ባምላክ ተሰማ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት ይመራል

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኮትዲቫር አስተናጋጅነት ሊጀመር ዛሬ አስራ ሰባት ቀን ቀርቶታል። የስፖርቱ ዓለም መገናኛ ብዙሃንም ትኩረታቸውን በዚሁ የ2023 አፍሪካ ዋንጫ ላይ ማድረግ ጀምረዋል። የውድድሩ አዘጋጆችም በርካታ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ፣ የውድድሩን መጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ከቅድመ ዝግጅቶቹ መካከል ውድድሩን የሚመሩትን ዳኞችና ባለሙያዎችን የመለየት ሥራ አንዱ ነው። በዚህም መሠረት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮምፌዴሬሽን (ካፍ) ሰሞኑን ውድድሩን የሚመሩትን ዳኞችን ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ከሚመሩ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ ታውቋል።

በአፍሪካ አንጋፋና ስመ ጥር ከሆኑ የእግር ኳስ ደኞች ውስጥ አንዱ የሆነው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ዘንድሮ የአህጉሪቱን ታላቅ የእግር ኳስ ውድድር ለመምራት ከኢትዮጵያ በብቸኝነት እንደተወከለ ተረጋግጧል። ባምላክ ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ዓለም አቀፍ ዋና ዳኞች ውስጥ አንዱ ሲሆን በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል ብቃቱን ማሳየት ችሏል። አርቢትሩ ቆፍጣናና ጨዋታዎችን ሲመራ ባለው የራስ መተማመን እና ያመነበትን ውሳኔ ለመወሰን ወደ ኋላ የማይል መሆኑን ባለፈው የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ላይ ይበልጥ በማሳየት አድናቆት ማትረፉ ይታወሳል።

ይሄ በራስ መተማመኑ እና ከፍተኛ የሆነ ልምዱም ካፍ ዘንድሮም ውድድሩን በኮትዲቯር፣ ከሚመሩት ዳኞች ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ዋና ዳኛ አድርጎ እንዲመርጠው አድርጓል። የእሱ መመረጥ ኢትዮጵያ ብቻም ሳትሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮምፌዴሬሽን ከሚተማመንባቸውና ዳኞች ውስጥ አንዱ መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠበት ነው። ለዚህ እንዲበቃ ያደረገው ጉዳይ ደግሞ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ወጥነት ባለው መልኩ ጨዋታዎችን የመምራት ብቃት ማሳየት በመቻሉ ነው። ኢትዮጵያ በዘንድሮ ውድድር እንደማትሳተፍ የሚታወቅ ሲሆን በዳኝነቱ ግን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ የሚወክላት ይሆናል።

ባምላክ የእግር ኳስ ዳኝነቱን ዓለም አንድ ብሎ የጀመረው እአአ በ2003 ሲሆን በ2009 የፊ (FIFA) ዳኛ መሆን ችሏል። በ2010 ጂቡቲ ከሶማሊያ ያደረጉትን ጨዋታ በመምራት የመጀመርያውን ዓለም አቀፍ ተሳትፎውንም ጀምሯል። በዚሁ ዓመት የሴካፋ (CECAFA) ውድድር ሲካሄድ ንቁ የሆነ ተሳትፎን በማድረግ እስከ ፍጻሜ ድረስ 5 ጨዋታዎችን መርቷል። በ2011 የሴካፋ ውድድር እንደዚሁ አራት ጨዋታዎችን መርቷል። በ2012 ታንዛኒያ በተካሄደ የክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የመጀመርያውን ዙር በመምራት ግስጋሴውን ቀጥሏል። በተጨማሪም ግብፅ የተካሄደውን ሁለተኛ ዙር የክለቦች ኮምፌዴሬሽን ጨዋታንም መምራት ችሏል።

የአፍሪካ ዋንጫንም በብቃት መምራት እንደሚችል በተደጋጋሚ ያስመሰከረው ኢትዮጵያዊ አርቢትር በ2022 በሴኔጋልና ቡርኪና ፋሶ መካከል የተካሄደውን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ተቆጣጥሮ በመምራት ብዙዎችን አስደምሟል። በወቅቱ የፍጹም ቅጣት ምት የሚያሰጡ የሚመስሉትን ጥፋቶች ተመልክቶ የቫርን ውሳኔ ስላላመነበት፤ ለሁለቱንም ጥፋቶች ፍጹም ቅጣት ሳይሰጥ ቀርቷል።

በ2009 የፊፋ ዋና ዳኛ መሆን የቻለው ባምላክ ለ2014 የዓለም ዋንጫ የተካሄዱትን የመጀመርያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎችን በመምራት ሥራውን የጀመረ ሲሆን ጂቡቲ እና ናሚቢያ ያካሄዱትን ጨዋታ መርቷል። በ2018 በራሽያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የዓለም ዋንጫም አፍሪካን በመወከል ከተመረጡት 6 ዋና ዳኞች አንዱ ነበር።

ከጥር 4 እስከ የካቲት 3 በኮትዲቫር አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ጨዋታዎችን ከሚመሩት ዋና ዳኞች አንዱ ባምላክ ተሰማ እንደሆነም ካፍ ከቀናት በፊት ይፋ ባደረገው ዝርዝር አሳውቋል። ለዚህ ትልቅ የአህጉሪቱ ውድድር 68 ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ያካተተው ካፍ በቅርቡ የአካል ብቃትና ሌሎች የሚያስፈልጉ መመዘኛዎችን በመስጠት የሚያዘጋጃቸው ይሆናል። የተመረጡት ዳኞች በሙሉ እአአ ጥር 5 2024 ኮትዲቯር ይደርሳሉ የተባለ ሲሆን የማነቃቂያ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ውድድሩን ይመራሉ።

ተጠባቂውን ውድድር በዋና ዳኝነት ለመምራት ከአህጉሪቱ ሁሉም ክፍል በዋና፣ በረዳት፣ በቫር ዳኝነት የተካተቱ ሲሆን ባምላክን ጨምሮ 26 ዋና ዳኞች ውድድሩን ለመምራት ተመርጠዋል። በተጨማሪም 30 ረዳት ዳኞችና 12 የቫር ዳኞች ውድድሩን ለመምራት ከወዲሁ ተለይተው ተካተዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You