በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈጠራ ሥራ ለማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለደህንነት፣ ለትምህርት፣ ለግብርና፣ ለጤና አገልግሎት መሻሸል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው። በአጠቃላይ በዚህ ዘመን ያለቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ ከባድ እየሆነ በመምጣቱ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ሆኗል።
ያደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂን በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ እንደሆነ ያታወቃል። እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ፋይዳው ከምንለው በላይ ትልቅ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ከመቸውም ጊዜ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።
በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎች ቢሆኑም የፈጠራ ሃሳባቸውን ለመተግበር የመሥሪያ ቦታ አለማግኘት፣ የገንዘብ ብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የክህሎት ክፍተቶችና መሰል ችግሮች ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ እንደተግዳሮት ያነሳሉ።
ይሁን እንጂ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ስኬታማ የሆኑና በአርአያነት የሚጠቀሱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አሉ። እኛም ለዛሬ የወጣቶች አምዳችን በሥራ ፈጠራው ውጤታማ ከሆነው ወጣት እግዜርያለው አየለ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ወጣት እግዜርያለው፤ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ ገርጂ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአካባቢው በሚገኝ ቅዱስ ዮሴፍ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቀው። የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከታተለ ሲሆን፤ በ2008 ዓ.ም በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ፣ በመካኒካል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝቷል።
በሥራ ዓለምም በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በቀጠርና በማማከር ሠርቷል። ወጣት እግዜርያለው እንደገለጸልን፤ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ የትምህርት ዘርፎች ውስጥ በጣም ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው በማሽነሪ ግንባታ ላይ ነው። ወጣቱ ከልጅነት ጀምሮ ፍላጎቱ ይህ ስለነበር በዛ መንገድ እራሱን መርቶ ውጤታማ ሆኖ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
ወጣቱ ከዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በወቅቱ በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በሚል እንቅስቃሴ ይካሄድ ስለነበር በማኑፋክቸሪንግ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት ተፈጥሮ ነበር። ብዙ ነገሮች ሀገር ወስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ አቅጣጫ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይሄ ለእርሱ መልካም አጋጣሚ ነበር “እኔም ወደዚህ ዘርፍ ተቀላቅዬ ሀገሬን ኢትዮጵያን ባለኝ እውቀትና ጉልበት ለማገልገል ትልቅ ጉጉት ፈጥሮብኛል” ሲልም ይገልጻል።
ሮዳ የሚባል ኩባንያ ውስጥ ሥራ መጀመሩን የሚናገረው እግዜርያለው፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ አንጋፋና ለኮንስትራክሽን፣ ለግብርና የሚሆኑ ማሽኖችን ሀገር ውስጥ በማምረት እንደሚታወቅና በድርጅቱ ውስጥ በነበረው የአንድ ዓመት የሥራ ቆይታም በንድፈ ሃሳብ ያገኘውን እውቀት በተግባር እንዳዳበረለትና ልምድ ያገኘበት እንደሆነ ያስረዳል። የተሻለ እውቀት ማግኘት በመቻሉና አቅምም በመፍጠሩ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በታዳሽ ኃይል ዘርፍ በጀማሪ አማካሪነት ማገልገሉን ይገልጻል። በተጨማሪም የተለያዩ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ዲዛይን በማድረግ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የምርምር ሥራዎችን መሥራቱን ይናገራል።
ወጣት እግዜርያለው በቅጥር መቆየቱን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ አልያዘውም። ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት የሆነውን የቡና ልማት የሚያዘምን ቴክኖሎጂ መሥራቱን ይገልጻል። እርሱ እንዳለው ቡና ከተለቀመ በኋላ ለማድረቂያ የሚውል ቴክኖሎጂ ነው የሠራው። ቴክኖሎጂው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡናን ማድረቅ የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪ ጊዜንም ይቆጥባል። በዚህም ቡና ለማድረቅ ቀናትን ይጠብቁ የነበሩ በሥራው ላይ የተሠማሩትን ድካም አቃልሎላቸዋል።
በ2012ዓ.ም ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት ብዙ ሰው በቤቱ ውስጥ ተወስኖ እንዲቆይ ተደርጎ ስለነበር ወጣት እግዜርያለው ይህን አጋጣሚ በከንቱ አላሳለፈውም። በወቅቱ የጥሞና ጊዜ በመውሰድና በደንብ በማብላላትና ዲዛይን በመሥራት ሰፊ የምርምር ሥራ በማከናወን የታዳሽ ሃይል ከሰል ማሽን ሰርቶ ዕውን በማድረግ ጊዜውን ተጠቅሞበታል።
ወጣቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተካሄደው ነጋድራስ የፈጠራ ሥራ ውድድር ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ የ 500 ሺህ ብር ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። በግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ለመሥራት ያለው ፍላጎት ወደ ፈጠራና ምርምር ሥራ እንዲገባ እንዳደረገውም ይገልጻል።
ወጣቱ በፈጠራ ቴክኖሎጂ የሠራውን የቡና ማድረቂያ ማሽን፤ ልማቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሲያስተዋወቅ፤ የቡና ገለባን ወደ ጥቅም መለወጥ የሚፈልግ አንድ ቡና አልሚን ያገኛል። እርሱ እዳለው፤ ቡና አልሚው በቀን እስከ 200 ኩንታል ገለባ ከቡና ውስጥ እንደሚያወጣና ገለባውንም ለማስቀመጥ የቦታ ችግር እንደገጠመው ነበር የነገረው። አልሚው ይህን ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ዘዴ ነበር ከወጣቱ የፈለገው። በተለይም በቴክኖሎጂ ወደ ጥቅም እንዲለውጥለት ነበር ፍላጎቱ።
ወጣቱ ቀደም ሲልም ይሠራበት የነበረው ድርጅት ከግብርና ተረፈ ምርት የሚሠራ የድንጋይ ከሰል ማግኘት አልቻልኩም የሚል ጥያቄ አቅርቦለት የነበረውንና የአሁኑ ቡና አልሚው ደግሞ እንዲሁ ተረፈ ምርቱን ምን እንደሚያደርገው መቸገሩ ፤ በአጠቃላይ በግብርና ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች ችግር መገጣጠሙ እንዲያስብበት አደረገው። በዚህም ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ በመሥራት ለውጤት እንደበቃ ይናገራል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወጪ በማውጣት በተለይ ለኢንዱስትሪ የሃይል ፍጆታ የሚውሉ ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች የሚለው ወጣት እግዜርያለው፤ የድንጋይ ከሰልን አሁን እርሱ በሠራው ማሽን መተካት እንደሚቻል ይገልጻል። በሀገር ውስጥ መተካቱ የውጭ ምንዛሪን ከማዳን በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ለማቅረብና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት እንደሚያግዝ አስረድቷል።
የግብርና ተረፈ ምርት በከፍተኛ መጠን መኖሩን የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው፤ ለኢንዱስትሪዎች የኃይል ግብዓት ለማቅረብ ችግር እንደማይኖር፣ በሌላ በኩልም ከግብርና ተረፈ ምርት የሚገኘው ከሰል በዋጋ እርካሽም እንደሆነ ያስረዳል።
የኢንዱስትሪዎች ኃይል ፍላጎታቸውን በርካሽ ወጪ ማግኘት ከቻሉ ብዙ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያስችላቸው እንደሆነም ይናገራል። በኃይል አቅርቦት አለመኖር ምክንያት የሚሸሹ የውጭ ኢንቨስተሮችንም ለመሳብ የሚረዳ እንደሆነም ያስረዳል።
ወጣቱ እንዳለው በዚህ ወቅት በዋጋ እጅግ ውድ የሆኑት የወረቀት፣ የጅብሰም፣ የሲሚንቶ ምርቶች የውድነታቸው ምክንያት የኃይል አቅርቦት ነው። በኢንጂነሪንግ፣ በኢኖቬሽን፣ በቴክኖሎጂ ብዙ መፈታት የሚችሉ ችግሮች መኖራቸውንና ለነዚህ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች የመፍትሔ ሃሳብ ለማመንጨት መትጋት የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነ ይገልጻል።
እግዜርያለው እንደሚናገረው፤ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በሌሎችም የኢትዮጵያን ዕድገት በሚያሳልጡ ዘርፎች ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ቢገኙም ያላቸውን ርዕይ ወደ ተግባር ለመለወጥ በርካታ ተግዳሮቶች ይጋፈጣሉ። ስለዚህ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ማድረግ አለባቸው። እነርሱም እጅ ባለመስጠት እስከመጨረሻው መትጋት እንዳለባቸው ያሳስባል።
‹‹ወጣቱ በፈጠራ ለሀገሬ ምን ማበርከት እችላለሁ ወይም እፈልጋለሁ ከሚል ሃሳብ ነው መነሳት›› ያለበት የሚለው ወጣት እግዜርያለው፤ ኢኖቬሽን ወደራስ ያተኮረ እንዳልሆነ፣ ሌላውን መጥቀም፣ ማገዝ፣ መርዳት፣ መደገፍ ችግሩን መፍታት ለይ ያነጣጠረ መሆኑን ይገልጻል። ‹‹ችግርን በፈጠራ በምርምር መፍታት መቻል አስደሳችና ለሕይወት ትልቅ ትርጉም ይሰጣል። ወጣቶች፣ በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ትኩረትና ሃሳባቸው ችግሮችን በመፍታት ላይ እንዲሆን ማበረታት ያስፈልጋል›› ሲልም ሃሳብ ሰጥቷል።
ወጣቱ እንዳለው ጊዜው የቴክኖሎጂ ነው። በመሆኑም መሥራት ስለምንፈልገው ነገር ማንኛውንም መረጃ በእጃችን በስልካችን በቤታችን ውስጥ ሆነን በመጠቀም የፈጠራ ባለሙያ መሆን እንችላለን። ዘመኑ ያመጣውን የቴክኖሎጂ ዕድል ፋይዳ ለሌላው ነገር ሳይሆን፤ ለቁምነገር በማዋል እራስን ለተሻለ ነገር ማዘጋጀት ይገባል። ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ በውጭ ሀገር ላይ ጥገኛ እንዳትሆን ወጣቶች ሀገር ውስጥ ያለውን ሀብት በመጠቀም መሥራት እንዳለባቸው ያስረዳል።
ወጣቱ ፈጠራና ምርምር ላይ ትኩረት ቢያደርግ ከራሱ አልፎ ሀገርንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚናገረው ወጣት እግዜርያለው፤ በሀገር ደረጃ ዘላቂ የሆነ ዕድገት እንዲረጋገጥ ካስፈለገ የሚሠሩ ሥራዎች በቴክኖሎጂ የተደገፉ መሆን እንዳለባቸውም አመልክቷል። አዲስ ነገር ለማወቅና ለመሞከር የተዘጋጀ ወጣት መኖር እንዳለበትም ይናገራል።
በሥራ ወቅት ነገሮች እንደታሰቡት አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ትክክል እንዳልሆነ ወጣቱ ግንዛቤ ሊይዝ ይገባል የሚለው ወጣት እግዜርያለው፤ ‹‹ያለን ገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የሥራ ቦታ፣ የገበያ ትስስር ወዘተ በምንፈልገው ልክ የመሆን ዕድሉ ጠባብ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ያሉንን ነገሮች ቅደም ተከተል በማስያዝና በሁነኛ መንገድ በማቀናጀት መሥራት መቻል አለብን›› ሲልም ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።
ወደፊት ማሳካት ስለሚፈልገውም የፈጠራ ባለሙያው ወጣት እግዜርያለው እንደገለጸልን፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማሽን ማምረቻ ኩባንያ የማቋቋም እቅድ አለው። የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትን ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢትዮጵያ ግብዓት ለመግዛት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ወጭ ለማዳን ነው ፍላጎቱ። በሥራውም ለሌሎች ተምሳሌት ለመሆን ነው ጥረቱ።
የምርምርና የፈጠራ ሥራ በእጅጉ ፅናት፣ ትጋት፣ ሀብት እንደሚፈልግም ይገልጻል። እርሱ እነዚህንና ሌሎችንም ተግዳሮቶች ተቋቁሞ አሁን ላይ መድረስ ቢችልም ከሀገር አልፎ ለውጭ ለማቅረብ የሚያስችለውን ግዙፍ ኩባንያ ለማቋቋም ያቀደውን ለማሳካት ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠበቅበት አስረድቷል። ወጣቱ ጥረቱን በሃሳብና በተለያየ መንገድ በማገዝ ከጎኑ ለነበሩት ሁሉ ምስጋና አቅርቧል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም