አንጋፋው የኢትዮጵያ ዋንጫ ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ ዘንድሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ውድድሩ ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ዙሮች ሲካሄድ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን የ3ኛ ዙር ጨዋታዎችን አስተናግዶም ሩብ ፍጻሜ የተቀላቀሉ ክለቦችን በመለየት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎችም የካቲት ወር ላይ የሚካሄዱ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና የታችኛውን የሊግ እርከን ክለቦችን አካቶ እየተከናወነ የሚገኛው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ባለፉት ሦስት ዙሮች ያልተጠበቁ ውጤቶችን አስተናግዷል፡፡ የውድድሩ ሦስተኛ ዙር ጨዋታዎች ከኅዳር 11 ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ አዳማና ሃዋሳ ከተሞች ተካሂደው በጠንካራ ፉክክሮች ታጅበው ነው የተጠናቀቁት፡፡
ለአራት ተከታታይ ቀናት ሁለት ሁለት ጨዋታዎችን በቀን እያስተናገደ ከትላንት በስቲያ በተጠናቀቀው የ3ኛው ዙር ውድድር የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በአብዛኛው ጠንካራ የሚባሉ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦችም ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወደ ወሳኙ ምዕራፍ ማለፍ ችለዋል፡፡
በመጀመሪያው ቀን ጨዋታ ነገሌ አርሲ ከሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ክለብ ኢትዮጵያ መድን ተጫውቶ ኢትዮጵያ መድን 2 ለ 1 አሸናፊ ሆናል፡፡ ለኢትዮጵያ መድን ግቦቹን በርናንድ ኦቼንግና ቻክዋሜ ጎድሰን ሲያስቆጥሩ የነገሌ አርሲን ብቸኛ ግብ ታምራት ኢያሱ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ሌላኛው ደብረብርሃን ከተማን ከፋሲል ከነማ ያገናኘው ጨዋታ በፋሲል ከነማ 1ለ 0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ፍቃዱ ዓለሙ በፍጹም ቅጣት አስቆጥሯል፡፡ ይሄንን ውጤት ተከትሎ ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ መድን የሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል፡፡
በሁለተኛው ቀን የመጀመሪያ መርሐግብር ባሕርዳር ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ተገናኝተው አዞዎቹ 1 ለ 0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፈው ሩብ ፍጻሜ መግባት ችለዋል፡፡ ብቸኛዋን ግብ አሕመድ ሁሴን ከመረብ አሳርፏል፡፡ ቢሾፍቱ ከተማ ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአዳማ ከተማ 3 ለ 1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቦና አሊ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አሸናፊ ኤልያስ ቀሪዋን ግብ አስቆጥሯል። ቢሾፍቱን ከመሸነፍ ያልታደገችውን ብቸኛ ግብ ሲሳይ አማረ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በዚህም መሠረት አዳማ ከተማና አርባምንጭ ከተማ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች መሆን ችለዋል፡፡
ቅዳሜ እለት የተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች በግቦች የተንበሸበሹ ውጤቶች ተመዝግበውባቸዋል። በነዚህ ጨዋታዎች 14 ግቦች ከመረብ አርፈዋል። የሊጉን ሁለት ክለቦች ያፋለመው የሀድያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በወላይታ ድቻ 5 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ቢንያም ፍቅሬ 2 ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር፣ አብነት ደምሴ፣ ዮናታን ኤልያስ እና ዘላለም አባተ ቀሪዎቹን ጎሎች ለወላይታ ድቻ አስቆጥረዋል፡፡ ሀድያን ከሽንፈት ያልታደጉትን ሁለት ግቦችን መለስ ሚሻሞ አስቆጥሯል፡፡
በጎል የተንበሸበሸው ሌላው ጨዋታ ፈረሰኞቹን ከ አዲስ የሊጉ አዳጊ ክለብ ሻሸመኔ ከተማ ያገናኘ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፋል፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አቤል ያለው 2 ጎሎችን ሲያስቆጥር፤ ቢንያም በላይ፣ ሄኖክ አዱኛና አማኑኤል ኤርቦ ቀሪዎቹን ጎሎች ማስቆጠር ችሏል፡፡ ይሄን ውጤት ተከትሎ ወላይታ ድቻና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል፡፡
በሦስተኛ ዙር ማጠናቀቂያ ቀን በተካሄዱ ጨዋታዎችም ሁለት ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች ተለይተዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ ከመቻል ያካሄዱት ጨዋታ በመቻል 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ዓሊ ሱለይማን ሦስቱንም ግቦች በማስቆጠር ሃትሪክ መሥራት ችሏል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ያካሄዱት ጨዋታ በቡናማዎቹ 2 ለ 0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ፤ ጎሎቹን ማሐመድ ኑር ማስቆጠር ችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ቀጣዩን ዙር የተቀላቀለ የመጨረሻው ክለብም ሆኗል።
እነዚህን ውጤቶች ተከትሎ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ድልድል ይፋ የተደረገ ሲሆን በየካቲት ወር ወደፊት በሚገለጽ ቀንና ቦታ ጨዋታዎቹ እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ተጋጣሚዎቻቸውን በከፍተኛ ብልጫ በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉት ቅዱስ ጊዮርጊስና ወላይታ ድቻ እርስ በርስ የሚገናኙ ሲሆን የሚያደርጉት ፉክክር በጉጉት ይጠበቃል፡፡ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን የሚያካሄዱት ጨዋታ ሌላኛው ጠንካራና የብዙዎችን ትኩረት የሚስብ ይሆናል፡፡ አርባምንጭ ከተማን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘው ድልድልም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ፋሲል ከነማን ከኢትዮጵያ ቡና የሚያገናኘው ጨዋታም ሁለት ጠንካራና ባለብዙ ደጋፊ ክለቦችን ያፋጠጠ ሆኗል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም