የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን የስፖርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አበረከተ

የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ለአዲስ ከበባ ከተማ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን የፑል ቦይ እና የኪክ ቦርድ የስፖርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

ፌዴሬሽኑ ለውሃ ዋና ሥልጠና መሠረታዊ የሆኑ የስፖርት ቁሳቁሶችን ከዓለም አቀፉ ውሃ ዋና ማህበር ጋር በመተባበር ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሠረት ደምሱ የአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን ባደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ድጋፍ እንደተደረገለት ገልጸዋል።

‹‹ታዳጊዎች ላይ በመሥራታችን በአፍሪካ የሚወዳደሩ ታዳጊዎችን ማፍራት ችለናል›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ አሁን ያበረከቱት የስፖርት ቁሳቁሶቹ ከዚህ በፊት ከውጭ ሀገራት በውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡና ዋጋቸውም ውድ እንደነበር አስታውሰዋል። ከዓምና ጀምሮ ግን እነዚህን ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎችን በማነጋገር እየተመረቱ የውጭ ምንዛሬን በማዳን አበረታች ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ ለተለያዩ ክልሎች የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቷ፣ የፌዴሬሽኑ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተለያዩ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ‹‹ድጋፉን የምናደርገው ታዳጊዎችን ማፍራት ለነገ የምንተወው የቤት ሥራ አለመሆኑን በሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ከተወሰነ በኋላ ተተኪ ስፖርተኞች የሚያስፈልጋቸው ምን እንደሆነ በመለየት ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ ወጣትና ታዳጊ ስፖርተኞች የሚሰለጥኑበት ቁሳቁስ እጥረት እንዳለባቸው ገልፀዋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ማህበር ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር ፕሮጀክቶችን ቀርፆ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የቁሳቁስ ርዳታውን ማድረግ ችሏል። ከዓለም አቀፍ ማህበሩ የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለትክክለኛው ዓላማ እንዲውልም ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድጋፎች ምን ላይ እንደደረሱም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

‹‹የውሃ ስፖርት ውድ ስፖርት ነው፣ ቢዚያው ልክም ተወዳጅ ነው፣ ኢትዮጵያ በዚህ ስፖርት በሚገባት ልክ በዓለም አቀፍ መድረክ አልተወከለችም፣ ስፖርቱም በዚያ ልክ አድጓል ብለን አናምንም›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ ይህንን ለመቀየር ፌዴሬሽኑ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ ለታዳጊዎች በማዋል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።

ፌዴሬሽኑ ዓምና ለመጀመሪያ ጊዜ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች ውድድር ያደረገ ሲሆን በዚያ ውድድር የተገኙ ስፖርተኞች በአፍሪካ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያን ወክለው እንዲወዳደሩ እያደረገ ይገኛል። በቀጣይም በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉበትን እቅድና ራዕይ በመያዝ እየተሠራ ነው።

ፌዴሬሽኑ ባለፈው ህዳር 19/2016 በጊዮን ሆቴል ባካሄደው ውድድር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚወክሉ ዋናተኞችን መርጧል። እነዚህ ዋናተኞች በዋናነት በ2024 በኳታር ዶሃ በሚካሄደው የዓለም የውሃ ስፖርቶች ቻምፒዮና የሚወክሉ ሲሆን ከወራት በኋላ በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክም የሚሳተፉ ይሆናል። ጊዜው ሲደርስም ዋናተኞቹ ሆቴል ገብተው ዝግጅት እንደሚያደርጉ ወይዘሮ መሠረት በመጠቆም፣ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋርም በቅርበት እየሠሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

በድጋፍ እርክክቡ ወቅት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃ ዋና ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ዳዊት እምሩ፣ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ በፕሮጀክት ለሚሠሩ የውሃ ዋና ስፖርቶች እግዛ ከማድረጉ ባሻገር ለውሃ ዋና ስፖርት ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የስፖርት ቁሳቁሶችን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደመቀ በበኩላቸው፣ የተደረገው ድጋፍ ታዳጊ ወጣቶችን ለማሠልጠን የሚረዳና ተተኪዎችን ለማፍራት ፌዴሬሽኑ እያደረገ ላለው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You