“ደላላ”ከመሠረታዊ የፍጆታ ግብይት ይውጣ

 ባለፉት 5 ወራት የግብይት ሰንሰለቱ ላይ እንቅፋት በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲባባስ ያደረጉ 790 ደላላዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን፤ በእህልና ጥራጥሬ፣ በአትክልትና ፍራፍሬና በቁም እንስሳት ግብይት ውስጥ የነበሩ ደላላዎችን ፈቃድ በመሰረዝ ከግብይት ሒደቱ እንዲወጡ መደረጉን፤ በቀጣይ የደላላን ጣልቃ ገብነት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን “አዲስ ዘመን” የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ጠቅሶ ሰሞኑን መዘገቡ ለዛሬ መጣጥፌ መነሻ ሆኖኛል።

ከተቀረው ዓለም የሀገራችንን የኑሮ ውድነት ለየት የሚያደርገው ማለትም ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ባሻገር እሴት የማይጨምሩ ደላሎች በገበያ ሰንሰለቱ ከማሳ እስከ ገበያ መሰግሰጋቸው፤ መንግሥትም ተገቢውን ቁጥጥርና የእርምት እርምጃ አለመውሰድ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል ይላል ጥናቱ:: በዚህም ምክንያት ምርት አምራቹ ከሚሸጥበት 58 በመቶ ዋጋው ከፍ ብሎ ሸማቹ ጋር እንዲደርስ አድርጓል:: ይህ ማለት ዛሬ በሀገራችን ከሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ያህሉ የተከሰተው በደላሎች አማካኝነት መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል። በሕግና በሥርዓት ሊስተካከል በሚችል የግብይት ሰንሰለት ሸማቹ ምን ያህል ፍዳውን እያየ መሆኑንም ቁልጭ አርጎ አሳይቶናል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከስንት ውትወታ በኋላ ሕገ ወጥ ደላላን ከግብይት ሰንሰለቱ የሚያስወጣ መመሪያ ያዘጋጀ ቢሆንም ገና ሥራ ላይ ባለመዋሉ የሀገሪቱ የግብይት ሰንሰለት የደላላ መፈንጫ እንደሆነ ቀጥሏል። በነገራችን ላይ የደላላ ተፅዕኖ ከገበያው አልፎ የኢኮኖሚውን፣ የፖለቲካውንና የማኅበራዊ ጉዳዩን መሠረት እየነቀነቀው ከመሆኑ ባሻገር ስውር “አራተኛው መንግሥት” እስከመሆን ደርሷል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በዚሁ ጋዜጣ ደላላን ከአራተኛ መንግሥት በትይዩ ያቀረብኩበትን መጣጥፍ ልመለስበት ወደድሁ። ለመሆኑ አራተኛ መንግሥት ማለት ምን ማለት ነው ?

“አራተኛው መንግሥት” (The Fourth Estate ) የሚለው ስያሜ፣ ሐረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው የዛሬ 232 ዓመታት በሀገረ እንግሊዝ ነው:: አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ደግሞ ከዚህ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቀድሞ እንደነበረም ያወሳሉ፤ በዛ ጊዜ ሦስቱ መንግሥታት በመባል ይታወቁ የነበሩት ፤ 1ኛ. ቤተ ክርስቲያኗ 2ኛ. መሳፍንቱ 3ኛ. ተራው ሕዝብ ሲሆን፤ 4ኛ. ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን ነበሩ:: አራተኛው መንግሥት የሚለውን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት የታላቋ ብሪታኒያ የፓርላማ አባል ኤድሞንድ ቡርክ ሲሆኑ፤ ዓመቱም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1787 እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ከትበው አቆይተውናል ::

ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት ንግሥቷ፣ የሕግ ባለሙያዎች lawyers እና ዝቅተኛው መደብ፣ ላብ አደሩ proletariat እንደ አራተኛ መንግሥት ይቆጠሩ ነበር:: ከጊዜ በኋላ ስያሜው ወደ ጋዜጠኞችና ሚዲያ ቋሚ መጠሪያነት ተሸጋግሯል :: በተመሳሳይ ሁኔታ በሂደት ሦስቱ መንግሥታት ቀደም ሲል ከነበራቸው ስያሜ ወደ ሕገ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈፃሚ መለወጣቸውን እነዚሁ ድርሳናት ያስረዳሉ:: እነዚህ የመንግሥት አካላት መንግሥታቸውን የመቆጣጠሪያ ሚዛንና የመመዘኛ መድለው check & balance በመሆን ያገለግላሉ ::

ሚዲያው አራተኛው መንግሥት መባሉ በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳይ ምን ያህል ከፍ ያለ ቦታ ፣ ሚና እንዳለው ያሳያል:: በምዕራባውያን በተለይ በእንግሊዝና በአሜሪካ ሚዲያው ከሦስቱ የመንግሥት አካላት ተርታ መሰለፍ ችሏል:: በአህጉራችን በደቡብ አፍሪካ፣ በጋና፣ በናይጄሪያ፣ …፤ በተወሰነ ደረጃ በኬኒያ፣ በኮትዲቯር እና በሌሎች ሀገራት ሚዲያው የአራተኛው የመንግሥት አካልነት ሚናቸውን፣ ኃላፊነታቸውን ከእነ ውስንነታቸው እየተወጡ ነው:: እንደ አለመታደል ሆኖ ሀገራችን የጎለበተ፣ ጥንታዊ የሀገረ መንግሥት ልምምድ ቢኖራትም ሚዲያችን ግን አራተኛው የመንግሥት አካል ለመባል ገና ብዙ ብዙ ይቀረዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ መድረክ በሀገራችን የገነገነውን ሙስና አራተኛው መንግሥት በማለት እንደገለፁት ሁሉ፤ እኔም በሀገራችን አሉታዊ ተፅዕኖው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣውን፤ በጊዜ ሀይ ካልተባለ ለሀገራችን ሕልውና አደጋ እየደቀነ ያለውን፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከጉልት እስከ ጅምላ ንግድ፤ በአጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ ሕይወታችንን እየናጠ ያለውን፤ አደገኛ እየሆነ የመጣውን፣ በሰዓት የተጠመደ ቦንብ time bomb ይገልጽልኛል ብዬ ስላመንሁ “ድለላ !?”ን ሳልወድ አምባሻ ሳልቆርስ “አራተኛው መንግሥት !?” ብዬዋለሁ ::

አዎ ! ከላይ ስለ ሐረጉ ስርወ ቃል etymology ሳትት ፅንሰ ሀሳቡ በቀደመው ዘመን ንግሥቷን፣ የሕግ ባለሙያን ፣ ሠራተኛውን ለመግለፅ ይውል እንደነበረው ሁሉ፤ እኔም ዛሬ ድለላ በሀገራችን ከደቀነው ወቅታዊና ከባድ ተፅዕኖ አኳያ አራተኛው የመንግሥት አካል ብለው ያንስበት ይሆን እንደሁ እንጂ አይበዛበትም:: እንዲያውም ከሕግ አውጭው፣ አስፈፃሚውና ተርጓሚው እንዲሁም ከሚዲያው በላይ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ ጓዳ ጎድጓዳችንን አንዳንድ ጊዜም አልጋ ተጋሪያችንን፣ አንሶላ ተጋፋፊያችንን እስከ መወሰን ከፍ ሲልም ውሃ አጣጫችንን እስከመምረጥ፣ …፤ ስለተሸጋገረ “ ድለላ !? “ 1ኛው የመንግሥት አካል ቢባል ያንሰው ይሆናል እንጂ አይበዛበትም ::

አዎ ! ደላላ ስንበላ የሚበላ፣ ስንጠጣ የሚጠጣ፣ ስንለብስ የሚለብስ፣ ስንገዛ የሚገዛ፣ ስንሸጥ የሚሸጥ፣ ስንከራይ የሚከራይ፣ …፤ ምን አለፋችሁ ስንሠራ ካለመሥራቱ፣ ስንራብ ካለመራቡ፣ ስንታረዝ ካለመታረዙ፣ በችጋር ስንገረፍ ካለመገረፉ፣ በኑሮ ውድነት ስንሰቃይ ካለመሰቃየቱ፣ በዋጋ ግሽበት ኪሳችን፣ ቦርሳችን ሲገለበጥ ካለመገልበጡ፣ …፤ በስተቀር የማይገባበት የሕይወታችን ቅንጣት፤ የማያንኳኳው በር የለም:: ታዲያ አይደለም 4ኛው፣ 1ኛው መንግሥት ቢሆን ይበዛበታል !?

በእያንዳንዳችን ሕይወት አዛዥ ናዛዥ የሆነው” ድለላ!? “ የቃሉ ትርጉም ምን ማለት ይሆን!? ምንም እንኳ በሥነ ልሳን lingustic አስተምህሮ በስያሜውና በተሰያሚው መካከል የባሕሪ ግንኙነት እንደሌለ ቢበየንም፤ የቃሉ ግብርና ምግባር ስለተማታብን፣ ስለተጣረሰብን ትርጉሙን እንመልከት ፦የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፤ በ1993 ዓም የአዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ “ደላላ”ን ፦ ‘ ገንዘብ እየተከፈለው ተፈላላጊዎችን (ሻጭና ገዥን፣ አከራይና ተከራይን፣ …፤ ) አገናኘ፣ አስማማ :: በማለት ይተረጉመዋል:: በመደለል ሥራ ላይ የተሠማራ ሰው፤ አታላይ፣ በውሸት አግባብቶ ለማሳመን የሚሞክር፤” ድላል “ን ደግሞ ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ በማለት ይተረጉማል:: የደስታ ተክለወልድ ዘሀገረ ወግዳ በ1970ዓ.ም የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ፤ ደለለ፦ አሞኘ፣ አታለለ፣ ሸነገለ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ አለ ፤

ደላላ፦ አመልካች፣ ጠቋሚ ድላል ፦ ለጠቋሚ ፣ ላስማሚ፣ የሚሰጥ ገንዘብ ሲል ይተረጉመዋል ::

ይሄኛው ትርጉም ከቀደመው ይልቅ የሀገራችንን ደላላ ቁልጭ አርጎ ይገልፀዋል:: የእንግሊዘኛውን ትርጉም ‘ broker ‘ ስረወ ቃል ስንመለከት “brocour” ከሚለው የፈረሳይኛ ቃል የመጣ ሲሆን ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቋንቋው አካል መሆኑን ሜሪያም ዌቢስተር የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ያወሳና ትርጉሙም ፦broker : a person who helps other people to reach agreements, to make deals, or to buy and sell property (such as stocks or houses) ነው ይለናል ::

የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዘኛው መሠረታዊ ትርጉም ተቀራራቢ ቢሆንም፤ “ድለላ” ሲነሳ አብሮ ማታለል፣ መሸንገል ፣ ማሞኘት፣ በውሸት አግባብቶ ማሳመን፤ የሚሉ አሉታዊ አንድምታዎች ግዘፍ ከመንሳት አልፈው “ድለላ” በተነሳ ቁጥር ቀድመው ወደ አዕምሯችን የሚመጡት እነዚህ አሉታዊ ብያኔዎች ናቸው:: በሀገራችን ያለውን አብዛኛውን ደላላም ይገልፁታል ተብሎ ይታመናል:: ሆኖም እጅግ፣ እጅግ ያነሱ በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ታማኝ፣ ሐቀኛና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ደላሎች መኖራቸው ግን ሊዘነጋ አይገባም:: ድለላን ከመንግሥት አካላት ተርታ ከማሰለፍ አልፌ እንደ 1ኛው መንግሥት የቆጠርሁበትን ዓብይ መግፍኤና መገለጫ ስለሆነው ኢኮኖሚ ላነሳሳ።

ኢኮኖሚያችን ከሌሎች ሀገራት ለየት ያደርገዋል ብዬ ከማምንባቸው ግርምቶች ቀዳሚው፤ በአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚክስ ሀ ሁ … ዝቅተኛ መስፈርት በሆኑት ፍላጎት demand እና አቅርቦት supply አለመዘወሩ ነው:: ከጉልት እስከ ጅምላ ንግድ፣ ከጎጥ እስከ ፌዴራል፣ ከሽንኩርት ማሳ እስከ አትክልት ተራ፣ ከሚዛን ተራ እስከ እህል በረንዳ፣ ከአንድ ክፍል ጭቃ ቤት እስከ ተንጣለለ ቪላና ፎቅ፣ ከአንድ ጥማድ መሬት እስከ ጋሻ መሬት፣ ከአራጣ ብድር እስከ ባንክ ብድር፣ … ፤ ከታች እስከ ላይ በተሰገሰጉ ሕልቁ መሳፍርት ደላሎች ሳምባ የሚተነፍስ ኢኮኖሚ መሆኑ ነው ::

አንድ ወዳጄ በዚያ ሰሞን እንዳጫወተኝ ከሆነ የደላላ እጅ ሀይ ባይ በማጣቱ እረዝሞ እረዝሞ በአንድ ወቅት ሀገራችን በምትፈርማቸው ብድርና እርዳታ ሳይቀር ፈርቅ እስከመያዝ ደርሶ ነበር:: እግራችን እስኪ ቀጥን ብንዞር የደላላ እጅ ያልገባበት የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም:: ከላይ ከትርጉሙ እንደተመለከትነው የድለላ ሥራ ሻጭና ገዥን ማገናኘት ለዚህም ድላል ( የአገልግሎት ክፍያ ) መቀበል ቢሆንም ፤ የሀገራችን ደላላ ግን በዓለም ታይቶም፣ ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ ዋጋ ቆራጭ ፣ ተማኝ፤ ገበያ መሪ እስከመሆን ደርሷል ::

አሁን ያለው የእህል፣ የአትክልት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ፤ የመኪና የንግድም ሆነ የኪራይ ቤት ክፍያ፣ የመሬት ዋጋ ፣ …፤ የተቆረጠው፣ የተተመነው በገበያ ሳይሆን በደላላ ነው:: በዚህም ገበያ አመጣሽ ሳይሆን፤ ደላላ ዘራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ጎንቁሏል:: በዚህ የተነሳ ዜጋው በኑሮ ውድነት ፍዳውን እያየ ነው:: የሸቀጡ፣ የምርቱ፣ የአገልግሎቱ አምራች፣ አቅራቢም የሚገባውን ጥቅም እያገኘ አይደለም:: ከሸማቹም፣ ከሻጩም በሁለት ቢላዋ እየበላ ያለው ሕገ ወጥ ደላላው ነው ::

ዛሬ በመላው ሀገራችን ያሉ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጥያቄ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውና ለምርታቸው፣ ለገበያ ከሚቀርቡ እንስሳትም ሆነ ተዋፅዖ ተገቢውን የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ሲወተውቱ፣ ሲማፀኑ በየሚዲያው ብንሰማም፣ ብንመለከትም መፍትሔ ባለማግኘታቸው ዋጋ የሚቆርጥላቸው ደላላው ነው:: በምርቱ ተጠቃሚዎች እነሱ ሳይሆን ደላላው ነው:: አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የድካሙ፣ የላቡ ተጠቃሚ ካለመሆኑ ባሻገር፤ ደላላ አመጣሽ የሆነው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የኢኮኖሚውን ወደለየለት ቀውስ እያንደረደረው ነው ::

ሕገ ወጥ ደላላው ያለ አዛዥ ናዛዥ ገበያውን በብቸኝነት መቆጣጠሩ፤ መንግሥት በነፃ ገበያ ስም መነሻ ዋጋ ተመን እና የትርፍ ሕዳግን profit margin አለመወሰኑ፤ ከሕገ ወጥ ደላላው ጋር እሳትና ጭድ ሆኑ የኑሮ ወድነቱን እያቀጣጠለ፤ በዜጋው ላይ ብሶትን፣ ምሬትን ተስፋ መቁረጥን እየከዘነ ይገኛል:: በዚሁ ከቀጠለ ወደለየለት ፓለቲካዊ ቀውስ የማያመራበት ምክንያት የለም:: የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በሰሞነኛ የጥናት ግኝቱ ያስጠነቀቀው ይሄንኑ ነው። በዓለማችን የነፃ ገበያ አባት የምንላቸው ምዕራባውያን ሳይቀሩ የትርፍ ሕዳግንም ሆነ የመነሻ ዋጋ ደረጃን እየወሰኑ፤ ገበያውን እየተቆጣጠሩ ባለበት፤ እኛ ለዛውም ያልሠለጠነውን ኢኮኖሚ ስድ መልቀቃችን ዛሬ ለምንገኝበት ምሬት፣ እሮሮ ዳርጎናል ::

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You