ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአትሌቲክስ አቋም መለኪያ ውድድር አሸናፊ ሆነ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ የኢትዮጵያ የአጭር መካከለኛ፣ የ3 ሺ ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራትና የእርምጃ የአቋም መለኪያ ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ፍጻሜውን ባገኘው በዚህ የአቋም መለኪያ ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለቱም ፆታ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን መቻልና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

በውድድሩ በርካታ ፉክክሮች የተካሄዱ ሲሆን ከተለያዩ ክለቦች የተወጣጡ ጠንካራ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል። በወንዶች መካከል በተደረገው ፉክክር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 169.5 ነጥቦችን በመሰብሰብ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል። ጠንካራ አትሌቶችን ይዞ በመቅረብ ተፎካካሪ መሆን የቻለው መቻል ስፖርት ክለብ 134 ነጥቦችን በመያዝ የሁለተኝነቱን ደረጃ በመያዝ ሲያጠናቅቅ፤ ሌላኛው ጠንካራ ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ125.5 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽሟል።

በሴቶች መካከል በተካሄደው ፉክክር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ191 ነጥብ ቀዳሚውን ደረጃ በመያዝ የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል። መቻል 164 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 87 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችሏል።

በአጠቃላይ በአምስቱ ቀን የአቋም መለኪያ ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ361 ነጥብ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፣ መቻል 298 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሁለተኛና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ213 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ፈጽመዋል።

ከውድድሩ ጅማሬ ቀን እስከ መጨረሻ ድረስ በተለያዩ ፉክክሮች በርካታ የማጣሪያና የፍጻሜ ውድድሮች ተስተናግደዋል። በመጨረሻው የውድድር ቀንም በአምስት ውድድሮች የፍፃሜ ፉክክሮች ተደርገዋል። በ1 ሺ 500 ሜትር በሁለቱም ፆታ የተከናወነው የፍፃሜ ውድድር አንዱ ሲሆን፣ በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድር አድሃና ካሳይ ከንግድ ባንክ 1ኛ፣ ሳሙኤል አባተ ከመቻል 2ኛ እና ዮሐንስ አስማረ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ኛ በመሆን ውድድራቸውን ጨርሰዋል። በሴቶች ሂሩት መሸሻ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ትዕግስት ግርማ ከመቻል ሁለተኛ በመሆን ፈጽማለች። ሕይወት መሐሪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስተኛ ሆናለች።

በተመሳሳይ በሁለቱም ፆታ በተካሄደው የ4 x 100 ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር በሴቶች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ47.32 1ኛ፣ መቻል በ47.94 ሁለተኛና ንግድ ባንክ በ48.20 3ኛ በመሆን አጠናቀዋል። በ4 x 400 የዱላ ቅብብል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ኛ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ኛ እና መቻል 3ኛ መሆን ችሏል። በ4 x 800 ሜትር በተደረገው የዱላ ቅብብል ውድድር ደግሞ ሸገር ከተማ 1ኛ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ኛ ኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሰዋል።

ሌላኛው በመጨረሻ ቀን የተደረገው የወንዶች የምርኩዝ ዝላይ ውድድር ሲሆን አበራ ዓለሙ ከጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል አንደኛ ሆኖ አጠናቋል። ቴዎድሮስ ሽፈራው ከመቻል፣ ሳምሶን ባሻ ከሸገር ከተማ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በየውድድር ተግባሩ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ አትሌቶች ከሜዳልያ በተጨማሪ ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። 1ኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁ አትሌቶች የ 3 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን 2ኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁ አትሌቶች 2 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት እና 3ኛ ደረጃን ይዞ ለጠናቀቁ አትሌቶች 1 ሺ 500 ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሽልማቱ በድብልቅ ሪሌይም ከ1-3 ለወጡት ቡድኖች የተሰጠ ሲሆን 1ኛ ለወጡ ቡድኖች 6 ሺ ብር 2ኛ ለወጡ ቡድኖች 4 ሺና 3ኛ ለወጡ ቡድኖች የ2ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ሊበረከትላቸው ችሏል።

በውድድሩ ከ20 ክለቦችና ተቋማት የተወጣጡ 460 ወንድና 319 ሴት አትሌቶች በጥቅሉ 779 አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን ለክለቦችና አትሌቶች የውድድር እድልን ለመፍጠርና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ዓላማ አድርጎ መካሄዱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You