የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት፤ የዳኝነት ነፃነትን እንዲረጋገጥ ለማስቻል የተቋቋመ ሲሆን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። በቀጣይ የሚስተካከሉ ጉዳዮች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ማከናወኑን የሚናገረው ተቋሙ፤ ከማስረጃ አቀራረብ እና ጥናቶችም አኳያ አሁን ላይ ቀደም ሲል ከነበረው አሠራር እየተሻሻለ ስለመሆኑም ይነገራል።
በተለይም ቴክኖሎጂው የፍትሕ ሥርዓት አሰጣጡን ጥሎ እንዳይሄድና በቴክኖሎጂ ተደግፈው የሚሠሩ ወንጀሎችን በብቃት በመመርመር ፍትሕ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው። ይህን ለማሻሻል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተናበበ ግንኙነት መፍጠሩንና ከሀገር ውጭ ከሚገኙ አቻ ተቋማት ጋርም በተመሳሳይ መልኩ የሚከናወኑ አበረታች ተግባራት መኖራቸውን ይገለፃል።
በሌላ በኩል በቂ ባለሙያ ለመሳብና ለማቆየት አለመቻል፣ የሚጠኑ ጥናቶች በተግባር ላይ ያለመዋል፣ የምርምርና የማሠልጠን አቅም ያለመዳበር፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂና መሠረተ ልማቶች ያለመሟላት እና መሰል ችግሮች ደግሞ ተቋሙን እየተፈታኑት ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው። እነዚህንና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ቀደም ሲል የነበረውን ስያሜ ከመቀየር በዘለለ በተግባር የተለወጡ የሪፎርም ሥራዎች ምንድን ናቸው?
አምባሳደር ደግፌ፡- ተቋማችን በአሁኑ ወቅት መጠሪያው የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ነው። ቀደም ሲል የነበረው ስያሜ ደግሞ የፌዴራል ፍትሕ፤ ሕግ፣ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ነበር። በእርግጥ የስያሜ ለውጥ የተደረገበት ዓቢይ ምክንያት የተቋቋመበትን ዓላማ የበለጠ ይገልጻል በሚል እምነት ነው። ዋናው ቁም ነገር የስያሜ መለዋወጥ ሳይሆን ኢንስቲተዩቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ምን ምን ተግባራት እያከናወነ ነው? የተከናወኑ ተግባራትስ ምን ወጤት አስገኙ? የሚለው ነው።
ከዚህ አንፃር ሲታይ ኢንስቲትዩቱ ቀደም ሲል ሁለት ተቋም ነበር። የዳኞችና ፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ለብቻው፤ የጥናትና ምርምሩም ለብቻ ነበር። ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ነው የተዋሓዱት። የመዋሓዱ ዓላማው እርስ በእርሳቸው እንዲደጋገፉ ታስቦ ነው። ይህ ማለት ሥልጠና ላይ የሚታዩ ክፍተቶች በጥናትና ምርምሮች እንዲደገፉ ለማድረግ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ የሪፎርሙ አካል ነው?
አምባሳደር ደግፌ፡- የሪፎርም ሥራዎችን በተመለከተ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል። ምንም እንኳን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጥናቶችን ያከናወነ ቢሆንም በዋናነት በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ የመወሰን ልምድ በአግባቡ የዳበረ አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህን ለማሻሻልና አዳዲስ ሕጎችን ለማውጣት ወይም ለሪፎርም ሥራዎች በግብዓትነት አገልግለዋል።
ለአብነት ያህል የወንጀል ሕግ፣ የቤተሰብ ሕግ፣ በቅርቡ የወጣው የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ረቂቅ፣ አዲሱ የንግድ ሕግ፣ እንዲሁም በቅርቡ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነትን በተመለከተ ጥናት ተከናውኗል።
የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነትን በተመለከተ ወደፊት ፖሊሲ እንዲወጣ ስለሚፈለግ ይህን መሠረት በማድረግ በርካታ ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይህ ጥናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሪፎርሙን ሥራ ለማገዝ ነው።
ከአደረጃጀት አኳያ የተበታተኑ ሥራዎችን ወደ አንድ የማምጣት ሥራ የተከናወነ ሲሆን፤ ቀደም ሲል ጥናትና ምርምሩ የተበታተነ ነበር። በአሁኑ ወቅት መዋቅሩን የማሻሻል ሥራዎች ተሠርተዋል። በፍርድ ቤቶች፣ በዓቃቤ ሕግ፣ እና ሌሎችም የሪፎርም ሥራ ድጋፍ እናደርጋለን።
ይህንና ሌሎች ተዛማጅ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ሕግ የማርቅቅ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል። የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ሥራዎች የሚገኝበትን ደረጃና ማሻሻያውን ለማጠናከር እና ለወደፊቱ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ተከናውኖ ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው ተቋማት ተላልፏል።
በፍትሕ አካላት የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር አስመልከቶ በተከናወነው ጥናት መነሻነት በፍትሕ ዘርፉ ላይ በአዲስ መልክ የሪፎርም ሥራዎችን ለማካሄድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመራ የሪፎርም ሥራ ለማከናወን የዝግጅት ሥራ ተጀምሯል።
ከዚህም በተጨማሪ የሕግ ትምህርትን ሪፎርም ጨምሮ የፍትሕ ዘርፉን ሪፎርም የማስተባበር ሥራ እንዲሁም ለፍትሕ ዘርፉ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን የማደራጀት እና ለአጠቃቀም ዝግጁ የማድረግ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ለፍትሕ አካላት በዕውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአመለካከቱ፣ እንዲሁም በሥነ ምግባሩ ብቁ የሆነና የተሟላ ስብዕና ያለው አመራርና ባለሙያ ለማፍራት በፌደራል እና በክልል የሚገኙ በርካታ ባለሙያዎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት እና ሃይማኖትን ግንኙነት በተመለከተ ወደፊት ፖሊሲ እንዲወጣ ስለሚፈለግ ይህን መሠረት በማድረግ በርካታ ጥናቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ይህ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው የሚለው እሳቤ ምን ያክል ያገናዘበ ነው?
አምባሳደር ደግፌ፡– በሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተቀመጠው ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው። አንዱ በሌላኛው ጣልቃ አይገባም። ይሁንና ይህን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የሕግ ወይንም የአፈፃፀም ፖሊሲ አልወጣም። ነገር ግን ይህን ጉዳይ በተመለከተና በሀገራችን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከት አንዳንድ የሚታዩ ነገሮች አሉ። ቀደም መንግሥት በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ ይገባ ነበር። ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ ይገባ ነበር። ይህን የመደበላለቅ ሁኔታ መልክ ለማስያዝ አስፈላጊው ጥናት መካሄድ አለበት የሚል ሃሳብ በመንግሥት በኩል የተሰጠ አቅጣጫ ነበር። ይህን መሠረት አድርጎ የተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጥናቱ ከብዝኃነት አኳያ ሲመዘን ምን ይመስል ነበር?
አምባሳደር ደግፌ፡- ይህን መሠረት በማድረግ 11 ምሑራን የተሳተፉበት ጥናት እንዲካሄድ ተደርጓል። በዚህ ጥናት ውስጥ የተለያዩ ምሑራን ተሳትፈዋል። ከእነኝህ መካከል በሃይማኖትና ሥነ-መለኮት ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ፤ በታሪክና ሌሎችም ብቃትና ችሎታ ያላቸው እንዲሁም ሌሎች ከጥናቱ ጋር የተገናኙ ምሑራን ተሳትፈውበታል።
ጥናቱ ሀገራዊ በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማትም እንዲሳተፉበት ተደርጓል። በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው። በመሆኑም ጥናቱ በርካታ ሐሳቦች እንዲካተቱበት አስችሏል።
በሌላ መልኩ ደግሞ ጥናቱን የተሻለ ለማድረግ በዘርፉ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራትን አሠራርን ለማየት ተሞክሯል። ለአብነትም የፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ሌሎች ከኢትዮጵያ ጋር ቅርበት ያላቸው ሀገራት ተሞክሮ ለመቀመር ተሞክሯል። ጥናቱ ተደርጎ በአሁኑ ወቅት ‹‹ቫሊዴሽን ወርክሾፕ›› ተደርጎ የጥናቱ ውጤት ለፍትሕ ሚኒስቴር ተልኳል።
ሚኒስቴሩ ሕግ የማርቀቅ ኃላፊነትም ስላለው ይህን ጥናት መሠረት በማድረግ ፖሊሲ ያዘጋጃሉ፤ ፖሊሲውን መሠረት በማድረግም ሕግ ይወጣል። ከዚህ አኳያ የተደረገው ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሃይማኖትና መንግሥት ጎራ መደበላለቅ ለማስወገድና ድንበሩን ለማወቅና በጋራ የሚሠሩባቸውን ጉዳዮችም በደንብን ለመለየት የሚያስችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከኢንስቲትዩቱ ዓላማ አኳያ የሕግ ምርምሮችና ሥልጠናዎች የትኩረት ነጥቦች መሆናቸው ይታወቃል። ከዚህ አኳያ በተጨባጭ የተገኙ ለውጦች ምንድን ናቸው። ጥናቶች ተደርገዋል? ካሉ ምን ያመላክታሉ?
አምባሳደር ደግፌ፡- ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የተከናወኑ ምርምሮች ለሕግ ማሻሻያና አዳዲስ ሕጎችን ለማውጣት እንዲሁም በፍትሕ ዘርፉ ለሚከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች በግብዓትነት የዋሉበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ሌላ ምንም እንኳን በሚፈለገው ልክ ሥራ ላይ ያልዋሉ ቢሆንም የፍትሕ ተቋማትን ጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸው ምን እንደሆነ ግንዛቤ እንዲኖርና ዘርፉን የማሻሻል ሥራ ትኩረት እንዲያገኝ እገዛ አድርገዋል።
የተደረጉ ግምገማዎች እንደሚያመላክቱት፤ የተከናወኑት ጥናቶች የፍትሕ አካላትን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች አስገኝተዋል። ሆኖም የተደረጉት ጥረቶች የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አላስገኙም።
አሁንም የፍትሕ አካላቱ ያልተሻገሯቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉና እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ሥራዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ያሳያሉ። የሚሰጡ ሥልጠናዎችን በተመለከተ በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሥልጠናዎች የፍትሕ ተቋማቱን ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ ብሎም ተቋማቱ ወጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል። ሆኖም የበለጠ መጠናከር እንዳለባቸው አመላክተዋል። ሌሎች ሥራዎችም እንዲሁ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና እንደሚሰጥ ይታወቃል። ይሁንና የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ፣ የንግድ ሕግና የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጎች በዓለማችን ላይ በየጊዜው ከቴክኖሎጂ መበራከትና መፈጠር ጋር በተያያዘ ተለዋዋጭ እየሆኑ ነው። በዚህ ረገድም ሀገራት ለትግበራም እየተፈተኑ ነው። ኢትዮጵያስ?
አምባሳደር ደግፌ፡- የፍትሕ ዘርፉ ለበርካታ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች የተጋለጠ ነው። በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚከሰቱ ሁኔታዎች በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ በዘርፉ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በመሆኑም ሥልጠናዎች ይህን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡ ሊሆኑ ይገባል።
በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው የሚከሰቱ ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው። ይህን ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር ማስኬድና መዳኘት የሚቻል አይደለም። በሀገራችን ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሰው አዕምሮ ብቻ ማስተካከል ያስቸግራል። በመሆኑም የነበረውን ሕግ ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተቋሙን ሥራዎች ለመደገፍ እየተሠራ ነው። ለአብነት እኛ ዘንድ በአሁኑ ወቅት የሚሰጥ ‹‹ፎረንሲክ›› ሥልጠና አለ። ቀደም ሲል ይህ የሚታወቀው በቲዮሪ ነው። በአሁኑ ወቅት ግን በተጨባጭ መሣሪያው ሀገር ውስጥ ገብቶ በዚህ ላይ ሥልጠና ይሰጣል።
ቀደም ሲል ማስረጃዎች ሲቀርቡ ሰዎች በአካል ቀርበው ወይንም በአካል ፍርድ ቤት ተገኝተው መሆን ነበረበት። በአሁኑ ወቅት ግን አንዳንድ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በድምፅ እና በቨዲዮ ሊቀርቡ ይችላሉ። ስለዚህ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎችን የመሥራት ሁኔታዎች አሉ። አሠራራችን ከማስተካከል አኳያ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
እንግዲህ በኢንስቲትዩቱ የሚሰጡ ሥልጠናዎች በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርጉት አዳዲስ በሚወጡ ሕጎች፣ አሠራሮችና የሚከሰቱ ሁኔታዎች ላይ ባለሙያዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ተግባራቸውን ከሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲያከናውኑ ማድረግ ላይ ነው። ለዚህም ሲባል የሥልጠና ካሪኩለሞች በየጊዜው እየተፈተሹ ወቅታዊ ይደረጋሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበሩ ሁኔታዎች የተሻሻሉ አሠራሮች እየተተገበሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ አሁንም ድረስ የሚተገበሩ የፍትሐብሔርና መሰል ሕጎች አሉ። እንደ ኢንስቲትዩት ለመንግሥት የምታቀርቡት ምክረ ሐሳብ ምንድን ነው?
አምባሳደር ደግፌ፡– ከተቋቋምንባቸው ዓላማዎች አንዱ የሕግ ማሻሻያ ጥናቶችን ማካሄድ እንደመሆኑ መጠን ትኩረት ከተሰጣችው ሕጎች አንዱ የፍትሐብሔር ሕግ ነው። በዚህም መሠረት ሕጉን ለማሻሻል እና ከወቅታዊው የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የሚረዳ ጥናት አከናውኖ የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦችን ለሚመለከተው አካል ልኳል። በቀጣይም ሌሎችን ሕጎች ለማሻሻል እና አዳዲስ ሕጎችን ለማውጣት የሚረዱ ጥናቶችን የሚያከናውን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ዘመኑ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጭምር ነው። ከዚህ አኳያ አሁን የሚሰጡ ሥልጠናዎችስ ዘመኑን የዋጁ ናቸው?
አምባሳደር ደግፌ፡- ተቋማችን በሦስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ሥልጠና ይሰጣል። የመጀመሪያው የቅድመ ሥራ ሥልጠና ሲሆን፤ አንድ የሕግ ባለሙያ ከዩኒቨርሲቲ ወጥቶ በቀጥታ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ለስድስት ወይንም ለዘጠኝ ወራት ሥልጠና ይወስዳል። ይህ ማለት ዩኒቨርሲቲ በቲዮሪ የተማሩትን በተግባር እንዲማር ያስችለዋል።
ሁለተኛው የሥራ ላይ ሥልጠና ነው። ይህ ማለት ደግሞ ተቀጥረው የሚሠሩ ባለሙያዎች ክህሎታቸውንና አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ ሥልጠናዎችን ያገኛሉ። ሦስተኛው ልዩ ሥልጠና ሲሆን፤ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ የሕግ ባለሙያዎች፣ ጠበቃዎችና ነገረ ፈጆችን የማሠልጠን ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ ተቋማችን ስንመለከት በዓለም ላይ ካሉት ሀገራት ደረጃ ላይ አልደረሰንም።
ከቴክኖሎጂ አኳያ እኛ በርካታ ጥረቶችን እያደረግን ነው። በእርግጥ ቴክኖሎጂ እንዳይቀድመን ስጋት አለን። የአርቴፊሻል ኢንተለጀንሱን ስንመለከት አሁን ሰው ብዙ ሳያነብ በቀላሉ መረጃ የሚያገኝበት ዘመን ነው። ይህን ከእኛ ሁኔታ ጋር ለማናበብ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዋል። አንዳንድ ጊዜ ባለጉዳዮች በአካል ሳይገኙ በኦንላይን ዳኝነት የሚሰጥበት ጊዜ ላይ ነን። ከዚህ አኳያ በጣም ብዙ ይቀራል። በዚህ ዙሪያ በደንብ ልንሠራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የፍትህ ሥርዓቱን የበለጠ ለማጠናከር እና በተማረ የሰው ኃይል የተገነባ በማድረግ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች የላቀ ሚናቸው አላቸው። ከዚህ አኳያ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ምን እየሠራ ነው?
አምባሳደር ደግፌ፡- ተቋማችን በፍትሕ ላይ ይሠራል። አሁን በውስጥ አቅም ከምንሠራው ውጭ ሌሎች አማራጮችን እንመለከታለን። ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው፤ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ተቋማችን ሙሉ ለሙሉ በቂ ባለሙያ የለውም። በመሆኑም አወዳድረን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብረን እንሠራለን። በተለይም ጥናትና ምርምር ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፋሉ። ሌላው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ኮንፈረንስ እናዘጋጃለን። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በሕግ መዝገበ ቃላት ላይ አብረን እየሠራን ነው።
በተጨማሪም ከሌሎች ተቋማት ጋር አብረን እንሠራለን። በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ በክልል ከሚገኙ የምርምር እና ሥልጠና ተቋማት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች የፍትሕ ተቋማት፤ እንዲሁም ከተወሰኑ የውጭ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሠራበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ግንኙነቶች በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት ፣ልምድና መረጃ ለመለዋወጥ እና ለመደጋገፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
የውጭ ሀገራትን ልምድ በተመለከተ ብዙ አልገፋንበትም። በተወሰነ ደረጃ ከኬንያ እና አሜሪካ ጋር ከሚገኝ አንድ ድርጅት ጋር ልምድ ልውውጥ እናደርጋለን። ሌላው አውሮፓ ከሚገኘውና ‹‹ሂል›› ከሚሰኝ ድርጅት ጋርም ማኅበረሰቡን ማዕከል ያደረገ ፍትሕ የሚል ጥናት አብረን እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጥናቱ የተለዩት የፍትሕ ችግሮች ምንድን ናቸው?
አምባሳደር ደግፌ፡- ሦስት ጉዳዮችን ለይተናል። አንደኛው መሬት ጋር በተያያዘ ያለው ነው። መሬት ላይ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ። ፍርድ ቤትም በብዛት የሚመጡ ጉዳዮች ከመሬት ጋር የተያያዙ ናቸው። ሌላው ከጎረቤት ጋር ያለው ግጭት ነው። ይህ በገጠርም በከተማው ማኅበረሰብ የሚስተዋል ነው። ሦስተኛው የተደራጀ ወንጀል ነው።
ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ችግሮችን ለመቀነስ አውሮፓ ከሚገኝ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር እየሠራን ነው። የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮም እያመጣን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከ‹‹ሂል›› ጋር በተደረገው ጥናት የመሬት፣ የማኅበረሰባዊ እሴት መሸርሸር ወይንም የጎረቤት ግጭትና የተደራጁ ወንጀሎችን የተመለከተው ነው። ጥናቱ ምን የሚያመለክተው ነገር አለ?
አምባሳደር ደግፌ፡– ‹‹ሂል›› ጥናቱን ያከናወነው በራሱ ተነሳሽነት ነው። ይህ ድርጅት መሰል ጥናቶችን ከኢትዮጵያ ባለፈ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማለትም በዑጋንዳ፣ ኬኒያ እና ናይጄሪያ እና ሌሎች ሀገራትም አከናውኗል። በአሜሪካም ይህን ጥናት ያካሂዳሉ። ከእኛ ጋርም ሥምምነት አድርገው ጥናት የጀመሩት የቀድሞ ፍትሕ ሚኒስትር ጀኔቫ ሄደው ተፈራርመው ስለነበር ነው። የእኛ ተቋም ደግሞ ሥራውን ያስተባብራል። ጥናቱም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ 7ነጥብ4 ሚሊዮን ጉዳዮች መካከል እልባት የሚሰጣቸው 2ነጥብ2 ሚሊዮን ጉዳዮች ብቻ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት አለመውሰድና በሽምግልና የመጨረስ ሁኔታ አለ። ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣው ጉዳይ በጣም አነስተኛ ነው። 7ነጥብ4 ሚሊዮን ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት መምጣታቸው ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ያሳያል። ይህ ጥናት ሲካሄድ ሦስት ወርክሾፖች ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ ሲሆን፤ የተለያዩ አካላትም ተሳትፈውበታል። ጥናቱን መሠረት በማድረግም ተጨምቀው የወጡ ጉዳዮች ደግሞ ሦስቱ ጉዳዮች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ፓይለት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው። ይህም እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ለማየትና በተወሰነ ቦታ ሞክሮ ለማዳበር ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ጥናቱ ተጠናቋል፤ የሚቀረው ትግበራው ነው። በዚህ ከተሠራበት የኢትዮጵያን የፍትሕ ችግር ማቃለል ይቻላል የሚል ተስፋም አለ።
አዲስ ዘመን፡- አሁናዊ የሀገሪቱ ሁኔታ እና የተቋሙ ሥራዎች ምን ያክል ተናበዋል ማለት ይቻላል?
አምባሳደር ደግፌ፡- ኢንስቲትዩቱ የሚያከ ናውናቸው ተግባራት በመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ እና በኅብረተሰቡ ወቅታዊ የፍትሕ ፍላጎት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ችግሮችንና ክፍተቶችንም በሚገባ የሚለይ ነው። ሆኖም በሀገራችን ትኩረት የሚፈልጉ በርካታ የፍትሕና ሕግ ጉዳዮች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ከተቋሙ አቅም አኳያ ሲታይ ለሚስተዋሉት ችግሮች እና ፍላጎቶች የተሟላ ምላሽ ለመስጠት በሚያችልበት ቁመና ላይ ነው ለማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን-፡- በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሕግ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት የሚያስችል 10 ሚሊዮን ብር ሥምምነት በ2013 ዓ.ም ተፈርሞ ነበር። ይህ ሥራ ከምን ደረሰ?
አምባሳደር ደግፌ፡- በእኛ በኩል በዳኞችና በፍትሕ በኩል የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል ተቋማችን ጥናት አድርጓል። ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ስንመለከት የፍርድ አጻጻፍንና አተረጓጎምን ጨምሮ ችግሮች መኖራቸውን ለይተናል። ወደ ተቋማችን መጥተው ሥልጠና የሚወስዱ አሉ። የእነርሱንም ጉድለት ተመልክተን ለይተናል። በዚህ ላይ የተረዳነው በቃላት ትርጉም ጭምር ልዩነቶች መኖራቸውን ነው። ተገልጋዮች ወይንም ባለጉዳዮችም በፍርድ ቤት በሚሰጡ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የጠራ ግንዛቤ የላቸውም።
ይህን ስናይ በሀገሪቱ ያለው የሕግ መዝገበ ቃላት ችግር ስለፈጠረ ለመጀመሪያ ጊዜ የአማርኛ የሕግ መዝገበ ቃላት እንዲዘጋጅ ነው የተወሰነው። የመዝገበ ቃላቱ ሥራ የተቃና እንዲሆን አግባብነት ያላቸውን ባለሙያዎችን በማሳተፍ እየተሠራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
መዝገበ ቃላቱ ከአማርኛ በተጨማሪም አቅም በፈቀደ መጠን በኦሮሞኛ፣ ሶማሌኛ፣ ትግርኛ እና ሌሎች ቋንቋዎች የሚዘጋጅ ነው። በአሁኑ ወቅት መዝገበ ቃላቱ ተዘጋጀቶ ለገምጋሚዎች ቀርቦ የታየ ሲሆን፤ የሚቀረው ከገምጋሚዎች በተሰጠው ሐሳብ መሠረት የማስተካከልና የማጠናቀቅ ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ አሁን ለሚያከናውናቸው ተግባራት ፈተናዎች ምንድን ናቸው፤ እንደ መፍትሔ የተቀመጠውስ ምንድን ነው?
አምባሳደር ደግፌ፡- ተቋሙ ዋናው ችግር የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በሚችልበት ደረጃ ላይ ያለመሆኑ ነወ። ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል በቂ ባለሙያ ለመሳብና ለማቆየት አለመቻል፣ የሚጠኑ ጥናቶች በተግባር ላይ ያለመዋል፣ የምርምርና የማሠልጠን አቅም ያለመዳብር፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ያለመሟላት ናቸው።
ተቋሙን ለማጠናከር በቅርቡ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደርጓል። በተለይ የምርምር ክፍሉ ደረጃው ከፍ ብሎ ተደራጅቷል። ሌሎችም የሥራ ዘርፎች እንዲሁ በአዲስ መልክ ተደራጀተዋል። የበለጠ ውጤታማ ይሆናል በሚል እምነትም ተጠሪነቱ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲሆን ተደርጎ የማቋቋሚያ ሕጉን የማሻሻል ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል። የሕጉን መሻሻል ተከትሎም አደረጃጀቱንና አሰተዳደሩን የማስተካከል ሥራ የሚከናወን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበረዎት ቆይታ አመሰግናለሁ።
አምባሳደር ደግፌ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም