ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመዋጋት የማኅበረሰብ የመሪነት ሚና

እ.ኤ.አ በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ 39 ሚሊዮን ሰዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝ ፤ከ630 ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ያጡ መሆናቸውንና በዚሁ ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ አዲስ ሰዎች በኤች አይ ቪ የተያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በአንፃሩ ኤች አይ ቪ ኤድስን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር አዲስ በኤች አይ ቪ ኤድስ የመያዝ ምጣኔ ከፍተኛ ከነበረበት እ.ኤ.አ ከ1995 ጋር ሲነፃፀር 59 ከመቶ መቀነሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ከነበረበት እ.ኤ.አ ከ2010 ጋር ሲነፃፀር 51 ከመቶ መቀነሱን እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያም እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የኤች አይ ቪ የስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 91 ከመቶ ሲሆን በዚህ ስሌት 610 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ኤች አይ ቪ በደማቸው እንደሚገኝ፤ 8 ሺ 257 ሰዎች በዓመቱ ውስጥ አዲስ በኤች አይ ቪ የተያዙ ስለመሆናቸውና ወደ 11 ሺ 322 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በኤድስ ምክንያት እንደሚሞቱ እ.ኤ.አ በ2022 የወጣው ሀገራዊ የኤች አይ ቪ ስርጭት ግምት ያሳያል። ሆኖም የስርጭቱ ምጣኔ ከክልል ክልልና ከከተማ ከተማ የሚለያይ መሆኑን የስርጭት ምጣኔ ግምቱ ይጠቁማል።

ለምሳሌ በከተማ የኤች አይ ቪ ስርጭት መጠን ከፍተኛው ጋምቤላ በ3 ነጥብ 69 በመቶ፣አዲስ አበባ 3 ነጥብ 47 ከመቶ፣ ሀረሪ 2 ነጥብ 97 ከመቶ፣ ድሬዳዋ 2 ነጥብ 9 ከመቶ እና ዝቅተኛው ሶማሌ 0 ነጥብ18 ከመቶ መሆኑ ተመላክቷል። በክልል ደግሞ የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ ከቦታ ቦታና በማህረሰብ ክፍሎች መሆኑንና በከተማ 2 ነጥብ 9 ከመቶ እንዲሁም በገጠር 0 ነጥብ 4 ከመቶ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

እ.ኤ.አ በ2030 ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ማድረስ የሚለውን ራእይ ለማሳካት ሀገሮች ስምምት ተቀብለው ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም ይህን ራዕይ ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ግቦችን አስቀምጣ እየተገበረች ትገኛለች። የተቀመጡ ግቦችም እ.ኤ.አ በ2025 ሶስቱን ዘጠና ማሳካት ነው። ይህም ኤች አይ ቪ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች 95 ከመቶ የሚሆኑትን ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ፣ ተመርምረው ኤች አይ ቪ በደማቸው መገኘት ካወቁት ሰዎች ውስጥ 95 ከመቶ የሚሆኑትን የፀረ ኤች አይ ቪ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግና ህክምና ከጀመሩት ሰዎች ውስጥ ደግሞ 95 ከመቶ የሚሆኑት ህክምናቸውን በሚገባ ተከታትለው በደማቸው ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን በሚጠበቀው ልክ ዝቅ እንዲል ማድረግን ያጠቃልላል።

ከዚህ በፊት የኤች አይ ቪ ስርጭት ከፍተኛ ከነበረበት አሁን ወዳለበት 0 ነጥብ 91 ለመቀነስ ማህረሰቡ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ዘንድሮም ኤች አይ ቪን በመከላከል ረገድ የማህረሰቡን ሚና ለማጉላት የዓለም ኤድስ ቀን ‹‹የማህበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች አይ ቪ መከላከል›› ለ36ኛ ግዜ ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ተከብሯል።

አቶ ፍቃዱ ያደታ በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት /UN AIDS/ እ.ኤ.አ በ2022 ያቀረበው ሪፖርት ኤች አይ ቪ በአብዛኛው በአዋቂዎች ላይ የሚታይ ቢሆንም ሴቶች ጋር እንደሚበዛና አሁንም ሴቶች በይልጥ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭና በቫይረሱ በጣም እየተጠቁ እንዳለ ያመላካታል። ይህ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ግዜ ከኤች አይ ቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ከማፍራት አኳያ ብዙ መስራት ይጠይቃል።

ለዚህም ማሳያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ልጆችም ጭምር በኤች አይ ቪ እየተጠቁ መምጣታቸው ነው። በኤች አይ ቪ ኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም በተጓዳኝ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን ጨምሯል።

እንደሀገርም ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከል ረገድ ገና ብዙ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ የሚወጡ አሀዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ኤች አይ ቪ ኤድስ በሴቶች ላይ ይበልጥ እንደሚብስም ነው መረጃዎቹ የሚያሳዩት። በተለይ ደግሞ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ሴቶች ለኤች አይ ቪ ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው በነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል። ከአስራ አምስት አመት በታች በሆኑ ታዳጊዎች በኩልም የኤች አይ ቪ ስርጭት እንዳለ በመታየቱ በዚህ በኩልም ጠንካራ ሥራ መስራት ይገባል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት በአሁኑ ግዜ በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ ከ1 በመቶ በታች ነው። ይሁንና በከተማና በገጠር አካባቢ ሲታይ የስርጭት መጠኑ በከተማ ሰባት እጥፍ ከገጠሩ ከፍ ያለ ነው። ይህም በከተሞች አካባቢ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ያመለክታል። ምንም እንኳን የኤች አይ ቪ ስርጭት አሁንም ድረስ የቀጠለና የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ችግር እያስከተለ የመጣ ቢሆንም ስርጭቱን በመቆጣጠር ረገድ የመጡ ለውጦች አሉ።

መንግስት፣ ህብረተሰቡና አጋር ድርጅቶች ተባብረው በሰሯቸው ስራዎች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል። የኤች አይ ቪ ስርጭት ባለፉት አስር አመታት በ50 በመቶ እየቀነሰ መጥቷል። በአዲስ ኤች አይ ቪ የመያዝ ምጣኔም እንደዛው እየቀነሰ መጥቷል። በአንፃሩ የተጓዳኝ በሽታዎች መምጣትና ከአድሜ ጋር ተያይዞ የኤች አይ ቪ የሞት ምጣኔ ጨምሯል።

ሶስቱን ዘጠና አምስቶችን በሚመለከት ደግሞ ከ610 ሺ 350 ከኤች አይ ቪ ጋር ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመቱት ውስጥ ራሳቸውን አውቀው ወደ ፀረ ኤች አይ ቪ አገልግሎት የመጡ ሰዎች 84 ከመቶ ናቸው። ራሳቸውን ካወቁት ውስጥ ደግሞ የህክምና አገልግሎቱን እያገኙ ያሉት ከ95 በመቶ በላይ ሲሆኑ ህክምናቸውን በሚገባ ተከታትለው በደማቸው ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን በሚጠበቀው ልክ ዝቅ እንዲል የተደረገላቸው ከ96 በመቶ በላይ ናቸው።

ይህም ጥሩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ማሳያዎች ናቸው። ይሁንና ከቫይረሱ ጋር እየኖሩ ራሳቸውን ያላወቁ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል የኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍን በተመለከተ ጠንካራ ስራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2010 ከ46 ከመቶ በላይ የነበረውን እ.ኤ.አ በ2022 ወደ 12 ከመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ምንም እንኳን ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ቢሆኑም ባሉት እቅዶችና ከዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር በተገባው ውል መሰረት እንዲሁም ከኤች አይ ቪ ኤድስ ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር ከተገባው ቃል አኳያ ኤች አይ ቪ ኤድስን ከእናት ወደ ልጅ የመከላከል ሥራ አሁን ብዙ ሥራ ይቀረዋል። በቀጣይ እ.ኤ.አ በ2025 ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ኤች አይ ቪ ኤድስ ቢያንስ 5 ከመቶ ማድረስ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ትብብር ወሳኝ ነው።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራትና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ አካላት ተረባርበው ኤች አይ ቪን በመከላከል ረገድ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። ነገር ግን በዚህ አመት ትኩረት የሚሻው ህብረተሰቡ ማለትም ተጠቂው፣ ተጋላጩ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኤች አይ ቪ ዙሪያ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ይፈለጋል። በተለይ ደግሞ ህብረተሰቡ ኤች ኣይ ቪን በባለቤትነት ይዞ የመሪነት ሚናውን በዘላቂነት ካላረጋገጠ አሁን ባለው ሁኔታ ለመጓዝ አስቸጋሪ ይሆናል። ለዛም ነው የዘንድሮው የዓለም ኤድስ ቀን ‹‹የማህበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች አይ አይ ቪ መከላከል›› በሚል መሪ ቃል እንዲከበር የተወሰነው።

እነዚህ ይበልጥ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች ሴተኛ አዳሪዎች፣ አደንዛዥ እፅ በመርፌ የሚጠቀሙ፣ የህግ ታራሚዎች፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ ለኤች አይ ቪ አጋላጭ በሆኑ የስራ መስኮች ላይ የሚገኙ ሰዎች፣ የተለያዩ የኤች አይ ቪ ምርመራ ውጤት ያላቸው የትዳር አጋሮች፣ የትዳር አጋራቸውን በሞት ያጡና የፈቱ ሴቶችና ወንዶች፣ ለኤች አይ ቪ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ አፍላና ወጣት ሴቶች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተከሰቱባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሰዎችና ለኤች አይ ቪ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ መለዮ ለባሽ ወንዶችና ሴቶች ናቸው።

ባለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ውስጥ ኤች አይ ቪን አስመልክቶ በተሰሩ ስራዎች በአሁኑ ግዜ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ከነዚህም ውስጥ ተስማሚ ፖሊሲ መኖሩ ነው። የህብረተሰቡ ተሳትፎም እየጨመረ መጥቷል። ህብረተሰቡ ኤች አይ ቪን በባለቤትነት ይዞ የመቀጠል ሁኔታም ተፈጥሯል። በሌላ በኩል ሌሎች አጋር አካላትም ትኩረታቸውን በዚሁ በኤች አይ ቪ ላይ አድርገው እየሰሩ ነው። መንግሥትም በኤች አይ ቪ ላይ እያፈሰሰ ያለው ሃብት እየጨመረ መምጣት እንደመልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው።

ኤች አይ ቪን መከላከልና የመቆጣጠር ስራውን ለማስቀጠል መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ሆነው በተለይ አሁን የሚታዩ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች ለጤናው ስርዓት ፈታኝ ሆነዋል። ይህንኑ ተግዳሮት ባማከለ መልኩ ስትራቴጂዎችን ለመቃኘት ሙከራዎች እየተደረጉ ቢሆንም ግብአትን ከማቅረብ፣ ተገቢውን አገልግሎት ከመስጠት፣ ተደራሽነትን ከማረጋገጥና ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አኳያ አሁንም ችግሮች ይታያሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ኤች አይ ቪ ጠፍቷል፤ የለም በሚልና በተገኘው ውጤት በመርካት በህብረተሰቡ በኩል የሚታየው መዘናጋትም እንደ ስጋት የሚታይና በቀጣይ ጠንካራ ስራ ሊሰራበት የሚገባ ነው። ለህፃናት የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግና በተለይ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ኤች አይ ቪ ለመቀነስ የሚሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ግብአቶችን ከማቅረብ አንፃርም ክፍተት በመኖሩ በዚህም ላይ ተጨማሪ ስራ መስራት ይገባል።

ቀደም ሲል የነበረው ሀገራዊ እሴቶችን በመጠቀም በተለይም ወጣቶች ከጋብቻ በፊት ከግብረ ስጋ ግንኙነት መቆጠብ፣ አንድ ለአንድ መወሰንና ሌሎችም ኤች አይ ቪን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ አሁን ላይ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት መስራት ይኖርበታል። ተጋላጭና ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያም በተመሳሳይ ክፍተቶች ስለሚታዩ ክፍተቶቹን ለመሙላት ተጨማሪ ስራ መስራት ይጠይቃል።

 አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You