መስመር የሳተው “ቤቲንግ”

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናችን እየተስፋፋ የመጣ ድርጊት ነው። በተለይ ወጣቶች የሚያዘወትሩት። ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ድርጊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይጨምራል። ምክንያቱም ድርጊቱ በአብዛኛው የተመሠረተው በአውሮፓ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ነውና። ወጣቶች ረጃጅም የተጠቀለሉ ወረቀቶችን እየገዙ ከጨዋታው ይበልጥ ውጤቱን እየጠበቁ የሚበሳጩበትና የሚደሰቱበት አልፎ አልፎም የሚጋጩበት የቁማር ጨዋታ ነው -የስፖርት ውርርድ ጨዋታ (ቤቲንግ)።

ይህን ጨዋታ የሚያዘወትሩ ወጣቶች አንዳንዶቹ ለመዝናናት ሌሎች ደግሞ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ እንደሚጫወቱት ይናገራሉ። ዓላማው ምንም ይሁን ምን ለመጀመር የሚቀል፣ ለመተው ሲሞክሩ ግን መልሶ የሚጣራ ሱስ የሚያሲዝ ጨዋታ መሆኑን የቤቲንግ ደንበኞች ይመሰክራሉ።

ይህ ተግባር ኢኮኖሚን ከማቃወስ አልፎ የቤተሰብን ሠላም ሲያደፈርስ የተመለከቱ ቤቲንግን ስሙን ያሳመረ “ቁማር” ነው በማለት ይገልጹታል። ወርሐዊ ደመወዛቸውን ጭምር ለጨዋታው የሚያውሉ ደንበኞችንም ያፈራው ቤቲንግ ለትዳር መፍረስ ምክንያት እየሆነ እንደመጣም እየተሰማ ይገኛል። ጨዋታው እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ያስተዋሉ ወገኖች ይሄ ነገር ሕጋዊ መሠረት አለውን? ብለው ይጠይቃሉ። ሕጋዊ ከሆነስ እውቅና የሰጠው አካል እንዴት እያስተዳደረው ነው? አሉታዊ ጎኑንስ አጢኖታል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችንም ያስከትላሉ።

“ቤቲንግ ተጫውቼ ባውቅም፣ ሥራዬ ብዬ የምከታተለው አይደለም” ያለንና ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርነው ወጣት ዘካሪያስ መንበሩ፣ የቤቲንግ ደንበኛ ባልሆንም በቤቲንግ ጫወታ የተጠመዱ፤ እተዋለሁ ብለው ደጋግመው የውርርዱን ቲኬት የሚቆርጡ፣ ከዚህ የተነሳ የቤተሰባቸው ሠላም የደፈረሰ፣ አልፎም ትዳራቸው የፈረሰ ሰዎችን በቅርበት እንደሚያውቅ ይናገራል።

በሌሎች ሀገራት እንዲህ ያሉ ስፖርታዊ የውርርድ ጨዋታዎች በመዝናኛነታቸው እንጂ፣ አሉታዊ ጫናቸው ብዙም ትኩረት የሚሰጠው አይደለም የሚለው ወጣት ዘካሪያስ፣ በሀገራችን ግን፣ ቤቲንግን የሚጫወቱ ሰዎች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኢኮኖሚና ሥነ ልቡና በማይጎዳ መልኩ በኃላፊነት ስሜት የሚጫወቱት ካለመሆኑ የተነሳ ጨዋታው አሉታዊ ጎኑ እንዲበረታ አድርጓል ይላል።

በተጨማሪም፣ ቤቲንግ ቤቶች በትምህርት ቤቶችና በእምነት ተቋማት ቅርብ ርቀት ላይ እንዳይከፈቱና እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዳይጫወቱት የሚከለክል መመሪያ ቢኖርም፣ መመሪያውን የማያከብሩ መኖራቸው የቤቲንግን ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ ጫና ጨምሮታል ይላል።

የሚጠቅመውን አውቆና መርጦ ማድረግ ከኅብረተሰቡ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ እንደ ማኅበረሰብ እንዲህ ያለው ግንዛቤ ላይ የደረስን ባለመሆናችንና ጨዋታው ዓላማውን እየሳተ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን እያስከተለ በመሆኑ፣ መንግሥት ከሚያስገኝለት ገቢ ይልቅ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ጫወታውን ቢያስቆመው የተሻለ ነው የሚል አስተያየቱን የሰጠው ወጣት ዘካሪያስ፣ ከእምነት አንጻርም ሳይለፉ ማግኘት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ወጣቱ ሠርቶ ማግኘትን ያገኘውንም አግባብ ያለው ቦታ ላይ ማዋልን ሊለምድ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

ልጆቻቸው በቤቲንግ ሱስ ተጠምደው የተቸገሩት የሦስት ልጆች አባት አቶ ግርማ ሹመቴ ደግሞ፣ ትውልዱ እንዲህ ባለው ጫወታ በብዛት የሚሳተፈው፣ ዋጋ ከመክፈል፣ ሠርቶ ከመለወጥና ደክሞ ከማግኘት ይልቅ ተዓምር እንዲወርድለት የሚጠብቅ ወኔው የሳሳ ትውልድ በመሆኑ ነው በማለት ትዝብታቸውን ይገልጻሉ።

በእርግጥ ይህ አገላለጽ ትውልዱን ሁሉ የሚወክል አይደለም ያሉት አቶ ግርማ፣ አዕምሮውንና ጉልበቱን ተጠቅሞ መለወጥን የሚሻ ትውልድ መኖሩ እንዳለ ሆኖ ድንገት መክበርን ለጠማው እንዲህ ያለውን አደንዛዥ ጨዋታ ማቅረብ የበለጠ ሥነ ልቡናውን መስለብ ነውና የሚመለከታቸው አካላት ይህን ጨዋታ ቢያስቆሙልን በማለት መልዕክታቸውን ይቋጫሉ።

ከቤቲንግ ሕጋዊነትና አሉታዊ ጎኖች ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጉዳዮች የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ፤ የስፖርት ውርርድ በመጀመሪያ በሕግ የታወቀው በ1999 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ እንደነበርና በ2001 ዓ.ም በወጣውም ላይ እንዲሁ በሕግ መደንገጉን ያወሳሉ። ከ2005ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ፣ የአተገባበር መመሪያ ወጥቶለት ተግባር ላይ የዋለ ሲሆን፣ ከ2012ዓ.ም ሚያዚያ ወር ጀምሮ እየተስፋፋ እንደመጣም ይናገራሉ።

ጨዋታው ለብዙዎች የሥራ እድል የፈጠረ፣ በኮሚሽንና በታክስ ብዙ ገቢ የሚገኝበት መሆኑ እሙን ቢሆንም፣ አስተዳደሩ የስፖርት ውርርድን ሲጀምር መነሻ ምክንያቱ ገቢ አልነበረም ይላሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ በተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች ሰዎች የስፖርት ጨዋታዎችን እያዩ ከተወራረዱ በኋላ፣ ገንዘቤን ከለከለኝ በሚል መነሻ፣ ሕገወጥ ወደሆኑ ተግባራት ሲገቡ በመስተዋሉ፤ ስፖርታዊ ውርርድን ሕጋዊ መስመር ለማስያዝ በማሰብ ወደ ሕጋዊ አሠራር እንደገባም ያስታውሳሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ ጨዋታው ተለምዶ መነጋገሪያ እየሆነ ሲመጣና ጥያቄዎች ሲከተሉ አስተዳደሩ ፈቃድ የመስጠቱን ሥራ በማቆም፣ በገለልተኛ አካል ጥናት እንዲካሄድ አድርጓል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በጥናቱ መሠረት ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ፣ በብዙ የዓለም ሀገራት ስፖርታዊ ውርርድ ሕጋዊ መሠረት ይዞ እንደሚካሄድና ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገራት ተለይታ እንደማትታይ የተነሳው ሐሳብ ጎልቶ በመታየቱ መመሪያው ላይ መሻሻል ተደርጎ ጨዋታው እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል።

ሥራው ቆሞ በነበረበትም ወቅት በየስርቻውና በየመጠጥ ቤቱ ውርርዶች ይካሄዱ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ውሳኔ በኋላ ስፖርታዊ ውርርድ ጫወታውን በማያበረታታ መመሪያ እንዲመራ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ብቻ እንዲያጫውቱት ለማድረግ ቀደም ሲል 400 ብር የነበረው የፈቃድ ማግኛ ወደ 500 ሺህ ብር እንዲያድግ፤ እንዲሁም ፈቃድ ጠያቂ አካል የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ዋስትና እንዲያቀርብ መደረጉን ይገልጻሉ።

በተጨማሪም በመመሪያው አንድ የስፖርት ውርርድ አጫዋች ቤት፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከትምህርት ቤቶች 500 ሜትር የመራቅ፣ እድሜቸው ከ21 ዓመት በታች የሆኑ እንዳይጫወቱ የመከልከልና፣ ዩኒፎርም የለበሱ ልጆችን በቤቱ እንዳይጫወቱ የመጠበቅ ግዴታ እንደተጣለበትም ነው የገለጹት።

አሁን አሁን ይህንን መመሪያ የማይተገብሩ ቤቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ አስተዳደሩ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጋር በመተባበር እንደነዚህ ባሉ ንግድ ቤቶች ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ለሕገ ወጥ ተግባር መበራከት አንዱ ምክንያት የቤቲንግ ቤቶች ከአስተዳደሩ በወሰዱት ፈቃድ አስተዳደሩን ሳያስፈቅዱ ቅርንጫፎችን እየከፈቱ መሆናቸውና ጨርሶ ከአስተዳደሩ ፈቃድ ሳያገኙ በሚያጫውቱ አካላት እንደሆነ አንስተዋል።

ከመመሪያ ውጪ በመሆን ማኅበራዊ ጉዳት እያደረሰ ያለ የስፖርት ውርርድ ቤት ካለና ኅብረተሰቡ ጥቆማ ከሰጠ አስተዳደሩ እርምጃ የማይወስድበት ምክንያት የለም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በአስተዳደሩ ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት ብቻ ጫወታውን እንዲያሄዱ በቀጣይም መመሪያ የማሻሻል ሥራዎችን እየተሠሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You