ግርግር የሚፈጥሩ አስተባባሪዎች

ባለፈው ሐሙስ ማታ የመንግሥት ሠራተኞች መውጫ ሰዓት ላይ ነው። ከፒያሳ የሚነሳ የመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ለመያዝ፤ በዚያውም እግሬን ላፍታታ ብዬ ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ሄድኩ። ብዙ ጊዜ መንገድ ላይ ስለሆነ የምይዘው ከመነሻው ምን እንደሚመስል አላውቀውም።

አውቶብሱ ተከፈተና አስተባባሪው ቀድሞ ገባ። ጊዜ ስላለው ነው መሰለኝ መታወቂያ የሚያየው የእያንዳንዷን ፊደል አቀማመጥ ሁሉ ይመስላል። መነሻ ስለሆነ እንጂ መንገድ ላይ የሚገቡት እኮ የታጠፈ 50 ብር ሁሉ ቢያሳዩት ልብ አይለውም። ያም ሆኖ ግን ጥንቃቄውን እያመሰገንኩ አልፌ ተቀመጥኩ።

የሰውየው ጥንቃቄ ግን ከአስተዋይነት የመጣ ሳይሆን ከግል አጉል ባህሪ የመጣ መሆኑን ያወቅኩት ቆይቼ ነው። በትንሽ ትልቁ ይጨቃጨቃል። ገና ሰርቪሱ ሳይነሳ ነው ከአንዷ ጋር ቀበቶ አላሰርሽም ብሎ የተጣላው። ማንም እንኳን ብዙ ሰው በሚጭኑ ትልልቅ አውቶቡሶች ውስጥ ተግባራዊ ባይደረግም ቀበቶ ማሰር ግዴታ መሆኑ ይታወቃል። የሰውየው ችግር ግን ግላዊ ባህሪ ነው። በመንገር ብቻ የሚያልቅን ነገር በቁጣ ይጀምራል። ትንሽ መልስ ከሰጡት ‹‹መታወቂያ አምጡ›› ይላል።

ይሄ የአንድ ተራ ግልፈተኛ ግለሰብ ባህሪ ስለሆነ ንቀን መተው እንችል ነበር፤ ዳሩ ግን ሌሎችም የዚህ ዓይነት ሰዎች በየአገልግሎት መስጫ ቦታው ስላሉ ሥርዓት እንዲኖራቸው ሊነገራቸው ይገባል።

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ለጋራ ደህንነት ሲባል በየአካባቢው ነዋሪዎች ማታ ማታ ሰፈር ይጠበቅ በነበረበት ወቅት የነበረ ሁነት ትዝ አለኝ። በጠባቂዎችም ሆነ በነዋሪዎች ልክ ያልሆኑ እና አጉል ግርግር የሚፈጥሩ ድርጊቶችን አስታውሳለሁ። በጥንቃቄ መፈተሽ እና በጥንቃቄ መታወቂያ ማየት፣ በጥብቅ መመርመር እንዳለ ሆኖ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ልክ ያልሆነ ጥንቃቄ ደግሞ ሌላ ግርግር ይፈጥራል።

አንድ ዕለት ምሽት በየቤታችን ሳለን ድንገት ‹‹ያዘው! ያዘው! ያዘው….›› የሚል የብዙ ሰዎች ድምጽ ሰማን። ሁላችንም ከየቤታችን እየከፈትን ስንወጣ ግምታችን ለጥፋት የተዘጋጀ ሰው ተያዘ የሚል ነበር። የውጭውን በር ከፍተን ስንወጣ ሰብሰብ ብለው አንድ ከ30 ዓመት በታች ሊሆን የሚችል ወጣት እያናገሩ ነው። ራቅ ራቅ ያሉ ሰዎች የገመቱት አለመከሰቱን ስላወቁ ነው መሰለኝ ይስቃሉ።

ነገሩን ስንጠይቅ፤ ጠባቂዎቹ ‹‹ያዘው! ያዘው!›› ያሉት ልጁ ለግል ጉዳዩ ሲሮጥ ሌላ ዓላማ ያለው መስሏቸው ነው። በዚያ ላይ መታወቂያ አሳይቶ በአጠገባቸው ያለፈ ልጅ ነው። ድጋሜ አገላብጠው ሲፈትሹት ምንም ነገር የለበትም። ‹‹ያዘው! ያዘው!›› ሲባል እሱም ግራ ገብቶት የሚያዘውን ሰው ለማየት ሲቆም ነው የያዙት።

ልጁ አስቸኳይ ጉዳይ ቢኖርበትም በዚያን ወቅት ባይሮጥ ጥሩ ነበር፤ የ20 ምናምን ዓመት ወጣት ግን ይህን ሁሉ አርቆ ላያሳብ ይችላል። ግርግር የፈጠሩት ጠባቂዎቹ ናቸው። ልጁን ከጠረጠሩት ቀስ ብሎ በአንድ ሰው ድምጽ መጥራት ነው። ለደህንነት ሲባል ብዙ ሆነው መከተል ቢያስፈልግም ‹‹ጠብቀን ጠብቀን›› ብለውት ፈቃደኛ ካልሆነ ለሁሉም ነገር ያደርስ ነበር። ምንም በሌለበት ግርግር መፍጠር ግን ያልታሰበ አመቺ የግርግር ሁኔታ መፍጠር ነው። ያልታሰበ ግርግር ሲፈጠር ደግሞ ‹‹የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል›› ነው።

አንዳንዶቹ ደግሞ የመገላመጥ ምልክት ሳያሳይ አይቀርም በሚል መጠራጠር የሚጋጩም ነበሩ። ቢያጋጥም እንኳን ለወደፊቱ እንደዚያ እንዳያደርግ ነግሮ ቶሎ ማሰናበት ወይም በትህትና መምከር ሲገባ፤ እንደዚያ ዓይነት ሰው መገላመጥና ማስፈራራት ሌላ ግርግር መፍጠር ነው። እልህ ተጋብተው ድብድብ ቢፈጠር በእንደዚያ ዓይነት ወቅት አስደንባሪ ነው የሚሆነው።

አሁንም ቢሆን ያለንበት ወቅት ሙሉ ለሙሉ ነፃ ነው ማለት አይደለም። ከድብደባ እስከ ሞት ድረስ የሚደርሱ አደጋዎችን እየሰማን ነው። ለመደበኛ የፀጥታ አካላትም ሆነ የአገልግሎት አስተባባሪዎች መታወቂያ በትህትና ማሳየት፣ የሚጠይቁትን ሁሉ በተጠየቀው አግባብ መመለስ ያስፈልጋል። በዚያው ልክ ግን የፀጥታ አካላትም ሆኑ አስተባባሪዎች በግልምጫ እና በስድብ መጀመር የለባቸውም። ምክንያቱም በሥራቸው ላይ ግርግር ይፈጥራል።

አንዳንድ የፀጥታ አካላት ተጠያቂው አካል ምንም ዓይነት ማንገራገር ሳያሳይ በግልምጫ እና በቁጣ የሚጀምሩ አሉ። ወይም አንዳንድ ዜጎች ባለማወቅ የተከለከለ ነገር ሊያደርጉ ሲሉ እንደማይቻል መንገር ሲገባ በግልምጫ አለፍ ሲልም በጥፊና በእርግጫ የሚማቱ አሉ። ምንም እንኳን ግልምጫም ሆነ መደባደብ አግባብ ባይሆንም ቢያንስ ሰውየው እምቢ ካለ በኋላ አይሻልም? አንዳንዶቹ ለምን አላወቅክም በሚል ብቻ ሊማቱ ይችላሉ።

እንደ ዜጋ ቢቻል ሁላችንም መሰልጠን አለብን። ሁላችንም አስተዋይ መሆን አለብን። ይህ ግን እንኳን ገና ብዙ ለሚቀረን ለእኛ የበለጸጉ ናቸው ለሚባሉ ሀገራትም አይቻልም። ሁሉም ዜጋ አስተዋይ ይሆናል ማለት በፍፁም አይቻልም። ወጣ ያለ ባህሪ ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ስለዚህ አስተዋይነትና ትህትና ሊያስተምሩ የሚገባቸው ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው። ምክንያቱም ለዚያ ኃላፊነት (አስተባባሪነት) የተመረጡት የተሻሉ ናቸው ተብለው ነው።

ለምሳሌ አንድ ተረኛ የሆነ ጠባቂ ወይም የሆነ አገልግሎት አስተባባሪ፤ አንድ የሰከረ ሰው አጋጠመው እንበል። የሰከረ ሰው ሊያደርጋቸው የሚችሉ ነገሮች ይታወቃሉ። ሊሳደብ ሁሉ ይችላል። ብልጠትና አስተዋይነት ማለት ከዚህ ሰው ጋር እልህ ሳይጋቡና ሳይገላምጡ ቀስ ብሎ እያሳሳቁና እያጫወቱ መፈተሽ ነው፤ መታወቂያውንም ማየት ነው። ከዚያ ውጭ ግን፤ ወደ ቁጣ እና ማደነባበር ከሄዱበት እንኳን የሰከረ ሰው ያልሰከረውም ግርግር ካልፈጠርኩ ሊል ይችላል። ምንም ዓላማ አስቦ ባይሆን እንኳን በጊዜያዊ ስሜታዊነት ወደ ሌላ ነገር ሊገባ ይችላል።

ያልታሰበባቸው በእልህ መጋባት ብቻ የተፈጠሩ ብዙ ግጭቶችን አስተውየ አውቃለሁ። ግጭቶች የተፈጠሩት በአንደኛው ወገን አላዋቂነትና አጉል ጀብደኝነት ነው። አንዳንድ ጊዜ በአስተባባሪ አንዳንድ ጊዜ በባለ ጉዳይ ግልፍተኝነት አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። አንዳንዱ ባለጉዳይ (ተገልጋይ) ወይም መንገደኛ በግሉ ያጋጠመውን ችግር ሌላ ሰው ላይ ለመወጣት ያስባል። በመሆኑም እንደ ነዋሪ የሚጠየቃቸውን ሕጋዊ ግዴታዎች ሁሉ ‹‹ምን አገባችሁ!›› ይላል። አንዳንዱ የፀጥታ አካል ወይም አስተባባሪ ደግሞ ሥነ ሥርዓት ያለውን የሰለጠነ ዜጋ ሁሉ ሲጠይቅ በግልምጫ ሊሆን ይችላል።

በየቦታው ብዙ ዓይነት ባህሪ ያለው ሰው ቢኖርም ቢያንስ ግን ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች (ትንሽም ብትሆን) የተሻለ አርዓያ ሊሆኑ ይገባል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You