ጠንካራ መሠረት የጣለው የንግድ ሥራ- ከኢትዮጵያ እስከ ቻይና

የንግድ ሥራቸውን አሀዱ ያሉት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ባጠናቀቁ ማግሥት ነው። ‹‹ወጣት የነበር ጣት›› እንዲሉ የንግድ ሥራውን በከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት፣ በብዙ ጥረትና ትጋት ነው የተቀላቀሉት፡፡ የንግድ ሥራውን በዕውቀት ለመምራትም በኢትዮጵያም በቻይናም ብዙ ወጥተዋል፤ ወርደዋል፡፡ የትናንቱ ሩጫ፣ ጥረትና ትጋታቸውም ዛሬ ላይ የኢንቨስትመንት ባለቤት አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡

እኚህ የዛሬው የስኬት እንግዳችችን አቶ እስመለዓለም ዘውዴ ይባላሉ፡፡ ገና በጠዋቱ ሕይወትን ቀላልና ምቹ ከሚያደርገው ቴክኖሎጂ ጋር የመተዋወቅ ዕድል ያገኙት እኚህ ሰው የኢዜድ ኤም ትሬዲንግና ኢንቨስትመንት መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የተማሩት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ ገና የ20 ዓመት ጎረምሳ ነበሩ። ‹‹ዕድሜ ቁጥር ነው›› እንዲሉ ያወቁትን ለሌላው ለማሳወቅ፣ ለማስተማርና እግረ መንገዳቸውን ደግሞ ነጋዴ ለመሆን አልቦዘኑም፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ እስመለዓለም፣ ከዜሮ ክፍል ጀምረው ፊደል የቆጠሩት በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ነው። የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውንም እንዲሁ በዚሁ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ /አራት ኪሎ ካምፓስ/ ተከታትለዋል፤ በዚህም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕውቀትን ታጥቀዋል፡፡ በወቅቱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አዲስ ነገር በመሆኑ ቴክኖሎጂውን የማወቅና የመጠቀም ጉጉታቸው እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት የተከታተሉትን የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት በተግባር ለማዋል ጊዜ ያላጠፉት አቶ እስመለዓለም፤ አራት ኪሎ አካባቢ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ቤት ሲከፍቱ እርሳቸው ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች ለማካፈል ከውስጥ የመነጨ ፍላጎት ነበራቸው። የንግድ ሥራቸው መነሻ የነበረው የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ቤትን ሲከፍቱ የቤተሰቦቻቸው እገዛ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው አጫውተውናል፡፡

በተለይ ኮምፒውተር በሚሰጠው አገልግሎት በእጅጉ ይገረሙ የነበሩትና በንግድ ሥራ የተሰማሩት ወላጅ አባታቸው አቶ ዘውዴ፤ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የኮምፒውተር ማስተማሪያ ትምህርት ቤት እንዲከፍቱ ትልቅ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ‹‹አባቴ እኔ ያገኘሁትን ዕውቀት ለሌሎች እንዳደርስ ብርቱ ጥረት አድርገዋል›› የሚሉት አቶ እስመለዓለም፤ እርሳቸውም በዘርፉ የቀሰሙትን ዕውቀት ለሌሎች ለማስተላለፍ ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት እንደነበራቸው በማስታወስ የንግድ ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

ከመደበኛው የኮምፒውተር ትምህርታቸው በተጨማሪም ተያያዥ የሆኑትን የኮምፒውተር ጥገና፣ የኮምፒውተር ኔትዎርኪንግና ሌሎች ትምህርቶችንም ተከታትለዋል፡፡ የማስተማር ሥራንም እንዲሁ ጎን ለጎን አከታትለዋል፡፡ በወቅቱ መምህራንን ቀጥረው በቀንና በማታው ክፍለ ጊዜ ጭምር ነበር የሚያስተምሩት፡፡

በቤተሰባቸው ድጋፍና በግል ጥረታቸው ጭምር ወደ ንግድ ሥራ የገቡት አቶ እስመለዓለም፤ ወላጅ አባታቸው በሥጋ ሲለዩአቸው ደግሞ የእርሳቸውንም የንግድ ሥራ ደርበው የማስተዳደር ኃላፊነት ወደቀባቸው፤ ቢሆንም እጅ አልሰጡም፡፡ ሁኔታው ይበልጥ ጠንካራና ብርቱ ነጋዴ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ የግል ሥራቸውን ከወላጅ አባታቸው የንግድ ሥራ ጋር ደርበው ለመሥራት የቤተሰብ እገዛ ያስፈለጋቸው በመሆኑ ወንድማቸውን አጋር አድርገው በጋራ መሥራት ጀመሩ፡፡

ወላጅ አባታቸው ለንግድ ሥራቸው አስፈላጊ የሆኑ እንደ ኮምፒውተር፣ ቀለም፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን እና ሌሎች ቁሳቁስን ከጣልያን ሀገር ያስመጡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እስመለዓለም፤ ይህን ማድረግ ባይችሉም ቁሳቁስን ለማሟላትና የወላጅ አባታቸውን እንዲሁም የግላቸውን የንግድ ሥራ ለማስቀጠል መፍትሔ ይሆናል ወዳሉት ሀገረ ቻይና አቀኑ፡፡

‹‹ወደ ቻይና ስሄድ ሥራ ፍለጋ ነበር›› የሚሉት አቶ እስመለዓለም፤ ሀገር ውስጥ ያለውን የንግድ ሥራ ወንድማቸው እንዲመራው በማድረግ እርሳቸው ደግሞ የተሻለና አዲስ የሥራ አቅጣጫን ለመፍጠር ጭምር አቅድው ነው የተጓዙት፡፡ በ2002 ዓ.ም በዘመነ ሚሊኒየም ወደ ቻይና ያቀኑት አቶ እስመለዓለም ከቻይናውያኑ ቋንቋን ጨምረው ብዙ ተምረዋል፡፡ በዚህም ጠንካራ ትስስር በመፍጠር የንግድ ሥራቸውን ማስፋፋት ችለዋል።

ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ አፍሮ ቻይና የተባለ ቢሮ በቻይና ከፍተው የንግድ ሥራቸውን ማሳለጥ የጀመሩት አቶ እስመለዓለም፤ በወቅቱ ሀገር ውስጥ ላለው ድርጅታቸውና ለሌሎች ደንበኞችም ተያያዥ የሆኑና ጥራት ያላቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቁሳቁስ በመላክ ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡ በወቅቱ ቻይና ውስጥ አሉ የተባሉ ፋብሪካዎች አካባቢ በመሄድ ምርቶቹ ሲመረቱ ተመልክተው የጥራት ደረጃቸውን አረጋግጠውና ሞክረው ወደ ሀገር ቤት ይልኩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ምርቶቹም በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው፡፡

በንግድና በቴክኖሎጂ ሰፊ ውቅያኖስ ከሆነችው ቻይና ገብተው የንግድ ሥራቸውን ማቀላጠፍ የጀመሩት አቶ እስመለዓለም፤ ወደ ቻይና ከሚመጡ ነጋዴዎች ጋርም እንዲሁ ትስስር በመፍጠር ነጋዴው የሚፈልገውን ዕቃ በማቅረብ ለነጋዴዎች ወኪል በመሆን ብዙዎችን አግዘዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ የንግድ ሥራቸውን እያሰፉ በመሄድ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወደ ግንባታ ዕቃዎች ተሸጋግረዋል፡፡

ለአብነትም አንድ ባለሀብት ለሚገነባው ሆቴል ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ የፊኒሺንግ ዕቃዎችን ፍለጋ ወደ ቻይና ካቀና በቀዳሚነት የሚፈለጉት አቶ እስመለዓለም መሆን ቻሉ፡፡ እሳቸውም ሰውዬው የሚፈልገውን እቃ አንድ በአንድ መግዛት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሥራውን ያቀሉለታል፡፡ ለዚህ ሥራቸውም ለቻይናውያን እና ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል በመፍጠር ነጋዴው ቻይና ሲገባ ጀምሮ ሆቴል በመያዝ የሚፈልገውን ዕቃ በሙሉ ገዝተው ይልኩለታል፡፡ ነጋዴውም ያለድካምና እንግልት የሚፈልገውን ዕቃ መርጦ ይገዛል፡፡

አቶ እስመለዓለም በሀገረ ቻይና በነበራቸው የመጀመሪያ ቆይታ ቋንቋ ማወቃቸው ዛሬ ለደረሱበት ትልቅ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ መሠረት እንደጣለላቸው ይናገራሉ፡፡ አንዱ ሥራ ለሌላ ሥራ በር እየከፈተ በመሄዱ ኑሯቸው ቻይና ሊሆን ግድ ሆነና በቻይና ለ13 ዓመታት ቆይታ አድርገዋል፡፡

ከዚህ ቆይታ በኋላ ደግሞ በከፊል ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የንግድ ሥራቸውን ማስቀጠል ጀመሩ፡፡ በአሁን ወቅትም ቻይና ውስጥ አብረው ለሚሰሩባቸው ድርጅቶች በኢትዮጵያ ወኪል በመሆን ኢዜድ ኤም ንግድና ኢንቨስትመንት የተባለውን ድርጅት ማቋቋም ችለዋል፡፡ ድርጅቱ የግንባታ ዕቃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን በማስመጣት አንድ እግሩን ቻይና ሌላኛው እግሩን ደግሞ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ አድርጎ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡

ከግንባታ ዕቃዎች በተጨማሪ የሕክምና ቁሳቁስን ወደ ሀገር ውስጥ በማስመጣት የሚታወቀው ኢዜድኤም ንግድና ኢንቨስትመንት በተለይም የላብራቶሪ ቁሳቁስንና የኤክስሬይ ማሽኖችን ያስመጣ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እስመለዓለም፤ ዓለም አቀፍ ስጋት በነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ግብዓቶችን ከቻይና በማስመጣት ሰፊ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አጫውተውናል፡፡

‹‹ቻይና በነበረኝ ቆይታ ከቻይናውያኑ ብዙ ተምሬያለሁ›› የሚሉት አቶ እስመለዓለም፤ ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በንግድ ሥራ መሰማራታቸው ጠቅሟቸዋል። ከኢትዮጵያ እስከ ቻይና ያደረጉት የንግድ እንቅስቃሴም በሀገር ውስጥ ችግር ፈቺ በሆነው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት አስችሏቸዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ ያስገቧቸው የነበሩ የግንባታ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ ለዚህም የዳበረ ግንኙነት ካላቸው ከቻይናውያኑ ዘንድ ማሽነሪዎችን ጨምሮ ዕውቀትና ልምድን ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት ችለዋል፡፡

የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ይዘው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ እስመለዓለም፤ ለፋብሪካ ግንባታ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 10 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ወስደዋል። ይሁንና ፋብሪካው ተገንብቶ ወደ ምርት ለመግባት የሚወስደው ጊዜ ረዘም ያለ በመሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርክን አማራጭ አድርገዋል። በመሆኑም በቶሎ ወደ ምርት ለመግባት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ፤ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባገኙት 3000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሼድ 14 ነጥብ አምስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በማድረግ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

ፋብሪካውን በተረከበ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት የገባው ኢዜድኤም ንግድና ኢንቨስትመንት፤ በአሁን ወቅትም የጥራት ደረጃቸው ከውጭ ከሚመጡት ጋር ተወዳዳሪ የሆኑና ዘመኑን የዋጁ የግንባታ ዕቃዎችን በሙሉ አቅሙ በሀገር ውስጥ እያመረተ ይገኛል፡፡ ኢዜድኤም ንግድና ኢንቨስትመት ከሚያመርታቸው የግንባታ ዕቃዎች መካከልም ፒፒአር፣ ኤችዲፒኢ፣ ፒቪሲ ቧንቧዎች እና ቱቦዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ምርቶቹ አስፈላጊ ከሆኑ የመገጣጠሚያ ዕቃዎች ጋር የሚመረቱ በመሆናቸው በዘርፉ ከፍተኛ ዕድገትን የሚያስመዘግብ ነው ያሉት አቶ እስመለዓለም፤ ፋብሪካው፤ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ፒፒአር ትቦዎች እና አንድ ሚሊዮን 900 ሺህ የፒፒአር መገጣጠሚያዎች፣ አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የፒቪሲ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች እና 900 ሺህ የፒቪሲ መገጣጠሚያዎች እንዲሁም ሶስት ሚሊዮን 500 ሺህ ሜትር በላይ የፒቪሲ ኮንዲዩት ማስተላለፊያ ትቦዎችን የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው አንድ ሕንፃ ሲሰራ ለሕንፃው አስፈላጊ የሆኑ የኤሌክትሪካልና የውሃ መዘርጊያ ቁሳቁሶችን በሙሉ የሚያመርት ሲሆን፤ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን የቧንቧ እና የቱቦ ዝርጋታ ሥርዓት አቅርቦትና ጥራት እጥረትን መፍታት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም እነዚህን ምርቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድም አበርክቶው ጉልህ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ሀገር በብርቱ እየተፈተነች ያለችበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት የማቃለል ዕቅድ ያለው ኢዜድኤም ንግድና ኢንቨስትመንት በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሲገባ በዓመት አስር ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ምርት የማምረት አቅም እንዳለውና ይህም ማለት ሀገሪቷ ለግንባታ ማጠናቀቂያ ዕቃዎች ታወጣው ከነበረው የውጭ ምንዛሪ በዓመት አስር ሚሊዮን ዶላር ማዳን ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ በግንባታ ላይ እንደመሆኗ የግንባታ ማጠናቂቂያ ግብዓቶች በስፋት ይፈለጋሉ ያሉት አቶ እስመለዓለም፤ የሚገነቡ ሕንፃዎች በሀገር ውስጥ ምርት መጠናቀቅ እንዳለባቸውም ያምናሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ባለው የሕንፃ ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ግብዓቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ በመሆናቸው ሕንፃውን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ያህል ነው፡፡ በእነዚህ የግንባታ ግብዓቶች የሀገሪቷ ኢኮኖሚ እየተናጋ ነው፡፡

ይሁንና ለዚህ ችግር እነሆ መፍትሔ ያለው ኢዜድኤም የንግድና ኢንቨስትመንት በአሁን ወቅት አንድን ሕንፃ መቶ በመቶ በሀገር ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም አስፈላጊና መሠረታዊ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ ከውጭ በማስመጣት ግብዓቶችን የሚያመርት ሲሆን፤ በቀጣይም ጥሬ ዕቃዎቹን በሀገር ውስጥ የመተካት ዕቅድ አለው፡፡ ለዚህም ጥናት እያደረጉ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ እስመለዓለም፤ ማንም ሰው ለሚገነባው ሕንፃ ሙሉ የፊኒሺንግ ዕቃዎችን ከውጭ ሀገር ማስመጣት እንደሌለበትና ድርጅታቸው ኢዜድኤም ንግድና ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ጥራት እያመረተ መሆኑን በልበ ሙሉነት ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው በምርት ሥራው ብቻ ከ300 ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ሲኖረው በቀጣይ ምርቶቹን ወደ ገበያ በሚያወጣበት ወቅትም እንዲሁ ወኪል ሻጮችን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡ በቀጣይ በሶስት ፈረቃ ያመርታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፋብሪካ በአሁን ወቅት በአንድ ፈረቃ ለሚያመርተው ምርት 85፣ የቢሮ ሥራ ለሚሠሩ 100፣ ስቶር ላይ ለሚሰሩ 40 በድምሩ ለ225 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡

በርካታ ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድ ያለው ኢዜድኤም ንግድና ኢንቨስትመንት ከሚያመርተው ምርት 50 በመቶ ለሀገር ውስጥ ገበያ ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን 50 በመቶውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡ በቀጣይም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወሰደው 10 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ፋብሪካ በመገንባት ሥራውን የማስፋፋትና በርካታ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ አለው፡፡

ባለቤቱ እንደሚናገሩት ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ድርጅቱ ከኮንስትራክሽን ጋር በተያያዘ ለማህበረሰቡ ውሃ የማውጣት ሥራዎችን በመሥራት የሚታወቅ ነው። ሀገራዊ በሆኑ ማንኛውም ጥሪዎችም እንዲሁ ምላሽ በመስጠት ቀዳሚ ነው፡፡ የመንግሥትን ግብር በአግባቡ የሚከፍለው ኢዜድ ኤም ንግድና ኢንቨስትመንት ታማኝ ግብር ከፋይ በመሆን ተሸላሚ ከሆኑ ድርጅቶች መካከልም ተጠቃሽ ነው፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You