የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን ለ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የማጣሪያ ውድድር ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ዝግጅቱን ከጀመረ አንድ ሳምንት የሞላው ሲሆን አጭር የመዘጋጃ ጊዜ እንዳለው ተገልጿል፡፡
በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ አፍሪካን በወርልድ ቴኳንዶ የሚወክል ሀገር ለመለየት የማጣሪያ ውድድር ከአንድ ወር ከግማሽ በኋላ በሴኔጋል ዳካር የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያም የማጣሪያ ውድድሯን ታከናውናለች። ለዚህም የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ተከናውኖ ጠንካራ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያን በማጣሪያ ውድድሩ የሚወክለው ቡድን 6 ወንድና 4 ሴቶችን አካቶ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ሲሆን፣ አካል ብቃትና ሌሎች ቴክኒኮችን ያካተተ ልምምድ በማድረግ ለማጣሪያ ውድድሩ ብቁ ለመሆን እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል። ቡድኑ ዝግጅቱን ሲጨርስ ሁለት ወንዶችንና ሁለት ሴቶችን በኦሎምፒክ ማጣሪያ ውድድሩ የሚያሳተፍ ሲሆን፣ በዝግጅት ወቅት የተሻለ ብቃት የሚያሳዩ አትሌቶች ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። የተቀሩት ስፖርተኞች ደግሞ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉ በመሆኑ ዝግጅቱም ሁለቱን ውድድሮች ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ በአሰልጣኝ ማስተር አዲስ ኡርጌሳ የሚመራ ሲሆን አራት ረዳት አሰልጣኞችን አካቶ ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከሶስት ወራት በፊት ለአፍሪካ ቻምፒዮና የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ተደርጎ ውድድሩ በመራዘሙ ቡድኑ የጀመረውን ዝግጅት አቋርጦ ከተበተነ በኋላ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት አዲስ ብሔራዊ ቡድን እንደተመረጠ ተጠቁሟል፡፡ የቡድኑ አባላት ልምምዳቸውን በተጠበበ ጊዜ በከፍተኛ ተነሳሽነትና ጥረት እያደረጉ ሲሆን በውድድሩ ውጤት አስመዝግቦ ኢትዮጵያን ዳግም በኦሊምፒክ ለመወከል እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡
ቡድኑ በማጣሪያው ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥረት እያደረገ መሆኑን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ማስተር አዲስ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ መድረክ መወከል የቻሉ ስፖርተኞች ጥሪ ቢደረግላቸውም ቡድኑን እንዳልተቀላቀሉና ቡዱኑ አዳዲስና ልምድ የሌላቸው ስፖርተኞች ይዞ እየተዘጋጀ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አንጻር የሌሎች ሀገራት አትሌቶች ከፍተኛ ልምድና ተደጋጋሚ የውድድር መድረኮችን የሚያገኙ በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር ሊገጥማቸው እንደሚችልም አሰልጣኙ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አሰልጣኙ ገለፃ፣ ለዝግጅት የተሰጠው ጊዜ በጣም አጭርና የተጣበበ መሆኑ በቂ ዝግጅት እንዳይኖርና ስፖርተኞቹ ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል። ‹‹ለኦሎምፒክ ለማለፍ የአራት ዓመት ዝግጅትን የሚጠይቅ ነው፡፡›› ያሉት አሰልጣኙ በዚህም ምክንያት በአንድ ወር ተኩል ዝግጅት አራት ዓመት ከተዘጋጁ ሀገራት ጋር እንደሚወዳደሩ ጠቁመዋል፡፡ በ2020 ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ መሳተፏን ያስታወሱት አሰልጣኙ በዚያን ወቅት አራት ዓመት ሙሉ ዝግጀት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
የክለቦች አለመኖር ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ጫና መፍጠሩን የጠቀሱት አሰልጣኙ፣ ክለቦች መቋቋም ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ክለቦች የሚቋሙ ከሆነ ስፖርተኞችን በብቃታቸው ደረጃ እንዲገኙ ስለሚያደርግ በአጭር ጊዜ ብሔራዊ ቡድን ለማዘጋጀት ችግር እንደማይሆንም አክለዋል።
የስፖርተኞቹን የአካል፣ የቴክኒክና የታክቲክ ደረጃን በአንድ ወር ተኩል ውስጥ አዘጋጅቶ አራት ዓመት ከሚዘጋጁ ስፖርተኞች ጋር ማወዳደር እንደሚያስቸግርም ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ ሌሎች ሀገራትን አትሌቶች በቅርበት እንደተመለከቱና ጠንካሮች መሆናቸውን ገልፀው፤ በዝግጅቱ አትሌቶቹ ላይ ጫና በመፍጠር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ነባር ስፖርተኞች ቡድኑን ባለመቀላቀላቸው ምንም የውድድር ልምድ በሌላቸው ስፖርተኞች ቡድኑን እንደ አዲስ እየሰሩ እንደሚገኙ ነው የገለፁት፡፡
ይሁን እንጂ በቡድኑ ውስጥ የተካተቱት ስፖርተኞች ከልምድ ማነስ በስተቀር ጥሩ ብቃት እንዳላቸውና በፍላጎት ልምምዳቸውን እየሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ስፖርቱ ድግምግሞሽ የሚፈልግ በመሆኑ ጉዳት በማስከተል ስፖርተኞቹ በትክክል እንዳይሰሩ ስለሚያደረግ ረጅም ጊዜ መሠራት እንደሚኖርበትም ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም እንዳይጎዱ የሥልጠናውን ጫና በጥንቃቄ በመቆጣጠር እየተጓዙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የቡድኑ አባል ጌትነት አጥናፉ ለብሔራዊ ቡድኑ በመመረጡ እንደተደሰተና የሚሰጠው ሥልጠናም ጥሩ መሆኑን ጠቁሞ፣ ከአቅማቸው በላይ በተገቢው ሁኔታ እየሰሩ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የዝግጅት ጊዜው ቢያንስም አሰልጣኙ በሚሰጣቸው ሥልጠና በደንብ ተዘጋጅተው ውጤት ለማምጣት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጿል፡፡ በውድድሩ ልምድ ባይኖራቸውም ሁሉም በጉጉትና በመረዳዳት መንፈስ እየሰሩ እንደሆነም ይናገራል፡፡ ውጤት ለማምጣትና ልምድ ለማካበት እንደሚረዳቸውም አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ሌላኛዋ ቡድኑ አባል መስከረም ዘመድኩን አሰልጣኙ በሚሰጣቸው ሥልጠና ዝግጁታቸውን በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ መሆኑን ጠቁማለች፡፡ ሥልጠናውን ከጀመሩ በኋላም ብዙ ቴክኒኮችን እየለመዱ በመሆኑ ችሎታቸውን እያሻሻሉ እንደሚገኙ አስረድታለች፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም