ከአደፍርስ ጥላ ሥር

ነገር ከዓይን ይገባል፤ እውነት ግን ከልብ ነው… እውቀትን ሰፍረው ሰጡንና ብዙ ያወቅን እየመሰለን የምናውቀው ግን ጥቂት መሆኑ ነው። ይህን እንዳስብ ያደረገኝ አደፍርስ ነበር። ያኔ ገና ትውውቃችን ከመጀመሩ አስቀድሞ ዳኛቸው እያሞካሸ ያወራለትንና ከአዲስ አበባ ወጥቶ በገበሬ ማህበር ውስጥ የተቀመጠውን አደፍርስን ለማየት ጓጓሁና እኔም ተከትዬ ለመሄድ ወሰንኩ። ልቤ ቀደመ ማለት ነው…ካለበት ደርሼ ዓይኔን ሳማትር ከአንዱ ዋርካ ስር ገበሬውን ሰብስቦ ተመለከትኩ።

ሲያዩት ለዓይን የማይሞላ፤ ገበሬ ያውም የገበሬ አምባሳደር እንጂ ሀገርና ሕዝብን በብዕር የተሸከመ ሊቀ ሊህቃን አይመስልም። ብቻ ግን ከስሩ ለተሰበሰቡት ገበሬዎች ምኑን እንደሆን እየቀዳ ያንዠቀዥቅላቸዋል፤ እነርሱም አፋቸውን ከፍተው ይሄን የነገር ውሃ የሚጠጡት እንጂ በተመስጦ እያደመጡት ብቻ አይመስሉም። የወሬ ሱስ አይደለም፤ የሚነግራቸውን ለማድመጥ ቋመጥኩና በቶሎ መጽሐፉን ገለጥኩት። አደፍርስ… ዳኛቸው ወርቁ የዓይን ሳይሆን የልብ እንቁ መጽሐፍ ነው። ስለመኖር ሳይሆን መኖርን፤ ስለሀገር ሳይሆን ሀገርን ያሳየናል።

እየወደድን ባናነበው እንኳን አንብበን መውደዳችን ግን የማይቀር ነው። ዳኛቸውም አደፍርስም፤ ሁለቱም እንዲህ ያሉ ናቸው። ሲያዩዋቸው የማይመስሉ ሲገልጧቸው በሀገር የሚመሰሉ ናቸው። በብዙ ጥራዝ በተጠገጠጉት በእያንዳንዱ የመጽሐፉ ገጾች ውስጥ የምናውቃቸው የመሰሉን፤ ግን የማናውቃቸው ደብዛዛ መሳይ የእውቀትና የጥበብ ወጋገን እንደዋዛ ይንቦገቦግባቸዋል።

ዳኛቸው ወርቁ፤ እንዲህ ለተመለከተው ሁሉ መልኩ እንደ ‘አብስትራክት’ ስዕል እየተለዋወጠ ምሁራኑን ሳይቀር በጎራ ለይቶ በሙግት ለማፋጀት ያበቃውን፤ እንዲህ ያለ ጠብሰቅ ያለ መጽሐፍ ለመጻፍ እንዴት ተቻለው? ብዬ እራሴን ጠየኸሁና…ከብዙ የምናብ ድክርቴ መሃል ያገኘሁት አንድ ነገር ቢኖር ደራሲው ለጥበብ የቆመ አብዮተኛ፤ እንዲሁም በዘመኑ ማንም ልብ ብሎ ያላጤነው አንድ ግዙፍ ጽንሰ ሃሳብ የተሸከመ ስለመሆኑ ነው። አደፍርስ የዋዛ መጽሐፍ ብቻ አይደለም።

የአደፍርስ ጽንሰ ሃሳብ ላልገባው ሰው፤ በቃ ምኑም የማይገባ ድፍን ስሜት ነው። ወዲያ ቢሉት ወዲህ ፍንክች አይልም። ለዚህም ነው ጥቂት የማይባሉ አንባቢያን “አሁን ይሄ ምኑ የሚሞገስ መጽሐፍ ነው? ያለ ቂቤ እንደበሰለ ቋንጣ ችክ ብሎ ከጣዕም አልባነቱም ለጥርስ የማይታኘክ ችኮ ነው” በማለት ይህን ያህል ስለመወደዱ ግርምትን ያጭርባቸዋል። የአደፍርስ ሕብለ ሠረሠር የሚገኘው በዓይን አልፈው ከሚገቡት ፊደላት ላይ አለመሆኑ ነው። ከፊደላቱ ምስል የሚወጣው ብናኝ፤ ላልገባው ዓይን የሚያጠፉ አቧራ፤ ለገባው ልብን የሚያበሩ የብርሃን ጨረር ናቸው።

አደፍርስ የዚህ መጽሐፍን የታሪክ ወርቅና አልማዝ የተሸከመና ሠረገላውን ይዞ የሚወነጨፍ መንኩራኩር ነው። ዳኛቸው ወርቁ ከሁሉ መርጦ የዋና ገጸ ባህሪውን ማህተብ፤ የሃሳቡን ክታብ ከአንገቱ አስሮለታል። አደፍርስ እራሱን መጽሐፉን የመሰለ ለዓይን የማይሞላ የልብ አውቃ ልብ አድርስ ነው። ከወዲያ ቆሞ ከተመለከተው ይልቅ ወዲህ ቀርቦ ላደመጠው ድንቅ ወጣትነቱ ይገለጣል። የ 24 ዓመቱ አደፍርስ ሰበብ፤ መዘዝ የማያጣው ነውና የርሱ መዘዝ በምናብ ለወለደው ዳኛቸውም መትረፉ አልቀረም ነበር። አደፍርስ እንደ ስሙም አደፍርስ ነው።

ስምን መልአክ ያወጣዋል፤ ዳኛቸውም እንደ መልአክ ሆነ። መጽሐፉ ለሕትመት ከበቃ በኋላ ብዙዎቹን አስኮርፏል፤ አለቆቹንም አስቆጥቷል። ‘አይ አደፍርስ…የስራህን ይስጥህ’ ሲል፤ በ1966ዓ.ም የነበረበትን የሥራ ገበታ ጥሎ ለመሄድ ተገዷል። ዳኛቸው፤ አደፍርስን እንዲህ ነበር የገለጸው፤ “… አደፍርስ፣ ፊተ ሰልካካው ባለሃያአራት ዓመቱ ወጣትን፤ ነገርተኛ ቀርቦ ሲከብበው እና ሲያደምጠው ደስ እያለው ምክር በተለይ በመስጠት ያስተናግዳቸው አለ…. ደብረሲና አደፍርስ ትንሽ ከርሞ በመቀጠል ወደ አጎቱ ችሎት ወረደ።

ብዙዎች የዋና ዳኛው እህት ልጅ በማለት ለምልጃ ይቀርቡት ጀመር። ዳሩ፤ ከማማከር እና ማውራት በቀረ ብዙ ማማለዱን አይከውንም ነበር” አደፍርስ መቼቱ የታነጸው በሰሜን ሸዋ ከደብረ ሲና ተራሮች አናትና እምብርት ላይ ነው።

ዳኛቸው የተወለደባት፤ እትብቱ የተቀበረባት ሥፍራ ናት። በአደፍርስ ገና ሲጀምር እንዲህ በማለት ይቀድሰዋል፤ “በሰሜን ሸዋ ዞን፤ ይፋት እና ጥሙጋ አካባቢ ኑሮው፤ ከሌላ ሞቅ ያሉ መኖሪያዎች በተለየ፤ እጅግ ቅዝቅዝ ብሎ በህመም ላይ እሚገኝ ነው።

መልክዐምድሩ በከባዱ አስቸጋሪ ሆኖ፤ አኗኗር እጅግ አርብቶ እና አርሶ አደርነት የሞላው እና ከእጅ ወደአፍ እንደሆነ የቀረ፤ በሃይማኖት እና ታሪክ ሥነሥርዓት እና ሂደት የተተበተበ፤ በጠቅላላው እጅግ አስቸጋሪ፣ ያንቀላፋ እና የታመመ ሕይወት ነው” ታሪኩ ሲቀጥልም አደፍርስ ለሥራ ተመድቦ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ በመውጣት ወደዚህ ይሄዳል።

አካባቢውን ከመልመድ ጀምሮ ኖሮ ቤተኛ እስከሚሆንበት ድረስ የገጠመውንና የሚገጥመውን ሁሉ በአስደናቂ የቋንቋ ፍልስፍና ጠፍጥፎ ሞልሙሎታል። አደፍርስ ሙልሙልም ድንጋይም ነው። ያወቀበት በልቶ ረሃብን ያስታግስበታል፤ ያልገባው አድርቆ ይፈናከትበታል። ብዙዎች “አወዛጋቢው ደራሲ…አወዛጋቢው መጽሐፍ” እያሉ የሚገልጹትም ለዚሁ ነው።

አደፍርስ ልቦለዳዊ ዘውግን የተከናነበ እንዲሁም ደግሞ ቁመናና መልኩ ሁሉ በልብወለድ ልኬት የተሰፋ ቢሆንም፤ ከሌሎች የልብወለድ ሥራዎች አንጻር ስንመለከተው ግን ወጣ ያለ ሌላ ባህሪም ጭምር የተላበሰ ስለመሆኑ እንገነዘባለን። በ1962ዓ.ም ታትሞ ለንባብ የበቃው ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያ የዘመናዊ የሥነ ጽሁፉ ታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ ይነገርለታል። ከዚያ አስቀድሞ የዘመናዊ ሥነ ጽሁፍን የመግቢያ በር የደረሰበት ጸሐፊ እምብዛም አይታወቅም።

ታትሞ የወጣም መጽሐፍ ባለመኖሩ ዳኛቸው፤ የማንን ፈለግ ተከተሎ አገኘው ቢባል፤ ምናልባትም ምላሹ ሊሆን የሚችለው…የራሱን ነው የሚል ነው። ይህ ጥያቄ ለራሱ ለዳኛቸው ቢቀርብለት ኖሮ “የራሴን ጥላ ምናባዊ ዱካ ተከትዬ ስሄድ ወስዶ ከአንዱ ጋር አደረሰኝና ከዚህ ነው ሲል ልቡስጥላዬ አመለከተኝ” በማለት የሚመልሰው ይመስለኛል። ባይሆን እርሱን ተከትለው ወደ ዘመነኛው የሥነ ጽሁፍ መንደር የገቡ ብዙ ናቸው። የልቦለድ መሳጭነቱ ከልብ አንጠልጣይነቱ ላይ መሆኑን የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ መጽሐፍት ይነግሩናል። እኛም ይህቺን አብዝተን እንወዳታለን። አድፍርስ ግን ይህችንም ልማድ ሳያደፈርሳት አልቀረም።

ልብን እያንጠለጠሉ በስሜት ባህር ከመድፈቅ ይልቅ ጭንቅላትን እየሰቀሉ በእውቀት ውቅያኖስ ውስጥ መድፈቅን ይመርጣሉ። በአንዲት የታሪክ ሴራ ውስጥ ውሎ እያደረ አጀብ አያስነሳም። በዚህም ምክንያት ምንም አይነት ድግግሞሽ አይታይበትም።

ቋንቋ ጸሀፊው እፍ..ብሎ ነብስን የሚዘራበት የሥነ ጽሁፍ እስትንፉስ ነው። ከአዕምሮ እየፈለቀ በጠብታ የብዕርን ጓዳ የሚሞላ እንቁ ሀብት ነው። በአደፍርስ ግን ከምንጩ ተኝቶ የዋኘበት ይመስላል። ለአፍላና ትኩስ አንባቢማ ‘ይህ መጽሐፍ ግን አማርኛ ነውን? ወይንስ አማርኛን አላውቅም ኖሯል?’ እያስባለ እራሱን ማስረሳቱ የማይቀር ነው።

ደህና ይወስድ ይወስደንና ደግሞ እንደገና ምኑም ከማይገባን ግዙፍ የሾላ ዋርካ ስር አስቀምጦን እብስ ይላል። ተቀምጦ አዙሪቱ፤ ልብን ውርድ ሲያደርግ ‘ኤጭ ወዲያ! አሁንስ በዛ’ የሚያስብል ቢሆንም፤ ቅሉ ታግሶ ዙሪያ ገባውን ተመልክቶ ለታገሰ ከሾላዋ የሚረግፈውን ፍሬ ቀምሶ ያጣጥማል። ዳኛቸው እንደሆን ማንም በጊዜው ያልተረዳው የቋንቋ ፈላስፋ ነው።

የአማርኛ ቋንቋን ስጋ በልቼ በመረቁ ያወራረድኩ ነኝ በማለት ስንኩራራ ድንገት ‘ልቡስጥላ፣ ህግዘብ፣ ፍደሳ…’ እያለ ባበሳ፤ በግድንግድ ቃላቱ ሲገርፈን ልክ እየገባን፤ እኚህን ባለማወቃችንም፤ እንዴት በማለት ከራሳችን ጋር እንፋጅ ይሆናል። የአደፍርሱ ዳኛቸው ግን ፤ አልበቃህ ብሎት የራሱን አዳዲስ የአማርኛ ቃላት በመፍጠር ላይ መሆኑ ነው። ደግነቱ ድረሱበት ሲል አጋፍጦ አይተወንም። እናስ? ስትሉ “ልቡሰጥላ፣ በድብቅ ጭንቅላትዎችአችን ከልጅነት ጀምሮ እሚጠራቀምብን እምናውቀውን እምናየውን እምንወድድ እምንጠላውን ሁሉ የተሸከመ የመረጃ ቋት ነው። ያ እሚገነባው ከልጅነት ጀምሮ በምንሰማው፣ እምናደምጠው፣ እምንመለከተው፣ እምናነብበው፣ ከቤተሰብ ዙሪያ ሳለን እምንመለከተውን በአብነት በመቅዳት ነው” በማለት እያመራመረ ያስተምረናል።

አደፍርስም እንዲያው ነው፤ ሰብስቦ ማስተማር…እየተከራከሩ እውቀት መቃረም…ከትንሽ ትልቁ እየተጨዋወቱ የማህበረሰቡን አዕምሮ መሞረድ በፍቅር የሚወደው ነገር ነው። ከዘመኑ ቀድሞ የመጣ ዘመነኛ ጌጥም ነው። የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች የትየለሌ ናቸውና ጨዋታ አያልቅበትም። ታዲያ ጨዋታውን ናፍቀው አደፍርስን ፍለጋ ካለበት ድረስ መጥተው ልባቸው እስኪሰወር በጨዋታው ተመስጠው ሲያደምጡት ይቆዩና መልሶ ልባቸውን ውልቅ እያደረገባቸው በመሃል ጥለውት ሲሄዱም እንመለከታለን።

ቅኔ አዘል ያልተገለጡ መጋረጃዎች ያሉት በትምህርትና ምክሮቹ ውስጥ ብቻ ከመሰለን ብዙ ስተናል። በጨዋታዎቹ ውስጥ ሸጎጥ የሚያደርጋቸው እልፍ ጉዳዮችም አሉ። ከመጽሐፉ በጥቂቱ ስንቀነጭብ፤

“እሺ ብሎ፤ እየቀጠለ፤ ተኝቼ ድምጽ ሰማሁ እና ስነቃ ጌቶች ስምአይጠሬን ሊጠሩ ነው ሲባባሉ ጓጉቼ ልመለከት ስነሳ የሆነ ነገር ጎትቶ በደረቴ ወደታች አነጠፈኝ። ስምአይጠሬ መስሎኝ ላየው ፈራሁ። ስጮኽ ሁለት እረኞች አጠገቤ አየሁ። አደፍርስ ሳታየው ጨረስክ እጅግ ሰነፍ ነህ አበቃ ወሬው ‘ሞት እና ሕይወት ድንቁርና እና ዕውቀት!’ ብሎ ሁሌ እሚጠቅሳትን አባባል አቀረበ።

….

ዶሮውን ሴትዎች በማመራረጡ እንደሰው አመለካከቱ ሳይቀየር አንዴ የወደዳትን እንደእማይቀይረው እሚፀኑ አለመሆንአቸውን በላይ ሲያነሳ፤ አደፍርስ ሰው ከውጭአዊ እይታ በላይ ውስጥአዊ እይታዎች እንደአሉት ጨምሮ ገለጠ

በላይ ግን ገና መጀመሬ ነው ብሎ ቀጠለ። ፍግ ላይ ቁስዎችን ቆለሉ። ሰውዬው ስም እየጠሩ ሲያነብቡ፣ ሰዎቹ ቀምበጥ ከመያዝ እና በሀፍረትአቸው ቅጠል ከማስቀመጥአቸው በቀረ ምንም ሳይለብሱ ራቁት በቂጥአቸው አካባቢ ይጨፍሩ አለ”

በአደፍርስ፤ ዳኛቸው ኖሮ ያለፈበትንና እየኖረ ያለውን ዓለም ብቻ አይደለም ሊያሳየን የሚሞክረው። በኖርነውና በምንኖረው ድክርታም የሕይወት ዓለም ውስጥ ምንም የተለየ ነገር አለመኖሩን ስለተረዳ መጋረጃውን ገልጦ ከአድማስ ወዲያ ማዶ ሌላ ያልታየ ዓለምን ያስመለክተናል። ቀን ላይ ካለፍንበት ሀሩርና አሁን ካለንበት ጨለማ ይልቅ የነገዋን ጸሐያማ የማለዳ ጀንበር እንድንናፍቅ ዘንድ ይነግረናል።

በአደፍርስ ስሞች ለመጠሪያነት የሚያገለግሉ እንዲሁ ስም ብቻ አይደሉም። ቆም ብሎ በአዕምሮው ላሰናሰናቸው አንዳች ስውር እንፋሎት አዘል ናቸው። የራሱን የፈጠራ ቋጫ እየገመደ በፍካሬ አጋምዷቸዋል። አንዳንዴም ከሚስማር ላይ እንደሚያርፍ መዶሻ የጠነከሩ ሆኖ እናገኛቸዋለን። ጭሰኛው ገበሬ አቶ የየየየ፣አፍአዊ፣ ፍሬዋ ቀጫጫ፣ አባ ስብከት፣ ጎርፉ፣ ዋና ዳኛ ጥሶ በበረንዳው እና ሌሎችም መዶሻዎች ይገኙበታል።

ዳኛቸው እነዚህን እየተጠቀመ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግብሮቻችንን ለማቅናት ክንዱን ሲያፈረጥም እናገኘዋለን። የሚከውነው ብዙ ነው። ይሞርድበታል፤እያረሰ ይዘራበታል፤ እያጨደ ይሰበስብበታል፤እየወቃ ያነፍስበታል። የተማረው ምርጡ ገበሬ፤ አደፍርስ ደግሞ ምርቱን ከግርዶ ለመለየት በገበሬ ማህበሩ የተገኘ፤ በዳኛቸው ተሹሞ በእውቀት ቅባት የተጠረገ አዲስና ልዩ የሆነ የብርሃን ፍኖት ነው። አንዳንዴም ከማህበረሰቡ ልማድና ወግ እያፈነገጠ ሊያመልጥ ሲል ከፊት በግንባሩ እየተጋጨ ሲወድቅ ሲነሳ እንመለከታለን። በዚህ ሁሉ የሚያስተምር ብቻም ሳይሆን የሚማርም ጭምር ነው። ሥልጣኔን፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥን ይሻል። የኛ የራሳችን የሆነውን ከዘመኑ ጋር ስለማወዳጀት እንጂ በባዕዳን ጫማ እግር ከተን መሬት ለመሬት እንድንጎተት አይፈልግም።

አደፍርስ የሚነግረን ብዙ ቢሆንም ይህችን ግን እህችን ግን እናድምጠው፤”ዛሬ፤ ከልጅአቸው ፍሬዋ ጋር ስለኢትዮጵያ መነጋገር የቀጠሉት ስለሀገር ማስተማሩን ሆኖ፤ መልካም ወግ፣ ልማድ እና ቅርስዎች ሀገርአችን እንዳላት እና ሥልጣኔ የግድ ከውጭ እንደእማይመጣ መክረው ነግረው እስአቸውም በሀገርአቸው እንደእሚኮሩ አሳውቀዋት እንድታጠና አበረታቷት።

….

ሁላችንም እኩል ባንሆንም፣ ከመሀከላችን የበላይ ወይም የበታች የለም። ሁሉም በገባው መጠን በምድር ይመላለሳል። በዚህ አጭር ከንቱ ኑሮ ሁለት ነገሮች እርግጥ ናቸው—ፍቅር እና ሞት። በፍቅር እየኖርን አንዴ ብቻ እንሙት። በቁም ከመሞት የከፋ ነገር የለም። ፍቅር አልባ ሕይወት በቁም ደጋግሞ መሞት ነው”

ዳኛቸው ወርቁ ብዕር ተፈጥሮ የቸረችው ስጦታው ነበር። ገና የ13 ዓመት ልጅ ሳለ “ያላቻ ጋብቻ ትርፉ ኀዘን ብቻ” የሚል ድንቅ ቲያትር በመጻፍ እውነተኛ የጥበብ ልጅነቱን አስመስክሮበታል። በርካታ ሥራዎችን የሠራ ቢሆንም፤ ከአደፍርስ ቀጥሎ ገዝፎ የሚታወቅበት ሌላኛው በእንግሊዝኛ ተጽፎ በብዙ የአውሮፓ ቋንቋዎች እስከመተርጎም የደረሰለት “ዘ ሰርቲንዝ ሰን” የተሰኘው መጽሐፉ ነው። መንታው ባይሆንም ልክ እንደ አደፍርስ ያለ ነው።

ዳኛቸው በሕይወቱ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በብዙ ነገሮች ደስተኛ አነበረም። ብቸኝነትና ቁዘማ እየተጫጫነው በዝምታ ተውጦ ነበር። ምናልባት ከአደፍርስ ጀምሮ የሻተውን ምኞት ለማየት አልቻለም ይሆናል። ከየካቲት 16 ቀን 1928ዓ.ም ከደብረሲና የጀመረው የሕይወት ጉዞ በኅዳር 22 ቀን በ 1987ዓ.ም በአዲስ አበባ ተገታ። ዳኛቸው፤አስክሬኑ ወደ ደብረሲና ተወሰደ። እንደሠራቸው ታላላቅ ሥራዎች ግን፤ ለአስክሬኑ እንኳን በቅጡ ሽኝት አልተደረገለትም ነበር። እሱ ሄዷል። እትብቱን ተቀብላ ወደ ሕይወት የሸኘችው ምድርም መልሳ በድን አካሉን ተቀበለች።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You