የባሕር በር ጉዳይ – ከዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ

የባሕር በር የሌላት ትልቋ ሀገር ኢትዮጵያ፣ ዛሬም እንዳለፉት በርካታ ዓመታት ሁሉ የወደብ አገልግሎትን ለማግኘት ጥገኛ ሆና ቀጥላለች፡፡

ይህ አካሄዷ መዳረሻው ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ክስረት እንደሆነ የተገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከወራት በፊት የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን በሚያስችል ጉዳይ ላይ እንወያይ ሲሉ ሐሳቡን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲመክሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የመሆን እንቀስቃሴዋን የጀመረችው በሐሳብ ደረጃ ሲሆን፣ ይህ ሐሳብ እየጎለበተ መጥቶ በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነቃቃት ላይ ይገኛል። ብዙዎችም ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንዛቤው እንዲኖረው በማድረግ ላይ በመሆናቸው ጥቂት የማይባለው የኅብረተሰብ ክፍል በጉዳዩ እየተሳበበት መምጣቱም እሙን ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ከ200 በላይ ከሚሆኑ ሀገራት መካከል የባሕር በር ከሌላቸው 44 ሀገራት መካከል አንዷ ናት፤ ይሁንና ሰፊ እና ታላቅ ሀገር እንደሆነች ግልጽ ነው፡፡ ከወደብ ጥገኝነቷ ለመላቀቅ እና ለራሷም ሆነ ለቀጣናው የሚጠቅም ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ደግሞ የባሕር በር ግድ እንደሚላት የታወቀ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እንዲያም ሆኖ የባሕር በርን ለማግኘት ቅድሚያ የምትሰጠው በሀገር ውስጥ በጉዳዩ ዙሪያ ከመወያየትና ከመነጋገር ባለፈ ከሀገራት ጋርም መነጋገርንና መስማማትን እንደሆነም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲነገር ቆይቷል፡፡ የባሕር በርን ለማግኘት ስትል ምንም አይነት ጠብ አጫሪነትን እንደማትፈጽምም ተደጋግሞ ተወስቷል፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ የባሕር በር ባለቤት የነበረች ሀገር እንደመሆኗ ሁሉ ዛሬም የባሕር በር ባለቤት ለመሆን ትሻለች፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት አካሄዷ ምን መሆን አለበት? በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣ ኮንቬንሽንስ የኢትዮጵያ የባሕር በር እና የወደብ ጥያቄ ከሕግ አኳያ ሲታይ ምን ይላል? ስንል የዘርፉን ምሑራን አነጋግረናል፡፡

የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ከፍተኛ የሕገ መንግስት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ዓምደገብርዔል አድማሱ እንደሚሉት፤ ከባሕር በር ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያፀደቀው ዋንኛ የዓለም አገራት የሚተዳደሩበት የባሕር ሕግ አለ፤ ይህ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ እና ከዚያ ጀምሮ ብዙ ችግሮችን መፍታት የቻለ ሕግ ነው። ይህ ሕግ ስለአፍሪካም መግቢያው አካባቢ ተንትኖ ያስቀመጠ ነው፡፡

የባሕር በር የሌላቸው ሀገራትን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ የሚያስቀምጠው ድንጋጌ አለ፤ በተለይም በአንቀጽ 69 ላይ ከንዑስ ቁጥር አንድ አስከ አምስት ባለው ላይ እንዲሁም አንቀጽ 25 እና አንቀጽ 125 ላይ በመሠረታዊነት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት እንዴት አድርገው ጎረቤቶቻቸው ካሉ እና የባሕር በር ካላቸው ሀገራት ጋር መጠቀም እንዳለባቸው የሚያስረዳ መሆኑን አቶ ዓምደገብርዔል ይናገራሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚህ አንቀጾች የባሕር በር በሌለው እና ባለው ማለትም በሁለቱ አገራት በሚደረግ ስምምነት መሠረት የባሕር በር እንዲጠቀሙ መንገድ የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡ ከአንዳንድ ጉዳዮች በስተቀር ሁሉንም አገልግሎት እንዲያገኙ የሚገልጽ ሐሳብም የያዙ ናቸው፡፡

የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት እቃቸውን ከማጓጓዝ አልፎ ከባሕሩ የሚገኘውንም በረከት መቋደስ የሚችሉ መሆናቸውን ሕጉ ያስቀምጣል ሲሉ የተናገሩት ከፍተኛ የሕገ መንግሥት ተመራማሪው፣ ለአብነት የዓሣ ምርት የመጠቀምንም መብት ያጎናጽፋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ያለፈው መንግሥት ወደብን የሚያክል ታላቅ ሀብት አሳልፎ የሰጠው ጉዳይ መሆኑን ያስታውሳል። ይህን ከእጅ የወጣን ታላቅ የሆነው የባሕር በርን ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ጠንካራ ሥራ የሚጠይቅ ትልቅ ጉዳይ ነው ብለዋል። የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ትልቋን ኢትዮጵያ የሚያክል ሥራ የሚጠይቅ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ የባሕር በር የሌለው አገር የባሕር በር የመጠቀም መብት አለው፤ መብቱ ግን ከጎረቤቱ ጋር በመግባባት እና በስምምነት ላይ የተመሠረተ መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለሁሉም ስምምነት እና ውይይት የግድ ይላል፡፡ ከሀገራቱ ጋር አብሮ በመጠቀም ለማደግ መልካም ግንኙነት መፍጠርን ይጠይቃል፡፡

ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ ልክ እንደ አቶ ዓምደገብርዔል ሁሉ ኢትዮጵያን የባሕር በር ተጠቃሚ ሊያደርጓት የሚችሉ አንኳር ጉዳዮች አንዱ ትልቅ ሀገር መሆኗ ነው ይላሉ። በተለይም ኢትዮጵያ ትልቅ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ ሀገር እንደመሆኗ የባሕር በር በማጣት እንዲህ አይነት ጫና ውስጥ መግባት የሌለባት ሀገር እንደሆነችም ያስረዳሉ። ስለዚህም የባሕር በርን ሕጉም በሚፈቅደው ሁኔታ በስምምነት መጠቀም ተመራጭ የሆነ አካሄድ ነው ሲሉ የአቶ ዓምደገብርዔል ሐሳብ ያጠናክራሉ፡፡

ስለዚህም ይላሉ የውሃ ጉዳይ ተመራማሪው ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ የባሕር በርን ለማግኘት ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የባሕር በር ተጠቃሚ የነበረች ብትሆንም አሳልፋ ለኤርትራ የሰጠች መሆኗ የሚታወቅ ነው፤ ይህን ደግሞ “መልሼ እወስዳለሁ” ማለት አይቻልም ሲሉ ጠቅሰው፤ ይህን ለማድረግ ሕጉም አይፈቅድም በማለት ይናገራሉ፡፡ በስምምነት ግን የሚሆን በመሆኑ ከወዲያኛውም ሀገር የሚፈልገው ጉዳይ ታውቆ በውይይትና በስምምነት የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያመለክታሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ይህ ስኬታማ ይሆን ዘንድ የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን መጠቀም አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ የተለያዩ ኮንፈረንሶችን መጠቀምም ሌላው ተጠቃሽ አካሄድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ጥናት እና ለድርድር የሚሆን ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃል። በቂ ትኩረትም ተሰጥቶት አስፈላጊ ከሆነ ኮሚሽንም ተቋቁሞለት ቢሠራ ኢትዮጵያ ተጠቃሚነቷን ከፍ እያደረገች ልትሄድ ትችላለች፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣ ኮንቬንሽንም በስምምነት መሆኑን ያዛል፡፡ ኢትዮጵያ በሌላ ሀገር ወደብ ስትጠቀም የዚያን የምትጠቀምበትን ሀገር ደህንነት ጠብቃ ፍላጎትን አሟልታ ነው፡፡ ይህ በስምምነት የሚቋጭ ጉዳይ ነው፡፡ በስምምነቱ ውስጥ ደግሞ ቁጥጥር አለ፡፡

ጂቡቲ በወደብ ከምታገኘው 70 በመቶ ያህል ሀብቷን የምትሰበስበው ከኢትዮጵያ እንደሆነ የሚገልጹት ተመራማሪው፣ እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ሁሉ በፈለጋት ጊዜ ማስገባት እንደማትችል አስታውሰዋል። በዚህ ውስጥ ሆና አጣዳፊና ድንገታዊ ጉዳይ ቢያጋጥማት እንኳ የምትፈልገውን ነገር በፈለገችበት ጊዜ ማስገባት እንደማትችል ሁሉ ደብቃ የሚጠቅማትን እቃ ማምጣትም አይሆንላትም ብለዋል፡፡ ልታስገባ ለፈለገችው እቃ ለማስገባት የቱንም ያህል አቅም ቢኖራት እንኳ አቅሟም ሆነ ፍላጎቷ የተገደበ መሆኑ የሚታወቅ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

እንደ ከፍተኛ የሕገ መንግሥት ተመራማሪ አቶ ዓምደገብርዔል ገለጻ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ከ200 በላይ ሀገራት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በርካታ ሲሆኑ፣ በላቲን አሜሪካ ውስጥ የምትገኝ የባሕር በር የሌላት ሀገር የሆነችው አንዷ ቦሊቪያ ናት፡፡ ሌሎች በመደራደር ማለትም ሰጥቶ በመቀበል ሕግ የባሕር በር ያገኙ ናቸው፡፡

ሌላው አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ኮንጎ ኪንሻሳ ከኮንጎ ብራዛቪል እና ከአንጎላ የባሕር በር የማግኘት እድል አግኝታለች፡፡

ልክ እንደ የውሃ ተመራማሪው ያዕቆብ (ዶ/ር) ሁሉ በዓለማችን የባሕር በር ከሌላቸው እና ትልቅ ሀገር ከሚባለት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ናት የሚሉት አቶ ዓምደገብርዔል፣ የባሕር በር አለመኖር ለብዙ የኢኮኖሚ ችግር የሚዳርግ ጉዳይ ነው ይላል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በሁለት ምክንያት የባሕር በር የመጠየቅ መብት እንዳላት ይታያቸዋል፡፡ ከአሰብ ወደብ ጋር በተያያዘ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ወስደው ጣሊያኖች ቅኝ ግዛት ሲገዙ ስምምነቶች ነበሩ፡፡ እነዛ ስምምነቶች በራሳቸው በጣሊያኖች የተጣሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ መጥተው ሲወሩ ስምምነቱን ጥሰዋል፡፡ ያ ስምምነት ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው፡፡

በተጨማሪም ኤርትራ ከኢትዮጵያ የወጣችበት መንገድ ቅቡልነት ያለው አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የባሕር በር የነበራት ሀገር ሆኖ ቆይታለች፡፡ በቅኝ ግዛት ምክንያትና በሌሎችም ምክንያቶች የነበራት ወደብ እንድታጣ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የባሕር በር ጥያቄ የመጠየቅ መብቷ በዓለም አቀፍ ሕግጋት የተጠበቁ እንደሆነ ይታያል፡፡

ይሁንና የባሕር በርን ለማግኘት የዓለም አቀፉ ሕግ የሚያስቀምጠውን ድንጋጌ መከተል ወሳኝ ነው። አንደኛው ጉዳይ ድርድር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሰጥቶ መቀበል የሚባለው መርሕ ነው፡፡ ጂቡቲም ሆነች ኤርትራ እንደሚታወቀው ትልልቅ የሚባሉ ወንዞች የሏቸውም፡፡ የጥሪት እጥረት አለባቸው፡፡ መሬታቸውም የዚያን ያህል ለእርሻ አመቺ አይደለም፡ ፡ በመሆኑም ይህን መሠረት በማድረግ በሰጥቶ መቀበል መርሕ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት ጋር መነጋገር ትችላለች፡፡

ያዕቆብ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የባሕር በር ሊሰጡን የሚችሉ ሀገራት ለሕዝባቸውና ለሀገራቸውም ልማት ከኢትዮጵያ የሚፈልጉት ብዙ ነገር ስላለ እኛ ሳንሆን እነሱም ፍላጎታቸውን እያቀረቡ ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻል ይሆናል ይላሉ፡፡ በእርግጥ ጥያቄው ከትልልቅ ነገር ሊጀመር ይችላል ሲሉ ተናግረው፤ ለአብነትም ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ሊሆን እንደሚችል የአቶ ዓምደገብርዔልን ሐሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ መሬት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፤ ከዚያም ያለፈ ነገር ሊጠየቅ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

የውሃ ጉዳይ ተመራማሪው፣ የራሳችን የሆነውን የዓባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግድብን ለመገንባት እንኳ የወሰደብን ጊዜ በጣም ብዙ ነው፡፡ ከመንግሥታት ጋር መከራከሩ፣ ያልገባቸውን ማስተማሩ፣ የሚሰነዘሩ ብሽሽቆችን መቋቋሙ እና ሌላ ሌላም ጫናን መጋፈጡ የወሰደው ሰፊ ጊዜ ነው፡፡ ይህ በሕዳሴ ግድብ ላይ የተወሰደው ጠንከር ያለ ሒደት ለአፍሪካ ቀርቶ ለሌላው ዓለም ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ተሞክሮ ነው።

እንዲያም ሆኖ የሕዳሴ ግድቡና የባሕር በሩን አንድ የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ ያሉት ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ዓባይ ወንዝ የራሳችን ሀብት ሆኖ ስንጋፈጥ የነበረው አትጠቀሙም ከሚሉ አካላት ጋር ነበር ብለዋል፡፡

አሁን ግን የጎረቤት ሀገር ሆኖ ወደብን አትጠቀሙ ማለት አይቻልም፤ ሕጉ እንደሚያስረዳው ስላጠቃቀሙ መነጋገርን ነው እንጂ በፍጹም አይቻልም የሚለውን አይደለም ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥያቄያችንን ውጤታማ ይሆን ዘንድ ክብደታችንን እዛ ላይ መጫን ይኖርብናል።

ስለዚህ ዓባይና የባሕር በር ልዩነት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዓባይን ለመገንባት የታየ የሁሉም ቁርጠኝነት ለባሕር በር ጥያቄው ስኬትም ሊደገም የሚገባው መሆን አለበት፡፡ ልክ የሕዳሴ ግድቡን ያለምንም ጦርነት ሰላማዊ በሆነ የዲፕሎማሲ ቋንቋ እዚህ ማድረስ እንደተቻለ ሁሉ የባሕር በሩ ጥያቄም በዚህ አግባብ ምላሽ እንዲያገኝ በቁርጠኝነት መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ልዩነቱ ዓባይ የገዛ ንብረታችን በመሆኑ ልናዝበት የምንችለው መሆኑ ሲሆን፣ ያኛው ግን የሰው እንደመሆኑ ልናዝበት ሳይሆን በስምምነት እና በውይይት ማምጣት የምንችለው መሆኑ ነው፡፡

የዓለም ከአስር በመቶ በላይ ንግድ የሚዘዋወርበት ቦታ ቀይ ባሕር ነው የሚሉት ከፍተኛ ተመራማሪው፣ ከዚህ ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት በብዙዎች እይታ ውስጥ ያለ ስትራቴጂክ ሆኗል ይላሉ፡፡ በቀይ ባሕር ዙሪያ ካሉ ሀገራት በተጨማሪ በርቀት ያሉ ሌሎች ሀገራት እንደ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ራሽያ፣ ቱሪክ እና መሰል ሀገራት ምን እያደረጉ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ በቀይ ባሕር ኮሪደር ውስጥ እነ ሳዑዲ ዓረቢያና የመንም በጣም ትልልቅ ወደብ ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል ሕግ እና በዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት የወደብ ኮሪደር የማግኘት መብት እንዳላት ያሳያል ብለዋል፡፡

ልክ እንደ ያዕቆብ (ዶ/ር) ሁሉ እርሳቸውም ከሁሉም ነገር በላይ የሚያስፈልገው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ነው ይላሉ፡፡ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑ አዋጭ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው ታሪካዊ ሀገር ናት፡፡ ነገር ግን ትልቁ ችግር በሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እምብዛም አለመኖሩ ተደማጭነትን ለማግኘት አሊያም ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲዊ ላይ ከፍ ብሎ ለመታየት የሚደረገውን አቅም ሲያዳክምብን ይስተዋላል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡

ይህ በመሆኑ እኔ በበኩሌ ቅድሚያ ቢሰጠው ብዬ የምለው የሀገር ውስጥ ሰላም ላይ በጣም መሥራት ይጠበቅብናል የሚለው ላይ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ያንን በአግባቡ ከሠራን ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከናይጄሪያ ቀጥላ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ሀገር ናት፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን በጣም ትልቅ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ አገር ናት። ጂዲፒዋ (አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገቷ) በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የሦስት ሺ ዓመት ታሪክ ያላት ትልቅ እና ቀደም ሲል ከ100 እና 150 ዓመታት በፊት የምታስተዳድራቸው ወደቦችም የነበሯት ሀገር ናት። እነዚህንና ሌሎችንም እውነታዎችን በመያዝ የባሕር በርን የመጠየቅና የመደራደር መብቷ የተጠበቀ ነው፡፡ ትችላለችም ብለዋል፡፡

ስለዚህ የባሕር በርን እስከወዲያኛው ማጣት ፈተናው በሀገራችን ላይ በጣም ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ጫና ያመጣል፡፡ እስካሁን በጂቡቲ የምንጠቀመው ወደብ የኪራይ ነው፡፡ የኪራዩ ክፍያ በጣም ከፍ ያለ ሲሆን፣ በቀን እየተከፈለ ያለው ዶላር ነው፡፡ ኢትዮጵያ አምራች የሰው ኃይል ያለባት ሀገር ሆና የባሕር በር ስለሌላት ብቻ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድርባት መሆኑ ይታወቃል በማለት አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ወደብ አለመኖሩ ገቢ እና ወጪ ምርቷን ያወሳስበዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚም በተፈለገው ልክ እንዳያድግ ጫና ያሳድራል፡፡ ሀገራችን ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ስለሆነች ተገቢው ኢኮኖሚ የማይኖር ከሆነ ዜጎቿ ምርጫቸውን ስደት ላይ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች መሰደዳቸው ጉዳቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሚሰደዱባቸው ሀገራትም ጭምር ነው፡፡ ምክንያት ቢባል በሀገራችን ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ደካማ የሚሆን ከሆነ ወጣቱ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መሰደድን ምርጫው ስለሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመዳረሻ ሀገራትም ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡

ስለሆነም በሕዝብ ብዛቷ፣ በታሪካዊት ሀገርነቷ እና በአፍሪካ ደረጃ ያላት የጂዲፒዋ ጠንካራ መሆን ከግምት ውስጥ ገብቶ የባሕር በር ሊኖራት የሚገባት ሀገር መሆኗ የማይታበል ሐቅ ነው ብለዋል፡፡

ምሑራኑ እንደሚሉት፤ የሕግ ጉዳይ ከተነሳ ኢትዮጵያ አሰብን ያጣችበት መንገድ ፍትሐዊ እና ተገቢ ያልሆነ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያ ሀገሪቱን መልቀቅ የነበረባት የወደብ ተጠቃሚነቷን አስጠብቃ መሆን ነበረበት፡፡

ኢትዮጵያ አሁን እያነሳች ላለችው የባሕር በር ጉዳይ የዓለም አቀፉ ሕግ የሚያስቀምጠው አንኳር ጉዳይ ቢኖር በሀገራት መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚወሰን መሆኑን ምሑራኑ ያመለክታሉ፡፡ ወደብ ካላቸው ሀገራት ጋር በሚደረግ ስምምነት የሚደረግ መግባባት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ይህም ስምምነት እንደየሀገሮቹ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል ሲሉ ጠቅሰው፤ ይህም መሬት ከመጠየቅ እስከ ትልልቅ ተቋማትን እስከመጋራት ሊደርስ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዲፕሎማሲውን የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

ትልቅ ሀገር እንደመሆናችን ከእኛ ጋር ሊስማሙ ለሚችሉ ሀገራትም የሚስገኘው ጥቅም ትልቅ እንደሚሆን የሚታወቅ እንደሆነ ጠቁመው፤ ይህን ሳይረዱና ሳይፈቅዱ ቀርተው ለዘመናት የሚሸሹ ከሆነ የእኛ ችግር የሚያመጣው ፈተና የእነርሱም ፈተና መሆኑን ማሰብ መቻል አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You