ከቀድሞዋ ላኮመልዛ ከአሁኗ ደሴ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቁርቁር ቀዬ አጎሮ ጨባ የምትሰኝ መንደር ውስጥ ሼህ ሙሃባ ይመርና ወይዘሮ የተመኙ ወልዴ የተባሉ ጥንዶች በፍቅር በቀለሱት ጎጆ ይኖሩ ነበር:: ታዲያ እነኚህ ጥንዶች በሀብት ረገድ ለሀገር ለመንደሩ ባይተርፉም ለራሳቸው ብሎም ለልጆቻቸው የማያንሱ ብርቱዎች ነበሩ:: በልጅ ረገድም ከአንድም በ12 ልጆች ተባርከው በፍቅር ይኖሩ ነበር:: ችግሩ 12ቱም ልጆች ወንድ መሆናቸው ላይ ነው::
ቤቱ ከምንም በላይ ሴት ልጅ ናፍቋል:: በቀጣይ ይሳካል እያሉ የወላጆቹ ሙከራ ቤቱ ላይ ያሉትን የወንድ ልጆች ቁጥር ከመጨመር አልዘለለም:: የሴት ልጅ ፍላጎታቸውን ማሟላት ያቃታቸው እናት ቢቸግራቸው በአካባቢው የነበሩ አዋቂን ደጅ እስከመጥናት አድርሷቸዋል:: ለአዋቂውም “ሴት ልጅ ከወለድኩ ነጭ በሬ እሰጣለሁ” ብለው እስከመሳል ደርሰዋል:: አዋቂውም “ሴት ልጅ ትወልጃለሽ፤ የዓለም ሕዝብም ያውቃታል” የሚል መልስ እንደሰጣቸውና በተስፋ እንደጠበቁ ታላቅ ወንድሟ ኢንስፔክተር የሱፍ ሙሃባ በአንድ ወቅት ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል::
እውነት የአዋቂው ንግርት ሰምሮ ይሁን፣ ወይም የአጋጣሚ ነገር እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፤ በ1959 ዓ.ም የቤቱ 13ተኛ ልጅ ሆና ጠይሟ ዚነት ሙሃባ ቤተሰቡን ተቀላቀለች:: ከበርካታ ጉጉትና መሻት በኋላ በ13ኛ ምጥ ላይ የተገኘች ልጅ ናትና የቤቱ ብርቅ የስስት ልጅ ነበረች:: እንደ ወንድሟ ምስክርነት ሴት ልጅ በስለት የወለዱት እናት በምን እንደምትታወቅ ባያቁም መታወቋን እርግጠኛ ሆነው “በምን ይሆን የኔ ልጅ የምትታወቅ?” ብለው በተስፋ ይጠብቁ ነበር:: እናቷ ወይዘሮ የተመኙ ድምፀ መረዋ ናቸውና የሠፈሩ ሰርግ አድማቂ ነበሩ:: ታዲያ ልጅም በዛ ወጥታ፤ ከብት ጥበቃ ከእኩዮቿ ጋር መስክ ብትውል ለአፍታ ዝም የማትል አንጎራጓሪ ወጣት:: እሷም እንደ እናቷ የሰፈር ሠርግ አድማቂ ብቻ ሳይሆን የጥምቀት በዓል አጃቢም ሆነች::
ዚነት ቤት ውስጥ ምንም ሥራ ብትሠራ ማንጎራጎር የማይታክታት፤ ከተሳፈረችበት ምስጠት (ተመስጦ) ለመመለስ ጊዜ የሚወስድባት ታዳጊ ዜመኛ ነበረች:: ጠሪው ደክሞት መጣራቱን ሲያቆም እሷ ከተሳፈረችበት የሙዚቃ ፈረስ ስትመለስ “ተጣራችሁ?” ብላ እንደ አዲስ ትጠይቃለች:: አባቷ ልጃቸው ሙዚቀኛ መሆኗን ሊደግፉ ቀርቶ ልጆቻቸው ከቁራን መቅራትና መሰል መንፈሳዊ ትምህርቶች ውጭ ዓለማዊ ትምህርት እንዲማሩ የማይደግፉ ነበሩ:: እናት የሠፈር ሰርግ አድማቂ ድምፀ መረዋ ነበሩና ከሳቸው በኩል የተሻለ ድጋፍ ነበራት::
እሷ ነብስያዋን ለሙዚቃ አስረክባለች። በዚህ ሁኔታ እያለችና ትምህርቷን እየተከታተለች ባለበት ወቅት እንደ ሀገር ልማድና ወግ ልጃችሁን ለልጄ የሚል ቤተሰብ መጣ:: ቤተሰብም ወደውና ፈቅደው ያለቻቸውን ብቸኛ ሴት ልጅ ለመስጠት ተስማሙ:: ይሄን የሰማችው ዚነት “ምን ሲደረግ እማላቀውን ሰው አገባለሁ?” አለች:: ቤተሰቦቿም በሷ የሚጨክን አንጀት አልነበራቸውምና በጥሎሽ የመጣውን ስጦታ መልሰው የልጃቸውን ፈቃድ ፈጸሙ:: በሂደት የእናትና አባት ትዳር መፍረሱን ተከትሎ እሷም በዋናነት እናቷን ተከትላ መኖሪያዋ ደሴ ሆነ::
ድምጸ መረዋዋ የጠይም ቆንጆ ዚነት ደሴ፣ ፒያሳ ካሉ ጭፈራ ቤቶች በአንዱ መዝፈን ጀምራለች:: ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲል መጽሐፉ በወቅቱ “መስከረም ሁለት” የደርግ ወታደራዊ መንግሥት የንጉሥ ኃይለሥላሴን ንጉሣዊ አስተዳደር ጥሎ ሥልጣን የተረከበበት ዕለት በደማቅ ሁኔታ በአደባባይ ይከበር የነበረበት ጊዜ ነበር:: በ1972 ዓ∙ም የሚውለውን ክብረ በዓል ለማክበር የደሴ ከተማም ትልቅ ሽርጉድ ላይ ነበረች::
የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድንም በዓሉን ለማክበር መዝሙር እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል:: የከተማው ሽርጉድ የደራው በዓሉ ከመቃረቡ አስቀድሞ ነው:: ሆኖም አብዛኛው የኪነት አባላት በእድሜ የገፉ ስለሆነ ለበዓሉ ድምቀት መዝሙር የሚያቀርቡ ታዳጊዎች ቡድኑን ቢቀላቀሉ የተሻለ እንደሚሆን ታምኖበታል:: ለዚህም በደሴ ከተማ ለነበሩ 21 ቀበሌዎች ከየቀበሌው አምስት አምስት ልጆች ተመርጠው ለልምምድ ወደ “ባሕል አምባ” እንዲላኩልን የሚል ደብዳቤ እንዲደርስ ተደረገ::
የኪነት ቡድኑ አባላት ወጣቶቹን ለመምረጥ ምርጫው በቀበሌ ብቻ እንዲገደብ አልፈቀዱም:: ይልቅስ ድምፃዊ ይገኝበታል ብለው ባሰቡበት ቦታ ሁሉ እየገቡ ምልመላውን ያደርጉ ነበር::
የባሕል ቡድኑ አባላት ደሴ፣ ፒያሳን አልፎ ቀይ መብራት የሚባል ጭፈራ ቤት በመዝፈን ላይ ያለች የጠይም ቆንጆ ቀልባቸውን ወሰደችው:: የባሕል ቡድኑ አባላት “እችን ልጅማ መውሰድ አለብን” ብለው ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከሷ ቀድሞ የባሕል ቡድኑ አባል የነበረውና በኋላ ጓደኛዋ የሆነው ሙሐመድ ይመር (ከመከም) ከአማራ ቲቪ ጋር በነበረው ቆይታ ይናገራል:: በማታ በቤቱ የነበረውን ድባብ ለማናገር የሚመች አልነበረምና በማግስቱ ሄደው “የላሊበላ የባሕል ቡድን የሚባል ተመሥርቷልና አባል መሆን ትፈልጊያለሽ ወይ?” አሏት፤ “እሞክራለሁ” ብላ ቡድኑን ተቀላቀለች::
ከየቀበሌው ተመርጠው ከመጡት ልጆች ጋር የመዝሙር ልምምድ ጀመረች:: ቡድኑ የሴት ተወዛዋዥ እጥረት ነበረበትና ተወዛዋዥ ተደረገች:: ሆኖም ዝፈኚ ቢሏት የምታኮራ፤ ድራማ ሥሪ ቢሏት የማታሳፍር፣ ተወዛወዥ ቢሏት ወገቧን ለመፈተሽ የማትሰስት ነበረች:: ድምፅም ከላይ የታደለችው፣ እሷም ከልጅነቷ አንስቶ ስትገራው የኖረችው ነውና በሂደት ወደ ቡድኑ ድምፃዊነት ተሸጋገረች::
የመጀመሪያ አልበሟ የተሠራው ለመድረክ ተብሎ ነበር:: የግጥምና ዜማ ደራሲው ዳምጤ መኮንን (ባቢ) ከስር ከስር የሚደርሳቸውን ግጥምና ዜማዎች ያለማዳላት ለሁሉም ሴት የቡድኑ አባላት ያስጠናል:: ሆኖም ዚነት የተሰጣትን ግጥምም ሆነ ዜማ በአንዴ በመያዝ የሚደርስባት የቡድን አባል የለም:: በዚህ የተነሳም ከቡድን አባላቱ በተለየ በርካታ ግጥምና ዜማዎችን መጫወት ጀመረች:: ወሎ ባሕል አምባ አዳራሽ “ዝክረ ኪነጥበብ” የተሰኘ ሳምንታዊ ፕሮግራም ነበር:: በመድረኩ ላይ በመሐል እያረፈች ስምንት ዘፈኖችን ዘፈነች፤ በመድረኩ ከታደሙት አንዱ ለዜማና ግጥም ደራሲው ዳምጤ “ይሄ እኮ ካሴት ይሆናል። ለምን በካሴት አታወጡትም?” አለው::
እውነትም ስምንት የተሟላ ዘፈን ኖሯልና የተወሰኑ ዜማና ግጥሞችን አሟልተው ካሴት ለማውጣት እንቅስቃሴው ተጀመረ:: በመድረክ ላይ ያለምንም መደናቀፍ ትሠራቸው የነበሩ ሙዚቃዎችን በካሴት ለማውጣት ምንም አልከበዳትም:: “ከምበል ደፋ”፣ “ምን ይሻላል”፣ “ሠላታ”፣ “ሽሽጌ”፣ “የኔ ዓለም”፣ “ለማን ላዋየው”፣ “ምስጢር”፣ “ያገሬ ልጅ”፣ “የንጋት ኮከብ” የተሰኙ አስር ሙዚቃዎችን የያዘው የዚኒት ሙሀባ አልበም ተጠናቀቀ:: ሆኖም የአልበሙ ሙሉ ዝግጅት ቢጠናቀቅም ለሁለት ዓመታት ያህል አልበሙ ገዢ አላገኘም::
ዚኒት ምንም እንኳን ቆንጆ ድምፅ ቢኖራትም በወሎ አካባቢ እንጂ በሀገሪቱ በሙሉ የተዳረሰ ሥም አልተከለችም:: በዚህ የተነሳ ሙዚቃ ቤቶች በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አንድ ሥም የሌላትን ድምፃዊ አልበም ደፍሮ ለመግዛት ወኔ አጠራቸው:: እንደአማራጭም በሌላ ዘፋኝ ቢዘፈን የሚል ሀሳብ ያመጡ ሙዚቃ ቤቶችም ነበሩ::
የማራቶን ሙዚቃ ቤት ባለቤት “ከምበል ደፋ” የሚለውን ሙዚቃ እንደሰማ “እሠራዋለሁ” ሲል ወሰነ:: የዛኑ ቀን ከሰዓት “ኑና ውል እንዋዋል” አለ:: የግጥምና ዜማ ደራሲውና ዚነት ተነጋግረው የራሳቸውን ውል አርቅቀው ወደ ሙዚቃ ቤቱ አመሩ:: ውላቸውም “ለግጥም 1ሺህ 500 ብር፤ ለዜማ 1ሺህ 500 ብር፤ ለድምጽ 1ሺህ 500 ብር፤ አጠቃላይ 4ሺህ 500 ይገባናል” ይላል::
ሆኖም “በዝቶበት እምቢ ይል ይሆን?” ብለው ሰግተዋል:: “በዛ ይላል” ብለው የሰጉት የሙዚቃ ቤት ባለቤት 1ሺህ 500 ብሩን በ3ሺህ ቀይሮ፤ አጠቃላይ 9ሺህ ብር አሰበላቸው:: ለመቅዳትም ምንም ስቱዲዮ ሳያስፈልጋቸው ወሎ ባሕል አምባ አዳራሽ ውስጥ የባሕል ቡድኑ በቀጥታ የባሕል መሣሪያውን እየተጫወተ፤ ዚነትም ቀጥታ እያዜመች ካሴቱ ተቀዳ:: ያም አልበም በመላ ሀገሪቱ ገበያውን ተቆጣጠረው::
ሙሉ አልበሙ ከከተማ እስከ ገጠር ተወዳጅ ቢሆንም “ከምበል ደፋ” የተሰኘው ሥራዋ ግን የዚነት ልዩ ምልክቷ፤ በአብዛኛው የሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ ተወዳጅ ሥራዋ ነው::
እንዲያው ከምበል እንዲያው ዘመም
እንዲያው ከምበል ደፋ ይላል ጎፈሬው
ወጥቶ እስከሚመለስ ልቤም አያምነው
መንገደኛው ልቤ መንገደኛ ወዶ – አይ ወዶ
ከማያውቀው ሀገር ተሻገረ ማዶ – አይ ማዶ
ቀንም ሥራ አልሠራ እረፍት የለኝ ማታ- አይ ማታ
በሆዴ ተቋጥሮ የሩቅ ሰው ትዝታ – ትዝታ
የሚያውቋት ከመልክ ይልቅ ደምግቧቷ ይበልጣል ይሏታል:: ያያትን የሚስብ የደስ ደስ ነበራት:: “ተይ፣ አሁን ታዋቂ ዘፋኝ ሆነሻል፤ ኮራ በይ” ብትባል እሷ “ምን ሲደረግ ይህን ፈራሽ ሥጋ ይዘን” ትላለች:: ያላትን ለነገ የማትል የሰው ደስታ የሚያስደስታት ነበረች ይሏታል:: የዚነት ካሴት መውጣት እሷን በመላው ሀገሪቱ ከማስተዋወቁም ባሻገር የላሊበላ የባሕል ኪነት ቡድንም በሀገሪቷ እንዲታወቅ፤ ብሎም በርካታ መድረኮችን እንዲያገኝ በር ከፍቷል::
የቡድኑ አባላት የነበሩት ካሴቱ ከወጣ በኋላና ሳይወጣ በፊት የነበረው የቡድኑ አቀባበል አይገናኝም ይላሉ:: ለዚህም ቡድኑ በየደረሰበት ተቀባይ ኮሚቴ ተዋቅሮ የደመቀ አቀባበል ይደረግላቸው እንደ ነበር ይገልፃሉ:: በመልክ ዚነትን ባያውቋትም በየሄዱበት ከተማ ቡድኑ ማረፉን ተከትሎ እሷን ለማየት የጓጓ ሕዝብ መኪናውን ይወረዋል::
በሙዚቃው ሕዝብን ከማስደሰትና ነብሷን ከማሳረፍ በዘለለ “ይህ ነው” የሚባል ገቢ አላገኘችም:: የዚነት አልበም ከተወዳጅነቱ የተነሳ ሕዝቡ ከገበያ ዋጋ በላይ እየከፈለና እየተሰለፈ ካሴቷ እንደ አስቤዛ ሁሉም ቤት ቢገባም፣ እሷ ጋ ግን ይህ ነው የሚባል ገቢ አልደረሰም:: ብዙ ባታገኝም ያገኘችውን አብቃቅታ ከመዘነጥ ወደ ኋላ አላለችም:: የሚያውቋት ሁሉ ዘናጭነቷን ይመሰክራሉ:: ከሁሉ የምትግባባና በሥራዋ ቀልድ የማታውቅ፤ ሕዝብን የምታከብር ነበረች:: እናቷ አርፈው አስቀድሞ በባሕል አምባ አዳራሽ የተያዘ ፕሮግራም ላይ ተገኝታ ታዳሚን አስደስታ እናቷን የቀበረች መድረክ አክባሪ ናት:: ሀብታም፣ ደሃ ሳትል ለሁሉም ቅርብ ሆና ኑራለች:: ሕዝብም በዛው ልክ ፍቅር ሰጥቶ ክሷታል::
የመጀመሪያ አልበሟ እንደወጣ አልበሙን ያሳተመላት መኖሪያዋን አዲስ አበባ ቀይራ ለራሷ የምሽት ቤት እንዲከፍትላት ቢያናግራትም ፈቃደኛ አልሆነችም:: ምርጫዋ እዛው ደሴ፣ ከወሎ ላሊበላ የባሕል ኪነት ጋር አብሮ ማደግ ነበር:: ቆየት ብላም እዛው ደሴ፣ ባሕል አምባ አዳራሽ አጠገብ የምሽት ክበብ ከፍታም ነበር:: ቤቱ ታዲያ የሰው መሰብሰቢያ፣ ብሎም የጸብ መነሻም ሆኖ ነበር:: ብዙም ሳትሠራ የምሽት ክበቡን አቁማ የባህል ቡድኑ ሥራ ላይ አተኮረች::
የደርግ መንግሥት ወርዶ ኢሕአዴግ ሥልጣን መያዙን ተከትሎ የኪነት ቡድኑ አባላት በባሕል አምባ አዳራሽ ልምምድ ላይ ባሉበት ማስታወቂያ ተለጠፈ:: ያም ማስታወቂያ ቡድኑ መፍረሱንና አባላቱ ወደየመጡበት አካባቢ መሄድ እንደሚችሉ የሚያረዳ ማስታወቂያ ነበር::
ለቡድኑ በስጦታ የተበረከተው አውቶብስ ተወስዶ አዳራሹንም እንዳይጠቀሙ ተከልክሎ ነበርና ከቡድኑ የተመረጡ አባላት አዲስ አበባ ባሕልና ሚኒስቴር ለአቤቱታ አቀኑ:: ከነዚህ የቡድኑ ተወካዮች መካከል ዚነትም ነበረች:: ያኔ ታዲያ አበልም ሆነ ደሞዝ የላቸውም:: ለአብዛኛው ሥራዎቿ ግጥምና ዜማ የሚደርሱላት ካሳዬ ዳምጤ ምንም ገቢ የላቸውምና በእንግድነት በሄዱበት አዲስ አበባ፣ ግራር ሆቴልን ኮንትራት ይዘው የሙዚቃ ሥራ ጀመሩ፤ ዚነትም እዛው መሥራት ጀመረች::
ግን በመሐል ታመመች፤ ገና በወጣትነቷና ብዙ ትሠራለች ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ለበሽታዋ እጅ ሰጠች:: እንግድነት የመጣችበት አዲስ አበባ ላትመለስ እችን ምድር ተሰናበተች:: ሆኖም በመላው ኢትዮጵያ ብትወደድም ከወሎ ሕዝብ ጋር ያላት ትስስር የተለየ ነውና የዘላለም ማረፊያ ወደ ሆነው ደሴ አስክሬኗ በክብር ተሸኝቶ የወሎ ሕዝብ የሷ ሞት ያልተጠበቀ ዱብ እዳ ቢሆንበትም በክብር አሳርፏታል::
የዚነት ድምጽ የተለየ፣ የራሱ ውበት አለው። ያልወፈረ፤ ያልፈጠነ፤ ደግሞም ያልዘገየ፤ የተለየ፣ የሷ የራሷ ድምፅ ነበር:: በቃ፣ የሚያምር የወሎ ድምፅ መለያዋ ነው:: ለዛም ይመስላል የሷ ዘፈን በገጠሩም በከተማውም ተወዳጅ የሆነው:: ለእናቷ የወደ ፊት የሴት ልጃቸውን ዕጣ ፈንታ የተነበዩት አዋቂ ትንቢት ሰምሮ ልጅት እንደተባለው በ70ዎቹ መጨረሻና በ80ዎቹ መጀመሪያ በሀገራችን ሙዚቃ ስማቸው ከሚጠሩ እንስቶች ቅድሚያ ለመሆን በቃች:: ቡድኑን በተወዛዋዥነት ብትቀላቀልም ከቡድኑ በላይ ስለገነነች የቡድኑ መታወቂያ ሁሉ ዚነት ሙሃባን ያፈራው የወሎ ላሊበላ ኪነት እስከመባል ደርሷል::
በፍቅር ተዳክማ መፍትሔው ቢቸግራት “ምን ይሻላል” ስትል ያዜመችው፤ በልጁ ትዝታ ያጋጠማትን እክል የምትዘረዝርበትና ምክር የምትሻበት ዜማ በበርካቶች አሁን ድረስ ተወዳጅ ሥራዋ ነው::
ምን ይሻላል ምን ይሻላል
ኧረ ምን ይሻላል
በዛ ልጅ ትዝታ ሰውነቴ ዝሏል
አዕምሮዬም ደክሟል
እስቲ መላ ስጡኝ
ሰዎች ምን ይሻላል?
ዚነት በአጭር የምድር ላይ ቆይታዋ አራት ካሴቶችን ሠርታለች:: የመጀመሪያው የብቻዋ፤ ሁለተኛ ካሴቷን ደግሞ ከያሲን መሐመድ ጋር በጥምረት ሠርታለች:: ሦስተኛ አልበሟን ልክ እንደመጀሪያው አልበሟ ግጥምና ዜማ ከሚደርስላት ዳምጤ መኮንን ጋር በመቀናጀት ሠርታለች::
ጥምረታቸው ያስቀና የነበረው ዳምጤ እንደሚያስረዳው አራተኛ አልበም ለመሥራት ልምምድ ላይ እያሉ ሞት ቢጨክንባትም፣ ልምምድ ላይ የተቀዳቻቸውን ሙዚቃዎች ሰብስቦ ለቤተሰቧ መደጉሚያ ይሆን ዘንድ መስጠቱን፤ ሆኖም ያለቀለት ቅጂ ስላልሆነ እንደቀድሞዎቹ የተሳካ አለመሆኑን ይናገራል:: ዚነት አሁንም በርካቶች በቁጭት የሚያስታውሷት የብዙዎች ትዝታ እንደሆነች አለች::
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም