መጠጥ ቤት ውስጥ የተፈጠረ ጊዜያዊ ፀብ ያስከፈለው ዋጋ

ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር። ክረምቱ ከባተ አስረኛው ቀን ላይ ደርሷል፡፡ ክረምቱ ጫን ያለ ነበር። በወሩ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከፍተኛ የሆነ ነጎድጓዳማና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ እየዘነበ ስለሰነበተ ሰው ብርዱን ለማጥፋት መላዬ የሚለውን በሙሉ እየሞከረ ነው፡፡ ያለ የሌለ ልብስ ደራርቦ ወደ ጉዳዩ ጣደፍ ጣደፍ ከሚለው ሰው አንስቶ ከአልጋው መውጣት እስካቃተው ሰው ድረስ ሁሉም ከብርዱ አመልጥበታለሁ የሚለውን መላ በሙሉ ይሞክራል።

በየመንገዱ ዳር የተቀመጡት ሐምሌ በብዙ ነገሩ የክረምትን ውበትና ጣዕም የሚያሳየን ሰዎችም ይታያሉ፡፡ ክረምትን ተከትለው የሚመጡት ለመብል የሚውሉት እነ በቆሎ፣ በለስና ስኳር ድንች ወዘተ ብርዱ ላራቆተው ሆድ መሙያነት ያቀርባሉ። ሐምሌ ክረምት ለማሰላሰያ ዕድል የሚሰጥ ወርም ነው። ለገበሬው የምርት ጊዜ፤ ተማሪዎችና መምህራን ሌሎችም ባመዛኙ የሚያርፉበት በመሆኑ የጽሞና ጊዜን እንዲያሳልፉ ዕድል ይሰጣል። ክረምት ሥራ የሳጣቸው የግንባታ ሠራተኞችም እንዲሁ ቤት አካባቢ መታየታቸው የተለመደ ነው።

ወሩ ሰማዩ በደመና የሚሸፈንበት ለምድርም ዝናብ የሚዘጋጅበት ሣር በተራሮች ላይ የሚበቅልበት ለምለሙ ሁሉ ለሰው ልጆች ጥቅም የሚውልበት ነው ክረምት፡፡ በረዶውና ውሽንፍሩ ብርቱውም ዝናብ በምድር ላይ የሚወድቁበት ነው። ከመብሉም አልፎ ጠንካራ መጠጥንም ለብርዱ ማጥፊያ የሚጠቀሙትም አልታጡም።

የዛሬዎቹ ባለ ታሪኮቻችንም የከበደውን ክረምት ማምለጫ ከቅዝቃዜው መሸሻ ይሆናል ሲሉ አረቄ ቤት ተቀምጠው በጠንካራው አልኮል ብርዱን ሊያባረሩ የመረጡ ወጣቶች ናቸው። ለዚህ ታሪክ መነሻ ሃሳብ እንድናገኝ የተባበሩንን የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዝገብ ቤት ሠራተኞችን ከልብ እያመሰገንን ታሪኩን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

ምሽቱን መኮንን አረቄ ቤት

በነጩ የያዘው ዝናብ ክፍ ክፍ ሲል፤ ደግሞ ጠንከር፤ ደግሞ እንደማባራት ሲል ነው የዋለው። የክረምቱን ማየል ተከትሎ ረገብ ያለው የግንባታ ሥራ ሥራአጥ ያደረጋቸው ወጣቶች ቀኑን ሙሉ ተኝተው ውለው እኩለ ቀን ሲያልፍ ከቤት ይወጣሉ። ያገኟትን ቀማምሰው ምሽት ላይ የበረታውን ብርድ ለማባረር ብሎም ሰዓት ለማሳለፍ ብለው ከመኖሪያቸው አቅራቢያ የሚገኝ አረቄ ቤት ገቡ።

ጠበብ ያለችው አረቄ ቤት ከአፍ እስከ ገደፉ ሰው ሞልቶታል፡፡ የቤቱን ግድግዳ ተከትለው የተደረደሩት አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተጠባብቀው የተቀመጡት ጎረምሶች ብርዱን በትቅቅፋቸው የሚያባርሩ ይመስላሉ።

ከቤቱ መካከል ትርክክ ብሎ የተያያዘ የከሰለ ምድጃ ይታያል። ምድጃው ዳርና ዳር ተቀምጠው አጠገቡ በተቀመጠችው ልጅ እጅ እየተገላበጡ የሚጠበሱት በቆሎዎችን ተራቸውን እየጠበቁ እየከፈሉ ለሚወስዱት ጠጪዎች እየተዳረሱ ነው። የጠጪውን እጅ እየተመለከቱ ቶሎ ቶሎ የሚቀዱት ተፍ ተፍ የሚሉት ወጣት ሴቶችም ቤቱን ድምቀት አላበሰውታል። ከቤቷ አቅም በላይ የተለቀቀው ሙዚቃም የደጁን ብርድ ሙሉ በሙሉ እንዲረሱት አድርጓቸዋል።

ጠባቧ አረቄ ቤት ውስጥ የተቀቀለ ድንች፤ የተቀቀለ እንቁላል፤ ቆሎና ንፍሮ በመያዝ ወጣ ገባ የሚሉት ትንንሽ ልጆች በአረቄ ባዶውን የቀረ ሆዳቸውን ታገስ እያደረጉ መለስ ቀለስ ይላሉ።

ሥራ ስላልነበራቸው በጊዜ አረቄ ቤት ገብተው ብዙም ሳይመሽ ሞቅ ያላቸው ወጣቶች ያንንም ያንንም እያነሳሱ ይጨዋወታሉ፡፡ ይከራከራሉ ጠብ ላይ ደርሰውም መለስ በማለት ጨዋታውን ይቀይራሉ። የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሱ ከሚጨዋወቱት መካከልም ወጣቶቹ ሞገስ ይገዙን ምትኩ ይመር ይገኙበት ነበር። ወጣቶቹ ብዙም የጠበቀ ግንኙነት ባይኖራቸውም በተደጋጋሚ በመተያየታቸው የተነሳ የአንገት ሰላምታ ይለዋወጣሉ። እንኳን ለፀብ የሚያደርስ ቂም ሊኖራቸው ይቅርና ለፍቅር የሚሆንም ትውውቅ አልነበራቸውም።

የወጣቶቹ እሰጣ ገባ

ሰሞኑን ሥራ ማጣቱም፤ ወጪውም አመል ነሰቷቸዋል። የእለት እለት እየሰሩ የአለት እለቱን የሚኖሩት ወጣቶቸ ብዙም ሳይዘጋጁ ነበር ክረምቱ የደረሰባቸው። ያላቸውን አብቃቅተው ሥራ እስኪያገኙ ለመቆየት ግማሹን ቀን በመኝታ ነበር የሚያሳልፉት። ከዛም በቀን አንዴ በልተው አንድ ሁለት መለኪያ አረቄ እላዩ ላይ ደፍተው መልሰው ጥቅልል ማለት ልማዳቸው ነው።

የእለቱ ብርድ ከወትሮው ለየት ያለ ስለነበር ከተሟሟቀችው አረቄ ቤት መውጣት ያልፈለጉት ወጣቶች አንድ ሁለት እያሉ ደጋግመዋል። ጨዋታን ጨዋታ እያነሳ ስለ ብዙ ጉዳይ ሲያነሱ ቆይተው ሁለቱን የማያግባባቸው ጉዳይ መወራት ጀመሩ።

በንግግር አለመግባባት ውስጥ የገቡት ወጣቶች ጉዳዩን እንዳያከሩት ሌሎች ጣልቃ ቢገቡም ንግግሩ እየተሟሟቀ ከመጠጥ ጋር ተደምሮ አለመግባባታቸውን ከፍ አደረገው። ያን ጊዜ ቆመው ለመተናነቅ ሲዳዱ፤ ገላጋይ ሲይዛቸው ቆይቶ ድንገት አንደኛው እመር ብሎ አንዱ ላይ ተከመረበት።

ብርዱን ለመሸሽ ከገቡባት አረቄ ቤት ውስጥ ኃይለኛ ትርምስ ተነሳ። ከተጣላው ሰው ሌላ የተቀሩትን ሰዎች ጨምሮ ምትኩ ይመር የተባለው ሲሳደብ እና ሲዝት የተመለከተው ሞገስ ይገዙ የተባለው ወጣት «ተው እንዲህ አትበል» ሲለው ነበር ያልተሰበው ነገር የተከሰተው።

«ፀብህ ከእኔ ጋር ነው ሌሎቹን አትሳደብ» ብሎ የተናገረውን ሞገስ ይገዙን «አንተ ምናገባህ» በማለት ግብግብ ሲያያዙ ምትኩ በያዘው ቢላዋ በስለት ጀርባው ላይ በመውጋት በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ እንዲያልፍ ሆነ።

ያች በዘፈንና በጨዋታ ሞቃ የነበረችው አረቄ ቤት ደብልቅልቋ ወጣ። ያ ሳቅና ሁከታ በለቅሶና በዋይታ ተቀየረ። ያን ጊዜ በስካር የሰው ሕይወትን ያጠፋው ወጣት ትርምሱ ሰምተው በመጡ ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ዋለ።

ፖሊስ

የእለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩት ፖሊሶች ከብርዱ ጋር በመተናነቅ የአካባቢውን ፀጥታ ሊያስጠብቁ ወዲያ ወዲህ እያሉ ነበር። አካባቢውን እየጠበቁ የነበሩት ፖሊሶች ድንገት ሙዚቃና ሁከት ቀርቶ በለቅሶና በዋይታ ሲተካ ጉዳዩን ለማየት በፍጥነት በቦታው ደረሱ።

ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ጉርድ ሾላ ሰዓሊተ-ምህረት እየተባለ ከሚታወቀው አካባቢ መኮንን አረቄ ቤት ውስጥ ሲመለከቱ አንዱ ወጣት ጀርባው በደም ተለውሶ ተዘርግቷል። ሌላኛው ወጣት ደግሞ በእጁ ደም የተለወሰ ቢላዋ ይዞ ቆሞ ይመለከቱታል።

ወንጀል ሲሰራ ወዲያው ርምጃ መውሰድ ሥራቸው የሆነው ሕግ አስከባሪዎች ተጎጂውን ወደ ሆስፒታል በመላክ ጥቃት ያደረሰውን ወጣት ወደ ፖሊስ ጣቢያ አደረሱ።

ፖሊስ ወጣቶቹ የተጣሉበትን ጉዳይ በመመርመር፤ ከዓይን ምስክሮች ቃል በመቀበል፤ የሕክምና ማስረጃና የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል አንድ ላይ አድርጎ መረጃውን አደራጀቶ ጨረሰ። የተጠናከረውንም መረጃ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አቀረበ።

የአቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከሟች ጋር በተፈጠረ ወቅታዊ አለመግባባት ምክንያት በቢላዋ በመውጋት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርገሃል ባለው ተከሳሽ ላይ ክስ መሠረተ።

ይህን አሰቃቂ ድርጊት የፈፀመው ምትኩ ይመር የተባለው ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቧል።

በ 1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የግድያ ወንጀሎችን እንደ አገዳደል ባህሪያቸው ከባድ፣ ቀላል፣ ተራ እና በቸልተኝነት የሚፈጸሙ በማለት የደነገገ ሲሆን ተራ የሆነ ግድያ ማለት ከባድ ግድያ ሥር የተቀመጡ እንደ ሰውን ለመግደል አስቀድሞ ማሰብና መዘጋጀት፣ ያገዳደል ሁኔታው ላይ የታየ የተለየ ጨካኝነት እና አደገኛነት፣ ለመግደል የተጠቀመው መሳሪያ እና ዘዴ ከባድ የማያስብለው ያልሆነ እንዲሁም ቀላል ግድያን ለማቋቋም እንደተዘረዘረው በደም ፍላት ወይም ከመጠን ያለፈ ሕጋዊ መከላከል እና መሰል ከፊል ይቅርታ የሚሰጥ ያልሆነ በሁለቱ ስር የማይወድቅ ሲሆን የወንጀል ሕጋችን ተራ የሆነ የሰው ግድያ በማለት ያስቀምጠዋል መሆኑን ዐቃቤ ሕግ አብራርቷል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ጉርድ ሾላ ሰዓሊተ- ምህረት እየተባለ ከሚታወቀው አካባቢ መኮንን አረቄ ቤት ውስጥ ሟች ሞገስ ይገዙን በተፈጠረ ወቅታዊ አለመግባባት ተከሳሽ ሲሳደብ እና ሲዝት ሟች ተው እንዲህ አትበል ሲለው አንተ ምናገባህ በማለት ግብግብ ሲያያዙ ተከሳሽ በያዘው ቢላዋ በስለት ጀርባው ላይ በመውጋት በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ተራ ሰው መግደል ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል።

 ውሳኔ

 በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ የተከራከረ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቦ ክሱን በበቂ ሁኔታ ያስረዳ ሲሆን ፍርድ ቤቱ እንዲከላከል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት 2 የመከላከያ ምስክሮችን አቅርቦ ቢያሰማም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻሉ ተከሳሹ ይከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ነህ ብሎታል።

ፍርድ ቤቱም ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በተከሳሹ ላይ 3 የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውለት በእርከን 31 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ እና ለ3 ዓመት ከሕዝባዊ መብቶቹ ታግዶ እንዲቆይ ሲል ወስኖበታል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You