‹‹የዓለም መብራቶች››

ሠላም፣ ጤና ይስጥልኝ ልጆችዬ፤ እንዴት ናችሁ? የተገናኘነው የዛሬ ሳምንት ነበር አይደል? መቼም በአንድ ሳምንት ውስጥ በእናንተም ይሁን በእኛ በኩል ብዙ ክንውኖች መኖራቸው የታወቀ ነው። ለምሳሌ በእናንተ በኩል ትምህርት ስትማሩ፣ በጥናት፣ አልፎ አልፎ በጨዋታ ጊዜያችሁን በአግባቡ ስትጠቀሙ እንደነበር ተስፋ አደርጋለሁ:: በእኛ በኩልም ከምንሠራቸው ሥራዎች መካከል ደግሞ “ለልጆች ምን ይዘን እንቅረብ?›› በማለት ለእናንተ የሚሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት አድርገናል:: ስለዚህም ዛሬ የልጆች መጽሐፍትን የጻፈች አንዲት ጎበዝ ደራሲ እና የጤና ባለሙያ(ነርስ) እናስተዋውቃችኋለን፤ እሺ ልጆች::

ስሟ ማክዳ ሁሴን አርሺ ይባላል:: በሙያዋ ነርስ እና ደራሲ ናት:: የተወለደችው ኢትዮጵያ ሲሆን፣ አሁን የምትኖረው በአሜሪካ፣ ቨርጂኒያ ግዛት ነው:: ‹‹የዓለም መብራቶች›› የተሠኘ መጽሐፍ በማዘጋጀት ለልጆች “እንካችሁ›› ብላለች:: መጽሐፉ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝኛ ቋንቋ “The World Needs a Uniquely Happy You” በሚል ርዕስ የተጻፈ ሲሆን፤ በጋዜጠኛ አንተነህ ከበደ አማካኝነት “የዓለም መብራቶች” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሟል:: አንጋፋው ደራሲ ኃይለ መለኮት ደግሞ የአርትኦቱን ሥራ በሚገባ ሠርተውታል::

ደራሲዋ ባሳለፍነው ሐሙስ ታኅሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል በተዘጋጀው ‹የልጆች ፌስቲቫል እና የመጽሐፍ ምርቃት› መርሐ ግብር ላይ ተገኝታለች:: በዝግጅቱ ላይ ሙዚቃ፣ በአንጋፋና ወጣት ተወዳጅ የሙዚቃ ባለሙያዎች፤ እንዲሁም ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ቀርበዋል:: ልጆችም ልዩ ልዩ ተሰጥዖዋቸውን አሳይተውበታል:: ከዚህ ባሻገርም፣ ልጆች ላይ የሚሠሩ ተቋማት ራሳቸውን እንዲሁም ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር::

ደራሲ ማክዳ እንደምትናገረው ከሆነ መጽሐፉ ለሁሉም ሰው ሊደርስ የሚገባው መልዕክት ያለው ነው:: በዋናነት ሁለት መልዕክቶችን የያዘ ሲሆን፣ አንደኛው ልጆች የራሳቸውን ተሰጥዖ ፈልገው እንዲያገኙ እና በዝንባሌያቸው ደስተኛ ሆነው እንዲሠሩ የሚያበረታታ ነው:: ሁለተኛው መልዕክት ደግሞ ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተው ዘላቂ ጓደኝነት እንዲኖራቸው፤ እንዲሁም፣ በፍቅር አብሮ፣ ዘልቆ ስለመኖር የሚያሳስብ ነው::

ስለሆነም መጽሐፉ ለሀገር ይጠቅማሉ የተባሉ መልዕክቶችን የያዘ ሲሆን፤ አጠር አጠር ብሎ በግጥም መልክ ተዘጋጅቷል:: ልጆች የንባብ ፍቅራቸውንና ክሂላቸውን እንዲያጎለብቱ ብቻ ሳይሆን፣ ልጆችን ሊስብ በሚችል መንገድ ታስቦበት የተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል::

ደራሲ ማክዳ ለሌሎች ደራሲዎች መልዕክት አላት:: መልዕክቷ ምን መሠላችሁ ልጆች? ‹‹ልጆች የሚስብ እና የሚማርክ ቀለም ያስደስታቸዋል። ስለዚህም መጽሐፍት በሚጽፉበት ጊዜ የእነሱን ፍላጎት ሊያሟላ በሚችል መልኩ መሆን አለበት::›› የሚል ነው::

ልጆች ብሩህ አዕምሮ አላቸው:: ወላጆች የልጆችን ብሩህ አዕምሮ ማጎልበት አለባቸው:: እንዲሁም ልጆቻቸው ዝንባሌቸውንና ተሰጥዖዋቸውን እንዲያገኙ ማገዝ ይገባል:: ልጆች ‹‹ለምን አታነቡም?›› ብሎ ከመውቀስ፣ እንዲያነቡ መሥራት ይኖርብናል ያለችው ደራሲ እና ነርስ ማክዳ፣ “ሁሉም ወላጅ ልጆቹ ውጤታማ እንዲሆን ይፈልጋልና ሁላችንም በጋራ አብረን እንሥራ›› ስትልም ለወላጆች መልዕክቷን ታስተላልፋለች::

ልጆችዬ፣ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም ከልጆች መጽሐፍት ጋር በተያያዘ ሦስት ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን መቀበሏን ታውቃላችሁ? አዎ ልጆች፣ ደራሲ እና ነርስ ማክዳ ሦስት ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተቀብላለች:: በቀጣይም ልጆች ባሕላቸውን፣ ታሪካቸውንና ሌሎች ማንነታቸውን በሚገባ እንዲያውቁ የሚያግዙ ሁለት መጽሐፍትን በማዘጋጀት ላይ እንደሆነች ገልጻለች:: ይህንን መጽሐፍም ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎች እንዲዳረስ ለማድረግ ጥረት እያደረገችም ትገኛለች::

በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎች መጽሐፉን በተለያዩ የመጽሐፍት መደብሮች የሚያገኙት ሲሆን፤ በውጭ ሀገር ለሚገኙ ዜጎች ደግሞ አማዞን እና የተለያዩ የመጽሐፍት መሸጫ መደብሮች ማግኘት ይቻላል::

ልጆችዬ፣ የተለያዩ ደራሲዎች እናንተን እውቀት ለማስጨበጥ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ ለማድረግ መጽሐፍትን እየጻፉ ይገኛል:: ታዲያ እናንተም የንባብ ልምዳችሁን ከልጅነታችሁ ጀምሮ ለማዳበር አሁን በርትታችሁ ማጥናት፤ እንዲሁም የተለያዩ መጽሐፍትን ከጥናት ሰዓታችሁ ጋር ሳይጋጭባችሁ ማንበብ ይኖርባችኋል፤ እሺ ልጆች:: በሉ እንግዲህ ልጆችዬ፣ ለዛሬ በዚህ እናብቃ አይደል? ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ በሠላም ለመገናኘት እንዲያበቃን በመመኘት እንሰነባበት::

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You