መንግሥት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ነው:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሦስት ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አላቸው:: እነዚህ ተልዕኮዎቻቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማከናወን ናቸው:: ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል የሥራ ዕድል በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢን እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል::
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ሥፍራ ላይ ሰብስበውና አቀናጅተው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሠረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ:: ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም በአንፃራዊነት በዝቅተኛ ዋጋ የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል::
በአሁኑ ወቅት፣ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ፣ በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን፤ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ:: በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ ዘርፍ መናኸሪያ (Manufacturing Hub) እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተውበታል::
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙትን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን ለማስፋትና ከኢንቨስተሮች ጋር ያለውን ትስስር ለማሻሻል ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ልዩ ልዩ የአሠራር ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል:: እነዚህ የሪፎርም ተግባራት ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪያላይዜሽን ሂደት ለማፋጠን ለሚያደርገው ጥረት ቁልፍ ግብዓቶች እንደሚሆኑ ታምኖባቸዋል::
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሀገሪቱ ከውጭ ንግድ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንድታገኝና ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ 750 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንድትችል አድርጓል:: በእነዚህ ተግባራቱ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል:: ከዚህ ባሻገር ከ80 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል፤ ሠራተኞች በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እውቀትና ክህሎት ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል::
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ልማት ለማሳደግ ከተደረጉት ጥረቶች መካከል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከናወነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ጥረት መሠረት በማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪያላይዜሽን ሂደቱን ለማፋጠን የድርሻውን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ይገልፃሉ:: እሳቸው እንደሚሉት፣ ኮርፖሬሽኑን ለዘመኑ የሚመጥን እና ለኢንቨስተሮች ምቹ የማድረግ ጥረቶች አካል የሆኑት የሪፎርም አጀንዳዎቹ፣ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው::
ግልፅ የሆነ የኢንቨስተሮች መመልመያ መስፈርት፣ ቀጥተኛ የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን / ማስተዋወቂያ/ ዘዴዎች እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የማበረታቻ ማዕቀፎች ዝግጅት፤ አዲስ የመዋቅር ጥናትና ትግበራ፤ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ትብብር መፍጠሪያ እና የዲጂታል አሠራር ሥርዓት ተግባራት ኮርፖሬሽኑ እየተገበራቸው ከሚገኙት የሪፎርም ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው::
‹‹መንግሥት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች አመቺ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል:: የኢትዮጵያን እምቅ የኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ወሳኝ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳዎችን ይፋ አድርጓል:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሪፎርም አጀንዳዎችም እነዚህን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በብቃት የማስፈፀም ዓላማ አላቸው›› ይላሉ::
አቶ አክሊሉ፣ ኮርፖሬሽኑ ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ያስረዳሉ:: ኮርፖሬሽኑ የተገበረው የ ‹‹ጎልደን ሪሴፕሽን›› (Golden Reception) ሥርዓት ባለሀብቶች ከውጭ ሲገቡ በኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር አቀባበል ተደርጎላቸው በአጭር ጊዜ እንዲስተናገዱ ያስቻለ የአሠራር ሥርዓት ነው:: ይህ አሠራር ከዚህ ቀደም ኢንቨስተሮቹ መጥተው ለብዙ ቀናት እንዲቆዩና የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ለሚያስገድደው የአሠራር ችግር መፍትሄ ሰጥቷል::
የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ሃሳብ (Proposal) የሚገመገምበት ግልፅ የመመልመያ መስፈርት ተዘጋጅቷል:: ኮርፖሬሽኑ የጀመረው ‹‹ዜሮ ዌይቲንግ ታይም›› (Zero Waiting Time) የአሠራር ሥርዓት፤ የኢንቨስትመንት ሃሳብ በቀረበበት ቀን ተገምግሞ እንዲያልቅ፣ የሚስተካከሉ ነገሮች ከሌሉ፣ ባለሀብቶች ወዲያውኑ ወደ ፓርክ እንዲመሩ፣ ፓርኩን እንዲመለከቱና የቦታ ርክክብ እንዲያደርጉ የሚያስችል ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ ዘዴ ነው::
ገበያ የማፈላለግና የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራዎችም የሪፎርሙ አካል ናቸው:: ‹‹ኢንቨስትመንት መምጣት ያለበት ፈልጎን ሳይሆን እኛ ፈልገን ማምጣት አለብን ብለን ለአውሮፓ፣ ለእስያ እና ለአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ገበያ ይህን የሚከታተል ልዩ ቡድን አዋቅረን፣ ወደነዚህ አካባቢዎች በመሰማራት ኢንቨስትመንት የምናስተዋውቅበት አሠራር ቀይረናል:: ስለዚህ ኢንቨስትመንት የምናመጣው አስተዋውቀንና ጠይቀን እንጂ፣ ባለሀብቱ ወደ እኛ መጥቶ ጠይቆና ጠብቆ አይደለም የሚስተናገደው›› በማለት ይገልፃሉ::
ቀደም ሲል በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱት ምርቶች የ‹‹አጎዋ›› (AGOA) ገበያን ታሳቢ ያደረጉ ነበሩ:: ይህም ኢትዮጵያ ከ‹‹አጎዋ›› ተጠቃሚነት ስትሰረዝ በአምራቾች ላይ ችግሮችን ፈጥሯል:: ይህ አሠራር በኮርፖሬሽኑ የሪፎርም ሥራዎች አማካኝነት ተቀይሯል:: ከዚህ ቀደም የነበረው የምርት ዓይነት በአብዛኛው፣ ‹‹አጎዋ››ን ታሳቢ ያደረገ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ላይ ያተኮረ ነበር:: አሁን ግን የፓርኮቹ ምርቶች ዓይነታቸው በዝቶ በግብርና ማቀነባበር (Agro Processing)፣ በማሽነሪና አውቶሞቢል፣ በፋርማሲዩቲካል እና በጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ተደርጓል::
አቶ አክሊሉ እንደሚናገሩት፣ ከ‹‹አጎዋ›› መሰረዝ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ ጫናዎች ምክንያት በ2013 እና 2014 ዓ.ም ብዙ ኩባንያዎች ተጎድተው ከኢትዮጵያ እየወጡ ነበር:: በ2015 ዓ.ም እና ዘንድሮ ዓመት ግን አንድም ኩባንያ አልወጣም:: ይህ የሆነው የምርት ብዝሐነት እንዲኖር በመደረጉ እና የአውሮፓና የእስያ ገበያዎች የማፈላለግ ሥራ በመከናወኑ ነው:: ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ ገበያ የማፈላለግ ኃላፊነት አልነበረውም:: በሪፎርሙ አማካኝነት ይህን ኃላፊነት እንደ አንድ ክፍተት መሙያ አድርጎ በመውሰድ ኮርፖሬሽኑ ገበያ የማፈላለግ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል:: በ2014 ዓ.ም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ጥያቄ ያቀረቡት ባለሀብቶች ከ10 ያልበለጡ ነበሩ:: በ2015 ዓ.ም 53 አዳዲስ ባለሀብቶች ገብተዋል::
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ 177 ሼዶች መካከል አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን እየጠበቁ ያሉት 20ዎቹ ብቻ ናቸው፤ 157 ሼዶች በባለሀብቶች ተይዘዋል:: ቀደም ሲል በርካታ ፓርኮች ባዶ ነበሩ፤ አሁን አምስት ፓርኮች (አዳማ፣ ቦሌ ለሚ፣ አዲስ፣ ሰመራ እና ድሬዳዋ (የማኑፋክቸሪንግ ክፍሉ) በመሙላታቸው አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ አይቻልም::
‹‹ከዘጠኝ ወራት በፊት በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ኩባንያ ብቻ ነበር:: ከሰባት ወራት በፊት ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምንም ኩባንያ አልነበረውም:: አሁን እነዚህ ፓርኮች ውስጥ ውል ፈርመው፣ ክፍያ ከፍለው አንዳንዶቹ ሥራ ጀምረዋል (ለምሳሌ አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉት ሁሉም ኩባንያዎች ሥራ ጀምረዋል)፤ ሌሎቹ ደግሞ ማሽኖችን በማስገባትና በመትከል ላይ ይገኛሉ:: በሪፎርሙ የሠራናቸው ሥራዎች፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲሁም መንግሥት የሚተገብራቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራት የኢንቨስትመንት ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ ትልቅ እገዛ አድርገዋል›› ሲሉ ጠቅሰዋል::
በተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የተከናወኑ ተግባራት ከአርሶ አደሮች ጋር ያለውን ትስስር በማሻሻል አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችለዋል:: ለአብነት ያህል ጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከአቮካዶ ዘይት የሚያመርተው ‹‹አክሻይ ጄይ›› ኩባንያ (Akshay Jay Oil) ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ስምምነት ፈፅሞ ምርታቸውን ይቀበላል:: ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የቢራ ብቅል የሚያመርተው ‹‹ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ›› ፋብሪካ (Soufflet Malt Ethiopia) ከ70 ሺ በላይ ከሚሆኑ የአርሲና የባሌ አካባቢ አርሶ አደሮች ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሠራ ይገኛል:: ወደ ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የገባው ‹‹ቡርትማልት›› ኩባንያ (BOORTMALT) ከ50 ሺ በላይ ከሚሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሯል::
ከዚህ ቀደም ከነበሩ ችግሮች አንዱ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚሰጠው ቦታ አነስተኛ መሆኑ እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ አክሊሉ፣ በ2015 እና 2016 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲነቃቁ ባለሀብቶቹ ያሉባቸውን የፋይናንስና ሌሎች ክፍተቶችን የሚሞሉ ተግባራት እንደተከናወኑ ያስረዳሉ:: በመሆኑም በ2015 እና ዘንድሮ ከተመዘገቡት ባለሀብቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው›› ብለዋል::
አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ ጓዙን ጠቅልሎ የሚሄድ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ጥገኛ ሆኖ መቀጠል ተገቢ እንዳልሆነም አስታውቀው፣ ተወዳዳሪ የሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብት ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተጀመረው ሥራ ውጤት እያመጣ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል:: የውጭ ባለሀብቶች ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ባሉበት እንዲቆዩ ማድረግና እና አዳዲስ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራዎችን ማጠናከር የሪፎርሙ ማዕከል መሆናቸውንም አመልክተዋል:: በአጠቃላይ የሪፎርም አጀንዳዎቹን በብቃት በመተግበር ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ እሴት ሰንሰለት ተገቢውን ድርሻ የምታገኝ ተመራጭ የኢንዱስትሪ መነኸሪያ እንድትሆን ለማስቻል ጥረት እንደሚደረግ አቶ አክሊሉ አመላክተዋል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም