
አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ በማኅበረሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ ጫና እያደረሰ ያለውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለመከላከል ከሦስት ሺህ በሚበልጡ የቤቲንግ ቤቶች ላይ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በትናትናው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ቤቲንግ የተሰኘው ስፖርታዊ የውርርድ ጨዋታ በመዲናዋ ማኅበረሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው። እስካሁን በተሠራውም ሥራ ከ3 ሺህ በላይ በሚሆኑት ሕገ ወጥ የቤቲንግ አወራራጆች ላይ ርምጃ ተወስዷል ።
በርካታ ወጣቶች በቤቲንግ ስፖርታዊ ጨዋታ ጊዜያቸውን በማሳለፍ ለሥራ ያላቸው ተነሳሽት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጥቷል ያሉት ወይዘሮ ሊዲያ፤ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዳይገኙ አድርጓል፤ ወንጀል የሚፈጠርበት ቦታ ብቻ ሳይሆን የሰው ሕይወት የሚጠፋበት እየሆነም ነው ብለዋል።
ሕገ ወጥ ቤቲንግ ቤቶች እያደረሱት ያለውን ማኅበራዊ ጫና ለመከላከል እየተሠራ ሲሆን እስካሁን በተሠራውም ሥራ በሦስት ሺህ 241 የቤቲንግ ማጫወቻ ቤቶች ላይ ርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
ርምጃውም የተወሰደባቸው ብሔራዊ ሎተሪ ያወጣውን ከ21 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ታዳጊዎች እንዳይጠቀሙ የሚለውን እንዲጠቀሙ በማድረጋቸው፤ በትምህርት ተቋማት 200 ራዲየስ ክልል ማንኛውም አዋኪ ተግባራት እንዳይከናወን የሚከለክለውን ሕግ በመተላለፋቸው፤ የወንጀል መፈጠሪያና የሱስ መጠቀሚያ ሆነው በመገኘታቸው እንዲሁም መሰል ርምጃው እንደተወሰደባቸው በመግለጫው ተብራርቷል።
በቤቲንግ ስፖርታዊ ጨዋታ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዳይገኙ በማድረግ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይፈጠር እያደረገ ነው ያሉት ወይዘሮ ሊዲያ፤ ቤቲንግ በመዲናዋ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ “ልጆቻችን ትምህርት ላይ አሉታዊ ጉዳት ከማድረሱም ባለፈ ወደ አላስፈላጊ ነገሮች እንዲሠማሩ ጫና እየፈጠረ ነው፤ የቤት እቃ አውጥተው መሸጥ ድረስ አድርሷቸዋል፤ በሕግ ሊታይ ይገባል” ሲሉ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ሊዲያ፤ በማኅበረሰቡ ጥያቄ መሠረት ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።
ቤቲንግ እያደረሰ ያለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ መንገድ እየሠሩ ባሉ ቤቲንግ ቤቶችም ላይ ርምጃ የመውሰድ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ቤቲንግ ማኅበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው፤ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አመላክተዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም