ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት የአንበሳውንድርሻ እየተጫወተ ያለው ባንክ

 በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን የምርትና ምርታማነት እድገት ለማስቀጠል፣ አርሶ አደሩን ከእጅ ወደ አፍ አመራራት ለማውጣት ሚናቸው ከፍተኛ ከሆነ ቴክኖሎጂዎች መካከል የሜካናይዜሽንን ማስፋፋት አንዱ ነው። ሜካናይዜሽን ማሳን ለዘር በማዘጋጀት፣ በዘር በመሸፈን፣ ሰብሉ ሲደርስም ለማጨድና ለመውቃት፣ በመስኖ እርሻም በውሃ ማሳቢያ መሳሪያዎች ለመገልገልና ለመሳሰሉት ተግባሮች ወሳኝ ነው።

በኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን የዋጋው ውድነት፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የነበረው የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ደንቀራ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። መንግሥት እነዚህን መሰል የግብርናው ዘርፍ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ብዙ መሠራቱን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች፣ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችና የመሳሰሉት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆን ጀምረዋል።

አቅርቦቱም በክልል መንግሥታትና በፌዴራል መንግሥት በኩል ሲፈጸም ይስተዋላል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክም በማሽን ሊዝ ሥርዓት ለአርሶ አደሮችና የሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ ኮምባይነሮችን ትራክተሮችንና የመሳሰሉትን እያቀረበ ይገኛል። ባንኩ በቅርቡም የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉት የእነዚህ የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ርክክብ ከሊዝ ደንበኞቹ ጋር አድርጓል።

ባንኩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በተመረጡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ የፋይናንስ ደንበኞቹ ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል። በተለይ በማዕድንና በግብርና ሥራ ለተሰማሩ የሊዝ ደንበኞቹ የሚሰጠው ፋይናንስም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።

ከንግድ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛው ፋይናንስ አቅራቢ እንደሆነ የሚገለጸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት ችሏል። በቅርቡም በቃሊቲ ከሚገኙት ወረታ ኢንተርናሽናልና በሞይንኮ ኢንተርናሽናል እንዲሁም በቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኘው ሐግቤስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር ያስመጣቸውን 10 ኮምባይነሮች፣ 15 ትራክተሮች እንዲሁም 14 እስካቫተሮችን በግብርና ዘርፍ እና በማዕድን ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ የሊዝ ፋይናንስ ደንበኞቹ አስረከቧል።

በርክክቡ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው እንዳሉት፤ ባንኩ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ለሊዝ ደንበኞቹ የሚሰጠው የሊዝ ፋይናንስ ድጋፍ ከነበረበት ሁለት ቢሊየን ብር አሁን ወደ 11 ቢሊየን ብር አድጓል።

የሀገሪቱ የእርሻ ሥራ በአነስተኛ ማሳ አርሶ አደሮች ይዞታ ላይ የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ዓይነት ልምምድ ግብርናን ወደ ትልቅ ኢንቨስትመንት ማሳደግም አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፤ አርሶ አደሮች ትራክተር እና ኮምባይነር ገዝተው መሥራት እንደሚከብዳቸውም አስታውቀዋል።

በሊዝ ፋይናንሲንግ አሰራር /ሞዳሊቲ/ ግን እርሻው የኩታ ገጠም መልክ እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ ይሄንን አገልግሎት የሚሰጡ ደንበኞች አርሶ አደሮቹ ዘንድ ሄደው በኪራይ መሬታቸውን እንደሚያርሱላቸው፣ ሰብሉ ሲደርስም እንዲሁ አጭደው፣ ወቅተውና እህሉን ሰብስበው እንደሚያስረክቧቸው አብራርተዋል።

ይህ ዓይነቱ አሰራር የግብርና ሜካናይዜሽንን በቀላሉና በስፋት ወደ ግብርናው እንዲገባ እንደሚያግዝ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አስታውቀዋል፤ ሰብል በመሰብሰብ ወቅት 30 በመቶው ምርት እንደሚባክን ጥናቶች ማመላከታቸውን ጠቅሰው፣ ሜካናይዜሽን በአጨዳ ጊዜ ሊባክን የሚችለውን ምርት ለመጠበቅ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት እንዳስታወቁት፤ ብቸኛው የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ልማትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ኢንቨስትመንትን በመደገፍ ሰፋፊ ሥራዎችን ይሠራል። ባለፉት አምስት ዓመታት ሰፊ የሪፎርም ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህ የማሻሻያ ሥራውም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ፈትቶ ዛሬ በኢትዮጵያ ካሉ ባንኮች በካፒታል ደረጃ ሁለተኛው ከፍተኛ የካፒታል ደረጃ ላይ ደርሷል። በአሁኑ ወቅትም ባንኩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እስከ 40 ቢሊየን ብር የሚደርስ ካፒታል ያለው ሲሆን፣ በዚህም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በተመረጡ የአገልግሎት ዘርፎች የሚደረጉ ልማቶችን በመደገፍ በኩል ከፍተኛ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በግብርናው ዘርፍ በሁለት መልኩ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ አንደኛው በሊዝ ፋይናንሲንግ፣ ሁለተኛው ደግሞ በፕሮጀክት ፋይናንሲንግ የሚሰጠው ድጋፍ ናቸው። የሊዝ ፋይናንሲንግ ልዩ ሲሆን፣ ልዩ የሚያደርገውም ደንበኞች ለሥራ ማስኬጃ የሚያገለግለውን 20 በመቶ እንዲያዘጋጁ ተደርገው ቀሪውን 80 በመቶ ባንኩ በራሱ በሚያደርገው ፋይናንስ ማሸነሪዎችን አስመጥቶ በሊዝ መልክ በማቅረቡ ነው። በተለይ ከተለያዩ ተቋማት ተመርቀው ለሚወጡ ወጣቶች ቀላልና ቀልጣፋ አሰራር በመከተል ብዙ የካፒታል ንብረት ሀብት ለሌላቸው ግለሰቦች ማሸነሪው እንደማሰያዣ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋል።

የሀርቨስተር ኮምባይነር ርክክብ ሲደረግ ያገኘናቸው አቶ መሀመደ ሀጂ ከድር ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ቦቆጂ የመጡ የአርሶ አደር ልጅ ናቸው። እሳቸው የወላጅ አባታቸው በባህላዊ መንገድ አዝመራውን ሲያጭዱ ከፍተኛ የሆነ የምርት ብክነት ሲከሰት አስተውለዋል። በዝናብ ወቅት ለመሰብሰብም ከባድ መሆኑን ተረድተዋል። ልማት ባንክ እነዚህን ማሽኖች በሊዝ ማቅረቡ ምርትን በጊዜ ለመሰብሰብ እና ብክነትን ለመቀነስ ትልቅ እገዛ በማድረግ የአርሶ አደሮችን ችግር ያቃልላል፤ ሀገርንም ያሳድጋል ብለዋል።

‹‹አባቶቻችን ምርት ሲሰበስቡ ይቸገሩ የነበረበት ሁኔታ በእጅጉ ይሰማኝ ነበር›› ያሉት አቶ መሀመድ፣ እሳቸው በዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ወደሚታገዘው የግብርና ሥራ መግባት መቻላቸውን ነው የገለጹት። ወደፊትም ከልማት ባንክ ጋር በመሥራት በኢንዱስትሪው ዘርፍም መሰማራት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ልማት ባንክ ማሽነሪዎቹን በወቅቱ ማቅረብ እንዳለበት አስገንዝበው፣ ማሽኖቹ አሁን የመጡት አጨዳው እያለቀ ባለበት ወቅት እንደሆነም አመላክተዋል። እሳቸው በሊዝ ደንበኝነት ማሽኑን ለመግዛት አስፈላጊውን ቅደመ ሁኔታ አሟልተው ሁለት ዓመታት ያህል መጠበቃቸውን አስታወሰው፣ ልማት ባንክ ብቻ ሳይሆን ከልማት ባንክ ጋር የሚሰሩ ድርጅቶችም በመናበብ ማሽኖቹ ወደብ ላይ የሚኖራቸውን ቆይታ ማሳጠር እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። ማሽኑ የጭነት መኪና እንደሚፈለግ አቶ መሀመድ አስታውቀው፣ ለእዚህም 200 ሺህ ብር ያህል እንደሚጠየቅ ገልጸዋል። ይህም ከሊዝ ፋይናንሲንግ ጋር ቢታይ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሌላው ትራክተር የተረከቡት የአዲናስ እርሻ ልማት ባለቤት አቶ በሪሁን አበራ በበኩላቸው ወደ እርሻ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በእንቁላል ንግድ ተሰማርተው ሰርተዋል፤ በእዚህም ከጎጃም ወለጋ፣ ደምቢዶሎ፣ አሶሳ መንዲ ድረስ በበቅሎ እየተጓዙ ነግደዋል። ከዚህ በኋላ ነው ወደ እርሻ ሥራው የገቡት። ሌሎች ትራክተሮችም እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ በሪሁን፣ ትራክተሩን ከልማት ባንክ በሊዝ መግዛት በመቻላቸው ተደስተዋል።

አቶ በሪሁን ቀደም ሲል ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ላይ እርሻ እንደነበራቸውና በፀጥታ ችግር ሳቢያ እንዳቆሙ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ምስራቅ ጎጃም እና አዊ ዞን ላይ በ400 መቶ እና በ500 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ የግብርና ሥራቸውን እንደሚያከናወኑ ተናግረዋል።

የእርሻ ሥራ በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው በልምድ ላይ ተመስርቶ መሆኑን አቶ በሪሁን ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፌዴራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት ድጋፍ ትራክተሮች በብዛት ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአርሲ ዞኑ ሄጦሳ ወረዳው አቶ ፈይሳ ጉታም ትራክተር እና ሀርቨስት ኮምባይነር ተረክበዋል። አርሶ አደሩ ከአንድ ጥማድ በሬ በመነሳት ወደ እርሻ ሥራው የገቡ ናቸው። አሁን ግን ወደ ሜካናይዜሽን ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል። ከልማት ባንክ ትራክተር እና ኮምባይነር መረከባቸውን ጠቅሰው፣ ልማት ባንክ አርሶ አደርን ማዕከል በማድረግ ግብርናውን ወደ ዘመናዊ የእርሻ ሥራ እያሻገረ መሆኑን አስታወቀው፣ ለዚህም አመስግነዋል። ወደፊትም ባንኩ ከአርሶ አደሩ ጎን መሆን ከቻለ የተሻለ መሥራት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ከ15 ዓመታት ልፋትና ድካም በኋላ ዛሬ ላይ በተሻለ የግብርና ቀመና ላይ መድረስ እንደቻሉ የገለጹት አቶ ፈይሳ፤ በእርሻ ሥራ ላይ ወስኖ መግባት ከተቻለ መለወጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል። አሁን በክላስተር በመሆን ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ግብርናውን ወደ ሜካናይዜሽን በመቀየር በኩል ልማት ባንክ የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወተ ነው ብለዋል።

ከሀገሪቱ ሕዝብ አብዛኛው አርሶ አደርና አርብቶ አደር ለሆነባት ሀገር ትራክተሮችና ኮምባይነሮች ለአርሶ አደሮች መቅረባቸው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል። ብቻህን በበሬ በማረስ ብቻ ወደሚፈለገው ግብ መድረስ አይቻልም ያሉት አቶ ፈይሳ፣ ሜካናይዜሽኑ ሥራችንን የበለጠ በማሳለጥ ወደ ውጤታማነት ያደርስልናል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ትናንት ከእጅ ወደ አፍ የነበረው የእርሻ ሥራቸው ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ እየወጣ መሆኑን ጠቁመዋል። ‹‹ቀስ ብሎ በመሄድና በሩጫ በመሄድ መካከል ልዩነት እንዳለ ሁሉ በበሬ በማረስ እና በትራክተር አርሶ በሀርቨስት ኮምባይነር መሰብሰብ የጎላ ልዩነት አለው›› ብለዋል።

በሜካናይዜሽን ስንጠቀም ሀገራችን ራሷን በምግብ ለመቻል ከምታደርገው ጥረት አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተው፤ ‹‹እኔ ለራሴ ብዬ ሳመርት ለገበያም ጭምር በመሆኑ በተዘዋዋሪ ለሀገር እድገት የጎላ ሚና አበረክታለሁ ብለዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተከናወኑ ተግባሮችን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘር እና በአዝመራ መሰብሰብ ወቅት ትራክተሮችና የአዝመራ መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችን በስፋት ማየት ተለምዷል። ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችም እየተበራከቱ ይገኛሉ። የክልል መንግሥታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትራክተሮችንና ኮምባይነሮችን እና ለመስኖ ልማት የሚውሉ የውሃ ማሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሮች እያቀረቡ ይገኛሉ።

የአርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ፍላገት እየጨመረ ቢመጣም፣ አርሶ አደሮች በጠየቁት ልክና በጠየቁበት ወቅት ማሽነሪዎቹን ማግኘት እንዳልቻሉ እየጠቆሙ ይገኛሉ። ይህን የአርሶ አደሩን ጥያቄ መመለስ ላይ አሁንም በትኩረት መሥራት ይገባል። አርሶ አደሩ የሜካናይዜሽን ፍላጎት እንዲኖረው ተደርጎ አቅርቦት ላይ ፈጣን አለመሆን በግብርናው ዘርፍ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ በተያዘው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል።

በመሆኑም ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን የሚያቀርቡ ተቋማት፣ ክልሎች፣ የፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት በዚህ ላይ እያከናወኑ ያሉት ተግባር ሊበረታታ የሚገባው ሆኖ፣ እየተፈጠረ ያለውን የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You