እነተሰማ መንግሥቴ፣ ገብረየስ ገብረማሪያም እና ዘውዴ መታፈሪያ እንደልማዳቸው በማምሻ ግሮሰሪ ተገናኝተዋል:: የዕለቱ ውይይታቸው ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎችን እና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህል ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ጠንከር ያለ ቃላት ሲሰናዘሩ ነበር:: ተሰማ ‹‹ኢትዮጵያውያን ሰላም ለማምጣት የሚያግዝ መልካም ባህል አላቸው፤ ይህንንም ሲያሳድጉት ኖረዋል›› ሲል፤ ገብረየስ በበኩሉ ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ከሰላም ይልቅ እልህ በማብዛት ጦርነትን ያዘወትራሉ ይህ ተግባር አሁንም ሀገሪቱን እየጎዳት ይገኛል::›› የሚል ሃሳብ አቀረበ::
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹የኖረ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ሽምግልናን የመሰለ ምርጥ የመወያያ እና ተነጋግሮ ችግር የመፍታት ባህል አለ:: ነገር ግን በሴራ ፖለቲካ ምክንያት ይህ ምርጥ ተነጋግሮ ችግሮችን የመፍታት እና ከግጭት ይልቅ ሰላምን መርጦ ያንን የማስቀጠል ሁኔታ ቆሟል:: ቀድሞም ቢሆን ተማርን በሚሉ ሰዎች አጉል ጥያቄ ምክንያት የማህበረሰብ አስተሳሰብ ተበላሽቷል:: በአጉል የፖለቲካ አስተሳሰብ የመከባበር እሴት በመጥፋቱ፤ ማህበረሰቡ በጦርነት አዙሪት ተበርዟል:: በዚህ ላይ የማህበረሰብ አስተሳሰብ ዕድገት ካልመጣ ለውጥ ማስመዝገብ እና ከግጭት እንዲሁም ከጦርነት መውጣት አይቻልም:: ነገር ግን ኢትጵያውያን ከግጭት እና ከጦርነት ይልቅ ሰላም የሚያሰፍን ባህል አለን::›› ሲል ተናገረ::
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ እውነት ኢትዮጵያውያን በእልህ ብረት ከማንሳት የወጣ በመነጋገር የሚያምን ባህል ካለን ያ ባህል የት ገባ ? ብለን መጠየቅ አለብን:: እኔ በዘመኔ የተረዳሁት ኢትዮጵያውያን እልኸኞች እና በጦርነት የምናምን ሰዎች መሆናችንን ነው:: በእርግጥ እኔም የጦርነት ተሳታፊ ሆኜ በሂደቱ አልፌያለሁ:: የጦርነትን አስከፊነት በደንብ መግለፅ እችላለሁ:: ምክንያቱም በአካል ተሳትፌ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ አረጋግጫለሁ:: ጦርነት ጉዳቱ እንዲህ በቀላሉ ተገልፆ የሚያልቅ አይደለም::
በጦርነት ያለፈ ሰው የቅርብ ጓደኛው ሲሰዋ አይኑ ስለሚያይ እና ሌሎችም ሰዎች ሲሞቱ እና አካላቸው ሲጎድል ስለሚመለከት፤ እንዲሁም እርሱም እሞታለሁ ብሎ ሲያስብ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመትረፉ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ ሕሊናው ስለጦርነት ከማሰብ ወደ በኋላ አይልም:: እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ያ ቁስል ሲያመው፣ ሲያደማው እና ሲከተለው ይኖራል:: ጠባሳው እስከ ትውልድ የሚተላለፍ ነው::
በእርግጥ አሁን ይህ ኢትዮጵያ ላይ የማያቋርጥ ልማድ ሆኗል:: ልማዱ የመጣው ገዳይ እንደጀግና ስለሚቆጠር እና ባህላችንም በገዳይነት የሚያምን በመሆኑ ነው:: እንኳን ገዳይነት ማንኛውም አንድ ነገር ከተለመደ በኋላ ነገሩን ለማቋረጥ ስለሚከብድ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ አማራጮችን ማየት ያዳግታል:: በእኔ እምነት ኢትዮጵያውያን ልዩነትን ለመፍታት ከምንመርጠው አማራጭ ውስጥ ዋነኛው እና የምንወድው ጦርነትን ነው:: ይሔ ደግሞ በምንም መልኩ አዋጭ አይደለም:: ሕዝብ አልቋል:: ንብረት ወድሟል:: እልሃችን ሀገርን ወደ ፊት እንዳትራመድ እግሯን እየጎተተ አላላውስ ብሏታል:: በዚህ ላይ መተማመን ይገባል::›› ሲል ገብረየስ የሚያስበውን ተናገረ::
ዘውዱ ደግሞ፤ ‹‹በእኔ እምነት ኢትዮጵያውያን ሁል ጊዜም የሚመርጡት ጦርነት ነው በሚለው ሃሳብ አልስማማም:: ዋነኛው ችግር ሌላ ነው:: ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው እንደሚባለው አንድ ሰው በአንድ ምክንያት ተጎዳሁ ብሎ ሲከፋ እና ሲበሳጭ በምክር ለመታገስ መሞከር እና ጥያቄውን መመለስ እንጂ መጥፎ ነገር እንዲሠራ መገፋፋት ተገቢ አይደለም:: እኔ ግጭት ለመከሰቱ ዋነኛው ችግር ማህበረሰቡ ጥያቄ ሲያቀርብ ከመታገስ እና ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አንዳንዴ ችግርን ላለማየት አይንን የመጨፈን ያህል ጥያቄን ያለመመለስ ክፍተት በመኖሩ ነው የሚል እምነት አለኝ::
ለማየት የፈለገ አይኑን ይገልጣል፤ ፍላጎት ካለ የሚፈልገውን ተግባር ማከናወን ይቻላል:: ነገር ግን አንድ ማህበረሰብ የሚፈልገውን ጥያቄ ሲያቀርብ መልስ አለመስጠት ማህበረሰቡ የሃይል አማራጭ ውስጥ እንዲገባ መገፋፋት ነው:: በእኔ እምነት የሕዝቡ ባህል ግጭት ወዳድነት ላይ የተለጠፈ ሳይሆን ምላሽ ባለማግኘቱ ግጭት እየተፈጠረ ነው የሚል እምነት አለኝ:: ›› ሲል ተናገረ::
ተሰማ ዘውዴንም ገብረየስንም ሳይቃወም፤ መሃል ላይ መሆኑን በሚያሳውቅ መልኩ ‹‹ጦርነት እና ግጭት የኢትዮጵያውያን መገለጫ ስለመሆኑ መካድ ለእኔ ከባድ ነው:: ኢትዮጵያ በተለይ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በእርስበእርስ ጦርነት እና ግጭት ስትታመስ ቆይታለች:: ይህ ዘውዴ እንደገለፀው የማህበረሰብን ጥያቄን ከመመለስ እና ካለመመለስ ጋር ብቻ የተያያዘ አይመስለኝም:: ምክንያቱም ከእርስ በእርስ ባሻገር ጦረኞች መሆናችንን ጥንት ከድርቡሽ ጋር፣ ከጣሊያን እና ከሶማሌ ጋር ባካሔድነው ጦርነት ላይ አስመስክረናል:: ያለፉትም ሆኑ ያለው መንግሥታት የማህበረሰብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት አድርገዋል፤ ጥረትም እያደረጉ ነው::
ነገር ግን ሆድ እና ጀርባ ከመሆን መዳን አልተቻለም:: በክልሎች ውስጥ አንዳንዴም በክልሎች መካከል የሚደረግ ግጭትን ከሥሩ ለመንቀል አዳጋች ያደረገው ጥያቄዎች ባለመመለሳቸው አይመስለኝም:: እኔ እንደማምነው ጦርነትን ባህላችን በማድረጋችን ይመስለኛል::›› ሲል ተሰማም ያሰበውን ተናገረ::
ዘውዴ ተቆጣ፤ ‹‹ይህማ ትክክል አይደለም:: እንዴት ሰው ጦርነትን ባህል አድርጎ ዘላለሙን ሲዋጋ ይኖራል ? ለእኔ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሀገር ውስጥ ለሚፈጠሩ ጦርነቶችም ሆነ ግጭቶች መነሻው የፖለቲካ ሴራ ነው:: የሴራው ተሳታፊዎች እና የጦርነት ወይም የግጭት ደጋፊዎች የአንዱ መነካት ለሌላው መጎዳት ምክንያት እንደሚሆን የማወቅ ክፍተት ነበረባቸው::
ሰዎቹ ሃረጉን ሲስቡት ዛፉ ይወዛወዛል እንደሚባል ረስተዋል:: በየትኛውም መልኩ አንዱ ሲነካ ሌላው መጎዳቱ የማይቀር መሆኑን ዘንግተዋል:: በእርግጥ አሁን ላይ ግጭት አለ:: አሁን ያለው ያለፈው ውላጅ ነው:: አሁን ያለውን ግጭት ለማስቆምም ሆነ ችግሩን ከስሩ ለመንቀል፤ ለሚያስማማ እና ለሚያከባብር ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት በዚህም ሁሉንም ወደ አንድ መንፈስ በመሳብ ውጤት ማምጣት ይቻላል:: ከዚህ ውጪ ጦርነት ባህላችን ነው ብሎ በማህበረሰብ ጥያቄ ላይ ማሾፍ ጭራሽ የማይገባ እኛን ከመሰለ ትልልቅ ሰዎች ፍፁም የማይጠበቅ ነው::›› ሲል በቁጣ ተናገረ::
ተሰማ፤ ‹‹መቆጣትም አይገባም:: ሃሳባችንን እየገለፅን ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እና ግጭት እንደባህል እየታየ እየቀጠለ ያለ ጉዳይ ነው የሚል ሃሳብ በማቅረባችን ትክክል ካልሆንን በሃሳብ ልታሳምነን ይገባል:: ቁጣም ከጦርነት ወይም በሃይል ለማሳመን ወይም በሃይል ለመግዛት ከመሞከር የተለየ አይደለም:: ‹ጥንት መከባበር ነበር:: መከባበር በመኖሩ ጦርነት አልነበረም:: የአሁኑ ችግር መከባበር በመጥፋቱ የተፈጠረ ነው::› ካልክ በደንብ ማሳያ አቅርብና እንተማመን:: ከዚህ ውጪ ግን ማንም ቢሆን ድልድይ ከሌለ ወንዝ መሻገር ሲያምረው ይዋኛል፤ ሊሞግት ያማረው ይዳኛል እንደሚባለው ነው:: አንድን ጉዳይ ለመፈፀም የሚፈልግ፤ ያሻውን ለማግኘት ይሠራል:: አሁን እንዳየነው መጋጨት የሚፈልግ በግጭት ውስጥ እየዋኘ ይቆያል:: ነገር ግን ሰላም የሚፈልግ ደግሞ ሰላም እንዲመጣ ብረቱን ጥሎ ራሱን ለውይይት ያዘጋጃል::›› ሲል የራሱን ሃሳብ ገለፀ::
‹‹ግጭት በየትኛውም ዓለም የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ተፈጥሯዊ ክስተት መሆኑ ይታወቃል:: ነገር ግን ኢትዮጵያ በምንም መልኩ ከግጭት አዙሪት ወጥታ ሙሉ ለሙሉ ፊቷን ወደ ልማት አዙራ የሠራችበት ጊዜ የለም:: ለዚህ ዋነኛው ምክንያት በእኔ እምነት ፖለቲካው ለዜጎች ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠቱ ነው::›› የሚል እምነት አለኝ ሲል ዘውዴ ሃሳቡን ለማጠናከር ሞከረ::
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ግን ደግሞ መታየት ያለበት ነገር አለ:: ሁሉም ጦርነት እና ግጭት መነሻው ተገቢ ጥያቄ ነው:: ብሎ መደምደም አይቻልም:: ሁሉም ጥያቄ መመለስ አይችልም:: ለምሳሌ የፕሬዚዳንትነት ጥያቄ ቢነሳ ፕሬዚዳንት መሆን የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ነው:: ከእዛ ውጪ 150 ሺህ ሰው የፕሬዚዳንትነት ጥያቄ ቢኖረው ሁሉም ያሻውን ሊሰጠው አይችልም:: ለአንዱ ሲሰጥ ለሌላው መከልከል የግድ ነው:: በሌላ በኩል ይህ ሁሉ ቢሆንም በሆደ ሰፊነት ለሁሉም በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እየቀረበ ነው:: ነገር ግን ምላሽ በመስጠት በኩል መዘግየት አለ:: ኢትዮጵያውያን ጦርነትን እንደልማድ ተያይዘነዋል የምንለው ለዚሁ ነው::›› ሲል ተናገረ::
ዘውዴ፤ ‹‹በመንግሥት በኩል ረጅም መንገድ ሄዶ ለሰላም ጥሪ ማቅረቡ ተገቢ ነው:: ነገር ግን በውይይት ሂደት በሌላ ወገን ያለው ብቻ እሺ እንዲል ከመጠበቅ ይልቅ የራስንም ሚና መወጣት ያስፈልጋል:: ለእዚህ ዋነኛው መፍትሔ ሰጥቶ መቀበል ነው:: በእርግጥ ሰዎች ማሰብ ይችላሉ:: ሁሉም ፕሬዚዳንት እንሁን ብለው አይጠይቁም:: ቢጠይቁ እንኳ እንደማይቻል ከተነገራቸው እና በዛም ላይ እንዲያምኑ ከተደረገ ሰላም ማምጣት ይቻላል:: በሌላ በኩል መሳሪያ ይዘው ጫካ የገቡ ማንኛውም አካላት የሰላም አማራጭን በአንደኝነት ማስቀመጥ አለባቸው:: በዚህ ጉዳይ ላይ ካፈርኩ አይመልሰኝ የሚመስል ፈሊጥ አያዋጣም:: በዚህ ምክንያት የሚሞተው ሰው ነው:: ሀገር የሚወድ ለሰው ያስባል::
እኔ ኢትዮጵያውያን ጦርነትን እንደባህል ይቆጥሩታል፤ ይወዱታል መባሉን አልደግፍም:: ምክንያቱም ማንም ሰው ወዳጁ የሀገሩ ሰው እንዲሞት አይወድም:: ቢገፋበት እንጂ ማንም ቢሆን ጦርነትን እንደባህል አይለማመደውም:: አንደኛ ምርጫው አድርጎ አያስቀምጠውም:: ይህንን ልብ ማለት ይገባችኋል›› ሲል መከፋቱን በሚያሳብቅ መልኩ ተናገረ::
ገብረየስ፤ ‹‹የሚያሳምነን ማመን የማያሳምነን መተው የሁላችንም መብት ነው:: የሚዘፈነው ለገዳይ ነው:: ሰላም ላሰፈነ ሲዘፈን አናውቅም:: ገዳይ ግን ይሞገሳል:: ይህንን እውነት መካድ አይገባም:: ዋናው ጉዳይ ይህ ከሆነ በምን መንገድ ዜጎች ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጡበትን ሁኔታ እናመቻች፤ በሚለው ላይ ብንነጋገር ይሻላል::
ችግሩን ለማቃለል መጀመሪያ ችግሩ መኖሩን ፤ ችግሩ በምን ያህል መጠን ሥር እንደሰደደ ማወቅ ያስፈልጋል:: ብዙ የጦርነት ታሪኮች አሉን:: ይህንን በታሪክነት ትተን ባህላችንን በተቃራኒው ባለን የሰላም መንገድ ላይ መመስረት አለብን:: በእርግጥም ሰላም ማስፈን የሚያስችሉ በየባህሉ የሽምግልና ባህሎች አሉን:: ይህንን ባህል እንጠቀምበት::›› ሲል ሃሳቡን ሲያስተላልፍ፤ ተሰማ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ በመጨበጥ በሃሳቡ እንደሚስማማ ገልፆ የጠጡበትን ለመክፈል እጁን ወደ ኪሱ ሰደደ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም