አቶ አየለ አትናሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ከመመሥረታቸው በፊት ክለብ እንደሚመሠርቱ በሕልማቸው አዩ:: ይህንን ሕልማቸውንም ጓደኛቸው ለጆርጅ ዱካስ ኅዳር 6/1927 ዓ.ም እንደነገሯቸው በታሪክ ማሕደር ሰፍሮ ይገኛል:: ታላቁ ክለብ ከመመሥረቱ አንድ ዓመት በፊት 1927 ጆርጅ ዱካስ እና አየለ አትናሽ በመማሪያ ደብተራቸው ላይ ኅዳር 7/1927 ‹‹ክለብ ለመመሥረት እኔና ጆርጅ ዱካስ ተስማማን›› የሚል ስምምነት አሰፈሩ:: በወቅቱ የሚመሠረተው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደሚባል፣ የኢትዮጵያ ኃያል ክለብ እንደሚሆን ግን አልገመቱም ነበር:: ሕልም ግን ነበራቸው!
በአንድ ሰው ሕልም የተመሠረተው ክለብ የኢትዮጵያ ኃያል ክለብ ሆኖ እነሆ ዘንድሮ 88ኛ ዓመቱን ለማክበር በቅቷል:: ፈረሰኞቹ በነዚህ ዘለግ ያሉ ዓመታት በድል ደምቀው በኃያልነት ጎዳና መጓዛቸውን ቀጥለዋል:: ብዙ ውጣ ውረዶችንም አሳልፈዋል:: ከሀገር ውስጥ ስኬት ባሻገር በአህጉር አቀፍ ውድድሮችም ኢትዮጵያን በመወከል ትልቅ ታሪክ አላቸው:: እኛም 88ኛ ዓመታቸውን በማስመልከት በዛሬው የስፖርት ማሕደር ዓምዳችን የፈረሰኞቹን አህጉር አቀፍ ውድድሮች ጉዞ ከብዙ በጥቂቱ እናስታውሳለን::
ፈረሰኞቹ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ለበርካታ ጊዜ በኢንተርናሽናል ውድድር መሳተፍ የሚያስችላቸው ውጤት አስመዝግበዋል:: በዚህም ከሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦች በተሻለ ሁኔታ በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል:: በአህጉር አቀፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈሉትም 1959 ዓ.ም ነበር:: በወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን ክለቦች ዋንጫ ተብሎ ይጠራ በነበረውና አሁኑ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲሆን ፈረሰኞቹ በታሪክ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡበትም ነበር:: በመጀመሪያው ዙር የዑጋንዳው ቢቲማስቲክ ማሱን ራሱን ከውድድሩ በማግለሉ ጊዮርጊስ በቀጥታ አለፈ:: በሁለተኛው ዙር የግብፅን ኦሎምፒክ አሌክሳንዴርያን 5ለ2 በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው አለፉ ለፍፃሜ ለማለፍ ከዴሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ኢንግልበርት የአሁኑ ቲ.ፒ ማዜምቤ ጋር ተገናኝቶ 4ለ3 በሆነ ድምር ውጤት ተሸንፋል:: አዲስ አበባ ላይ 2ለ1 ቢያሸንፍም ኪንሻሳ ላይ 3ለ1 በመሸነፉ ነበር ለፍፃሜ የማለፍ እድሉ ያልተሳካው::
ጊዮርጊስ በቀጣይ ዓመታት 1968 እና 1969 በመጀመሪያው ዙር ተሰናበተ:: በ1972ም ከሁለተኛው ዙር ማለፍ አልቻለም:: በ1976 በመጀመሪያ በ 1986 በሁለተኛው ዙር ከውድድሩ ወጣ:: በ1983 በኢትዮጵያ በነበረው የመንግሥት ለውጥና አለመረጋጋት ምክንያት ራሱን ከውድድረ አገለለ:: በ 1992 እና በ 1993 ቅድመ ማጣሪያ በነበረባቸው ውድድሮች አልተሳካለትምና ወደ አንደኛ ዙር እንኳን አልደረሰም:: ከዚህ ዓመት በኋላ የወድድሩ ፎርማትና ስያሜ ተለወጠ::
ከ1997 ጀምሮ ይህ ውድድር የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በሚል ስያሜ ተተካ:: በመጀመሪያው ውድድር በመጀመሪያው ዙር ከውድድሩ ተሰናበተ:: ከግብፁ ታዋቂ ክለብ ዛማሊክ ጋር የተገናኘ ሲሆን ግብፅ ላይ 2ለ0 ተሸንፎ በመልሱ ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይቶ 3ለ1 በሆነ ድምር ውጤት ተበልጦ ነበር ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍ ያልተቻለው::
ቀጣይ ተሳትፎውን ያገኘው በ2000 ነበር:: በቅድመ ማጣሪያው የዑጋንዳውን ቪላ ካምፓላን 5ለ2 በሆነ ድምር ውጤት ረትቶ አለፈ:: ከሜዳው ውጪ ካምፓላ ላይ ሁለት አቻ ተለያይቶ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ 3ለ0 አሸንፎ ነበር ውጤታማ የሆነው:: በመጀመሪያው ዙር በቪታሎ ቡሩንዲ በመሸነፉ ጉዞው አልረዘመም:: ከሜዳው ውጭ 2ለ2 አቻ ቢለያይም በሜዳው 2ለ1 መሸነፉ ነበር በውድድሩ ላለመዝለቁ ምክንያት የሆነው:: በቀጣዩ ዓመት 2001 ከኬንያ ተስካር ጋር የተገናኘ ሲሆን አዲስ አበባ ላይ 1ለ1 ኬንያ ላይ ደግሞ ያለግብ አቻ ተለያዩ:: ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው ሕግ መሠረት ተስካር አላፊ ጊዮርጊስ ወዳቂ ሆኑ::
በ2003 ለአራተኛ ጊዜ የመሳተፍ እድል ባገኘበት ወቅትም ቅድመ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻለም:: ኡጋንዳ ላይ 1ለ0 ቢያሸንፍም አላለፈም:: ምክንያቱም አስቀድሞ አዲስ አበባ ላይ 3ለ1 ተሸንፎ ነበርና:: በቀጣይም ውድድር 2004 ላይ ደግሞ በሱዳኑ አልሂላል አምደርማን ተሸንፎ በመጀመሪያ ዙር ከውድድሩ ተሰናበተ:: በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳውና ደጋፊው ፊት አዲስ አበባ ላይ 2ለ1 ተሸንፎ ስለነበር ካርቱም ላይ አንድ አቻ መለያየቱ ሊያሳልፈው አልቻለም:: በእነዚህ ሁለት ዓመታት ከሜዳው ውጭ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ቢችልም በሜዳው ግን እድሉን አለመጠቀሙ ጎድቶታል::
በ2006 አወዛጋቢ የውድድር ዘመን ያሳለፈበት ነው:: በመጀመሪያው ዙር ከግብፅ ኢኤንፒፒ(ENPPI) ጋር ነበር የተገናኘው:: ይህ ክለብ በወቅቱ በዓረብ ቻምፒዮንስ ሊግ ለፍፃሜ የበቃ ስለነበር ጨዋታው ጠንካራ ይሆናል የሚል ግምት አድሮ ነበር:: ይሁንና ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ 0ለ0 በመለያየት በሜዳው ደግሞ 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ::
በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የጋናውን ኸርትስ ኦፍ ኦክል 4ለ0 አሸነፈ:: ይህ በኢንተርናሽናል ውድድር ታሪኩ ታላቅ ድል ስለነበር በቀጣይ ተስፋ ተጣለበት:: በመልሱ ጨዋታ ግን ያልተጠበቁ ክስተቶችን አስተናገደ:: ከሆቴል ጀምሮ የደረሰበት እንግልት እስከ ሜዳ ዘለቀ:: የእለቱ ዳኛ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን አሳለፉ:: ባለሜዳዎቹ 2ለ0 መሩ የፍፁም ቅጣት ምትም አገኙ፣ በዚህ ወቅት በደሉን መቋቋም ያልቻሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የኦህንጃን ስታድየም ሜዳ ጨዋታው ሳይጠናቀቅ አቋርጠው ወጡ:: የውድድሩ አስተዳዳሪ ፊፋ ውሳኔም ወደ ጋናው ክለብ ተጋዘ:: ጊዮርጊስ ወድቆ ኸርትስ ኦፍ ኦክ እንዲያልፍ ተደረገ::
በቀጣዩ ዓመት 2007 የመጀመሪያውን ቁጭት ይዘው አዲስ አበባ ላይ የኮንጎ ብራዛቪሉን ኤቶል ዲ ኮንጎን ያስተናገዱት ጊዮርጊሶች 1ለ0 አሸነፉ:: በመልሱ ጨዋታ 2ለ0 መሸነፋቸው ግን ሕልማቸውን አጨናገፈባቸው:: የመጨረሻዎቹ ቡድኖች ላይ ገብተው ኤቶልን ከመግጠማቸው በፊት ከሱፐር ኤስከም ጋር ተደልድለው ነበር:: ይሁንና የማላዊው ክለብ ራሱን በማግለሉ በቀጥታ አለፉ::
በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ፊፋ ሀገሪቱን ከማንኛውም ኢንተርናሽናል ውድድር ማገዱ ክለቦቻችንንም ይመለከታልና ጊዮርጊስም መሳተፍ በነበረበት 2009 ሳይሳተፍ ቀረ:: የተፈጠረው ችግር ተቀርፎ እገዳው መነሳቱ በ2010 ወደ ውድድር እንዲመለስ አስቻለው፣ የተደለደለውም ከሱዳኑ ኤልሜሪክ ጋር ነበር:: የመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ ሜሪኮች መምራት ችለው ነበር፣ መሐመድ ናስር በጭንቅላት በመግጨት ያስቆጠራት ግብ ግን ባለሜዳውን ነጥብ አጋራች:: የመልሱ ጨዋታ በኤልሜሪክ ስታዲየም ሲደረግ አዳነ ግርማ ጊዮርጊስን መሪ አድርጓል:: ማሪኮች ሦስት ግቦችን በማስቆጠራቸው ጊዮርጊስን ጥለው ማለፍ ቻሉ::
ጊዮርጊስ በዚሁ ዓመት በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍፃሜ መድረስ ችሏል። በዚህም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ክለብ ሆኗል። ምንም እንኳን ዋንጫውን ለመውሰድ የነበረው ሕልም በሩዋንዳው ኤ ፒ አር በመሸነፉ ቢጨናገፍም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም