እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ብቻ መብራት በምታገኘው ትንሽዬ መንደር ውስጥ ትልቅ ሕልም ያላት ሕፃን በወርሐ ግንቦት በ1974 ዓ.ም ተወለደች። ግንቦት ከባተ በአምስተኛው ቀን ምድርን የተቀላቀለችው ልጅ ለቤተሰቧ ሦስተኛ ልጅ ነበረች። የመጀመሪያዎቹን ሁለት ወንዶች በተከታይ የወለደችው የሕፃኗ እናት ሴት ልጇን በሦስተኝነት ስትታቀፍ እንደተመኘሁሽ አገኘሁሽ በማለት ስመኝ ብላ ስም አወጣችላት። ተናፍቃ የተወለደችው ሕፃንም በልጅነቷ የቤተሰቧ ድምቀት ነበረች።
አባቷ አቶ አሰፋ አማረ በሀገሩ የተከበሩ የሀገር ሽማግሌ ነበሩ። እናቷ ወይዘሮ ፅጌ ይትባረክ ደግሞ በደግነት የታወቁ የሁሉ ሰብሳቢ የሁሉ ጥላ የሆኑ እናት ናቸው። አባት በመንግሥት መሥሪያ ቤት በአስተዳደር ሥራ ላይ የተሰማሩም ቢሆኑም ቅዳሜና እሁድን በሬ ጠምደው ሲያርሱ የሚውሉ ጠንካራ የሥራ ምልክት ነበሩ። እናትም በአካውንቲንግ የተመረቁ የሂሳብ ሠራተኛ ቢሆኑም እንደ አካባቢው ማኅበረሰብ ግብርናውንም እናትነቱንም የሴት ሙያውንም በአንድ አዋሕደው የሚያስኬዱ የቤታቸው እመቤት ነበሩ።
ምሽቱን የቤት ውስጥ ሥራ ከልጆቻቸው ጋር በጋራ ሲሠሩ ያመሹና ሥራው ሲያበቃ ልጆቻቸውን በመናገር ሳይሆን በማሳየት የሚያስተምሩት ወይዘሮ ፅጌ ልጆቻቸው እንዲያነቡ ሲሉ ምሽቱን ሙሉ መጽሐፍትን ይዘው ያነቡ እንደነበር ታስታውሳለች።
ሀገሩ ሙቀት በመሆኑ እግራቸውን በውሃ ዘፍዝፈው ከኩራዝ ይልቅ ፋኖስን ጭሱን በመቀነስ በንባብ ተጠምደው ያድሩ ነበር። ̋አፍንጫችን በኩራዝ ጭስ ተሞልቶ ስናነጋ ዛሬ ላይ የምንደርስበትም በማለም ነበር ̋ የምትለው ሴት ከዛች ትንሽ መንደር ወጥታ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ጨለማ ሳይበግራት፤ ዳገት ቁልቁለቱ ሳይገድባት ትላንትን አልፋ ዛሬ ለብዙዎች ፈውስ መሆን ችላለች።
ከትንሿ የገጠር ከተማ ወጥታ ዛሬ ላይ በአለርት ኮምፕረንሲቭ እስፔሻላይዝድ ሆሰፒታል የጥርስ ሕክምና ክፍል አስተባባሪ የሆነችው ዶክተር ስመኝ አሰፋ የዛሬ የሕይወት ዓምድ እንግዳችን አድርገናታል፤ መልካም ቆይታ ።
ከውልደት እስከ ትምህርት ቤት
ስመኝ አሰፋ አማረ ተወልዳ ያደገችው በድሮ ጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር በከነባ ወረዳ ነው። የአስተዳደር ባለሙያ የነበሩት አባቷ አቶ አሰፋ አማረ በሥራ ምክንያት ወደ ቦታው በመሄዳቸው እዛ የተወለደችው ስመኝ የሁለት ዓመት ሕፃን እያለች ነበር በሥራ ምክንያት ቤተሰቦቿ ወደ ጎፋ ሳውላ የተመለሱት።
እድሜዋ ለትምህርት እንደ ደረሰ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ከአንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ኩስቲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳውላ ከተማ ውስጥ፤ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃን እዛው ሳውላ ቦተሬ የሚባል ትምህርት ቤት፤ ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ ሳውላ ከተማ ነበር የተማረችው።
በጣም ጎበዝና ጠንካራ የሆኑት የስመኝ አባት ከሰኞ እስከ ዓርብ በመንግሥት ሥራ ከፍተኛ የአስተዳደር እርከን ላይ እየሠሩ ቅዳሜና እሁድን ደግሞ በግብርና ሥራ በሬ ጠምደው ሲያርሱ ይውሉ እንደነበረ ታስታውሳለች። እናት ወይዘሮ ፅጌ ይትባረክ የተማሩ የአካውንቲንግ ባለሙያ ሲሆኑ ልጆቻቸውን በጥበብ ነበር ያሳደጉት።
ወላጆቿ ካፈሯቸው ዘጠኝ ልጆች መካከል ሦስተኛ የሆነችው ስመኝ እንደምታስታውሰው ቤት ውስጥ የተወለዱት ልጆች ዘጠኝ ቢሆኑም ሌሎች ወላጅ የሌላቸው ወይንም የተቸገሩ ልጆች ተጨምረው ሀያ አራት እህትና ወንድሞች በመሆን በጋራ ነበር ያደጉት። ̋ቤተሰቦቼ ሰው የሚወዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፤ ልጆቻቸው ሥራ ወዳድና ሰው አክባሪ እንዲሆኑ አድርገው ነበር ያሳደጉን ̋ ትላለች።
ከሁለት ወንድ ልጆች በኋላ የተገኘችው ሴት ልጅ በመሆኗ ስመኝሽ የተባለችው ልጅ ለወላጆቿ ጠቃሚ ከመሆን አልፋ እንደ ምኞታቸው በአደባባይ ወላጆቿን የምታስጠራ ልጅ ሆናለች።
አባቷ ለአረም ሲሄዱ ተከተላ የምትሄደው ስመኝ ቀን ቀን ደብተሯን ይዛ የሸመደደችውን ለማስታወስ የእንሰት ተክል ላይ እየፃፈች ወረቀት የለኝም ሳትል እና ድህነት ሳይበግራት ተምራ ስኬት ላይ መድረስ ችላለ ች።
ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከ10ኛ ክፍል እንዲያጠናቅቁ በተወሰነበት ወቅት ላይ የመጨረሻው አስራ ሁለተኛ ክፍል የነበረችው ወጣት በ1993 ዓ.ም ማትሪክ ወስዳ በነርሲንግ የትምህርት ዘርፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለች:: በትምህርቷም ብርቱ ስለነበረች በነርሲንግ ሙያ ለመመረቅ በቃች።
የስራ ሀሁ በአለርት ሆስፒታል
የነርስነት ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በወቅቱ ሥራ የሚመደበው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ስለነበር የመጀመሪያ የሥራ ዕጣ ስታወጣ በአለርት ሆስፒታል ነበር የደረሳት። በ1995 ዓ.ም የሥራ ዓለምን ሀ ብላ ስትጀምር አለርት ሆስፒታል ነበር የገባችው።
በወቅቱ ስለ ሥጋ ደዌ ሕመም ምንነት ምንም የሚገባት ነገር እንዳልነበረ የምትናገረው ወጣቷ ነርስ ወዲያው ግን በሽታው ማይኮባክታሪየም ሌፕሬ ተብሎ በሚጠራው ረቂቅ ሕዋስ አማካኝነት የሚመጣ መሆኑን ተረዳች:: ይህ የሕመም አይነት ብዙ ቦታዎች ላይ ተከስቶ ሊታይ ይችላል:: በተለይ ደግሞ በቆዳና በነርቮች ላይ የመከሰት እድሉ ሰፊ ነው:: የሕመሙ መከሰት የሚታየው በቅድሚያ ከመጠን በላይ የሆነ የሕመም ስሜት በመፍጠር፣ በማደንዘዝ፣ በማሽመድመድ፣ ቁስለት በመፍጠርና ሌሎች ችግሮችን በማስከተል መሆኑን መማራቸውን ታስታውሳለች።
ወደ ሥራው እንደገቡ ለአስራ አምስት ቀናት በተሰጠ ሥልጠና ስለ የሥጋ ደዌ ሕመም ዓይነቶች ሁለት አይነት መሆናቸውን በቂ ግንዛቤ ጨበጠች:: አንደኛው የሥጋ ደዌ ዓይነት አስመሳይ (tuberculoid) የሚባለው ሲሆን በዚህ ወቅት ቆዳ ፈዛዛ ቀይ ወይንም ሐምራዊ መልክ ይይዛል:: ይህ በጣም ገራገር የሚባለው የሥጋ ደዌ ሕመም ደረጃ ቢሆንም የሰውነት ጫፍ አካባቢ መደንዘዝ እና መላጥ ምልክቶች ይታያሉ::
ሌላው ሌፕሮማተስ (lepromatous) ነው:: በዚህ ወቅት በቆዳ ላይ የሚታዩ ቁስለቶች ቢጫ ወይንም ቡናማ መልክ አላቸው:: በተጨማሪም አፍንጫና፣ ጉሮሮ ላይ ችግር መፍጠር ይጀምራል:: በተለይ ፊትና ጆሮ አካባቢ ያለው ቆዳ ይወፍራል:: ከአስመሳዩ የሥጋ ደዌ ዓይነት በበለጠ ሁኔታ በቀላሉ የመዛመት እድል እንዳለው ግንዛቤ መጨበጧን ታስታውሳለች።
የሥጋ ደዌ ሕመም መነሻ ምክንያቶች በሕመም አምጪ ረቂቅ ህዋስ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ነው:: የሕመሙ ምልክቶች ለችግሩ ከተጋለጡ ከሦስት እና ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ሊታይ የሚችል ነው።
ሕሙማኑ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ በቅድሚያ መታየት ያለበት የዓይን ችግር፤ የቅንድብና የሽፋሽፍት መርገፍ፤ በፊት እና ጆሮ አካባቢ ሕመም የሌላቸው እብጠቶች መውጣት፤ የቆዳ ቀለም ለውጥ እና ሽፍታ፤ የቆዳ ወፍራምና ደረቅ መሆን ፤ የእግር መርገጫዎች ላይ ሕመም አልባ ቁስለት፤ በተለይ የእግርና የእጅ ጣቶች መደንዘዝ ወይንም ምንም መልስ አለመስጠት ብሎም የጣቶች ቅርፅ መለዋወጥ እና የመሳሰሉት ናቸው።
ሕሙማኑ የተገለልን ነን የሚል አስተሳስብ ስለነበራቸው እነሱን አረጋግቶ መያዝ አስፈላጊ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ የሥጋ ደዌ ሕመም በመድኃኒት አማካኝነት ሊድን የሚችል እንደመሆኑ የሕመሙ መከሰት መታየት በጀመረባቸው ጥቂት ጊዜያት ውስጥ የሕክምና ርዳታ ማግኘት እንደሚመከርና የሥጋ ደዌ በሽታ ሙሉ በሙሉ በሕክምና ይድናል:: የሥጋ ደዌ ሕመምተኛ ሕክምና ከጀመረ ወይም ታክሞ ከዳነ በሽታውን በፍፁም ሊያስተላልፍ አይችልም:: የሥጋ ደዌ በሽታ በንክኪ እጅግ በጣም ተላላፊ ስለሆነ አንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የማጥቃት እድሉ ከፍተኛ ነው::
በዚህም ምክንያት በሀገራችን አንዳንድ ቦታዎች ተላላፊ እንደሆነ ይታሰባል፤ ብሎም በበሽታው የተጠቃን ሰው እና ቤተሰብ የማግለል ሁኔታ ይስተዋላል:: ነገር ግን የሥጋ ደዌ በሽታ በዘር፣ በእርግማን ወይም በእርኩስ መንፈስ የሚመጣ በሽታ አይደለም:: እነዚህና መሰል የሕመሙ ባሕርያትን በአግባቡ የተረዳችው ወጣቷ ነርስ ሰዎችን የመርዳት ባሕሪዋ ተጨምሮበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ለመሆን በቃች::
ከሥልጠና በኋላ በአለርት ሆስፒታል ለመጀመሪያ ጊዜ የተመደበችበት ቦታ ሜዲካል ዋርድ የተባለ ቦታ ሲሆን ያላት ተፈጥሯዊ ባሕሪዋ ከሥልጠና ጋር ተዳምሮ ሕሙማኑን በአግባቡ መርዳት ቻለች:: በዚህም በአካባቢው ታዋቂ ሐኪም ሆነች።
ከሜዲካል ዋርድ በኋላ ነርሶች ቦታ መቀያየራቸው የተለመደ አሠራር ስለነበር ተመላላሽ ታካሚዎች የሚታከሙበት ቦታ ተመደበች። እዚህ ቦታ በሳምንት ሁለት ቀን ደም ግፊትና ስኳራቸውን ሊለኩ በሥጋ ደዌ የተጠቁ አረጋውያን ይመጡ ነበር።
̋እነሱን በማገልገል የሚገኘው ምርቃት የትም የማይገኝ ፀጋዬ ነው ̋ የምትለው ሰመኝ ̋አንዲት እናት በዚህች ቦታ ዶክተር ሆነሽ ልይሽ ብለው የመረቁኝን መቼም አልረሳውም ̋ ትላለች።
ከዛ በኋላ በኤች አይ ቪ ካውንስሊንግ ሥራ ሊሠሩ ለሚችሉ የሕክምና ባለሙያዎች በፊዴራል ደረጃ ለአስር ቀን ሥልጠና ሲፈቀድ በመሠልጠን የኤች አይ ቪ ካውንስለር በመሆን በአለርት ሆስፒታል ቢሮ ተሰጥቷት ማገልገል ጀመረች። በወቅቱ ይህ የሥራ ቦታ ብዙም ጫና የሌለበት በመሆኑ አሁን የትምህርት ሁኔታውን ለማሻሻል መዘጋጀት ጀመረች።
የጥርስ ሕክምና ትምህርት
ቀድሞውን የጥርስ ሐኪም የመሆን ሕልም የነበራት ወጣቷ ነርስ፤ ቤት ተከራይታ እየኖረች የጥርስ ሐኪም የመሆን ሕልሟን በምን መልኩ ልታሳካው እንደምትችል ሌት ከቀን ማሰብ ጀመረች።
የጥርስ ሕክምና መማር ፍላጎት እንዳደረባት በጥርስ ሕክምና ዶክተርነት የሚያሠለጥን የመጀመሪያው የግል ትምህርት ቤት ሀገራችን ላይ ተከፈተ። በወቅቱ የነርስ ደመወዝ በጣም ትንሽ ነው። በዛ ላይ የገጠር ልጅ ናት ይባስ ብሎም ቤት ተከራይታ ነበር የምኖረው። ከመሠረታዊ ፍላጎቷ ተርፎ ለመማር የሚያስችል ምንም አቅም አልነበራትም።
በወቅቱ የተከፈተው አትላስ የጥርስ ሕክምና ኮሌጅ ነበር። ሄዳ ክፍያውን ስትጠይቅ አይደለም ከመሠረታዊ ፍላጎቷ ተርፎ ልትከፍል ይቅርና ሙሉ ደመወዝዋን ብትመደብ እንኳን በቂ አለመሆኑን ስታውቅ በጣም ነበር ያዘነችው።
̋ምንም ይሁን ምን መማሬ ግን አይቀርም ̋ ብላ ቆርጣ የተነሳችው ወጣት የመጣው ይምጣ ብላ ተመዘገበች። በአጋጣሚ በሬዲዮ ዶክተር እሌኒ የተባለች ሴት በውጭ ሀገራት በብድር ተምሮ ሥራ ላይ ሲኮን የሚከፈልበት አማራጭ መኖሩን ስትናገር ትሰማታለች። በዚህ ሀሳብ የተደመመችውና የመማር ፍላጎቷን ማስቆም ያቃታት ወጣት ነርስ ሄዳ የኮሌጁን ኃላፊ አናገረች።
የኮሌጁ ኃላፊዎችም በዱቤ የመማሩን ጉዳይ በደብዳቤ እንድትጠይቅ አድርገው ግማሽ እየከፈለች እንድትማር ተፈቀደላት። ከኑሮዋ የሚተርፈው ግማሽ ክፍያውን እንደማይሸፍንላት ብታውቅም በድፍረት ተመዝግባ ታላላቅ ወንድሞቿ እንዲረዷት ትጠይቃለች።
ወንድሟ ሌላ ዓይነት ትምህርት እንድትማር በመፈለጉ የተነሳ ሊረዳት እንደማይፈልግ ስታውቅ ̋ፈጣሪ ያስተምረኛል ̋ በማለት ስልኩን ትዘጋዋለች። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነው ወንድሟ ይህን በተነጋገሩ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እስኮላር ሺፕ አግኝቶ ኖርዌይ ሀገር ሄደ።
ከዛም ፈጣሪ ያስተምረኛል ያለችውን በማስታወስ ደውሎ ̋ፈጣሪ በኔ በኩል ሊያስተምርሽ ነው ̋ በማለት እሱ እየተማረ በትርፍ ጊዜው በሚሠራው ገንዘብ እየላከ ዱቤውም ቀርቶ መማር ጀመረች። በወቅቱ የጥርስ ሕክምና ትምህርት ባለመለመዱ ሌላኛው ታላቅ ወንድሟ ሌላ ትምህርት እንድትማር ሊያግባባት ቢሞክርም ነፍሷ ያለ ጥርስ ሕክምና አሻፈረኝ በማለቷ ትምህርቷን እስከመጨረሻ ልትማር ወሰነች።
ከዛ ቀን እየሠራች ማታ እየተማረች ሦስተኛ ዓመት ላይ ደረሰች። በኋላ በማታ የትምህርት መርሐ ግብር በዲግሪ ፕሮግራም ማስተማር እንደማይቻል ክልከላ ወጣ። ያን ጊዜ የአለርት ኃላፊዎች በቀን እንድትማር ሥራዋም እንዳይቋረጥ ስትል ከልጅነት እስከ እውቀት ያሳለፈችውን የሕይወት ውጣ ውረድ ተናግራ በቀን እንድትማር አደረጓት። በቀን መርሐ ግብር ሥራዋንም ሳታቋርጥ የተማረችው ይህች ወጣት በ2005 ዓ.ም የጥርስ ሕክምና ዶክተር በመሆን ትምህርቷን አጠናቀቀች።
ሙያና ኃላፊነት
በቀን መርሐ ግብር ሥራዋንም ሳታቋርጥ የተማረችው ይህች ወጣት በ2005 ዓ.ም ትምህርቷን እንደጨረሰች ነበር አለርት ሆስፒታል የጥርስ ሕክምና ክፍልን በኃላፊነት እንድታስተዳደርና እንድታደራጅ አደራ የተሰጣት። በወቅቱ ለይስሙላ ያህል የጥርስ ሕክምና ክፍል የሚባል ቢኖርም በምንም መስፈርት የጥርስ ሕክምና ክፍልን የሚያሟላ አልነበረም:: የጥርስ ሕክምና ክፍል ተብሎ በጣም ጠባብ የሆነ ሁለት ያረጁ ወንበሮች ያሉበት ክፍል መረከቧን ታስታውሳለች።
በክፍሉ የሥጋ ደዌ ሕሙማንን ጥርስ መንቀልና ማከም ዓይነት ሥራ ብቻ ነበር የሚሠራው። በቀን አነሰ ቢባል አንድ በዛ ቢባል ስድስት ታካሚዎችን ብቻ በማገዝ ሙሉ ቀን ያለ ሥራ መዋል የተለመደ ነበር። ይህንን ያለ ሥራ መቀመጥ መታገስ የተሳናት ዶክተር ስመኝ የጥርስ ሕክምና አስፈላጊነትን በአግባቡ ስለተገነዘበች ይህ ዲፓርትመንት ሰፍቶ እና አድጎ በሆስፒታሉ ተጠቃሽ የሆነ ማዕከል እንዲሆን ምን ማድረግ እንደሚገባት ማሰብ ጀመረች።
ሀሳብዋን ወደ ተግባር ለመቀየር እያሰላሰለች ባለችበት ወቅት አለርት ሆስፒታል ዘጠና ዓመቱን ሲያከብር ያሳተመው መጽሔት በአጋጣሚ እጇ ይገባል። በወቅቱ መጽሔቱ ላይ የእያንዳንዱ ዲፓርትመንት ዝርዝርና ፎቶግራፍ የተቀመጠ ቢሆንም የጥርስ ሕክምና ማዕከሉ ግን ያስታወሰው አለመኖሩ ከባድ ቁጭት ወስጥ ይከታታል። ስለዚህ በሆስፒታሉ ውስጥ እንዳሉት እንደ ዓይን ሕክምናና እንደ ቆዳ ሕክምና የሚጠቀስ የሕክምና ማዕከል በማቋቋም በአለርት ሆስፒታል ውስጥ ታዋቂ ማዕከል ለማቋቋም ቆርጣ ተነሳች።
በጤና ጥበቃ በኩል ሐኪሞች የሚሰበሰቡበት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የጥርስ ሕክምና ማዕከሉን የማደራጀት ሀሳብ ብታነሳም ምላሽ ሳታገኝ ትቀራለች። በዚህ ተስፋ ያልቆረጠችው ይህቺው ጀግና ሴት የጥርስ ሕክምና ክፍሉ የተሰጠውን ጠባብ ክፍል የማሻሻልና የማዘመን እንቅስቃሴ ውስጥ ገባች::
̋መጀመሪያ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሕሙማን በሆስፒታሉ የጥርስ ሕክምና ማዕከል መኖሩን ይታወቅልኝ ስል ብጠይቅም መሣሪያ ሳይኖራት በምኗ ትሠራለች በማለት ያጣጥሉብኝ ነበር ̋የምትለው ዶክተር ስመኝ ምንም አይነት እንቅፋት ከመንገዷ የማያቆማት ብርቱ ሴት ናትና ጉዳይዋን ይዛ ወደ የበላይ አካል ሄደች:: እንደሄደችም ̋ተቸግሬ የተማርኩት ልሠራ ነው ታካሚ እፈልጋለሁ ̋ በማለት ሕሙማንን የማገዝ ፍላጎቷን ገልፃ ማመልከቻዋን አስገባች።
ከዛ በኋላ በዛች ጠባብ ክፍል ውስጥ ከአቅም በላይ የሆነ ሰው መምጣት ጀመረ። ያኔ የሰው ፍላጎት መብዛቱን የተመለከቱት የሆስፒታሉ ኃላፊዎች አዲስ በሚሠራው ሕንፃ ላይ ቦታ እንደሚሰጣት አበሰሯት:: እሷ ግን በዚህ አልረካችም:: በዚህም ላይ ገና ሕንጻው እስኪጠናቀቅ ቁጭ ብሎ መጠበቁ አልሆነላትም:: የአለርት ሆስፒታል ግቢ ከልጅነቷ ጀምሮ ያደገችበት ግቢ በመሆኑ ያሉትን ክፍት ቦታዎች ሁሉ ጠንቅቃ ታውቃቸዋለች:: ተዘግቶ የተቀመጠ በፊት የነርሶች ትምህርት ቤት የነበረ ቦታ መኖሩን ስለምታውቅ:: ይህንኑ ቦታ ጠየቀች:: በለስ ቀናትና በክፍሉ ውስጥ የነበረው እቃ ወጥቶ የጥርስ ሕክምና ማዕከሉ እንዲገባበት ተወሰነ።
ይህ ክፍል ሰፊ በመሆኑ ለጥርስ ሕክምና አገልግሎት ምቹ ነበር:: ሕልሟን ለማሳካት ደከመኝ፤ ሰለቸኝ የማታውቀው ዶክተር ስመኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኩል ከኖርዌይ ሀገር ለጥርስ ሕክምና የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ ወንበር እየመጣ መሆኑን ሰምታ ጤና ጥበቃ ሄደች። በወቅቱ ሚኒስቴሩ ጋ ገብታ ያላትን ፍላጎት ገለጸች:: ሚኒስትሩም ጥያቄዋን ተቀብለው ለጥርስ ሕክምና አጋዥ የሆኑ ዘመናዊ የሆነ መሣሪያ የተገጠመላቸው ወንበሮችን አስረከቧት::
ይህ ዘመናዊ ወንበር ወደ ክፍሉ በሚገባበት ወቅት ሌላ መጋዘን ውስጥ የተቆለፈበት ማሽን ስለመኖሩ ጠባቂዎች ሲያወሩ ትሰማለች። ያለ እውቀት የሚባክኑ ማሽኖች መኖራቸው እየገረማት ከተቆለፈበት አውጥታ አገልግሎት እንዲሰጥ ታደርገዋለች። በሕክምና ክፍሉ ውስጥ ስድስት ዘመናዊ የጥርስ ሕክምና ወንበሮች ኖሩ። በትጋትና በጥረት የሥራ ክፍሉ ተደራጀቶ በስፋት ሥራ ተጀመረ። የዶክተር ስመኝ የጥርስ ሕክምና ማዕከልም በአንድ ጊዜ ወደ ዘመናዊነት አደገ::
ዶክተር ስመኝ ስለሥራ ባልደረቦቿ ተናግራ አትጠግብም:: እያንዳንዱ የጥርስ ሕክምና ማዕከሉ የውጣ ወረድ መንገድ ላይ አብረው የተጓዙት ሐኪሞች ሁሉንም የለውጥ ሀሳብ ተቀብለው ያላቸውን አቅም ማውጣታቸው ለስኬቱ ዋና ጉልበት እንደሆነ ትናገራለች:: ከባልደረቦቿ ጋር ሆና ባላት አቅም ገቢ የሚያስገኙ የጥርስ ሕክምናዎችን በመሥራት፤ የጥርስ ማዕከሉ ተለማማጅ ተማሪዎች እንዲሠለጥኑበት በማድረግ ለሆስፒታሉ ገቢ በማስገባት ያለውን እምቅ አቅም ማሳየት ቻለች።
በዚህ ተግባሯ የሆስፒታሉ አመራሮችን ትኩረት መሳብ የቻለችው ዶክተር ስመኝ የምትናገረው ሁሉ መደመጥ ጀመረ። በጥርስ ማዕከሉ ያሉትን ማሽኖች የበለጠ ለማሻሻል አዲስ ሞዴል ማሽኖች ከስዊድን ሀገር በማስመጣት ክፍሉ የበለጠ ዘመነ:: ዛሬ ላይም የታወቀ የጥርስ ሕክምና ማዕከል ሊሆን በቃ።
በሕይወቷ በኑሮ መንገጫገጭና ውጣ ውረድ ሲበዛባት ከሆስፒታሉ ወጥቼ በግል ልሥራ የሚል ሃሳብ አንዳንድ ጊዜ ሽው ይልባት ነበር:: ̋ሆኖም ይህን እያገለገለችው ያለውን ማኅበረሰብ በትኖ መሄድ ቃል የገባችበትን የሙያ ግዴታ አለመወጣት መሆኑን በመረዳት ለቃሏ ታማኝ ሆና ለመኖር እንደቆረጠች ታስረዳለች::
የአለርት ሆስፒታል እድገት
በዶክተር ስመኝ ዓይን
አለርት ሆስፒታል ሥራ ከጀመረች ወደ ሃያ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ማሳለፏን የምትናገረው ዶክተር ስመኝ፤ በፊት የነበሩት አገልግሎቶች የሥጋ ደዌ፤ ቆዳና የዓይን ሕክምና ግልጋሎት በስፋት ከመሰጠቱ ውጪ እንደ አሁኑ የተስፋፋ አልነበረም።
አሁን ኮንፕረንሲቭ ሆስፒታል የተባለበት ምክንያት ሁሉንም አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል በመሆኑ ነው:: ዛሬ አለርት ከአጥንት ጋር ተያይዞ የሚሠራ የፕላስቲክ ሰርጀሪ የመሳሰሉት የሚሰጥበት ማዕከል ሆኗል። ከዚህም ባሻገር ከሥነ ልቦና ሕክምና አንስቶ፤ እስከ ውስጥ ደዌ፤ የጥርስና ሌሎች በአጠቃላይ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነ ሕክምና በሙሉ የሚሰጥበት ሞዴል የሕክምና ማዕከል መሆኑ ታላቅ እመርታ ነው ትለናለች።
የቤተሰብ ሁኔታ
የኮሌጅ ተማሪ እያለች ከተዋወቀችው የፍቅር ጓደኛዋ ጋር በትዳር የተሳሰረችው ዶክተር ስመኝ የሦስት ልጆች እናት ለመሆን ታድላለች። የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ እናት መሆኗን የምትናገረው ዶክተር ወላጆቿ ባሳደጓት መንገድ ልጆቿን ለማሳደግ የምትታትር ጠንካራ እናት መሆኗን ትናገራለች።
ስኬት በሁሉም ዘርፍ ሲሆን መልካም እንደሆነ የምታስበው ዶክተር ከሕክምናው ጎን ለጎን የቤተሰብ ግንባታ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ለልጆቿ አርዓያ የሆነች እናት ለመሆን እንደምትጥር ታስረዳለች።
በትዳር ሕይወት ውስጥ የጋራ የሚባለው ነገር የሚበዛ መሆኑን የምትናገረው ዶክተር ስመኝ፤ ባለቤቷም ሆነ እሷ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ስለሚወጡ ሰላማዊና ደስተኛ ቤተሰብ እንደሆኑ ገልፃለች።
የወደፊት ምኞት
በዘመናችን የጥርስ ሕክምና በጣም ተራቆ የሚያስደንቅ ደረጃ ደርሷል። ይህ የሕክምና ዘርፍ አድጎና ጎልብቶ ማየት ሕልሟ መሆኑን ትናገራለች። ሆስፒታሉም እነዚህን ዘመናዊ የጥርስ ሕክምና ቴክኖሎጂዎች ታጥቆ ማኅበረሰቡ የሚገባውን አገልግሎት ያገኝ ዘንድ ትመኛለች።
አስመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም