አሁን ባለንበት ‹‹ዘመነ ቴክኖሎጂ ›› የረቀቀ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial intelligence) በብዙ መልኩ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፤ ይህም የሰው ልጆችን ሥራ እያቀለለው ነው፡፡ በተለይ ያደጉት ሀገራት ይህን ሰው ሠራሽ አስተውሎት በብዙ መልኩ በመጠቀም ወደ ተራቀቀ የቴክኖሎጂ ደረጃ እየደረሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ያለ ቴክኖሎጂ መኖር ቀላል እንዳይደለ ያመላክታል፡፡ ታዳጊ ሀገራትም ይህንን ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመተግበር ዓለምን የሚቀላቀሉበት መላ መዘየድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) እንደ እሳቤ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ ገደማ ነው፡፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) የሚለውን ስያሜ የያዘው ግን እ.ኤ.አ 1955 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ቴክኖሎጂው እያደገ መጥቶ አሁን ዓለምን ከሰው ሠራሽ አስተውሎት እሳቤ ውጭ ከማትሆንበት ደረጃ ላይ አድርሷታል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ነገሮች ያለሰው ሰራሽ አስተውሎት አስቸጋሪና አዳጋች የሚሆኑበት ጊዜ ላይ ደርሳለች፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የዓለምን ኢኮኖሚ በስፋት እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ 2022 ሦስት ነጥብ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ሀብት እያንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በቀጣይ 2025 ደግሞ እስከ አምስት ትሪሊዮን ዶላር ሀብት ሊያንቀሳቅስ ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡
በዚህ ልክ የዓለምን ኢኮኖሚ እያንቀሳቀስ የሚገኘውን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምንድነው፣ ለምን አገልግሎት ይውላል፤ እንዴትስ መጠቀም ይገባል?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኃላፊ በአካል ግዛቸው (ዶ/ር) ሰው ሠራሽ አስተውሎት ስንል በተፈጥሮ የሰው ነው የሚባለውን አስተውሎት ለማሽን መስጠት ማለት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ እንደ ስልክ፣ ኮምፒዩተር፣ ኤሌክትሮኒክ የሆኑ መሣሪያዎች (እያንዳንዱ ኤሌክትሮኒክ መገልገያዎች) እና ለየትኛውም ኤሌክትሮኒክስ ማሽን ይህንን አስተውሎት መስጠት ማለት ነው፡፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ማድረግ ከሚችላቸው ነገሮች ቋንቋን ይማራል፣ ብዙ ትምህርቶችን ያውቃል፤ እርምጃዎችና ውሳኔዎችን ይወስዳል፡፡ ይህንን አስተውሎት ለማሽን ሰጠን ማለት በሰው የሚሠሩ ሥራዎችን በማሽን እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ በተለይ አንዳንድ ከሰው አቅም በላይ የሆኑት ሥራዎች ማሽኑ እንዲሠራ ማስቻል ነው ፡፡
ማሽኑ የሚሰጠውን እውቀት ተጠቅሞ ውሳኔ መስጠት ላይ አስፈላጊ እርምጃዎች እንደሚወስድ ጠቅሰው፤ ጠቀሜታውም ምርትና ምርታማነት ለመጨመር እና አንዳንድ ሥራዎች ለማቀላጠፍ የሚረዳ ጽንሰ ሀሳብ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለሀገር እድገት የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ስለሆነ ያደጉ ሀገራት ብዙ የሚጠቀሙበት ነው የሚሉት በአካል (ዶ/ር)፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እና በመሳሰሉት በርካታ ዘርፎች ላይ መጠቀም የሚቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ እንዲያውም የማንጠቀምበት ዘርፍ የለም ማለት ይቻላል ይላሉ፡፡ ለምሳሌም ወንጀልን ቀድሞ የመከላከል እና የመተንበይ ሥራዎችን ቀድሞ ሊሠራ ይችላል፡፡ የተፈጥሮ አደጋዎችን መተንበይና ቅድመ መከላከል ላይ ዝግጅት እንዲደረግ ለማወቅ ያስችላል፡፡ በግብርናው ረገድ በምን አይነት መሬት ላይ ምን አይነት እህል ብንዘራ የተሻለ ምርታማ መሆን እንችላለን ለሚለው ጥያቄ መረጃዎችን ሰብሰቦ የሚያሳውቅ ነው፡፡ የመሬቱን ለምነት ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋ የሚችለው ቀጥሎ ምን ቢደረግ የተሻለ ሊሆን ይችላል የሚሉ እና የመሳሰሉ በርካታ ማወቅ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ቀድሞ ማወቅ ያስችላል፡፡
በቱሪዝም ኢንዱስትሪውም እንዲሁ አንድ ጎብኚ ለመጎብኘት ከመነሳቱ በፊት ካለው አቅም ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የትኛውን ቦታ ቢጎበኝ የተሻለ እንደሚሆን ለማወቅ ከፈለገ መረጃ ሊሰጠው እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቢዝነስ ለመክፈት ለሚፈልግ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ዝርዝርና ጥልቀት ያለው መረጃ የሚሰጥ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
እስካሁን ብዙዎቹ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲስተሞች የተሠሩት በውጭ አገር ቋንቋዎች ስለሆነ ሀገራችንን ተጠቃሚ አላደረገም፡፡ ስለዚህ በሀገራዊ ቋንቋዎች ላይ መሠራት አለበት ይላሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስትቲዩት በኩል የተሠራ ድምፅን ወደ ጽሑፍ የሚቀይር ሲስተም አለ፡፡ ይህም በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የተሠራ ሲሆን ሌሎቹን በሀገሪቱ ያሉ ቋንቋዎች ለማካትት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ይገኛሉ።፡ እነዚህ ሥራዎች ለሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ልክ መሠረት የመጣል ያህል እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
አሁን ያለው ቋንቋዎችን የመጠቀም ያለበት ደረጃ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጠቀም በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ብዙ ቴክኖሎጂ ቢኖሩም ብዙዎች ደግሞ ሊጠቀሙበት አይችሉም። በተለይ በገጠር ያሉ ያልተማሩ ሰዎች ቀላል ስላልሆነ አይጠቀሙበትም። አሁን ያሉትን በማሳደግ ቋንቋዎች ላይ በመሥራት ተጠቃሚነት ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
‹‹አሁን ያለንበት ዘመን የዳታ (የመረጃ ዘመን) ነው። ዳታ ነዳጅ ነው ይባላል፡፡ ዓለምን እያንቀሳቀስ ያለው ዳታ ነው፡፡ ከዳታ ብዙ ነገሮችን እንማራለን፡፡ ስለዚህ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት መራቅ አይቻልም፤ ከራቅን ደግሞ በጣም እንጎዳለን›› የሚሉት በአካል (ዶ/ር) ግብርናው ላይ ባይሠራ የሚባክን ብዙ ነገር መኖሩን ይጠቅሳሉ። በትራንስፖርት፣ በአደጋ መከላከል፣ በምርጫ እና የመሳሰሉት ሥራዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሊደገፉ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግሮችን ለማጣራት የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ አሁን ላይ ከዓለም ወደኋላ ላለመቅረት ቴክኖሎጂን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ዓለምን እየመሩ ያሉት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ናቸው። ተራማጅ ሀሳቦች እያራመዱ ወደፊት መጓዝ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ‹‹ቆየት ብለን መጀመራችንን እንደተጎጂ ብቻ ማየት የለብንም፡፡ እኛ ዓለም የደረሰበት ለመድረስ አሁን ላይ ያሉት የታረሙ ቴክኖሎጂዎች ይዘን ወደኛ ዓውድ እየቀየርን መጠቀም እንችላለን፡፡ በጥሩ ሁኔታና አመራር በሁሉም ዘርፍ ቢሠራ ያዋጣል ብዬ አስባለሁ›› ብለዋል፡፡
በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚነሱ ብዙ ስጋቶች አሉ ያሉት በአካል (ዶ/ር)፤ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው ስጋት አውቶሜሽን ስለሆነ ሁሉንም ነገር ማሽን ከሠራው ሰዎችን ሥራ ያሳጣል የሚል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ስጋቱ እንዳለ ሆኖ ማሽኑ ደግሞ ተከታታይነት፣ ቀልጣፋነትና ምርታማነት የሚጨመር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሺ ሰው ከሚሠራው ይልቅ ማሽኑን ተጠቅሞ አምስት ሰው እየሠራው የአሥር ሺ እና ከዚያ በላይ ሰው ያህል የበለጠ ምርት ማምጣት ያስችላል፡፡
ምርታማነቱን በአሥር እጥፍ ሲያሳድገው የሚያመጣው ገቢም በዚያ ልክ በጣም ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ‹‹እንደ ኢትዮጵያ ስናይ በእኔ እምነት የትኛውን ሥራ የሚያስብል ነው፤ ለብዙዎቹ ሥራዎች አነስተኛ ክፍያ የሚከፈልባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ማድረግ ይሻላል ወይስ ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚገኘውን ዘጠኝ እጥፍ ጥቅም ጨምረን ለእነዚህ ሰዎች የተሻለ የሥራ እድል እንፍጠር በሚል የሚታሰብ ሊሆን ይችላል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሌላኛው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚነሳው ስጋት ማሽኑ አንዳንድ ውሳኔዎች ቢሳሳትስ የሚል ነው ሲሉም በአካል (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ፤ በአሜሪካ ‹‹ኮምፓስ›› የተሰኘው ሶፍት ዌር በፍርድ ቤት ተግባራዊ ሆኖ እንደነበር አስታወሰው፤ ሶፍት ዌሩ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የተደረጉት ጥናቶች የሰጠው ውሳኔ የተሳሳተ መሆኑን ማመላከታቸውን በአብነት ያነሳሉ፡፡
ይህ መሳሳት የሚመጣው ከሚሰጠው ዳታ እንደሆነ የገለጹት በአካል (ዶ/ር)፤ አሁን ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንዴት ኃላፊነት የሚሰማው ማድረግ ይቻላል የሚለው ላይ መታሰብ እንዳለበት አመላክተዋል። እሳት ላይ ስጋት አለ ብለን መጠቀም እስካልተውን ድረስ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሰው ሠራሽ አስተውሎት የአገራችንን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የሳይበር ደህንነትን ለመጠበቅ፣ የአቪዬሽንን ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ ምርታማነትን ለመጨመር፣ ገበያን ለማስፋት እና ለመሳሰሉት ሥራዎች በእጅጉ አስፈላጊ መሆናቸውን በአካል (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምሕዳሩ ላይ በአፍሪካ በተለይ በደቡብ አፍሪካ የሚታየው ተነሳሽነት እና በኢትዮጵያ ኢንስቲትዩት በማቋቋም እየተከናወነ ያለው ተግባር መነሳሳትና መነቃቃትን መፍጠሩን ጠቅሰው፣ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሠራሽ አስተውሎትና ሮቦቲክስ የፒ ኤች ዲ ተመራማሪ አቶ ዳንኤል ጌታቸው የበኩላቸው የበአካልን (ዶ/ር) ሀሳብ በመጋራት የሰው ሠራሽ አስተውሎት አዲስ ነገር አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደ ኢትዮጵያ ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በብዙዎች ዘንድ እንደ ቅንጦት ሲታይ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ሀገሮች ጥቅሙ ብዙም እንደማይታወቅ ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በደንብ ባይታወቅም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲሰተሞችን በመቆጣጠር ብዙ አገልግሎት እየሰጡ የቆዩ እንደ ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን እና ባንክ ያሉ ተቋማት እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አብዛኞቹ ዘርፎች ላይ ሊሠራባቸው የሚችሉ ቢሆንም እንደ ሌሎቹ ሀገራት በብዙ ሥራዎች ላይ እየተጠቀምን ነው ለማለት ይቸግራል ይላሉ፡፡ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳንኤል፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ቋንቋዎችን ዲጂታላይዝ ማድረግ እና የመሳሰሉትን ጠቅሰው፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ወደ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች በማምጣት ሁሉንም ማኅበረሰብ አካታች የሚያደርጉ ሥራዎች መሥራት እንደሚያስፈልግ አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በደንብ አውቆት ክህሎቱ ኖሮት የሚሠራ ሰው (ማኅበረሰብ) ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ግንዛቤ ሊያሰፉ የሚችል ተከታታይነት ያላቸው ሥልጠናዎች መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ለሰዎች አድካሚና ብዙ ወጪ የሚያስወጡ ጉዳዮችን ማቃለል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ወንጀለኛ ወንጀል ሠርቶ በካሜራ ታይቶ የሚፈለግ ቢሆን በሰው ፈልጎ ማግኘት በጣም አታካች ነው፡፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ግን ባለው መረጃ መሠረት ተናብቦ የመሥራት ሲስተም አማካኝነት በቀላሉ ወንጀለኛውን ሊይዘው ይችላል፡፡ ወንጀለኞችን በፍጥነት በመለየት የሰውን ድካም ማቅለል የሚችል ነው ብለዋል፡፡
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በትክክለኛ መንገድ ለትክክለኛ ዓላማ ጥቅም ላይ ከዋለ በተገቢው ፍጥነት ከተሠራበት ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ አንዳንድ ጊዜ ዘግይቶ መቀላቀል ጥሩ የሚሆንበት ሌሎች የሄዱበት መንገድ በማየት ብዙ ወጪ ሳይወጣ በቀላሉ የተሻለ ቴክኖሎጂ ገዝቶ ለመጠቀም ያስችላል፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክ በፍጥነት አለመጠቀም ሌላ ኪሳራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደኛ ሀገር ብዙ ሥራዎች ይፈልጋል የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት እና ብዙ ሥራዎች የሚሠሩ ተቋማት ማብዛት የመጀመሪያ ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሚሠራው ሳይኖር ተግባሩ ላይ ትኩረት ቢደረግ ብዙ ጥያቄዎች የሚያስነሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ከውጭ ሲስተሞች ሳንላቀቅ ጥገኛ ሆኖ ለመቅረት እንደሚዳርግ ሲገልጹ፤ ‹‹የእኛን ነባራዊ ሁኔታ የሚረዳ የተማረ ሰው ማብዛት እና ለባሕልና እምነት ቅርብ የሆኑ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል፤ ያ ካልሆነ ነገሮች ሊጋጩና እኛ ባላሰብነው መንገድ ሊያሄዱ ይቻላሉ›› በማለት ነው። ለዚህም ኢትዮጵያዊ ሁሉን አካታች የሆኑ ዳታዎች የሚሰበሰብ የሚተነትን ባለሙያ ያስፈልጋል በማለት አስረድተዋል፡፡
አሁን ያለው በተቋም ደረጃ መቋቋሙ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች ዝግጅቶችም መነቃቃት እየተፈጠረ ለመሆኑ አንድ ማሳያ ብለዋል፡፡ ይህንን በማስፋት ረገድ አስፈላጊ ከሆኑ ዘርፎች በመጀመር የግል ዘርፉን በማሳተፍ የአኗኗር ዘይቤ ማስተካከል የሚችሉ አዳዲስ ሲስተሞች ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሰው ሰራሽ ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች ላይ በተለያየ መልኩ ሥራዎችን የሚያሻሸሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ እንደ ስጋት የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ያመለክታሉ፡፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሐሰት የተፈበረኩ መረጃዎች ለመሥራት በጣም አመቺ መሣሪያ እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚለቀቁ መረጃዎች ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይገናኙ ሲሆን፤ እነዚህ መረጃዎች በተለይ በአፍሪካ ሀገሮች ለፖለቲካ አለመረጋጋት ስጋት የሚያመጡ ሲሆን፤ አደጋው ከፍተኛ የሚሆነው ይህንን መሣሪያ ለዚህ ዓላማ የሚጠቀሙ ሰዎች እየበዙ ከመጡ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ከሥራ ማጣት ጋር ተያይዞ ያለውን ስጋት አስመልክቶም ባለን ነገር ላይ ከቆየን ነው ሥራ ማጣት የሚመጣው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ‹‹በሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ምናልባት በሲስተሞች የሚተኩ ሥራዎች እየበዙ ሊሄዱ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ሥራዎችም ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ማሰብ ያስፈልጋልና ዛሬ ላይ አሳሳቢ ነገር ላይ አይደለምና መሥራት መድረስ ያለብን ነገር ላይ መድረስ አለብን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ሀገራት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ አሜሪካና ቻይና የመሳሰሉ ሀገራት እያበለጸጓቸው ያሉ ትልልቅ ሲስተሞች መኖራቸው ጠቁመው፤ እነርሱ በሚሠሩት ሲስተም የሚመጣ ጥፋት ካለ የመጀመሪያ ተጠቂዎችና ተጎጂ የሚሆኑት በሲሰተሙ ደካማ የሆኑ አገራት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በመሆኑም እኛም የእነሱ ሲሰተም እየተጠቀምን መቀጠል የለብንም በራሳችን መሥራት አለብን›› ሲሉ አቶ ዳንኤል ሀሳባቸው አጠቃለዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም