የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ይጀመራል

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ የ2016 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስቴድየም መካሄድ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በሊጉ 10 ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል። በውድድሩ የመጀመሪያ ቀንም አምስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ፡፡

ውድድሩ ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከ1ኛ-4ኛ ሳምንት ያሉት የሊጉ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ሊጉ ነገ ጠዋት ሶስት ጨዋታዎች ሲካሄዱ 2፡30 የመጀመሪያው ጨዋታ በመቻልና ኦሜድላ መካከል ይደረጋል፡፡ 3፡40 ላይ ከሶስት ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው መቐለ 70 እንደርታ ከፌዴራል ማረሚያ ይጨወታሉ፡፡ 4፡30 ፋሲል ከነማ ከሚዛን አማን ከተማ ይጫወታሉ፡፡ ከሰዓት ሁለት መረሀ ግብሮች የሚስተናገዱ ሲሆን ፤ ባህርዳር ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ 8፡00 እና ከምባታ ዱራሜ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጨዋታቸውን የሚያካሂዱ ክለቦች ይሆናሉ፡፡

ውድድሩ በየመሃሉ እረፍት እየወሰደ ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ ቀሪ መረሀ ግብሮች ተከናውነው የአራቱ ሳምንት ውድድር እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል። በፕሪሚየር ሊጉ 10 ክለቦች የሚያደርጉት ፍልሚያ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ለዚህም ክለቦችን በመደገፍ እና የተሻሻሉ ህጎችን ከማዘጋት አኳያ ፌዴሬሽኑ ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ቅድመ ዘግጅቶች በሚደረጉበት ወቅትም ከሀገራዊ ሁኔታው ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶች ማጋጠሙ ተጠቅሷል፡፡ አዲስ አበባ በሚደረገው ውድድርም 20 የሚደርሱ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ፣ የውድድሩን መጀመር አስመልክቶ ስለተደረገው ዝግጅት ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የሊጉ ውድድር ከተጀመረ ስምንት ዓመታትን ማስቆጠሩንና በርካታ እንቅፋቶችን በማለፍ እዚህ ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል። በዝግጅት ወቅት ብዙ ችግሮች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው፤ ከነዚህም ውስጥ የክለቦች የፋይናንስ ጉዳይ አንዱ እንደነበረ ገልፀዋል። ይሄን ችግር ለመፍታት ፌዴሬሽኑ ከየክለቦቹ አመራሮች ጋር በመነጋገር የፋይናንስ ችግራቸው እንዲፈታ በመደረጉ አስሩም ተሳታፊ ክለቦች ውድድራቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው ውድድር ላለፉት ሶስት ዓመታት በነበረው ጦርነት ምክንያት ከውድድር ርቆ የነበረው መቐለ 70 እንደርታ እጅ ኳስ ክለብ እንደሚሳተፍም አስረድተዋል።

የክለቦች መፍረስ ለፌዴሬሽኑ ዋነኛው ተግዳሮት እንደሆነና ለሊጉ መዘግየትም ምክንያት መሆኑን ያነሱት አቶ ሞላ፣ ይህም ክለብ ውስጥ በሚገኙት ባለሙያዎችና አሰልጣኖች መካከል በሚፈጠር ችግር ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም የኮልፌ ቃራኒዮ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ የአመራርና የፋይናንስ ችግር ሳይኖርበት በአሰራር ጉድለት አለመግባባት ተፈጥሮ ክለቡ ከውድድር ውጪ ሊሆንበት የሚችል እድል ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል። የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባደረጉት ጥረት ክለቡ ወደ ውድድሩ ሊመለስ እንደቻለ ታውቋል፡፡

የዘንድሮ ዓመት የክለቦች ፋይናንስ የተሻለ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሞላ፣ ክለቦች የውድድሩን ወጪ እራሳቸው እንዲሸፍኑ መደረጉንና እስከ አሁን ፌዴሬሽኑ የክለቦችን የውድድር ወጪ ሲሸፍን የነበረው የራሱ ገቢ ስለነበረውና ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ በቂ ስለነበር ነው ብለዋል። ከዚህ ቀደም ክለቦች ለውድድር ከ30-40 ፐርሰንት ብቻ የሚያወጡ ሲሆን ዘንድሮ 70 ፐርሰንት የውድድር ወጪን የሚሸፍኑ ይሆናል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት የሚያገኘው በጀት ትንሽ በመሆኑ ከክለቦች ጋር በመነጋገር የውድድሩን አብዘኛውን ወጪ እንዲሸፍኑ ሊደረግ ችሏል፡፡

ከስፖንሰርና ከመንግሥት በጀት በሚገኘው ገንዘብ የዘንድሮውን ውድድር ለማካሄድ ሙሉ ዝግጅት መደረጉ የተጠቆመ ሲሆን፣ ለውድድሩ አስፈላጊ የሆኑ ዳኞች ከየክልሉ ተመልምለው ውድድሩን የሚመሩ ኮሚሽነሮችም ተሰይመዋል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴውም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል፡፡

የመጀመሪያው ዙር አካል የሆነው የአራት ሳምንታት ውድድር እስከ ህዳር 20 ድረስ በወጣው መረሀ ግብር መሰረት ተካሂዶ ከተጠናቀቀ በኋላ የአንደኛ ዙር ማጠቃለያ ጨዋታዎች ከጥር 26 ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳሉ፡፡ በዚህም ከአምስተኛ እስከ 9ኛ ሳምንት ያሉት 25 ጨዋታዎች የሚካሄዱ ይሆናል፡፡

በውድድሩ ከስፖርተዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅድመ ዝግጀት ወቅት መሰረታዊና አዳዲስ የእጅ ኳስ ህጎችን ለክለብ ተወካዮችና አሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የስፖርታዊ ጨዋነትን ችግር በሚቀርፍ ሁኔታ በውድድር ወቅት ተጫዋቾች ህጎችን እንዲተዋወቁ የማድረግ ሥራ ይሰራል፡፡ በዚህም በውድድሩ የተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት፣ ፉክክርና በውድድሩ የሚያንጸባርቁ ወጣቶች ይታዩበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You