ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት

የአምራች ኢንተርፕራይዞች ችግሮች እንዲቃለሉና ኢንተርፕራይዞቹ በመዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ሂደት የሚኖራቸው ሚና እንዲያድግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲኖራቸውና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ የሚከናወኑት ተግባራት ከእነዚህ ጥረቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የዚህ ጥረት አካል የሆነና ‹‹የእኛ ምርት›› የተሰኘ፣ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ለማነቃቃት ያለመ ሀገራዊ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት፣ እኛም እንሸምት›› በሚል መሪ ቃል ከታኅሣሥ ሦስት እስከ ሰባት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከ85 በላይ አምራች ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን የመሸጥና የማስተዋወቅ እንዲሁም በጋራ መሥራት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች የማድረግ ተግባራትን አከናውነዋል፤ የዘርፉን እንቅስቃሴ በተመለከተ በተዘጋጁ የፓናል ውይይቶች ላይም ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሤ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ በምርት አቅርቦትና ትውውቅ፣ በገበያ ትስስር እና በልምድ ልውውጥ ረገድ ትልቅ ፋይዳ አለው። ኤግዚቢሽኑ ከ85 በላይ አምራች ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበትና ከ50ሺ በላይ ጎብኚዎች የጎበኙት ትልቅ መድረክ በመሆኑ አምራች ኢንተርፕራይዞችንና ሸማቾችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡

የአምራች ኢንተርፕራይዞችን የተወዳዳሪነት አቅም ለማሳደግ የገበያ እድሎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግና፣ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ኢንተርፕራይዞች የገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን የሚጠቁሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የእኛ ምርት›› ኤግዚቢሽንና ባዛር የኢንተርፕራይዞችን ምርቶች ለማስተዋወቅ፣ የሀገር ውስጥ የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠር፣ የእርስ በእርስ ትውውቅና የልምድ ልውውጥን ለማጠናከር እንዲሁም የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል እንደሚያስችል ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ኤግዚቢሽኑ አምራቾች ጥራቱን የጠበቀና በዋጋም ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲያቀርቡ እና ኅብረተሰቡም የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ያግዛል፡፡ ኢንተርፕራይዞች ከምርት ሽያጭ በተጨማሪ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና በትብብር እንዲሰሩ ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዘርፉ ልማት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ያሳያል›› በማለት ስለኤግዚቢሽኑ ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎች ያስረዳሉ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት፣ የአምራች ዘርፉን አፈፃፀም በማሻሻል ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት፣ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ፣ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ በተሰጠው ትኩረት በዘርፉ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ለማቋቋምና ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት የኢንተርፕራይዞችን ቁጥር ከ26 ሺ በላይ ማድረስና ከ570ሺ በላይ የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህም በየዓመቱ ከ100ሺ በላይ የሥራ እድል እየተፈጠረ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም ባለፉት አምስት ዓመታት የዘርፉን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከ15 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለሥራ ማስኬጃ እንዲሁም ከ14 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ ለማምረቻ መሳሪያ ብድር አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም ለዘርፉ በየዓመቱ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደቀረበ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፉን እንዲመራና እንዲደግፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 526/2015 በአዲስ መልክ መቋቋሙን ያስታወሱት አለባቸው (ዶ/ር)፤ የዘርፉን ፍኖተ ካርታ፣ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎች፣ የድጋፍ ማዕቀፎች፣ የአሰራር መመሪያዎችና ማኑዋሎችን በአዲስ መልክ ተዘጋጅተው እንዲቀርቡና ጥቅም ላይ እንዲውሉ፤ ከዚህ ቀደም የነበሩትም እንዲሻሻሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡ ዜጎች በአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ ወሳኝ የሆኑ ድጋፎችን በማመቻቸትና እድሎችን በመፍጠር የተሻለ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ አሰራር ሥርዓቶች እንዲዘረጉ የጀመረውን መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው እንዳሉት፤ መድረኩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መሠረት በማስፋት ጠንካራና ዘላቂ እድገት እንዲኖር በማስቻል ሂደት የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ ይረዳል፡፡ አምራቾችን ከሸማቾችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ለማቀራረብ የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት እና የሀገሪቱ ምርት የደረሰበትን የጥራት ደረጃ በማሳየት የገዢዎችን የመግዛት ፍላጎት ለማሳደግ ያስችላል፡፡

በተጨማሪም አላስፈላጊ የገበያ ተዋናዮችን ከግብይት ሰንሰለቱ በማስወጣትና ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ ለአምራቾች አስተማማኝ ገበያ ለመፍጠር ይህንንም ተከትሎ የሥራ እድል በመፍጠር፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በመሳብና ነባሮችን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ በተለይም ሀገራችን በወጪ ምርት ላይ ያላትን ጥገኝነት በሂደት በመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው፣ የዜጎችን በሀገራቸው ምርት የመጠቀም ባህልም በእጅጉ እንደሚያሳደግ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር መነሻነት የአሥር ዓመት የልማት እቅድ ነድፎ ለአምስቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች (ግብርና፣ ማምረቻ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘላቂና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ መላኩ፣ በዚህም አምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይገልፃሉ፤ የአምራች የዘርፉን ማነቆዎች ለማቃለል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንና አበረታች ውጤቶች ስለመመዝገባቸውም ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ የዘርፉ የፖሊሲ አቅጣጫ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቷል፡፡ ፖሊሲውን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከእነዚህ ስትራቴጂዎች መካከል የቆዳ ልማት፣ የአቅም ግንባታ፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ተግባርን የሚመራበት የተኪ ምርት እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የአመለካከት ክፍተት የሚሞላ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ተጨማሪ ስትራቴጂዎችም እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

ስትራቴጂዎቹና መመሪያዎቹ የአሰራር ማነቆዎችን ለመፍታት የተዘጋጁ የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ማዕቀፎች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ዘርፍ ምን ዓይነት መመሪያ እንደሚያስፈልገው የመለየት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ እነዚህ ስትራቴጂዎች ‹አሁን ያሉትን ችግሮች በጥናት ላይ በመመስረት መፍታት ካልተቻለ፣ ዘርፉ ሙሉ በሙሉ መውደቁ አይቀርም› በሚል መነሻ የተዘጋጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ስትራቴጂዎቹን የመጠቀም/ ያለመጠቀም/ ጉዳይ የአምራች ዘርፉን አፈፃፀም የማሻሻል/ ያለማሻሻል/ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበው፣ ለዘርፉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ስትራቴጂዎችን በሙሉ አቅም መተግበር እንደሚገባም ይገልፃሉ፡፡

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ በዘርፉ የሚስተዋለውን የቅንጅት ችግር ለመፍታት የሌሎች ሀገራትን ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም የኢትዮጵያን የወደፊት ራዕይ መሠረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ተጀምሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገብ ተጀምሯል፡፡ በተለይም ከአምስት ዓመታት በላይ ሥራ አቁመው የነበሩና በ10ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉ፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ከማቋቋም ያላነሰ ስኬት የተገኘበት የንቅናቄው ሥራ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ከ370 በላይ የሚሆኑ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በዓመት ከሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውና ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል፤ ይህም ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ፈጥሯል፣ አዳዲስ አምራቾች ሥራ እንዲጀምሩ አስችሏል፡፡

ቀደም ሲል ለአምራች ኢንዱስትሪው ይቀርብ የነበረው የብድር መጠን (12 በመቶ) ወደ 24 በመቶ ከፍ እንዲል ተወስኗል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ውስጥ አምራቾች ግብዓት ሊያቀርቡ የሚችሉ የውጭ ባለሃብቶች እስከ 100 በመቶ የግብዓት ትስስር እንዲፈጥሩና አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን እንዲደግፉ ተፈቅዷል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ እንዲጨምር የሚያስችሉ መመሪያዎች ተተግብረዋል፡፡ የሀገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ትስስር እንዳያጋጥማቸው የመንግሥት ተቋማት ከሀገር ውስጥ አምራቾች ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ልዩ የግዢ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ለውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ምቹ ያልሆኑ መመሪያዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ ለዘርፉ እድገት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ በየደረጃው የሚገኝ አመራር ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ማድረግ ተችሏል፡፡

እንደ አቶ መላኩ ማብራሪያ፣ አምራች ዘርፉ በሚቀጥሉት ዓመታት ገቢ ምርቶችን በመተካት ቀደም ሲል ከነበረበት 30 በመቶ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ወደ 65 በመቶ እንዲሁም በኤክስፖርት ረገድ አሁን ካለበት ዝቅተኛ አፈፃፀም (በዓመት የ400 ሚሊዮን ዶላር) ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር እንዲያድግ ይጠበቃል፡፡ በሥራ ፈጠራ ረገድ በዘርፉ ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የማምረት አቅም አጠቃቀምን አሁን ካለበት ወደ 85 በመቶ እንዲያድግ ትልቅ ግብ ተጥሏል፡፡

‹‹እነዚህና ሌሎች በዘርፉ የተያዙ እቅዶችን ማሳካት ሀገራዊ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ ማስቻል በመሆኑ፣ ግቦቹን ለማሳካት የተለየ መንገድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ዘርፉ ሰፊ እድሎች ያሉትና ከተሰራበት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያመለከተ አፈፃፀም ውጤት የታየበት ቢሆንም በቀጣይ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮችም አሉ›› የሚሉት አቶ መላኩ፤ የመንግሥት መዋቅር አገልግሎት አሰጣጥን መሻሻል፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን መፍታት እና የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ማሻሻል እንደሚገባ በትኩረት ያሳስባሉ፡፡

እሳቸው እንደሚገልጹት፣ የአገልግሎት ጥራት ማነስ የኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት የሚጎዳ ስለሆነ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በየደረጃው ያሉትን የቅልጥፍና ችግሮች ማሻሻልና በዘላቂነት መፍታት ይገባል፡፡

አምራች ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ ፍላጎት ያለው በመሆኑ፣ በተደራሽነትና በዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በተለይ ንግድ ባንኮች በዚህ በኩል ብዙ ክፍተቶች ስለሚታዩባቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ያለባቸውን የፋይናንስ ችግር የሚያቃልል አቅጣጫ መከተል አለባቸው፡፡

የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን በጠንካራ ትስስር መፍታት ይገባል፡፡ ኢንዱስትሪዎች በልዩ ሁኔታ ኤሌክትሪክ፣ ቦታ፣ ውሃ፣ መንገድ፣ ሎጂስቲክስና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ስለሚፈልጉ የእነዚህን አገልግሎቶች እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የሁሉም የመንግሥት አካላት ቁርጠኝነትና ትብብር አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም እንደሀገር የተጀመረውን ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የበለጠ ውጤታማ ማድረግና የተቋቋሙ ክላስተሮችን ማጠናከር አስፈላጊ ስለሆነ ሁሉም ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

የ‹‹ኮልባ›› ቆዳ ፋብሪካ የምርት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ሽፈራው፣ መሰል መድረኮች ለገበያ ትስስር አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ይናገራሉ። ‹‹ኢግዚቢሽኑና ባዛሩ ገበያ እንድናገኝ ይረዳናል፡፡ የሸማቹን ፍላጎት ለመረዳት እና የሌሎች አምራቾችን ሥራ ለመመልከት ያግዛል›› ይላሉ፡፡

የመንግሥት ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ ሀብታሙ፣ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንዳለ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የቆዳ ፋብሪዎች ብዙ ኬሚካሎችንና ማሽኖችን ይፈልጋሉ፤ ኬሚካሎችንና ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች እየተዳከሙ ያሉት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም፣ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራትን ለማስጠበቅ ብዙ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው አቶ ሀብታሙ አመልክተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን በኩል ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሊሰራ ይገባል። የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራትን ማሻሻል የኤክስፖርት ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል››፡፡ ያሉት አቶ ሀብታሙ ‹‹የቆዳ ፋብሪካዎችን እንደ በካይ ተቋም መቁጠር ተገቢ አይደለም›› ሲሉ አስገንዝበው፣ ፋብሪካዎቹ የፅዳት አጋርና መሳሪያ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ቆዳ ፋብሪካዎች ባይኖሩ ያ ሁሉ ከብት ታርዶ ቆዳ ተሰብስቦ የት ይደረግ ነበር?›› ብለዋል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You