የአዲስ አበባን የቦክስ ክለቦች ቁጥር ለመጨመር እየተሠራ ነውዓለማየሁ ግዛው

የአዲስ አበባ ከምትታወቅባቸው ስፖርቶች ውስጥ ቦክስ አንዱ ሲሆን በከተማዋ መዘውተር ከጀመረ ረጅም ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይነገርለታል። ስፖርቱ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ በተለያየ ደረጃ እየተዘወተረ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል። ከነዚህም ውስጥ ዋነኛው በክለብ ደረጃ የሚዘወተረው ሲሆን ለከተማው የቦክስ ስፖርት ዕድገት የራሱን የጎላ ድርሻ መጫወት ችሏል። ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ መወከል የቻሉ ቦክሰኞችን ያፈሩት የከተማዋ ክለቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመሄዱ ስፖርቱ መቀዛቀዝ አሳይቶ ቆይቷል።

ስፖርቱን ለማነቃቃትና ለማሳደግ የክለቦችን ቁጥር ለመጨመር እየሠራ እንደሆነ የአዲስ አበባ ቦክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ከ10 በላይ ክለቦች የነበሩ ሲሆን በዓመት በርካታ ውድድሮችም ይካሄዱ ነበር። በከተማዋ ከሚንቀሳቀሱ ጠንካራ ክለቦች መካከል በመንግሥትና ሚሊተሪ ተቋማት ስር ያሉ ክለቦች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። እነዚህ ክለቦች እየፈረሱ በከተማዋ የነበሩ ክለቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ ስፖርቱ እንዲቀዛቀዝ አድርጎታል።

አሁን በከተማዋ አራት ያክል ክለቦች ያሉ ሲሆን እነዚ ክለቦች የአዲስ አበባ ቦክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጃቸው ውድድርና ሀገር አቀፍ ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ከተማውን ወክለው ይሳተፋሉ። ክለቦቹ ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆኑም ቁጥራቸው አናሳ ነው። የክለቦቹን ቁጥር ከፍ በማድረግ ተፎካካሪና ከተማዋን የሚመጥኑ ለማድረግ ግን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ዘንድሮ አዲስ የተቋቋመውን ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ ኦሜድላ፣ ማረሚያ ቤቶችና አዲስ አበባ ፖሊስ የከተማዋ ቁንጮና ተፎካካሪ ክለቦች ናቸው። ከዚህ ቀደም ከተማዋ የምትታወቅበትንና ስሟ የገነነበትን ስፖርት ወደ ከፍታው ለመመለስ የክለቦችን ቁጥር ለማብዛት የተጀመረው በጎ እንቅስቃሴ በፌዴሬሽኑ በኩል ተጠናክሮ እንደቀጠለም ተገልጿል። በዚህም መሠረት በከተማዋ የሚገኙ የስፖርት ተቋማት ክለቦችን እንዲይዙ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን ለዚህም የሚያስፈልጉ ሰነዶች እንደተዘጋጁ ለማወቅ ተችሏል።

ቀደም ባሉት ዓመታት በቦክስ ስፖርት በጎ አስተዋጽኦ የነበረው መቻል (መከላከያ) ስፖርት ክለብ የቦክስ ቡድን እንዲያደራጅ ንግግሮች እየተደረጉ የሚገኙ ሲሆን ክለቡ በቦርድ የሚመራ በመሆኑ የክለቡን ቀደምት የቦክስ ታሪክን የሚዳስስ መረጃ ተደራጅቶ ለቦርዱ መላኩ ተጠቅሷል። በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክለብ እንዲይዙ ፍላጎትና ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል። ስፖርቱን ወደ ቀድሞ ዝናው ለመመለስ ከዚህ ቀደም የነበረው ሥራ አስፈጻሚ የጀመረውን አዲሱ አስፈጻሚ ጥረቶችና እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ ከጀመረም ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ቦክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ተስፋዬ፣ የከተማዋን የቦክስ ስፖርት ወደ ቀደመው ዝናው ለመመለስ የክለቦችን ብዛት የመጨመር እንቅስቃሴው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ቡና ክለብ እንደመሠረተና መቻልና አዲስ አበባ ከተማ ክለብ ለማቋቋም በሂደት ላይ እንዳሉ የገለፁት አቶ ግርማ፣ መሰል ሥራዎችን በመሥራት የክለቦቹን ቁጥር በመጨመር ከአሁን በፊት የነበሩትን በርካታ ውድድሮች ወደ ከተማው ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል። መቻል ስፖርት ክለብ በርካታ ቦክሰኞችን ያፈራ ክለብ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፣ በአንድ ውቅት በነበረ የግንዛቤ ችግር ክለቡ ከመፍረሱም በላይ የነበሩ ሰነዶች በመጥፋታቸው መረጃ ማግኘት ከባድ እንደሆነ አክለዋል። ክለቡን ለመመለስ ከመከላከያ ጋር በተደረጉ ውይይቶች የመከላከያን ቦክስ ታሪክ የሚገልጹ መረጃዎች ተሰባስቦና ተደራጅቶ ለመከላከያ እንደተሰጡና ኃላፊዎችን አሳምኖ ወደ ሥራ የመግባት ሂደት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ክለብ እንዲይዝ እየተደረገ ባለው ጥረት ቦክስ በሀገር አቀፍ ከሚደረጉ ውድድሮች የአዲስ አበባ መለያ ሆኖ ውጤት የሚመዘገብበት ስፖርት በመሆኑ በከተማ አስተዳደሩ በኩል የቦክስ ክለብ እንዲቋቋም ጥረቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ቦክስን በክለብ ደረጃ ለማቋቋም ከክለቡ አመራሮች ጋር ውይይቶች እየተደረጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ክለብን ለማቋቋም የሚያስፈልግ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለክለቦቹ ተልኳል። ከነዚህ በተጨማሪም እንደ ኮልፌና ልደታ ክፍለ ከተሞች የቦክስ ክለብን ለማቋቋም በሂደት ላይ የሚገኙ እንደሆኑም አስረድተዋል።

በዚህም አንዳንድ ክለቦች የበጀት ችግር ያለባቸው በመሆኑ የተወሰኑ ስፖርተኞችን ይዞ ወደ ሥራ ለመግባት ከክለቦቹ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል። ፌዴሬሽኑ ካለበት የሀብት እጥረት አኳያ ክለቦችን በሚጠበቀው ልክ እንዳልደገፈ እና በዓመት ስድት ውድድሮችን ብቻ እንደሚያካሂድ ገልጿል።

የቦክስ ክለቦች ቁጥር መጨመር ስፖርቱን ከማሳደጉ ባሻገር በርካታ ጥቅሞች አሉት። ለብዙዎች የሥራ ዕድልን መፍጠርና ታዳጊዎችን ተቀብሎ እንዲጎለብቱና ኤሊት ስፖርተኛ እንዲሆኑ አስተዋጽኦን እንደሚያበረክትም ይታመናል። በተጨማሪም የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ክለቦች ሴት ስፖርተኞች እንዲይዙ ይደረጋል። በዚህም መሠረት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ክለቦች ፍቃድ የሚሰጣቸው ሴት ቦክሰኞችን ሲያካትቱ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You