ከተስፋ መቁረጥ ለመውጣት

ሰዎች በብዙ ምክንያቶች ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ተስፋ መቁረጥ ግን ድሮም አሁንም ያለ ክስተት ነው፡፡ ልዩነቱ ተስፋ የሚያስቆረጡ ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው ነው፡፡ ሰው በኑሮ ውድነት ተስፋ ይቆርጣል። በጤና እጦት ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በገቢ ዝቅተኛነት ተስፋ ይቆረጣል፡፡ አግኝቶ በማጣት ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በነገሮች አለመሳካት ተስፋ ይቆርጣል። በትዳር ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በቃ! ሰው ተስፋ ለመቁረጥ እንኳን ተስፋ እንደሚያስፈልገው እያወቀ ተስፋ ይቆርጣል።

በሰው ልጆች የሕይወት ዑደት ውስጥ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሺህ ምክንያቶች እንዳሉ ሁሉ ተስፋን የሚያስቀጥሉና ተስፋ የሚሰጡ ሺህ ምክንያቶች እንዳሉ መረዳት ይገባል። በርግጥ አንዳንዴ ከሰዎች ጋር ላንስማማ እንችላለን፡፡ ሕይወት ተስፋ ሊያስቆርጠን፣ ትምህርታችንና ሥራችን እኛ በፈለግነው መንገድ ላይሄድልን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለከፋው፣ ላዘነና በእጅጉ ተስፋ ለቆረጠ ሰው ሁሉ መድኃኒት እንዳለ ልብ ማለት ይገባል፡፡

መቼም የጓደኛን ሥራ ታውቁታላችሁ። በእናንተ ውስጥ ያለውን ምርጡን ማንነት እንደመስታወት ሆኖ ማሳየት ነው፡፡ ለእናንተም ይህ ጽሑፍ ምርጡን ማንነታችሁን እንድታዩበት ይረዳችኋል። ከፍቶኛል፣ ደብሮኛል፣ ከሰዎች ጋር መስማማት አቅቶኛል፣ እየተጎዳሁ ነው ለምትሉ ሁሉ ጽሑፉ ያግዛችኋል፡፡ እነሆ አምስቱ ተስፋ ሰጪ ነገሮች፡፡

1ኛ.ነገሮችን ቁጭ ብሎ መተንተን

አንድ ሰው ከእስር ቤት መውጣት ከፈለገ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት እስር ቤት እንዳለ ማወቅ ነው፡፡ ከእስር ቤት እንዴት ልውጣ የሚለው እስር ቤት እንዳለ ካመነ ነው፡፡ አያችሁ! ከተስፋ መቁረጥ መውጣት የምትፈልጉ ከሆነ ተስፋ ያስቆረጣችሁን ነገር ምን እንደሆነ መተንተንና ማሰብ ይጠበቅባችኋል፡፡ ስለችግሩ በደንብ ባወቃችሁ ቁጥር ወደ መፍትሔው የመቅረባችሁ ዕድል ይሰፋል። ነገሩን እንደፊልም አስቡት፡፡ ‹‹እኔን ተስፋ ያስቆረጠኝ የሥራ ጉዳይ ነው፣ የትዳር ጉዳይ ነው፣ የኑሮ ጉዳይ ነው፣ ትምህርቴ ነው፣ ቢዝነስ ነው፣ ምንድን ነው›› ብላችሁ እንደፊልም ሕይወታችሁን እዩት፡፡ አጥኑት፡፡ ጎዶሎው የቱ ጋር እንደሆነ ፈልጋችሁ አግኙት፡፡

ይህን የማድረግ ዋናው ዓላማ ችግሩን ተረድታችሁ መፍትሔ እንድታመጡና በሕይወታችሁ ማስተካከያ እንድታደርጉ ነው። ለምሳሌ የመስታወት ዓላማ አየት አድርጋችሁ የተንጨባረረ ፀጉራችሁን ወይም ነጭ የሆነ የፊታችሁን ክፍል አየት አድርጋችሁ እንድታስተካክሉ ነው፡፡ ስለዚህ እናንተም እንደ መስታወት ራሳችሁን እዩት፣ አጥኑት፣ ምን እየሆንኩ ነው በሉ፡፡ ለምሳሌ ውሻችሁን ሐኪም ቤት ብትወስዱት ሐኪሙ ራሱ ውሻው ምኑ ጋር እንዳመመው ገምቶና አጥንቶ ለበሽታው መፍትሔ ይሰጣል፡፡

እኛ ሰዎች ብንታመም ግን ስለሕመማችን ራሳችን ነው የምንናገረው፡፡ ትንሽ ራሴን እያመመኝ ነው፣ ሆዴን፣ ጨጓራዬን፣ ኩላሊቴን… ወዘተ እንላለን፡፡ ስለዚህ ችግራችንን የሚፈታው ሌላ ሰው አይደለም። ራሳችን ነን፡፡ የቱ ጋር ነው ችግሩ ብለን ማጥናት አለብን፡፡ የዚህ መፍትሔ ዓላማ ወይም ችግራችንን የመተንተናችን ዋና ዓላማ ‹‹አሃ!›› እንድትሉ ማድረግ ነው፡፡ ‹‹አሃ!›› ለካ እዚህ ጋር ነው የኔ ችግር እንድንል ነው፡፡

2ኛ.መቀየር የምትችሏቸው ነገሮች

ላይ አተኩሩ

ሰዎችን፣ ነገሮችን፣ ሁኔታዎችን እንዳስቀመ ጧቸው አያገኟቸውም፡፡ እንዳስቀመጡ የሚያገኙት ስቀው የተነሱትን ፎቶ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ራስዎን መለወጥ ላይ ብቻ ያተኩሩ፡፡ ሰዎችን ልትቀይሯቸው አትችሉም። የሚገርማችሁ ነገር ሚስት በባሏ እናት በጣም ተማረረች። ሁሌ ይጣላሉ ይደባደባሉ፡፡ መረራት፡፡ ‹‹እኔ እኚህን ሴትዮ ምንድን ነው የማደርጋቸው›› ትላለች። በቃ መስማማት አቃታት፡፡ ከዛ ‹‹ሊሆን የሚችለውና ከባሌ ጋር በሰላም መኖር የምችለው እኚህ ሴትዮ ከሌሉ ነው፤ እናቱ ከሞቱ ነው›› ማለት ጀመረች፡፡ ‹‹እንዴት አድርጌ ገድያቸው ሰላሜን እንደማገኝ›› ትላለች ሁሌ፡፡ ቀጥላ ምክር ለማግኘት አንድ ጠቢብ ሰው ጋር ሄደች፡፡ ጉዳዩንም አማከረችው፡፡ ‹‹እየውልህ! እንዳትመክረኝ፤ ሰላም ፍጠሪ፤ ፀባይ ፍጠሪ እንዲህ ሁኚ እንዳትለኝ፡፡ እንዴት አድርጌ ሰው ሳያውቅብኝ እንደምገድላት ብቻ ንገረኝ፡፡ አንተ ጠቢብ ስለሆንክ እርሱ አያቅትህም›› አለችው፡፡

ጠቢቡ ሰው በደንብ ከሰማት በኋላ ‹‹ልክ ነሽ መፍትሔው የባልሽን እናት መግደል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ አንድ አስገራሚ መፍትሔ እሰጥሻለሁ›› አለና የሆነች የውሃ ቀለም ያላት ትንሽዬ ብልቃጥ አመጣና ሰጣት። ይህን እናቲቱ ምግባቸው ውስጥ ወይም የሚጠጡት ነገር ላይ ትቀላቅይዋለሽ፤ ደስ የሚለው መርዙ በአንዴ አይገላቸውም፡፡ ቀስ እያለ፣ እያሳመመ፣ እየጎዳ ይገድላቸዋል፡፡ ያኔ አንቺም አይነቃብሽም›› አላት፡፡

ሚስት በጣም ደስ አላት፡፡ ‹‹በጣም አመሰግናለሁ›› አለችው ጠቢቡን ሰው፡፡ ልትሄድ ስትል ግን ጠቢቡ ሰው እንዲህ አላት፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ መጨቃጨቅ ማቆም አለብሽ። ምክንያቱም በሳምንታትና በወራት ውስጥ እኚህ ሴትዮ ሲሞቱ የምትጨቃጨቂያቸው ከሆነ ሰው ይጠረጥራል። ድሮም እሷ ናት ነገር እየገፋች ጎድታ የገደለቻቸው ይሉሻል፡፡ ስለዚህ አሁን እንደምንም ብለሽ አንገትሽን ድፊ፡፡ የምትወጃቸው ምሰይ፡፡ ቢቆጡ፣ ቢጮሁብሽ ተንከባከቢያቸው›› አላት፡፡

‹‹አሁንማ አረጋገጥኩ እኮ! ከአንድ ወር በኋላ ከሌሉ ለምን አንገቴን አልደፋም፡፡ እንደምወዳቸው እሆናለሁ ችግር የለውም፤ አመሰግናለሁ›› ብላ ሄደች፡፡ ቤቷ ሄዳ ማታ ላይ ሻይ ስታቀርብላቸው ያንን ፈሳሽ ቀላቅላ ሰጠቻቸው፡፡ ከሰጠቻቸው በኋላ ግን ቢሞቱስ ብላ መፍራት ጀመረች፡፡ ‹‹ግን ችግር የለውም ይሙቱ እኔ ፀባዬን አሳምራለሁ›› አለች። ከዛ ሲቆጧት ዝም ትላለች፡፡ ሳቅ እያለች ትመልሳለች። ጥሩ ምግብ አዘጋጅታ ታቀርብላቸዋለች፡፡ እግራቸውን ታጥባቸዋለች፡፡ ድሮ ነገር የሚፈልጓትና የሚሳደቡት ሴትዮ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገው ተውት፡፡ እሷን መመረቅ ጀመሩ፡፡ ልጄ ምን ዓይነት መልአክ የሆነች ሴት ነው ያገባው ማለት ጀመሩ። እሳቸውም ሳያውቁት ተቀየሩ፡፡ ሚስትና እናት ፍቅር በፍቅር ሆኑ፡፡

ከዛ ነገሮች ተቀየሩ፡፡ ለቤተ ዘመድ ሁሉ ሲያስተዋውቋት ‹‹እየውላችሁ እንዴት ያለች መልዓክ የሆነች ሚስት መሰለቻችሁ ልጄ ያገኘው›› ማለት ጀመሩ። ከዛ እሷም ሳትፈልግ ተቀየረች። ወደደቻቸው። መጠራጠር ጀመረች፡፡ ‹‹ወይኔ ከሶስት ሳምንት በኋላ ቢሞቱስ›› ብላ መፍራት ጀመረች፡፡ ቢጨንቃት ጠቢቡ ሰው ጋር ሄደች። ጠቢቡ ሰውም ‹‹ምን ተፈጠረ፤ ሞቱ አይደል›› አላት። ኧረ አልሞቱም! ጉድ ሆኜልሃለሁ፡፡ የኔ ፀባይ ሲቀየር እርሳቸውም ወደዱኝ፡፡ አሁን እንዲሞቱ አልፈልግም፡፡ በጣም ጥሩ ሴት ናቸው፡፡ እኔም ባሌም ማዘን አንፈልግም፡፡ ስለዚህ ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ ? መርዙን የሚያሽር ነገር ስጠኝ አለችው፡፡

ጠቢቡ ሰው ፈገግ እያለ ድሮስ እኔ የሚገድል ነገር እኮ አልሰጠሁሽም፡፡ ውሃ ነበር በብልቃጥ የሰጠሁሽ። እንደዚህ እንደሚፈጠር አውቃለሁ አላት፡፡ አያችሁ አይደል! እኛ ስንቀየር ነገሮች፣ ሰዎችና ሁኔታዎች ይቀየራሉ፡፡ ሰዎችን ለመቀየር መሞከር የለብንም፡፡ ስለዚህ የምንቆጣጠረውንና ልንቀየር የምንችለው ነገር ላይ ማተኮር አለብን፡፡

3ኛ.መዝጋት ያሉብን በሮች አሉ

መዝጋት ያሉብን በሮች አሉ፡፡ ያውም ጥርቅም አድርገን፡፡ አብዛኛዎቻችን የምንኖረው ትላንት ላይ ነው። ስለትናንት ነው የምናስበው፡፡ የካዱንን፣ የጎዱንን በቃ! እርሱ እኮ እንዲህ እንዲህ አድርጎኝ፣ እንዲህ አድርጋኝ፣ እንዲህ ተፈጥሮ፣ ከስሬ፣ አብድሬው ካደኝ፣ ንፁህ ልቤን ሰጥቻት ካደችኝ ….ሃሳባችን ትላንት ላይ ነው፡፡ ዛሬን እየኖርን አይደለም፡፡ ስለነገም አናስብም፡፡ ትላንት የተጎዳነውንና የተበደልነውን ነው የምናስበው፡፡ ስለዚህ ጥርቅም አድርገን የምነዘጋቸው በሮች መኖር አለባቸው፡፡ እስከመጨረሻው የማንከፍታቸው ፋይሎች ያስፈልጋሉ።

ከትላንቱ መማር አለብን፡፡ ግን አንዳንዴ ደግሞ ትናንትን መዝጋትም አለብን፡፡ ትላንት ላይ መኖር የለብንም፡፡ ትላንት ቤቱን ሰራብን እኮ፡፡ አንድ ሰው እቃ ተሸክሞ ይሄዳል። ረጅም ጉዞ ነው የተጓዘው፡፡ እቃው ትንሽ ትከሻውን አድክሞታል፡፡ መንገድ ላይ ባለመኪና አገኘ፡፡ ባለመኪናው አዝኖለት መኪናውን አቁሞ ና! ግባ ብሎ እቃውን ኋላ መኪና እሱን ደግሞ ከፊት አስገብቶ ጉዞ ጀመረ፡፡ ግን የሚገርመው እቃውን የተሸከመው ሰውዬ ትከሻው ዘምበል ብሎ ነበር፡፡ አሁንም የተሸከመ ነው የሚመስለው፡፡

ለምን መሰላችሁ? እቃው ከትከሻው መውረዱን አላመነም፡፡ እቃው እኮ ግን ወርዷል፡፡ ከመኪናው ኋላ ነው የተቀመጠው፡፡ እርሱ ግን ትከሻውን አጎምብሷል። የጀርባ በሽታ ኖሮበትም አይደለም። አላመነም፡፡ እናንተም ትናንትናችሁን፣ ከባዱን ጊዜ፣ መጥፎውን ጊዜ ፈጣሪ አሳልፎላችኋል። የሚያሳዝኑ ነገር ግን ያለፉ ስንት ቀናት አሉ፡፡ ቀናቶቹን አልፋችኋል፡፡ ግን አልረሳችኋችሁም፡፡ የምትኖሩት ትላንት ውስጥ ነው። የትናንት ችግር አሁንም ተብትቦ ይዟችኋል፡፡ ስለዚህ በጥሱት፡፡

4ኛ. እንኳንም ተበላሸ!

አንዳንድ ነገሮች ካልደፈረሱ አይጠሩም። በሕይወታችን መበላሸት ያለባቸው ነገሮች አሉ። እንኳንም ተበላሸ! ብለን ማመን አለብን። አመለካከታችንና አተያያችን መቀየር አለብን፡፡ ንጉሡ ሁለት ስጦታዎች ተሰጡት። የሚያማምሩ ወፎች፡፡ አንዷ በሰማይ ላይ ስትበር ታፈዛለች፤ታምራለች። አንዷ ግን ቅርንጫፉ ላይ ቆማ ቀረች፡፡ ንጉሡ ደግሞ ይችኛዋን ስትበር ማየት ፈለገ፤ ጓጓ። ስለዚህ አማካሪዎቹን ጠራና ‹‹ጠቢብም ይሁን ማንም ሰው ጥሩና ይችን ወፍ እንድትበር ያድርግልኝ›› አላቸው። ብዙ ጠቢባን መጡ፡፡ ወፏ እንድትበር የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ፡፡ አልቻሉም። ንጉሡ ‹‹እየውላችሁ ወፏ ስትበር ከማየት በላይ የምፈልገው ነገር የለም›› እያለ አማካሪዎቹን ማስጨነቅ ጀመረ፡፡ ግን አልተሳካም፡፡

የሆነ ቀን ንጉሡ ሰገነቱ ላይ ሆኖ እየተዝናና እያለ ያቺ ወፍ ከፍ ብላ ስትበር ያያታል፡፡ በጣም ነው የምታምረው፡፡ ልቡ ተነካ፡፡ አማካሪዎቹን ጠራና ይችን ወፍ እንድትበር ያደረጋትን ጠቢብ ጥሩልኝ አለ፡፡ የመጣው ግን ጠቢብ ሳይሆን ገራገር ገበሬ ነበር፡፡ ንጉሡ ተገረመ። ‹‹የምትፈልገውን ነገር ሁሉ እሸልምሃለው፡፡ ‹‹ግን ምን አድርገህ ወፊቱን እንዳበረርካት፣ ምን ዓይነት ጥበብ ብትጠቀም ወፊቱ የበረረችው እስኪ ንገረኝ›› አለው፡፡

ገበሬው መለሰ ‹‹የዛፉን ቅርንጫፍ ቆረጥኩት፤ በረረች›› አለ፡፡ ንጉሡ በጣም ተገረመ፡፡ እኛም በሕይወታችን ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ከፍ ብለን እንድንበር፣ የምንፈልገውን እንድናሳካ፣ ነፃነት እንዲኖረን አንዳንድ መቆረጥ ያለባቸው ነገሮች አሉ። ከሕይወታችን መበላሸት፣ መደፍረስ ያለበት ነገር አለ፡፡ ለምን? እንደወፏ ከፍ ብለን እንድንበር። ነፃነት እንዲሰማን፡፡ አዲስ ነገር እንድሞክር ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡

5ኛ. አለኝ የምትሉትን ነገር ዘርዝሩ

አይታችሁ ከሆነ ብዙዎቻችን ካለን ነገር ይልቅ የጎደለንን ማየት ይቀድመናል፡፡ ቆይ ይችን ነገር ብሞላት፣ እዛች ጋር ገቢ ባገኝ እኮ፣ ይችን እቃ ብገዛ፣ ይችን ባሟላ ደስ ይለኛል…. እንላለን፡፡ ግን ይሄ አለኝ፣ እንዲህ እኮ አለኝ አንልም፡፡ ሁልጊዜ ጉድለታችንን ነው የምናስበው፡፡ ልጁ በጣም አምርሮ እያለቀሰ ነው፡፡ ሰውዬው መጣና ‹‹አይዞህ! ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?›› አለው፡፡ ‹‹አጎቴ ሞተብኝ፤ ምን ላድርግ›› አለ፡፡ አይዞህ! አይዞህ! ይለዋል፡፡ አይ አጎቴ እኮ ሲሞት ያወረሰኝ ገንዘብ አለ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር አለ፡፡ ታዲያ ለምን ታዝናለህ አጎትህ እኮ ጥሩ ነገር አስቀምጦልሃል አለው፡፡ ቢሆንም የዛሬ ዓመት ደግሞ ሌላኛው አጎቴ ሞቶ ነበር አለ፡፡ ወይ! አይዞህ ለዛኛውም አጎትህ አይዞህ! አለው፡፡ ያኛውም አጎቴ ያስቀመጠልኝ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብብ እኮ አለ አለው፡፡ በጣም ደስ ይላል አንተ አጎቶችህ ጥለውልህ የሄዱት ነገር አለው ሰውዬው፡፡

አሁንም ግን ልጁ እያለቀሰ ነው፡፡ ለምን ታዲያ ታለቅሳለህ ሲለው የዛሬ ሁለት ዓመት ደግሞ ሌላኛው አጎቴ ሞቶ ነበር አለው፡፡ እንዴ! አለ ሰውዬው በመገረም። አዎ! እሱም ሲሞት ግን ያስቀመጠልኝ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብትና ንብረት ነበር አለው። ታዲያ አንተ ለምን ታዝናለህ? ሶስቱም አጎቶችህ ሲሞቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውረሰውህ ነው፡፡ ታዲያ አንተ ማዘን አለብህ? አለው፡፡ አሁንማ የሚያንገበግበኝ ሌላ የሚያወርሰኝ አጎት የሌለኝ መሆኑ ነው፡፡ ሶስቱ ሞተው አለቁ አለ፡፡

አስባችሁታል በሕይወታችን ብዙ የተሰጠንን አናይም፡፡ የጎደለን ምን አለ፣ ምን አነሰ፣ እጄ ላይ ምን ጎደለ፣ ምንድነው ቀዳዳው የምንለው። ምን ተደፈነ አንልም፡፡ ፈጣሪ ምን ሰጠኝ፣ ምን አደረገልኝ አንልም። ተስፋ አሳጣኝ፣ አነሰኝ፣ ጎደለኝ የምንለው ነገር ግን እጃችን ውስጥ ያለ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You