ኢትዮጵያ እንደ ሲሚንቶ፣ ብረትና የመሳሰሉት ፋብሪካዎች ላሉት ኢንዱስትሪዎቿ የሚያስፈልጋትን የድንጋይ ከሰል ምርት ከውጭ በማስመጣት ስትጠቀም ቆይታለች። ለእዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ አውላለች። ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በሀገሪቱ ለድንጋይ ከሰል ምርት የሚያስፈልገው ጥሬ እቃ በበቂ ሁኔታ ባለበት ነው።
ሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ምርቱን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሠራች ትገኛለች። በዚህም ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ 186 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ማምረት መቻሉን የማእድን ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ የሚመረተውን ይህን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
የማእድን ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ባደረገው ጥናት መሠረት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ360 ሚሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ይገኛል። በሌላ መረጃ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም የራሳቸውን ጥናት አድርገው በቂ ክምችት መኖሩን በማረጋገጥ በዘርፉ ልማት መሰማራታቸውን እየገለጹ ናቸው።
በሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ምርት ላይ የጥራት ጉዳይ ሲነሳ ይደመጣል። ይህን ችግር ለመፍታትም የሀገሪቱን የድንጋይ ከሰል ኢነርጂ የማቃጠል አቅም ለማሳደግና የእርጥበት ሁኔታውንም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ የማእድን ሚኒስቴር ይገልጻል። የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ከድንጋይ ከሰል አምራቾች ማህበር ጋር ዘርፉ ያለበትን ደረጃ፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ በቅርቡ ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በሰው ሃይል ሥልጠና እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ተገልጿል።
በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ዓለምአቀፍ ተሞክሮንችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሳይንሳዊ መንገድ በማምረት የድንጋይ ከሰልን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የተጠቆመው። የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ በሙሉ በመተካት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም ከማዕድን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በድንጋይ ከሰል ልማቱ ለመሳተፍ ከስድስት በላይ ኩባንያዎች እየሠሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ መካከልም አንዳንዶቹ ወደ ልማቱ የገቡ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በፋብሪካ ግንባታና በመሳሰሉት ላይ ናቸው።
በቅርቡ የተካሄደውና ከዘጠና በላይ ኩባንያዎች እንደተሳተፉበት የተነገረለት የማእድን ኤክስፖም የተለያዩ ኩባንያዎች በድንጋይ ከሰል ልማት ላይ መሠማራታቸውን አመላክቷል። ኩባንያዎቹ የድንጋይ ከሰል ምርታቸውን ናሙናም ይዘው ቀርበው ታይተዋል።
ከእነዚህ ኩባንያዎች አንዱ ‹‹ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ›› የተሰኘው ሀገር በቀል ኩባንያ ነው። ኩባንያው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል።
የኩባንያው የአቅርቦት ሰንሰለት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍቅሬ ኤክስፖው የኩባንያውን ምርቶች በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ማስቻሉን ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህም በሀገሪቱ ካሉት ውስን የድንጋይ ከሰል ተጠቃሚ ትልልቅ ፋብሪካዎች ጋር በመነጋገር የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። እስካሁን የድንጋይ ከሰል የማይጠቀሙ ኩባንያዎች እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ምክረ ሃሳብ መለገስ እና ማሳመን የሚያስችሉ ተግባሮችን ማከናወን ተችሏል።
ከኤክስፖው ጎን ለጎን ከፋብሪካዎች ጋር ከተደረገው ውይይት የተረዳነው የድንጋይ ከሰል ለመጠቀም ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ለዚህም በቅድሚያ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ቴዎድሮስ አስታውቀዋል። የብረት፣ የወረቀትና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች እና አዳዲስ ፋብሪካዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው ለመረዳት ችለናል ይላሉ።
ይህንን ችግር በቀላሉ ለመቅረፍ መጀመሪያ የድንጋይ ከሰል ለመጠቀም የሚያስችሉ ዘዴዎችን መቀየስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ይህም ሲሆን አንዳንድ ፋብሪካዎች ቴክኖሎጂዎቻቸውን በመቀየር አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮች መጠቀም እንደሚጠቅባቸው አመላክተዋል።
አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት፤ እሳቸው በኤክስፖው ላይ ከተሳተፉ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር የድንጋይ ከሰል መጠቀም የተሻለ የኃይል አማራጭ እንደሆነ ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል። በነዳጅ እና የድንጋይ ከሰል ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት አይገናኝም፤ የድንጋይ ከሰል ዋጋ በጣም ትንሽ መሆኑን መጠቆማቸውን ገልጸው፣ ልዩነቱ ለውድድር እንደማይቀርብም ጠቅሰዋል። ስለድንጋይ ከሰል የጥራት ደረጃም እንዲያውቁ በማድረግ አብሮ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት የገበያ ትስስሩን ለመፍጠር ተችሏል ብለዋል።
የማዕድን ዘርፉ ገና ያልተነካ ብዙም ያልተሠራበት ነው የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ‹‹ነዳጅንም ሆነ የድንጋይ ከሰልን የምንጠቀመው ለኃይል አገልግሎት ነው። ይህ ሲባል ደግሞ ነዳጅ በፈሳሽ መልኩ ያለ ኃይል ሲሆን የድንጋይ ከሰል ደግሞ በጠጣር መልኩ ያለ ኃይል ነው። በድንጋይ ከሰል ላይ በሀገር ውስጥ ከሠራን በእርግጠኝነት ከውጭ የሚመጣውን ብዙ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙትን ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል። ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን የሀገሪቷን ነዳጅ ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በድንጋይ ከሰል መተካት ይቻላል›› ብለዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ይህ እንዲሆን ከተፈለገ ደግሞ አሁን ያሉት ፋብሪካዎች የሚጠቀሙትን ኃይል ለመቀየር ወደሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ መምጣት ያስፈልጋል። የድንጋይ ከሰልን በኃይል አማራጭነት መጠቀም መልመድ አለበት። ለዚህም በኢንዱስትሪው ላይ መሥራት ይኖርበታል። መንግሥትም በዚህ ረገድ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ኢንዱስትሪዎቹ ሀገር ውስጥ የሚመረተውን የድንጋይ ከሰል እንዲጠቀሙ ሊያበረታታ ይገባል። ይህ ከተተገበረ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከተደረገ፣ በመረጃ የተደገፈ አሠራር ሥራ ላይ ከዋለ ፣ ፋብሪካዎች ዘመናዊ አሠራሮች ከተከሉ፣ የሰው ኃይሉ እየበቃ ከመጣ ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይቻላል። እንደዚህ አይነት ኤክስፖዎች ይህ እንዲፈጠር ያግዛሉ፤ እጅግ በጣም ጥሩና ብቃት የሚፈጥሩ ናቸው።
አምናም ሆነ ዘንድሮ የተካሄደው የማዕድን ኤክስፖ ማዕድናትን ያስተዋወቀ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ እይታዎች የተመላከቱበት ነው፤ በቀጣዩም ከዚህ በበለጠ መልኩ ሊዘጋጅ ይገባል ብለዋል። ለምሳሌ የድንጋይ ከሰል ከሀገር አንጻር ያለው አንድምታ ምንድነው? ከውጭ የሚመጣው የድንጋይ ከሰል ምርት መተካት ብቻ ነው ወይስ ነዳጅን መተካት ይችላል የሚለው በሚገባ ተጠንቶ መሥራት እንዳለበት ይጠቁማሉ። እንደዚህ አይነት ኤክስፖዎችን በማስፋት በርካታ ድርጅቶች እና ተቋማት በማሳተፍ ትልቅ ሥራዎች መሥራት እንደሚቻልም አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የኤክስፖው ዋና ዓላማ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ ፣ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግ፣ ድጋፎችን እንዲኖሩ እና አማራጮችን በማስፋት ረገድ ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር ማገናኘት ነው። ያንን ለማስፋትና ውጤታማ ቴክኖሎጂ ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ ለማምጣት አስቀድሞ ማህበረሰቡ ማወቅ አለበት ፤ በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ከተሰራ የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻላል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በድንጋይ ከሰል ጉዳይ ላይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ይገኛል። በሠለጠነ የሰው ኃይል ላይ ኢንስቲትዩት በማቋቋም ጭምር በተደራጀ መልኩ ሊሠራበት ይገባል። የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ድንጋይ ከሰል ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ነው። ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቱርክ እና የመሳሳሉት በድንጋይ ከሰል ላይ ይሠራሉ። እነዚህ ሀገሮች በኢንስቲትዩት ደረጃ የተቋቋመ የድንጋይ ከሰልን ጉዳይን የሚመራ ተቋም አላቸው። በሁሉም መልኩ የተደራጁ ናቸው።
በእኛ ሀገርም በዚህ መልኩ ከተሠራ ኢትዮጵያ በድንጋይ ከሰል በኩል ከየትኛውም ሀገር በላቀ ደረጃ ላይ ትደርሳለች ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህም አንድን ሀገር ከድህነት ለማውጣት፣ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ አብዮት ለማምጣት የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ጠቅሰው፣ መንግሥት ትልቁን ትኩረት ሰጥቶ በቴክኖሎጂም፣ በሰው ኃይል በአቅርቦትም ድጋፍ ማድረግ አለበት ሲሉ አመልክተዋል።
በሜድሮክ ኢንቪስትመንት ግሩፕ ስር ከሚተዳደሩ ኩባንያዎች አንዱ የብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው፤ ኩባንያው በኤክስፖው ተሳትፏል። ኮርፖሬሽኑ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ከኦሮሚያ ክልል ነቀምት አርባ ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አርጆ አካባቢ እየገነባ ይገኛል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ በየነ ጨመዳ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካውን ለመገንባት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ከቱርክ ተገዝተው አገር ውስጥ መግባታቸውን ይገልጻሉ። ፋብሪካው በሰዓት ሁለት መቶ ቶን የድንጋይ ከሰል ለማጠብ እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለ150 ሰዎች በቋሚነት የሥራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ኮርፖሬሽኑ የድንጋይ ከሰል እጥበት ሥራ ለመሰማራት በመንግሥት በኩል ከተመረጡ ኩባንያዎች መካካል አንዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በየነ፤ በዘርፉ መሠማራቱ በሀገሪቱ በብዛት ያለውን የድንጋይ ከሰል ጥሬ አቃ ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም እንደሚችል ገልጸዋል። ይህንንም ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ጠቁመዋል።
የፋብሪካው ግንባታ ባለፈው ዓመት መጀመሩን ጠቅሰው፤ አሁን የአፈር ሥራው ተጠናቅቆ የሲቪል ሥራው እየተሠራ ነው ይላሉ። በአካባቢው ያለው አለመረጋጋትና የጸጥታ ችግር ግንባታውን በሚፈለገው ፍጥነት አከናወኖ ሥራ ለመጀመር እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱንም ይገልጻሉ። ሌላው ዋና ተግዳሮት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደነበር ጠቅሰው፤ ይህ ችግር ተቀርፎ ለፋብሪካው ግብዓት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
የኮርፖሬሽኑ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ እየተገነባ ቢሆንም፣ የድንጋይ ከሰል ማምረት የሚቻልበት ማምረቻ ቦታ ማግኘት አለመቻሉም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን አቶ በየነ ጠቁመዋል። ‹‹እኛ የድንጋይ ከሰል የማምረቻ ቦታ ስንጠይቅ ክልሎች የሚሰጡት መልስ ቀደም ሲል ፈቃድ የወሰዱ ሰዎች አሉ፤ ከእነርሱ ጋር ሥሩ የሚል ነው። ከግለሰብ ገዝቶ መሥራት ምንም አይነት መተማመኛ አይኖርም። እንደዚህ አይነቶቹ ችግር ቢስተካከሉ ጥሩ ይሆናል ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
ኮርፖሬሽኑ ትልቅ አቅም ይዞ ታምኖበት የድንጋይ ከሰል ለማምረት ፋብሪካ ከገነባ ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆነው ጥሬ እቃ የሚመርትበት ቦታ መስጠት የግድ ነው የሚሉት አቶ በየነ፤ ‹‹እንደዚህ አይነት ችግሮች በየክልሉ ስላሉ ችግሩን ማዕድን ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ድርጅቱ እያነሳ መሆኑን አስታውቀዋል። ክልሎች የማዕድን ሚኒስቴር የሚሰጠውን አቅጣጫ መፈጸም ላይ ክፍተት እንዳለባቸው አቶ ገመቹ ጠቁመዋል።
ማዕድን ላይ የፌዴራልና የክልሎች ኃላፊነት በተመለከተ የተወሰነ ነገር እንደሌለም ጠቅሰው፣ ክልሎች የፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር የሰጠውን አቅጣጫ ለመቀበል የሚቸገሩበት ሁኔታ እንዳለም ይናገራሉ። የማእድን ጉዳይ ከላይ እስከታች ያለው መዋቅር በደንብ ትኩረት ሰጥቶት ተናብቦ መሥራት ያለበት መሆኑንም አመላክተዋል።
አሁን በማዕድን ልማት ላይ የሚታየው ማዕድን አለማለሁ ብለው የወሰዱትን ፈቃድ ብቻ ይዞ ወደ ሥራ ሳይገቡ መቀመጥ ነው ያሉት አቶ በየነ፣ ለማዕድን ዘርፉ ምንም አይነት አስተዋጽኦ የማያበረክቱ እንደነዚህ አይነት በርካታ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል። ይህም ለድንጋይ ከሰል ልማቱ ቀጣይነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስገንዝበዋል።
‹‹ፋብሪካ ገንብተን ለፋብሪካ የሚሆነውን ጥሬ እቃ የሚያቀርበው አካል አላቀርብም ቢል ችግር ውስጥ መግባታቸው አይቀርም›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ልማቱ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲሰራ ለፋብሪካዎችና ትልቅ አቅም ለሚፈጠሩ ሰዎች የድንጋይ ከሰል እጥበት ሥራውን እንዲያከናወኑ ማድረግ መልካም ይሆናል ብለዋል። እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው ሥራው በሚገባ የሚሠራበት ሁኔታ ከተፈጠረ በድንጋይ ከሰል ውጤታማ መሆን የሚቻልበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አቶ በየነ አመልክተዋል።
አቶ በየነ ኮርፖሬሽኑ የማዕድን ሚኒስቴር ባዘጋጀው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ ባለፈው ዓመትም ዘንድሮም መሳተፉን አስታውሰዋል ። እንደዚህ አይነት ኤክስፖዎች የመዘጋጀታቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የማዕድን ዘርፉን ለማስተዋወቅም ሆነ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ በእጅጉ ይጠቅማሉ፤ አምራቾችን ከገዥዎች ጋር ያገናኛሉ ብለዋል። እንደ ድርጅት ምርቶቻችን በርካታ ናቸው ያሉት አቶ በየነ፣ መድረኩ ከብዙዎች ጋር እንዲንተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር እንድንችል አርጎናል ሲሉ ገልጸዋል።
በኤክስፖ ላይ ከብዙ ድርጅቶች ጋር ተገናኝተናል የገበያ ትስስር ለመፍጠር ችለናል ሲሉ አቶ በየነ ገልጸዋል ፤ እንደዚህ አይነት ኤክስፖዎችን በየዓመቱ ማካሄዱ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ መድረኩ በየዓመቱ እየተሻሻለ እንዲካሄድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጠም በማድረግ እያሰፉ እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም