ተልዕኮ ቆስጠንበር

በፈንጂ ወረዳ ውስጥ ሴራና ገፀ ባህሪያቱ በምናባዊ ፈጠራ የተሽሞነሞኑ ቢሆንም፤በእውነታ ላይ ተመርኩዞ የተጻፈ ስለመሆኑ ለውድ አንባቢያን ለማስገንዘብ እወዳለሁ።

የተጠመደች፤የፈነዳችና ገና የምትፈነዳ…አምካኝና ጠማጅ የሚፈራረቁባት ወጣት ፍንዳታ። ጠምደው ካጠመዷት ሥፍራዎች መሃከል አንደኛው በቆስጠንበር እምብርት ሥር ይገኛል። ቆስጠንበር ከተማ ነው፤ያውም የኢትዮጵያን መልክ ከነወዙ ይዞ የነበረ። ከፈንጂ ወረዳ ማዕከል ከሆነው ሚቅራድ እና ከወዲያ በአዋሳኝ ዞን፤ከሲልዞራ ወረዳ የዚክራድ ከተማ፤እንደ አሸማጋይ በሁለቱ ከተሞች መሃከል በተመሳሳይ እርቀት የከተመ አዛውንት ከተማ ነው።

ቆስጠንበር በሕዘበ ውሳኔ ለፈንጂ ወረዳ ቢሰጥም፤ሲልዞራዎች ነጥቀው ለራሳቸው ለማድረግ አንድ እጁን እየጎተቱ አወላልቀውታል። በዝሆኖች እርግጫ ሳሮች…’ እንደሚባለው ሆነና በመሃል አጎንብሦ አሳር ፍዳውን ይግጣል። በቆስጠንበር በዋናነት ሁለት ቋንቋዎች በእኩልነት የሚነገርበት በመሆኑ ማን በየትኛው ቋንቋ አፉን እንደፈታ እንኳንስ ሌላው እነርሱ እራሳቸው አያውቁትም። በገበያውም ቢሆን፤በአንደኛው ተደራድረው በሌላኛው ተመራርቀው ይሸኛኛሉ። ከወዲያና ወዲህ ተሰባጥረው፤ተዋልደውና የዘር ሐረግ ተማዘው በቆስጠንበር የኖሩ እነዚህ ሁለት ማህበረሰብ መሃከል፤አሁን ዘር ሳይሆን ጦር የሚማዘዝ በቅሏል። ጦሩም ከየአቅጣጫው ሲምዘገዘግ መጥቶ በዚሁ ከተማ እምብርት ላይ ተሰቀሰቀ።

“ድሮ ድሮማ…የቆስጠንበር ሕዝብ ከአሸዋ ክምር ላይ የተበተነ ጤፍ ነበር። እንኳንስ የሰው ክፉ ጂኒ እንኳን በስውር ዓይን ፈልጎ የማያገኘን የእግዜር የፍቅሩ መንበር ነበርን። ነበ..ርን…እህህም..እህህ…” ይላሉ ጋሽ ደጅይጥኑ፤ከቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ የጠዋቷን ፀሐይ እየሞቁ። እህህ…እያሉ መቆዘሙ…ለብቻ ቁጭ ብሎ ከራስ ጋር ማውራቱ ለቆስጠንበር ሕዝብ ቁርስ ምሳ እራቱ ነው። ይህን ተመልክቶ እከሌ አበደ…ምን ሀሳብስ ገባው..ምንስ ነካው…የሚል አንድም የለም። ምክንያቱም ሁሉም በራሱ እብደት ተነክቶ ሠርግና ለቅሶው የተቀላቀለበት ብቻ ነው።

****

ቆስጠንበርን ተነጥቀናል በማለት በወዲያኛው ጫፍ የትግል ንቅናቄ የሚያደርጉት የዝክራድ ወረዳ ወጣቶች ቢሆኑም፤ነገሩ ግን ከላይ ከዞናቸው ጀምሮ የብዙ አመጸኞች እጅ ያለበት ነው። ቆስጠንበርን ከሚቅራዶች እጅ ለማስወጣት ለሚደረገው የሴራ ፖለቲካ የዝክራድ ወጣቶች መጠቂሚያ መሳሪያ ተደርገዋል። ዋነኞቹ በእነርሱ ውስጥ ተደብቀው፤ሰይጣን እንደጋለበው ፈረስ ቼ በለው!እያሉ እንዳሻቸው ያስፈረጥጧቸዋል። ለዚህ ጉዳይ ተብሎም በገንዘብና መሳሪያ የተደራጀ አደገኛ የሆነ የወንበዴዎች ቡድን አቋቁመዋል። ቡድኑ በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን፤ ያገባኛል እያሉ እጃቸውን ከከተቱና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ የዞኑ ተወላጆችም ጭምር ረዥም የግንኙነት ሰንሰለት ፈጥሯል። “ተልዕኮ ቆስጠንበር” በዚሁ ቡድን የተቀነባበረ የሴራ ተልዕኮ ነው። “ቆስጠንበር የኛ እንጂ የማንም አይደለም። በፈንጂ ወረዳዎችም አይተዳደርም!፤በሚቅራድ ስር አይሆንም!…የከተማው ግዛትም የኛና ለኛ ብቻ ነው” በማለት ለ”ተልዕኮ ቆስጠንበር” ተሰናዱ።

“ተልዕኮ ቆስጠንበር” በፖለቲካዊና በሀይል ሴራ የተቀመመ ፈንጂ ነው። ሴራውን ከግብ ለማድረስም አራት ዋና ዋና እቅዶችንም ጠነሰሱ። አራቱ የቆስጠንበር ተልዕኮ የእቅድ ንድፎችም እነዚህ ነበሩ፤ 1ኛ.ከሰማይ ይሁን ከምድር በማይታወቅ መልኩ፤ በቆስጠንበር በሚኖሩ የፈንጂ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ በየጊዜው ድንገተኛ የሆነ ጥቃት ማድረስና በዚህም ተማረው ከተማውን እንዲለቁ ማድረግ። 2ኛ.በእቅድ አንድ የተዳከሙትን እነዚህን ሕዝቦች፤ ብልሃት በተሞላበት መንገድ መሬትና ቤታቸውን እንዲሸጡልን በመገፋፋት ቀስ በቀስ የኛን ጎሳዎች ከመሃል እያመጡ በቦታው ማስፈር። 3ኛ.የፈንጂ ወረዳ መንግሥት ግብር ከመሰብሰብና ከማስተዳደር ጀምሮ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ኃይልና ሥልጣን በቆስጠንበር ላይ እንዳይኖረው ማድረግ። 4ኛ.በመጨረሻም በከተማውና ዙሪያው የኛ የሕዝብ ቁጥር ከእነርሱ ከፍ እንዲል ማድረግና በሕዝበ ውሳኔ የተነጠቅነውን ቆስጠንበር ዳግም ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በማድረግ ያለምንም ጥያቄ ከተማውን የኛ ማድረግ፤ የሚሉ ነበሩ። ከዚህ በኋላ ቆስጠንበር የፈንጂ ወረዳ የፖለቲካ እሳት ሆነ። ወላፈኑ ከቀድሞው በአስር እጥፍ ጨመረና የሲኦል ፍም የተደፋበት መሰለ። ውጥንቅጡ ወጥቶ መላ ቅጡ ጠፋ።

ቆስጠንበር…ሕግ አልባ፤ሰላም አልባ፣ፍቅር አልባ፤በመጨረሻም ባለቤት አልባ ወደመሆን ገሰገሰ። በሁለቱም ወረዳዎች ካሉ ደቃቃ ከተሞች ሁሉ የተሻለና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ቢሆንም ሚቅራዶች ግን ግብር መሰብሰብም ሆነ በቅጡ ማስተዳደር አልቻሉም። በፖለቲካ እሳት እንደ ገሀነም እረመጥ እየተንተከተከ፤ ለዚህም ለዚያም ሳይሆን ቀርቶ በመሃል ለሁሉም በአጥር የተከለለ ሥፍራ ሆነ። ፈንጂ ወረዳዎች አንድ መላ ዘየዱ። ለሁሉም ነገር መፍትሔ ይሆናል ያሉትን የከተማውን ማዘጋጃ ቤት በአዲስ መልክ አዋቅረው ወደ ሥራ አስገቡት። ውጤቱ ግን እንደ ጉም የሚተን እንጂ የሚጨበጥ አልነበረም። ሰዎች ለሥልጣን በሚሻኮቱባት በዚህች ሀገር ውስጥ ለዚህ ከተማ ባለሥልጣን የሚሆን በመብራት ተፈልጎ ታጣ። እባክህን ኃላፊ ሁን ተብሎ ብዙ ሰው ቢለመንም እምቢ አሻፈረኝ አለ። ሥልጣን ሲያቅለሸልሽ የቆስጠንበር ማዘጋጃ ቤት በታሪክ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። ኃላፊ አድርጎ ለመሾም የሚታሰበው ሁሉ፤የሚታየው በሥልጣን ወንበሩ ላይ የተጠመጠመ ዘንዶ እባብ ነውና በሠፈሩ ማለፍም አይፈልግም። “ሥልጣን ባፍንጫዬ ይውጣ” እያለ ሁሉም ይሸሸዋል። ለአንዳንድ ጅቦች እንኳን ሁኔታው ለመብላት የሚያመችና የሚያስጎመጅ ቢሆንም፤በልቶ እንደማይሰነብቱ ያውቃሉና ‘ከነገሩ ጾም ይደሩ’ን ይመርጣሉ። ሥልጣን ናፋቂው ሁሉ እዚህ ጋር ሲደርስ ሽንቱ እየመጣ ለመብረክረኩ ምክንያት አለው። የሲልዞራዎቹ “ተልዕኮ ቆስጠንበር” ነው።

እንደሚታወቀው ከ”ተልዕኮ ቆስጠንበር” ሴራዎች አንደኛው የፈንጂ ወረዳው ሚቅራድ፤በቆስጠንበር ምንም አይነት ፖለቲካዊ ሀይል እንዳይኖረው ማድረግ ነው። በቆስጠንበር ውስጥ ምንም አይነት መንግሥታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የቆመውን ቋንጃውን እየሰበሩ ወደቤቱ ማስገባት ነው። በዚህ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ቢሮውን ከፍቶ በወንበሩ የሚቀመጥ ኃላፊም ሆነ ሠራተኛ በራሱ ላይ የፈረደ ብቻ ነው። የሲልዞራዎቹ ዚክራዶች በሌላ ጊዜ አድፍጠው በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በራሳቸው ላይ ጥቃት ያደርሱባቸዋል። በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ሰባት ያህል ኃላፊዎች ተሹመዋል። ከአጥቂ እስከበረኛ ያልተፈራረቀ የለም ቀንቶት ግብ ያስቆጠረ ግን አልነበረም። ገና የተቀመጡበት ወንበር ሳይሞቅ፤ጅራቱን እንደተመታ ውሻ ጭራቸውን ቆልፈው ‘ጎመን በጤና’ እያሉ ወደ ቤታቸው ይገባሉ።

የፈንጂ ወረዳ አመራሮች ተሰባስበው ይሆናል ያሉትን አንድ የመጨረሻ አንድ ሌላ መላ ዘየዱ። እሾህን በእሾህ…የፍየሎችን እረኛ ከፍየሎች መንጋ…በሚቅድራት ከተማ በሚገኝ አንድ ሴክተር መስሪያ ቤት የምትሰራ ከሁለቱም ወገን የሆነች አንዲት ሴት ነበረች። በአባቷ የሲልዞራዎች የዘር ግንድ ያላት ሲሆን ውልደትና እድገቷም በቆስጠንበር ከተማ ነው። ይህቺን ሴት ሹመው ወንበሩ ላይ አስቀመጧት። ወንበሩ ግን ወፍጮ ነው፤ ባቄላም ይግባ ሽንብራ ከመፍጨት ወደኋላ አይልም። መቀመጫን የሚለበልብ እሳት ይለቃል። ልጅቷ በግል ስብዕናዋም ሆነ በስራዋ ጠንካራ ብትሆንም፤ በፍርሃት መንዘፍዘፏ ግን አልቀረም ነበር። ሥልጣን ያንዘፈዝፋል። የፈራችው አልቀረም። አንድ ምሽት ላይ በቆስጠንበር የነበረውን የእናትና አባቷን ቤት አመድ አደረጉት። ብዙ ሀብትና ንብረትም አወደሙባቸው። እርሷም የዛቻና ማስፈራሪያ መልዕክቶች ደረሷት። በሕይወት መሰንበት ከፈለግሽ አሁኑኑ ኃላፊነትሽን ለቀሽ ውረጂ…ወረደች።

****

“ሠላምና ሠላም ለቆስጠንበርና አካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ…በጥቂት የፀረ ሰላም ሀይሎች ሳቢያ፤በሁለቱ ወረዳዎች መሃከል የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት ለመፍታት የፊታችን እሁድ በሚደረገው የሰላም ኮንፈረንስ…” የሰላም ኮንፈረንስ ጥሪ ከጫፍ ጫፍ ይስተጋባል። ከአንዱ ሱቅ ቆመው እቃ በመግዛት ላይ የነበሩት ወይዘሮ ማዕረግ ዞር ብለው ግዙፍ የድምጽ ማጉያ በጀርባው አዝሎ ዘጭ…እንዘጭ እያለ የሚሽከረከረውን ትንሽዬ መኪና ተመለከቱ። “እኛስ መች ተገጫጭተን…እናንተ በግንባር ስትገጫጩ እኛ እንድማ እንጂ…” ሲሉ አልጎሞጎሙና ተመልሰው ዞሩ። በማጉያው የሚለፈፈውን ድምጽ ተከትሎ ከወዲያና ወዲህ ልዩ ልዩ ስሜቶችና ድምጾች ይስተናገዳሉ። “እና እሁድ ልንታረቅ ነዋ…ኸረ እኔ አይመቸኝም…እሁድ እኮ ሠርጌ ነው…ብቻ ተሳክቶ ሰላማችንን ባገኘን…አበል አለው?…እነማን ይመጣሉ?…አንተው እርዳን…እሰይ! እሰይ!…ቱሪናፋ…እንኳን በኮንፈረንስ በሲምፖዚየምም አታመጡ…ኸረ ዘይትና ስኳር…አብረሃም ይፈታ…” የሚሰማው ሌላ ነው ቀልድ…ፌዝ…ተስፋ መቁረጥ…ጉጉት…ምኞት…ብሶት…ደስታ…ችግርና መከራ።

ለአራት ቀናት ያህል በድምጽ ማጉያ እየተለፈፈ ነጋሪት ተጎሰመ። ብዙ ሚሊዮን ብሮች ወጪ በማድረግ ዝግጅቱ ተደረገ። ቀኑም ደረሰና ከክልል ጀምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሁለቱ አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ሹማምንት፤በቆስጠንበር ከተማ ተገኙ። የሰላም ኮንፈረንሱ ሕዝባዊ ቢሆንም ሕዝብ ግን አልነበረም። ከፈንጂ ወረዳ ጥቂት የማይባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኙ። ከሲልዞራዎች ግን እንዲሁ ለፖለቲካ ፍጆታ ታህል በጣት የሚቆጠሩ ተመርጠው መጡ። በዚህ የሰላም ኮንፈረንስ ለመሳተፍ በቆስጠንበር የተገኘ ማንኛውም ሰው፤ቅጣቱ የከፋ እንደሆነ የሚያስረግጥ መልዕክት ሲልዞራዎች ቀድሞ ደርሷቸዋል። ማስጠንቀቂያው የተነገራቸውም በፖለቲካ እሳት ከተጠበሱ ከራሳቸው ወጣቶች ነበር። ሕዝቡ እርቅ ፈጽሞ ወደ ሰላም መንገድ ከገባ፤ቀደም ሲል የነደፉት ቆስጠንበርን የማስመለስ እቅዳቸው የሚከሽፍ በመሆኑ፤ይህ እንዳይሆን ሕዝቡን ከሰላም መንገድ ማስወጣት ምርጫ አልባ ምርጫ አድርገው ውስጥ ውስጡን ተንቀሳቀሱ።

****

ከሲልዞራዎች መንደር፤የዚክራዱ ሲኖ ቡጢውን እየጨበጠ፤ጥርሱን ነክሶ የሰማይ ስባሪ በሚያህለው ቁመቱ ውጥር ንጥር እያለ ወደ ቤቱ ይሄዳል። መሬቱን ሲረግጥ ሣሮቹ ዳግም የሚነሱ እንኳን አይመስልመ። ግድግድ ረዥም ከመሆኑ የተነሳ፤የመንደር ጀሌዎቹ እንኳን አብረውት ሲራመዱ የሚከተሉት በሶምሶማ ነው። በሙሉ የሲልዞራ ወረዳ ለጉልበቱ አቻ አልተገኘለትም። እርሱም ይላል “ለኔ ጋብቻ እንጂ አቻ አይገኝም!” ከመንደሩ አልፎ ድንበር በጣሰው ካቦነቱ የማይፈራው የማይብረከረክለት የለም። ከገጨ የማያስተርፍ፤ከሄደም መቆሚያው የራቀው በመሆኑ ለመጠሪያው ሲኖትራክ ሊሉት አሉና ቢቆላመጥ ይሻላል ብለው “ሲኖ” ሲሉ ቅጽል ስያሜ አወጡለት።

የ”ተልዕኮ ቆስጠንበር” ዋነኛው አጋፋሪም ይሄው ወጣት ነው። ሲኖ፤ከእግር ጥፍር እስከ እራስ ፀጉሩ በንዴት እየተርገበገበ ደረሰና በወንበር ተደግፎ ገርበብ ያለውን የቤቱን በር ገና በእጁ ከመንካቱ ወንበሩ ክንብል ሲል ወለል አድርጎት ገባና ቁጭ አለ። አንዴ ጡንቻውን አንዴ ቡጢውን በመዳፉ እየፈተገ፤ከስር በጫማው ወለሉን ይደቃዋል። እናቱ አምራ፤ከወደ ጓዳው በእጇ ወንፊቱን እንደያዘች ቆማ በግራ መጋባት ትመለከተዋለች። መቼም የርሱ በደህና ወጥቶ በደህና መግባት፤ከሰማይ ላይ ደመናን እንደማጣት እንደሆነ ብታውቀውም የዛሬው ግን ተለየባት።

“አንተ ልጅ..ከእነዚያ የጅብ መንጋ ከሚመስሉ ጎረምሶች ጋር ተው ይቅርብህ ብልህ እምቢ አልከኝ አይደል…ይሄው ዛሬም ደንበኞችህ ሲፈልጉህ ነበር” “እነማናቸው?” “እነማናቸው…አንተ ከፖሊሶቹ ሌላ ምን ደንበኛ አለህ..አንተ እንደሆነ ውሎህ ከየመንደሩ፤አዳርህ ከፖሊስ ጣቢያ ከሆነ ሰንብቷል” “ደግሞ ምን ልሁን ብለው ነው የሚመጡት!” ” እስረኞቹ እንቅልፍ እንቢ ስላላቸው አባብለህ እንድታስተኛላቸው ልበልህ…” በማለት ቅሬታ የተቀላቀለበትን የንዴት ሳቅን የመሰለ ድምጽ እያወጣች፤ተመልሳ ወደ ጓዳዋ ገባች። ሲኖ የእጅ ስልኩን አወጣና ከጥሪ ስም ዝርዝሩ ውስጥ ‘ጆርጅ’ የምትለዋን ነካት። “ሄለው” አለ ጆርጅ። “ስማ ዛፓዎቹ ቤት ተከስተው ነበር አሉ፤እንዴት ነው ኢናው በጣም ተነጅሯል እንዴ? ሄደህ ክላም አደረክ?” ” አዎ በጣም ሳይጎዳ አይቀርም በአንቡላስ ወደሌላ ቦታ ወሰዱት አሉ። ሞተሩም የሌለ ደቋል። ሲለቃቅሙት እንዲያውም የፊት እግር ጎማውን ሳይረሱት አይቀርም…” አንተ ትቀልዳለሃ..ለማንኛውም እኔ እዚህ አልዋልኩም፤አላደርኩም ብዬ ሸመጥጣለሁ ዛፓዎቹ እናንተን መጠየቃቸው ስለማይቀር ይህን ለጀማው ሙሉ ንገር…” ስልኩ ተዘጋ።

****

በሁለቱ ሕዝቦች መሃከል የሰላም ኮንፈረንሱ ተካሄደ ተብሎ ተበላ ተጠጣ፤በየሚዲያው ተራገበ። ከሁለቱም ወገን ከሕዝብ የተባሉ ሰዎች እየተቃቀፉ ፎቶ ተነሱ። ድምጻቸውንም ካሜራቸውን ደግነው ለተኮለኮሉት ሚዲያዎች ሰጡ። “ደስ ብሎናል ደስ ይበላችሁ…ከአሁን ወዲያ ማንም አይለያየንም” ሲሉም ተናገሩ። እውነቱን ለመናገር ሰዎቹ ሕዝባቸውን የወከሉና በትክክልም ገብቷቸው እርቅን የፈጸሙ ሳይሆኑ በንግግር ችሎታቸው ተመርጠውና የሚሉትንም ከመሪዎቻቸው ተቀብለው ነገ ፈተና እንዳለበት ተማሪ፤በአጠሬራ መልክ ያጠኑ ነበሩ። ፈንጂ ወረዳዎች የሠላም ኮንፈረሱን በእርግጥም የሚፈልጉትና የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ቢሆንም፤ነገር ግን አመራሩ እርስ በእርስ በውስጥ ከነበራቸው ሹክቻ የተነሳ የእነርሱም ቢሆን እውነተኛ ነበር ለማለት ያዳግታል።

የሰላም ኮንፈረንሱ ከተጠናቀቀ ቀናት አልፈው ሳምንት ሊደፍን ሆነ። ሁሉም ነገር ጸጥ እረጭ ብሏል። ነገሩ ሁሉ ‘ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም’ ሆነ። ጦርነት እንዳይባል ሰላም ነው፤ሰላም ነው እንዳይባል ፍርሃት ነው። ሰው ሁሉ የህሊና ጸሎት ላይ ያለ መሰለ። የሰባተኛው ቀን እሁድ አልፎ ስምንተኛው ሰኞ ገባ። ይህ ስኞ በቆስጠንበር የእውነትም እንደሚሉቱ ጥላሸት የለበሰ ‘ብላክ መንዴይ’ ነበር።

ጊዜው የሐምሌ ክረምት፤ቀኑም ሰኞ ነበር። ቆስጠንበር፤ ከሰማይ በጭጋግ ከምድር በጭቃ ተጣብቃ በመሃከል የሳንዱዊች ቂጣ መስላለች። ቀን ላይ፤ገበሬው በየጓሮው፤ የተማረውም በየቢሮው፤ ስራ ፈቱም በየድድ ማስጫው ውሎ ምሽቱን በጦፈ እንቅልፍ ጭው ብሏል። በዚያን ምሽት ማን ምን ይመጣ ይሆን ብሎ የሰጋ ያለ አይመስልም። ድንገት በከተማው ውስጥ ተዘዋውሮ ለተመለከተ፤ በእርድ ላይ እንዳለ በሬ ከሚያንኮራፋ ሰው አፍንጫ የሚወጣው ዱርር…ቡርር…ከሚለው ድምጽ በቀር የሚሰማ አንዳች ነገር የለም። 6 ሰዓት…7 ሰዓት…8 ሰዓት ሆነ። አሁን የሚሰማው አፍና አፍንጫ እየቀደደ የሚወጣ ወፍራም ድምጽ አይደለም። ይልቅስ ከመሳሪያ አፈሙዝ የሚንዠቀዠቅ ከባድ የጥይት ባሩድ ነው። ‘አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው’ የቆስጠንበር ምድር መውጫ መግቢያው ሁሉ ተናወጸ።

ሁሉም አንድ ነገር ተረዳ፡፡ ሰላም የሚመጣው በህዝብ ፍላጎት ብቻ ነው፡፡ ፖለቲከኞችና ህዝብ እናውቃለን የሚሉ ወገኖች ሁልጊዜ ቂምና ጸብና ከመዝራት ውጪ ስለ ሰላም አስበው አያውቁም፡፡እናም ቆስጠነብር ህዝብ የተማረው አንድ ነገር ቢኖር ህዝቡ ከሚለያየውና ከሚያራርቀው ይልቅ የሚያቀራርበው መብዛቱ ነው፡፡ይህን አንድነትና አብሮነት ደግሞ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለዘላቂ ሰላም ዋስትና ነው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You