አሱሉህ – ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት

ባህል ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ እሴት ነው። የማኅበረሰቡንም ሆነ የግለሰቡን የኑሮ አቅጣጫ የሚቀረጽበትም መሆኑ ይገልፃል። የራሱ ባህል ያለው የራሱ ሥልጣኔ፣ ሀገር በቀል እውቀት፣ ሕግና ሥርዓት እንዳለውም ይታመናል።

ይህ እሴት ለአዳዲስ ፈጠራና ግኝቶች ምንጭና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ትብብር የመሠረት ድንጋይ እንደሆነ ይነገራል። የዕውቀት መገለጫና ማስተላለፊያ መንገድ በመሆን የነገን ተግዳሮቶች ለመቋቋም እንደሚጠቅምም፣ የማኅበረሰቡን ልማድ ለመጠበቅ እንደሚያስችልም የማኅበረሰብ ጥናት ዘርፍ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

የዘመናዊው ዓለም ሥልጣኔ፣ የኑሮ ዘይቤ፣ ሥርዓትና የሞራል ልዕልና ከቀደመው ጥንታዊ ባህል መሠረት ጋር ትስስር እንዳለውም እነዚሁ ተመራማሪዎች ያመለክታሉ። የሰው ልጅ ከአያት ቅድመ አያቶቹ የሥነ ምግባር፣ የሃይማኖት፣ ማህበራዊ ትስስር እና ሌሎችም መስተጋብሮችን እንደሚወርስ ይሄም ባህል አሊያም የተወረሰ ማንነት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የባህልና የትምህርት ድርጅት (ዮኔስኮ) ባህልን በተመለከተ የሚከተለውን ትርጓሜ ያስቀምጣል፤ ባህል አንድ ኅብረተሰብ ወይም የማኅበረሰብ ቡድን ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበትን መንፈሳዊ፣ ቁሳዊና ስሜታዊ ባህርያት ከነሁለንተናዊ ምሉዕነታቸው ያካትታል። ባህል ሥነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍን የአኗኗር ዘይቤን፣ ዕሴቶችን፣ እምነትና ልማዶችን ጭምር የሚይዝ ነው። እንዲሁም ባህል ከአካባቢያዊ ሁነቶች ሰው ሠራሽ ክፍሉ ሲሆን አንድ ሰው በአጠቃላይ በማኅበረሰብ አባልነቱ የሚያገኘው ባህሪ እውቀትና ክህሎት ነው።

በኢትዮጵያ ያሉትን እሴቶች ዩኔስኮ ባስቀመጠው ትርጓሜና መስፈርት መሠረት ብንመለከታቸው እንኳን እጅግ በርካታ ባህላዊ ሀብቶችን ማግኘት እንችላለን። ኢትዮጵያ ውብ ድብልቅ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት ምድር ነች። እነዚህን ሕዝቦች ከቀሪው ዓለም የሚለያቸው በርካታ ባህላዊ እሴቶች በመያዛቸው፤ ከራስ ማንነት የሚቀዱ ብዝሀ እሴቶችን በማካተታቸው ጭምር ነው።

የኢትዮጵያን ምድር የረገጠና አስተውሎ ለመረዳት የሞከረ ሁሉ በሕዝቦች ሕብረት፣ አመጋገብ፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል፣ የቋንቋ፣ የአለባበስና የተለያዩ የሃዘን፣ የደስታ ሥርዓቶቻቸው ሳይደመም አያልፍም። ከሁሉም በላይ ግን እጅግ ማራኪና በሌላ ሀገር የማያገኛቸው አስደናቂ እሴቶች እንደሆኑ መረዳት ይችላል። የጎዳና ፌስቲቫሎች እና ሌሎችም ልዩ ልዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻችን የተመለከተ የሀገሪቱን ሕዝቦች ቁልጭ አድርጎ የሚያሳዩ መሆናቸውን ይገነዘባል። እነዚህን ሀብቶቻችንን ከበርካታ ሺ ዘመናት በላይ ማኅበረሰቡ ሳይበረዙና ሳይጠፉ ጠብቆ ለአዲሱና መጪው ትውልድ ማስተላለፍ ተችሏል።

ከዚህ መነሻ የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው ሀገረኛ አምድ ላይ ከብዝሀ እሴቶች ውስጥ አንዱን በመምዘዝ ርዕሰ ጉዳይ ለማድረግ ፈልጓል። በዚህም በኢትዮጵያ ወደ ሰሜን ምዕራብ ክፍል በማቅናት የቤኒሻንጉል ጉምዝ (የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች) ላይ በማተኮር ሀገር በቀል እውቀትን ልናስቃኛችሁ ወድደናል። ብሔረሰቡ በርካታ ባህላዊ እሴቶችና ሀብቶች ባለቤት ከመሆኑ አንፃር ሁሉንም ዘርፎች መንካት ባለመቻላችንም ወሰናችንን በመገደብ ባህላዊ የእርቅ (ሽምግልና) ሥርዓቱ ላይ ብቻ ልናተኩር ተገድደናል። በቀጣይ ጊዜያትም በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች የብሔረሰቡን ሀብቶች የምናስተዋውቅ ይሆናል።

አቶ ሽመልስ አድሬ የባህልና ቱሪዝም ቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የቤኒሻንጉል ጉምዝ በርካታ የባህላዊ ሀብቶችን የያዘ ነው። ከእነዚህ ውስጥም ከነባር ማኅበረሰቦች ውስጥ አንዱ የሆነው የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ባህላዊ የእርቅ ሥርዓት አንዱ ነው።

ዳይሬክተሩ የክልሉን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያስጠናውን (የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች) ጥናታዊ ጽሑፍ መሠረት በማድረግ እንደሚናገሩት፤ በቤኒሻንጉል ማኅበረሰቡ ዘንድ በተለያዩ አጋጣሚዎች ግጭት ቢነሳና ግለሰቦች ጠብ ውስጥ ቢገቡ ባህላዊ የሽምግልና ወይም የእርቅ ሥርዓት / አሱሉህ – ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት/ መሠረት ግጭቱን ይፈታል።

ስለ ባህላዊ ዳኝነቱና ባህላዊ የፍትህ ሥርዓት ምንነት የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ መደበኛ ያልሆኑ የፍትሕ አካላት የሚባሉት ባህላዊ ሕጎችን፣ ኃይማኖታዊ ሕጎችን እና የፍትሕ ተቋማትን እንዲሁም ከመደበኛው የፍትህ አካላት ውጭ ያሉ አማራጭ የክርክር መፍቻ መንገዶችን የሚያጠቃልል መሆኑን ይገልፃሉ።

መደበኛ ያልሆኑት የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ የፍትህ አካላት እና ደንቦቻቸው በአብዛኛው ከማኅበረሰቡ ባህል፣ አኗኗር ወይም ኃይማኖት የሚመነጩ መሆናቸውን የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ ሕጎች ከአጠቃላይ ማህበራዊ እና ኃይማኖታዊ ዕሴቶች ጋር ተቆራኝተው የተፈጠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከባህላዊ ዳኝነት ሥርዓት ጋር ቁርኝት ያላቸው ማህበራዊ እሴቶች ከማኅበረሰቡ እምነት፣ ባህል፣ ሞራል እና ኃይማኖት የሚመነጩ ናቸው በማለት የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ ማኅበራዊ እሴቶች እውነት ስለመናገር፣ በሰላም አብሮ ስለመኖርና ግጭት ሲከሰት ፈጥኖ ስለመፍታት አስፈላጊነት የሚያስገነዝቡ እንደሆኑ ያስረዳሉ። ከባህል የሚመነጩት ከግለሰብ አስተያየት አልፈው በኅብረተሰብ ውስጥ ገንነው የሚገኙ፣ በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ እንደሁኔታው እውነት ወይም ሀሰት ትክክል ወይም ስህተት ስለሚባሉ ጉዳዮች አባላቱ ጥብቅ እምነቶች ናቸው። ከኃይማኖት የሚመነጩት፣ በኃይማኖት መጽሐፍት የተጻፉትን እና በሀገረሰብ እምነቶች ውስጥ በቃል የሚተላለፉትን የሚመለከት ነው።

የባህላዊ ዳኝነቱ ፋይዳ

የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ባህላዊ ዳኝነትና የግጭት አፈታት ብዙ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉት ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። ይህ ባህላዊ ዳኝነትና የግጭት አፈታት ዘዴው ከኅብረተሰቡ በተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች የሚደረግ የእርቅና የግጭት አፈታት ሥርዓት በመሆኑ በገንዘብ የማይተመን ፋይዳ አለው።

በዳዩ ጥፋቱን አምኖ ተበዳዩን ይቅርታ እንዲጠይቅና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል በማድረግ ሁለቱም ወገኖች ሁለተኛ በጠላትነት እንዳይተያዩ በመሃላ በማስታረቅ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ያስረዳሉ። እርቅ ከተደረገ በኋላ በጠላትነት መተያየትና ብቀላ ማሰብ እርግማን ያስከትላል ብለው ስለሚያምኑ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ኑሯቸው ይመለሳሉ።

በዘመናዊ የፍትህ ሥርዓት አጥፊው ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ከመስጠት ውጭ ግለሰቦቹ ከፍርዱ በኋላ እንዴት ሆነው በሰላም አብሮ መኖር እንዳለባቸው ስለማይሰራ ብዙ ክፍተት ሊፈጥር ይችላል የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ከፍርድ በኋላ በዳይና ተበዳይ ለዳግም ጥፋት እንዳይፈላለጉና በፍፁም ቅንነት አብረው መኖር እንዲችሉ የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ባህላዊ የእርቅና የዳኝነት ሥርዓት ልክ እንደ ሌሎቹ ባህላዊ ሥርዓቶች ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው የዳኝነት ሥርዓት ነው ብለዋል።

አሱሉህ – ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት

ግጭቶች በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያትና ምክንያቶች ይከሰታል የሚሉት የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ፤ ማንኛውም ብሔረሰብ ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት በዘመናዊ የሕግ ሥርዓት ከመዳኘት ባለፈ እንደ ግጭቱ ዓይነት ወይም እንደ ወንጀሉ ክብደትና ቅለት በሀገር ሽማግሌዎች ወይም በባህላዊ ሽምግልና በእርቅ እንደሚፈፅም ያስረዳሉ። የቤኒሻንጉል ብሔረሰብም አሱሉህ የሚባል ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት እንዳለው ይገልፃሉ። ይህ ባህላዊ ሥርዓት በሚከተለው መንገድ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መፍትሔ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

በቤኒሻንጉሎች ዘንድ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ወይም እንደ ወንጀሉ ደረጃ ወንጀለቹን ቀላልና ከባድ በማለት ይከፈሏቸዋል። በዚህም ረገድ በአብዛኛው በዳይ ወደ ተበዳይ ቤተሰቦች ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሽማግሌዎችን በመላክ ‘አስታርቁኝ’ የሚል መልእክት በመላክ የእርቁ ሥነ ሥርዓትና የባህላዊው ዳኝነት ሂደት እንዲጀምር የሚደረግበት ባህላዊ ሂደት ይጀመራል።

በቤኒሻንጉል ማኅበረሰብ ባህል ‘አልታረቅም’ ብሎ ማመጽ የተወገዘ ነው። የችግሩ ስፋት ወይም ክብደት ቢለያይም አጥፊው አካል ‘በድያለሁና አስታርቁኝ’ ብሎ ሽማግሌ ከላከ እርቁን መቃወም የተከለከለ ነው። ሽማግሌዎች ሲመረጡም ከሁለቱ ወገን ማለትም ከበዳዩና ከተበዳዩ አካላት ይሆናሉ። ሽማግሌዎቹ በመሰባሰብ የሁለቱንም ሃሳብ ከተቀበሉ በኋላ የወንጀሉ ክብደት እስከ መገዳደል የሚያደርስ ቢሆንም ‘በቃ ጥፋቱ አንዴ ተፈጽሟል ስለዚህ አንዴ የሆነ ነገር ሊመለስ ስለማይችል ለአላህ ብላችሁ ይቅር ተባባሉ’ በማለት ተበዳዮችን በፈጣሪያቸው ስም ይጠይቃሉ። ይማጸናሉ። ሁለቱ አካላት ከተስማሙ ወደ እርቅ ሂደት ይገባሉ።

የእርቅ ሂደት

የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ በሰዎች መካከል በሚፈጠረው ግጭት ምክንያት የሰው ሕይወት ቢያልፍ በሀገር ሽማግሌ በኩል እርቅ ይደረጋል። የእርቁ ሂደት የሚጀመረው ከገዳዩ ቤተሰብ በኩል ነው። ከሁለቱ ቤተሰቦች አስታራቂ የሀገር ሽማግሌዎች ይመረጣሉ። የገዳይ ቤተሰቦች ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችን በማስተባበር ወደ ተበዳይ ቤት ሄደው እንዲያስታርቋቸው የእርቅ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ያደርጋሉ። በጥያቄው መሠረት የሀገር ሽማግሌዎቹ ጥያቄውን ተቀብለው በማግስቱ ወደ ተበዳይ ቤተሰብ በመሄድ የማስታረቅ ሂደቱን ይጀምራሉ።

በቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ባህል መሠረት እርቅ ተጠይቆ እምቢ አሻፈረኝ ማለት የማይታሰብ የባህል ጥሰት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በበዳዩ በኩል የተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች ወደ ተበዳዮ ቤተሰብ ሄደው ‘የሰው ሕይወት በድንገት በእጃችን ጠፍቷልና የሀገር ሽማግሌዎችን ውሳኔ ተቀብለን ማንኛውንም ካሳ እንከፍላለን’ በማለት ይጠይቃሉ። ሌሎች አስታራቂ ሽማግሌዎች ደግሞ ‘ገዳዩ ለሟች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ እንጂ ገደለም አልገደለም ሞት አይቀርም፤ ይሄ የአላህ ፈቃድ ነው፤ አላህ ወደራሱ ወሰደ’ በማለት የማስታረቂያ ሃሳብ ያቀርባሉ።

የሟች ቤተሰብ ከተቀበለ እንደ ከዚህ በፊቱ በሰላም አብሮ እንዲኖሩ በመማጸንና የተለያዩ ባህላዊ የማስታረቂያ ግፊቶችን በማድረግ ያስታርቃሉ።

በቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ማንኛውም ወንጀል ተፈጽሞ በሀገር ሽማግሌ እርቅ የሚደረገው በሁለት መልኩ ሲሆን፤ አንደኛው የገዳይ ቤተሰብ ለሟች ቤተሰብ ካሳ እንዲከፍል በማድረግ ነው። ሁለተኛው በይቅርታ የሚታለፍ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ዘንድ የሟች ቤተሰብ ካሳ አይወስድም። ካሳ የሚወስድ ከሆነ ለሟች ቤተሰብ ወይም ልጆች መጠነኛ ካሳ እንዲከፈል ይደረጋል። አስታራቂ የሀገር ሽማግሌዎች “የቻላችሁትን ያህል ካሳ ክፈሉ” ይላሉ። የሟች ቤተሰብ “የደም ካሳ አልወስድም” ካለ የካሳ ክፍያው ይቀራል ማለት ነው።

ስህተት መፈጸማችሁን አምናችሁ፤ የሀገር ሽማግሌ ልካችሁ ለመታረቅ መምጣችሁ ጥሩ ነው። “እኛ የደም ካሳ አንበላም፤ ይቅር ብለናል፤ አፉ ብለናችኋል” ይላሉ። “ከእንግዲህ ታርቀናል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ ግንኙነታችን አጠናክረን እንኖራለን” በማለት በይቅርታ፣ በምህረትና በአክብሮት ይነጋገራሉ። በቤኒሻንጉል ብሔረሰብ በሟቹ ምትክ ሰው መሞት አለበት፣ ደም መፍሰስ አለበት የሚል የብቀላ አስተሳስብ የለም።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You