክንያት ከሚያነሱት ተግዳሮቶች ውስጥ አንደኛው የወርቅ ምርት ለማምረት ተደራጅተው የሚሠሩ አምራቾች ወርቅ የሚያመርቱበት ሂደት ለረጅም ዓመታት ባሕላዊ ሆኖ መዝለቁ ነው።
በባሕላዊ መንገድ የተመረተውን ወርቅ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ገበያ ለማውጣት የመሠረተ ልማት አለመሟላት ሌላው ችግር ነው። በተለያዩ ምክንያቶች ወርቅ በኮንትሮባንድ መንገድ ለሕገወጦች ይሸጥ ነበር። ይህንን ችግር ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍም የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አምራቾች ያመረቱትን ወርቅ ወርቁ በሚመረትበት አቅራቢያ ማስረከብ የሚችሉበት ባንክ እንዲቋቋም ተደርጓል። ባንኩ በወረዳው እንዲቋቋም መደረጉ አምራቾች ወርቁን በቀላሉ ለባንኩ እንዲያስረክቡ አስችሏል፤ ወርቁ በሕገወጥ መንገድ እንዳይወጣ እና እንዳይሸጥ ከማዕድን ቢሮ ደብዳቤ እየተጻፈ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ጥረት እየተደረገ ነው።
በክልሉ በ2014 እና 2015 በጀት ዓመት ከወርቅ ምርት 50 ኪሎ ግራም ወርቅ ማግኘት መቻሉን ምክትል የቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል። በ2015 በጀት ዓመት ክልሉ በማዕድን ዘርፍ 35 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 41 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ጠቅሰዋል። በ2016 በጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፉ 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም ነው ያመለከቱት።
ክልሉ በነበሩት ጸጥታና አለመረጋጋት የተነሳ ከወርቅ ምርትም ሆነ ገቢ አንጻር የተገኘው ውጤት አነስተኛ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የወርቅ ማምረት ሥራው በተጠናከረ መልኩ እንዲካሄድ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል። በወርቅ ልማት ላይ የተደራጁ ማህበራትም ሆነ ህብረተሰቡ ከወርቅ ሀብቱ መጠቀም እንዲችል ለማድረግ ማህበራቱን የማጠናከርና ተደራጅተው የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት እና የወርቅ ፍለጋን የሚያቀሉ ማሽኖችን በመስጠት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል::
አቶ ኢብራሂም በክልሉ በወርቅ ምርት ሥራ ከአንድ ሺህ 200 በላይ አባላት ያሏቸው 13 ማኅበራት መደራጀታቸውን ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ማህበራት መካከል በትክክል ወደ ሥራ ገብተው እየሠሩ ያሉት አምስት ማኅበራት ብቻ ናቸው ብለዋል። ዘርፉን ለማጠናከር በ2015 በጀት ዓመት ለሁለት ማኅበራት የወርቅ መፈለጊያና ማቅለጫ ማሽኖችን ተሰጥቷል፤ ይህም ወርቅ በተሻለ ሁኔታ እንዲያመርቱ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።
ማሽኖቹን ማህበራቱ እንዲያገኙ የተደረገው ወደ ብሔራዊ ባንክ በሚያስገቡት የወርቅ መጠን መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ምን ያህል ወርቅ ወደ ባንኩ አስገብተዋል የሚለውን በማመዛዘንና በማወዳደር ለመሸለም ታቅዶ መከናወኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል።
በክልሉ በነበረው የጸጥታና አለመረጋጋት ችግር ማህበራትን የመደገፉ ሥራ ተስተጓጉሎ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከሰመራ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመነጋገር በክልሉ በሁሉም ዞኖች የሚገኙ ማህበራትን እንደ አዲስ በማደራጀት ወርቅ የማምረት ሥራ ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል። በክልሉ የወርቅ ክምችት የሚገኘው ወርቅ በሚመረትበት በዞን ሁለት ብቻ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በስድስቱም ወረዳዎች በጥናት ያልተረጋገጠ ቢሆንም የወርቅ ክምችት ስለመኖሩ የተደረጉ ዳሰሳዎች ይጠቁማሉ ሲሉ ገልጸዋል።
በስድስቱ ዞኖች ከፍተኛ የሆነ ጥናት በማድረግ የወርቁን ሥራ የሚሠሩ ማህበራትን እንደ አዲስ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተው፤ የወርቅ ክምችት ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት አራት ማህበራትን በማደራጀት በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማምረት ሥራ ለ250 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል።
ምክትል የቢሮ ሃላፊው እንዳብራሩት፤ ክልሉ ከማዕድን ዘርፉ ማግኘት ካለበት የገቢ መጠን አንጻር አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው። የጥቁር ገበያ መስፋፋትና በባሕላዊ መንገድ የሚካሄደው ወርቅ የማምረቱ ሂደት ዋነኛ የዘርፉ ችግሮች ናቸው። በወርቅ ግብይት ላይ አሁን ለውጦች እየታዩ ናቸው። በተለይ ብሔራዊ ባንክ ወርቅን የሚገዛበት ዋጋ ከጨመረ በኋላ በተደረገ ክትትልና ድጋፍ ሕገወጥነት በመከላከል አበረታች ለውጦች እየታዩ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ባንክ የሚገዛበት ዋጋና በጥቁር ገበያው ላይ ያለው ዋጋ በእጅጉ ይለያዩ እንደነበር ጠቅሰው፤ ባንኩ ይህንን በማየት የማስተካከያ ሥራዎችን መሥራቱን አመላክተዋል። በቀጣይም ሕገወጦችን የመከላከሉን ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል ወርቅን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም አይነት የማዕድን ሀብት በክልሉ ያለፍቃድ እንዳይንቀሳቀስ የሚደረገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አስታውቀዋል።
አምራቾች በሕጋዊ መንገድ ታክስ ከፍለው የሚያቀርቡት የማዕድን ምርት ሲጨምር ክልሉ የሚያገኘው ገቢ ይጨምራል ያሉት አቶ ኢብራሂም፤ ይህም ለህብረተሰቡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል። በመሆኑም ወርቅ አምራቾቹ በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ ምርቱን እንዲያስገቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የማሳመን ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የጥቁር ገበያን እና ሕገወጥነት ለመከላከል በየኬላዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ።
ሌላኛው በወርቅ ምርት ላይ የሚነሳው ተግዳሮት የወርቅ አምራች ማህበራት ወርቅን ለማውጣት የሚያስፈልጋቸው የግብዓት (የማቴሪያል) እጥረት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ብዙ ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል። እጥረቱ ሀገሪቱም ሆነ ክልሉ ከማዕድን ዘርፉ ማግኘት ካለባቸው ገቢ በጣም ዝቅተኛውን እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፤ ከማዕድን ዘርፉ የሚገኘውን ምርትም ሆነ ገቢ ለመጨመር መፈታት ያለባቸው ችግሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።
የክልሉን የጨው ምርት በሰፊው ለገበያ ለማቅረብ ጠንካራ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልግም አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል። ክልሉ በማዕድን ሀብት የበለጸገ መሆኑ ብቻ ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረው፣ በየዘርፉ ባለሀብቱም ሆነ ወጣቱ በማህበር ተደራጅቶ በልማቱ ሊሳተፉ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ምክትል የቢሮ ሃላፊው እንዳስታወቁት፤ የማዕድን ዘርፉ በአግባቡ ከተሠራበት ከፍተኛ የሆነ የሰው ሃይል ሊሰማራበት የሚችል ዘርፍ ነው ። ክልሉ ሰፊ የሰው ሀብትም አለው፤ ይህንን የሰው ሀብት በማዕድን ዘርፉ ላይ እንዲሰማራ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
የማዕድን ሥራ ከፍተኛ የሆነ ልፋትና ጥረት እንደሚጠይቅ የጠቀሱት አቶ ኢብራሂም፤ በዘርፉ ልምድ፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ ያላቸው አካላት በዘርፉ እንዲሰማሩም ጠይቀዋል። በማንኛቸውም ማዕድን ዘርፍ (በኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪ ግብዓት ሊሆኑ በሚችሉ) በማህበር የተደራጁም ሆኑ ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራው መግባት የሚችሉበት ሰፊ እድል መኖሩን አመላክተዋል።
በማዕድን ሀብት ልማት ላይ በመሰማራት የማዕድን ሀብቱን በማልማት፣ የሥራ እድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት መሥራት እንደሚገባ ምክትል ኃላፊው ጠቁመው፣ በክልሉ ማዕድን ልማት ላይ ለመሰማራት ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም