
ከቀናት በኋላ በሚገባው የጎርጎሪሳውያኑ 2024 አዲስ ዓመት የዓለምን ፖለቲካ የሚወስኑ ከ40 በላይ ምርጫዎች ይካሄዳሉ፡፡ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ እስራኤል፣ ታይዋን እና ሕንድ ምርጫ ከሚያካሂዱ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው
የዛሬ ሳምንት ሰኞ እለት በሚገባው የ2024 አዲስ ዓመት 40 በመቶ የዓለማችን ሕዝቦች የሚያስተዳድራቸውን መንግሥት ለመወሰን ድምፅ ይሰጣሉ የተባለ ሲሆን አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ኢራን፣ እስራኤል፣ ታይዋን፣ ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ምርጫ ከሚደረግባቸው ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በጦርነት፣ በረሀብ እና በድህነት ስሟ ተደጋግሞ የሚነሳው አፍሪቃ በመገባደድ ላይ ባለው እ.አ.አ. 2023 በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች። በመጭው 2024 ከሚጠበቁ ክስተቶች አንዱ ምርጫ ነው። ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በአፍሪካ በመጭው ዓመት ብዙ ምርጫዎች ይደረጋሉ።
በጎርጎሪያኑ በየካቲት 2024 ከሚካሄደው ምርጫ በፊት በሴኔጋል ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ከወዲሁ ተቀስቅሰዋል። ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ግፊቱን ለማርገብ ለሦስተኛ ጊዜ ከእጩ ከመሆን ተቆጥበው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ባን ወደ ውድድር ልከዋል።
የምርጫዎቹ ውጤት የዓለምን የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ አሰላለፍ ሊቀይሩ ይችላሉ የተባለ ሲሆን የምርጫዎቹ ውጤቶች እና ወደ ሥልጣን የሚመጡት ተመራጮች አዳዲስ ውሳኔዎችን ሊወስኑ እንደሚችል አል አይን ዘግቧል።
ለታይዋን ሙሉ ነፃነት ለማረጋገጥ የሚሠራው ፓርቲ በምርጫው አብላጫ ድምፅ ካገኘ ቻይና ጣልቃ ለመግባት ስትሞክር ከአሜሪካ ጋር ወደ ጦርነት ልትገባ እንደምትችል ተሰግቷል፡፡
ሌላኛው ምርጫ የሚካሄድበት ሀገር እስራኤል ትሆናለች የተባለ ሲሆን በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አመራር ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎች መበራከትን ተከትሎ አዲስ መሪ ሊመጣ ይችላል ተብሏል፡፡
ሌላኛዋ ምርጫ የሚደረግባት ሀገር ሩሲያ ስትሆን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ጊዜ ተወዳድረው ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።
በጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን የፊታችን መጋቢት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ፕሮግራም የያዘች ሲሆን አዲስ ፕሬዚዳንት ሊመጣ ይችላል ተብሏል፡፡
አፍሪካዊቷ ደቡብ አፍሪካ የፊታችን ሚያዝያ ወር ላይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን ላለፉት 30 ዓመታት ሥልጣን በአብላጫ ይዞ የቆየው ኤኤንሲ ፓርቲ ሊሸነፍ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
ግንቦት ላይ ደግሞ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለ ሕዝብ ብዛት ባለቤት የሆነችው ሕንድ በታሪክ ግዙፉን ምርጫ እንደምታካሂድ ሲገለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የ28 ፓርቲዎች ጥምረት በሆነው የሕንድ ብሔራዊ ጥምረት ለልማት ፓርቲ የመሸነፍ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሕንድ አዲስ መሪ ወደ ሥልጣን የሚመጣ ከሆነ አሜሪካ ቻይናን በእስያ ለመገዳደር በያዘችው እቅድ ላይ እንቅፋት አልያም ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ተብሏል፡፡
ሌላኛዋ ምርጫ የምታካሂደው ሀገር ብሪታንያ ስትሆን ያለባትን የጠቅላይ ሚኒስትሮች አለመረጋጋት ምላሽ እንደምትሰጥ ተጠብቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ክሮሺያ እና ፊንላንድ ምርጫ ያካሂዳሉ የተባለ ሲሆን የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ምርጫም ይካሄዳል፡፡
በአውሮፓ የሚደረጉ ምርጫዎች በቀኝ ዘመም ወይም ስደተኞችን የሚጠሉ ፓርቲዎች ሥልጣን እየተቆጣጠሩ በመምጣት ላይ ናቸው፡፡
አስቀድማ በሴት ፕሬዚዳንት እንደምትመራ ያረጋገጠችው ሜክሲኮ ሐምሌ ላይ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ሁለት ሴት እጩ ፕሬዚዳንቶች ይወዳደራሉ ተብሏል፡፡
የዓመቱ የመጨረሻ ምርጫ የሚካሄደው በአሜሪካ ሲሆን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻ እጩ ሆነው እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በሥልጣን ላይ ባሉት መንግሥታት አለመርካትም በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ሥልጣን ወደ ተቃዋሚዎች እንዲሸጋገር ሊያደርግ ይችላል የሚል ግምት ተሰጥቶታል።
የሩስያ እና የቻይና ሁኔታ የአፍሪካ ሀገራትን በማጠናከር ሥራ በዴሞክራሲ ላይም ተፅዕኖ እንዳለው የዘርፉ የባለሙያዎች ይጠቅሳሉ። ከዚህም ባሻገር የምዕራቡን ዓለም የበላይነት ለመግታት እና በአህጉሪቱ ላይ ኃያላኑ የበለጠ ተፅዕኖ ለመፍጠር እየተፎካከሩ ይገኛል።
አሜሪካና የአውሮፓውያን በበኩላቸው ባላቸው ተፅዕኖ የተነሳ በአፍሪካና በእስያ ሀገራት በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ የእራሳቸው ጫና እንደሚኖራቸው ይገመታል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም