የፓራሊምፒክ የብሔራዊ ቡድን ማጣሪያ ውድድር ተካሄደ

የ2024 የፓሪስ ፓራሊምፒክ ውድድር ሊካሄድ የወራት ዕድሜ ብቻ ይቀረዋል። ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ይህ ውድድር በሺዎች የሚቆጠሩ የፓራ ስፖርተኞችን ያሳትፋል። ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያዊያን የፓራ ስፖርተኞች በውድድሩ ለመሳተፍ የሚያበቃ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ፌዴሬሽን ስፖርተኞቹ በውድድሩ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ነጥብ እንዲያገኙ የብሔራዊ ቡድን ማጣሪያን በማድረግ ሥራውን ጀምሯል። በመሆኑም በፓራሊምፒክ ለመሳተፍ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ላይ የሚሳተፉ ይሆናል።

ለዚህም የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ፌዴሬሽን ዱባይ በሚካሄደው የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ሚኒማ ማሟያ ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመለየት የማጣሪያ ውድድር አካሂዷል። ታኅሣሥ 12 እና 13 በአዲስ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በተካሄደው የማጣሪያ ውድድርም በተለያዩ የጉዳት ዓይነቶች አትሌቶችን ለይቷል። በሚኒማ ማሟያው ውድድር ኢትዮጵያን በፓራሊምፒክ ለመወከል የማጣሪያ ውድድራቸውን ያከናወኑ አትሌቶች ከዓመት በፊት ከተካሄደው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና የተመረጡና በተጨማሪም ጥሩ ውጤት ያላቸው አትሌቶች መሆናቸውን ተጠቅሷል።

ዓለም አቀፍ ውድድሩ ዱባይ ፋዛ በምትባል ከተማ የካቲት ወር መጀመሪያ የሚካሄድ ሲሆን ግራንድ ፕሪ (Grand prix) ይባላል። ይሄም የፓራ ስፖርተኞች በፓራሊምፒክ እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ሚኒማ የሚያሟሉበት ነው። በመሆኑም በፓራሊምፒክ ለመሳተፍ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ባሉት 18 ወራት አትሌቶቹ ሁለትና ሶስት የሚኒማ ማሟያ ውድድሮችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። የተመረጡት አትሌቶች ይሄንንና ሌሎች የሚኒማ ማሟያ ውድድሮችን እንዲሳተፉና እንዲዘጋጁ ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

በማጣሪያው እስከ 7 የሚደርሱ አትሌቶች የተመረጡ ሲሆን መጨረሻ ላይ የተሻለ ሰዓትና ብቃት ያላቸው አትሌቶች እንደሚለዩም ተጠቁሟል። ለዚህም ቴክኒክ ኮሚቴው በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ልየታውን የሚደርግ ይሆናል። በአትሌቲክስ 1 ሺ 500፣ 8 መቶ ፣ 400፣ 5 ሺ ሜትር፣ ጦርና አሎሎ ውርወራ እንደተመረጡ የተጠቆመ ሲሆን ዓለም አቀፍ ሰዓታቸው ታይቶ ከየዘርፉ አንድ አትሌት ለማካተት ጥረት እንደሚደረግ ተጠቅሷል። በማጣሪያው ድንክዬ፣ ሙሉ ለሙሉ ዓይነ ስውር፣ ጭላንጭልና እጅ ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ጊዮን ሴይፉ፣ የማጣሪያ ውድድሩ የተካሄደው በኢትዮጵያ ቻምፒዮና አትሌቶች በነበራቸው ውጤት ላይ ተመስርቶ እንደሆነ አስረድተዋል። በዚህም መሠረት ከየውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት የወጡትን እና ከዛ በኋላ ባሉት ጊዜያት ጥሩ ብቃትን ያሳዩ አትሌቶችን አካቶ መሆኑን ተናግረዋል። ይሄም የተደረገው አሰልጣኞች ያዩትንና የሚያምኑበትን አትሌት እንዲያወዳድሩ በመግባባት ነው። የቻምፒዮና ውድድር አዘጋጅቶ መምረጥ የሚቀል ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ባለበት የበጀት እጥረት ምክንያት በፊት የተመረጡትንና የተወሰኑ አትሌቶችን በመጨመር ማጣሪያውን ማካሄዱን ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንቱ የተመረጡት አትሌቶች በዱባይ ለሚካሄደው ውድድር ዝግጅታቸውን እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፤ ለዝግጅትና ለጉዞ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን በመጠየቅ እና ከተለያዩ ለጋሽ አካላት በሚደረግ ድጋፍ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል። ለዚህ ውድድርም 7 ሰው እንኳ ለማሳተፍ ቢታሰብ 10 ሺ ዩሮ ገደማ የሚያስፈልግ ሲሆን ወጪው የሌሎች ልዑካን ቡድንን ሳያካትት ነው። ለሁለተኛው የሚኒማ ማሟያ ውድድር 25 ሺ ዩሮ ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። ይሄም ምንጩ ከየት እንደሆነ መልስ ያላገኘ ጥያቄ ሲሆን ድጋፍ እንዲደረግ ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጥያቄ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የተነሳ አትሌቶች በግላቸው ልምምድ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን ይሄም እስከ ውድድሩ መጀመር ድረስ መሆኑን ጠቅሰዋል። አሰልጣኞች አትሌቶቹ በሚገኙበት ቦታ ሥልጠና መስጠትና የክትትል ሥራን በመሥራት አትሌቶቹን ለውድድሩ የሚያዘጋጁም ይሆንል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ የሚረዳው ገንዘብ በጣም ትንሽ ከመሆኑም በላይ የሚውለው ለታለመለት ዓላማ ብቻ ነው። ለእንደዚህ ዓይነቱ ውድድር ገንዘቡን መጠቀም የማይቻልና ኢትዮጵያ ከዛ በኋላ በሚኖሩት ዓለም አቀፍ ውድድርና ግንኙነቷ ላይ ችግር ይፈጥራል። በመሆኑም ሀገራት ለእንደዚህ ዓይነት ውድድሮች ወጪዎቻቸውን በመሸፈን ከኮሚቴው ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት መፍጠር ይኖርባቸዋል።

ፌዴሬሽኑ ለፓሪስ ፓራሊምፒክ ውድድር ተሳትፎ ለመብቃት በርካታ በሮችን ቢያንኳኳም ምላሽ የሰጠው አካል ባለመኖሩ መንግሥት እንዲደርስለትም ጥሪውን አስተላልፏል። የፓሪሱ ውድድር ሲመጣ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግ የሚችል ቢሆንም ለዛ ብቁ ለመሆን የሚያስፈልጉ ብዙ ነገሮች መኖራቸውንም ተጠቁሟል። ከዚህ በፊት በነበረው ውድድር የተሳተፈችው አትሌት የወርቅ ሜዳለያን ማስመዝገብ የቻለች ሲሆን በቂ ድጋፍና ዝግጀት ካልተደረገ ይሄ ውጤት ላይኖር እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You