አበበ ቢቂላ በጃፓኗ ከተማ የታሰበበት የግማሽ ማራቶን ውድድር

ፈር ቀዳጁ ጀግና ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላ ከአምስት አስርተ ዓመታት በፊት የሠራው ዘመን አይሽሬ ታሪክ ዛሬም ህያው ነው። እኤአ በ1960 የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን የባዶ እግር ገድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል ሆኖ ዛሬም ድረስ ይዘከራል። አበበ በሮም የጀመረው ወርቃማ ታሪክ ከአራት ዓመት በኋላም በቶኪዮ 1964 ኦሊምፒክ ማራቶን ቀጥሏል። ይህም የታላቁን አትሌት ድሎች ከጥቁር ሕዝቦች ባለፈ መላው ዓለም ሁሌም በልዩነት እንዲያስቡትና እንዲያከብሩት አድርጓቸዋል።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በተለይም ሁለተኛ የኦሊምፒክ የማራቶን ድሉን በዓለም ክብረወሰን ታጅቦ ባስመዘገበባት የሩቅ ምስራቋ ሀገር የተለየ ክብር ይሰጠዋል። ጃፓን ለአበበ ካላት ትልቅ ክብር የተነሳ ኢትዮጵያዊውን ጀግና በብዙ መልኩ በመዘከር የሚስተካከላት የለም። ጎዳናዎችንና ድልድዮችን በተለያዩ ከተሞቿ በስሙ ሰይማለታለች። በቅርቡም እሱን የሚዘክር ትልቅ ሙዚየም አቋቁማለታለች። ከዚያ በላቀም አበበን እንደ አንድ የፅናት ተምሳሌት አድርጋ በሥርዓተ ትምህርቷ ውስጥ ያካተተች ሀገር ናት።

ጃፓን ኢባራኪ ግዛት በምትገኘዋ ካሳማ ከተማ የምታካሂደውን ዓመታዊ የግማሽ ማራቶን ውድድር ከ2012 ጀምሮ በጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ስም ሰይማለች። ይህ ውድድር ትናንት ሲካሄድም ከ 1600 በላይ ሯጮች ተሳትፈዋል።

በጃፓን የኢፌዴሪ አምባሳደር ዳባ ደበሌ የግማሽ ማራቶን ውድድሩን ያስጀመሩ ሲሆን፣ መሰል ወድድሮች ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ አጠናክሮና አስተሳስሮ ለማስቀጠል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል። የጃፓን መንግሥት ይህን ውድድር በማዘጋጀቱና የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ በማድረጉም ምስጋና አቅርበዋል።

የካሳማ ከተማ ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ በበኩላቸው፤ የከተማው አስተዳደር ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እየሰራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ከከተማዋ አስተዳደር የተውጣጣ ልዑክ በመምራት ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙና ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ግንኙነት በመመስረት በትብብር መሥራት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።

650 አትሌቶችን በማሳተፍ የተጀመረው ይህ ውድድር ከዓመት ወደ ዓመት የተሳታፊዎቹን ቁጥር እያሳደገና እውቅናውም እየጨመረ ይገኛል። በጃፓን በሚካሄዱ የተለያዩ የማራቶን ውድድርሮች ማሸነፍ የቻሉ እንደ አበበ መኮንን አይነት አትሌቶችም ባለፉት ዓመታት በውድድሩ ላይ በተጋባዥነት ተገኝተው ሲያስጀምሩ እንደነበር ይታወሳል።

ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት የጃፓኗ ከተማ ካሳማ ነዋሪዎችና ባለሥልጣናት እንዲሁም በጃፓን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚታደሙ ሲሆን የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና ማፍላት ሥነሥርዓትም የውድድሩ አንድ ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል።

በተመሳሳይ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ያሸነፈበትን የማራቶን ውድድር በማስመልከት በጣሊያኗ ሮም ከተማም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመታሰቢያ ሩጫ ውድድሮች እየተካሄዱለት ይገኛሉ። አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም በጣሊያን መዲና ሮም በተካሄደ 17 ኛው የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ በመሮጥ 2 ሰዓት ከ 15 ደቂቃ ከ 16 ሴኮንድ በመግባት ታሪካዊ ድል ማስመዝገቡ ይታወሳል።

የአበበን ዘመን ተሻጋሪ ድል አስመልክቶ የመታሰቢያ የሩጫ ውድድር ከ60 ዓመት በፊት አትሌት አበበ ቢቂላ በሮጠበት ተመሳሳይ ቀን፣ ቦታ እና ሰዓት በሮም “ተርሜ ዲ ካራካላ” ስቴዲየም የድሉ መታሰቢያ የሩጫ ውድድር በሮም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ነዋሪነታቸውን እዚያ ባደረጉ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም “ACSI Italia Atletica” የአትሌቲክስ ክለብ ትብብር ይካሄዳል።

ይህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ከሶስት ዓመት በፊት መካሄድ ሲጀምር በውድድሩ 106 ሯጮች የተሳተፉ ሲሆን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ላይ ሯጮችን ማስጀመር ባለመቻሉ የመጀመሪያው ሯጭ 195 ሜትር እንዲሁም ሌሎች ቀሪ 105 ሯጮች እያንዳንዳቸው 400 ሜትር እንዲሸፍኑ ተደርጎ ነበር። የሮም ከተማ ማህበረሰብና የተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ኃላፊዎች በስታዲየም ተገኝተውም ውድድሩን ይከታተላሉ።

ከውድድሩ በተጨማሪ የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት እየቀረበ የአትሌት አበበ ቢቂላ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት እና መዳረሻዎች፣ የኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነትና የልማት እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለታዳሚዎች በመቅረብ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ሥራዎች ይሠራሉ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You