የሸገር አትሌቲክስ ክለብን ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው

የሸገር ከተማ ስፖርት ክለብ ከተቋቋመ ጥቂት ጊዜን ብቻ ነው የተቆጠረው፡፡ ክለቡ የተዋቀረው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ካሉት አምስት ከተሞች የተውጣጡ የተለያዩ ክለቦችን በመያዝ ሲሆን እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስን እና አትሌቲክስን አቅፎ ወደ እንቅስቃሴ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ክለቡ በነዚህ ስፖርቶች ተሳትፎውን የጀመረ ሲሆን አትሌቲክሱም በቅርቡ እንቅስቃሴውን የተቀላቀለ ስፖርት ነው፡፡

ክለቡ በአትሌቲክስ ስፖርት ተፎካካሪና አሉ ከሚባሉ የአገሪቱ የአትሌቲክስ ክለቦች አንዱ የመሆን ተስፋን ሰንቋል። ከተቋቋመ 2 ወራትን ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን ያደረጋቸው ውድድሮችም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት 198 አትሌቶችን በመያዝ ወደ ሥልጠና የገባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 60 አትሌቶችን ይዞ ጉዞውን ቀጥሏል። በቀጣይ የቡድኑን አትሌቶች ቁጥር በመጨመር እስከ 120 በማድረስ ጠንካራ ተፎካካሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ የአትሌቲክስ ክለብ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል። በዚህም ከአገር አቀፍ ደረጃ አልፎ በዓለም ኢትዮጵያን በመወከል ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን ለማፍራት አስፈላጊው ዝግጅት እንደተደረገ ተጠቁማል።

ክለቡ ከተመሠረተበት ወቅት ጀምሮ ዝግጅቱን በአግባቡ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ በ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ለመሳተፍ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሆነና ተፎካካሪና ውጤታማ ለመሆንም አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን ባዘጋጀው የአጭር፣ መካከለኛ፣ 3 ሺ ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራትና ርምጃ ውድድር የአቋም መለኪያ ሻምፒዮና በመሳተፍ የክለቡን ወቅታዊ ብቃት ለክቷል፡፡ ክለቡ አዲስ እንደመሆኑ በተወሰኑ ስፖርት ዓይነቶች የተወሰኑ አትሌቶችን ይዞ የቀረበ ሲሆን 35 አትሌቶችን አሳትፎ፣ በውድድሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡ ከወራት በፊት መቐለ በተካሄደው የሪሌይ ውድድርም የመጀመሪያ የነጥብ ተሳትፎውን አድርጎ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ፈጽሟል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው የአቋም መለኪያ ውድድር ክለቡ አቋሙን እንዲመለከትና ያለበትን ደረጃ አውቆ ከሌሎች ቡድኖች ጋር ለመፎካከር የሚያስችለውን ዕድል ለመፍጠር እንደሚረዳው አቶ ጌቱ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ ክለቡ አዲስ እንደመሆኑ በቀጣይ ምን መሥራት እንዳለበት፣ ጉድለቱን ለመለየትና አስተካክሎ

 ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና እንዲሁም ለሌሎች ውድድሮች ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡

ክለቡን ውጤታማና ተፎካካሪ ለማድረግ አመራሩ ቁርጠኛ እንደሆነና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለሟሟላት በጀት መመደቡን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም በግብዓት በኩል እስከ አሁን ችግር እንደሌለና ወደ ፊትም ይኖራል ተብሎ እንደማይታሰብ አክለውም፣ ክለቡ አሁን ያሳየውን ብቃት አጠናክሮ ከሠራ ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

ክለቡ ለሚፈልገው ውጤታማነት መስፈርቶችን አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ብቃትን ብቻ መሠረት በማድረግ ከሁሉም ክልሎች ሁሉንም መስፈርት ያማከለ የአትሌቶች ምርጫ በማድረግ ራሱን አጠናክሮ በአጭር ጊዜ ተፎካካሪ ከሆኑት የሀገሪቱ ክለቦች አንዱ የመሆን ዕቅድ አለው፡፡ ለዚህም ሁሉን አካታች፣ ውጤታማና ለሀገር  የሚጠቅም ዓላማን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ከተመሠረቱ ረጅም ዓመታትን ካስቆጠሩ፣ ልምድ ካላቸውና ጠንካራ ክለቦች ጋር ለመፎካከር ከተማው አካባቢ የሚገኙትን አትሌቶች አሰባስቦ ወደ ክለቡ መቀላቀልና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትንም አቅዶ እየሠራ ነው፡፡ በዚህም ከፕሮጀክቶች ከአካዳሚና ከሌሎች ቦታዎች አትሌቶችን በማሳደግ እራሱን የማጠናከርና ተፎካካሪ የማድረግ ሥራን ያከናውናል፡፡ ‹‹ተፎካካሪና ተፅዕኖ የሚፈጥር አትሌቲክስ ክለብ የማይሆንበት ምክንያት የለም፣ በአቋም መለኪያ ውድድርም ተፎካካሪ መሆኑን አሳይቷል›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ክለቡ በኦሮሚያ ክልል የተዘጋጁ ውድድሮች ላይ 30 አትሌቶችን ይዞ እንደተሳተፈ በማስታወስ በትንሽ አትሌቶች ተፎካካሪ በመሆን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዳጠናቀቀ ይናገራሉ፡፡

ክለቡ የቀጠራቸውና ቅጥር ሂደት ላይ ያሉት አሠልጣኞች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ማስጠራት የቻሉ ውጤታማና ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም አትሌቶችን ለመሳብና ውጤታማ ክለብን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አስተዋፅዖው የጎላ እንደሚሆን ሥራ አስኪያጁ ያምናሉ፡፡ በዚህም ክለቡ ማስታወቂያ አውጥቶ ከሀገሪቱ አሉ የተባሉትን አሠልጣኞች አወዳድሮ መቅጠሩንና የላቀ ብቃት ያለው የአሠልጣኞች ስብስብ መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

የክለቡ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አከፋፈል ብቃትን ብቻ መሠረት ያደረገና አትሌቶች በተሳተፉበት ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን ነው፡፡በዚህም መሠረት ኦሊምፒክ የተሳተፈ አትሌት መነሻ ክፍያ ከፍ የሚል ሲሆን ሌሎች አትሌቶችን ለመሳብ እንደ ጉርሻ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቅሷል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You