‹‹በከተማዋ የበጎ ፈቃድ ሥራ ባሕል እየሆነና ተጨባጭ ለውጥ እየመጣ ነው›› -አቶ አብርሃም ታደሰ የአዲስ አበባ የኅብረተሰበ በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የሚታወቁበት አንድ ባሕል አላቸው። እሱም በጎ መዋልና ማኅበረሰብን በቅን ልብ ማገልገል ነው። ሀገርንና ማኅበረሰብን በጋራ ሆኖ በማገዝ እውቀትንና ጉልበትን ሳይሰስቱ በመስጠት ስማቸው ይጠቀሳል። ለእዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በኅብረት መሥራት (ደቦ) ነው። ‹‹ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፤ ለሀምሳ ሰው ጌጡ ነው›› የሚለው የኢትዮጵያውያን ብሂላቸውም ሌላው የመረዳዳት አስፈላጊነት ማስገንዘቢያቸው ነው።

ባሕሉ ሲወርድ ሲዋረድ እየዳበረ የመጣና ከማኅበረሰቡ ጋር የኖረ ነው። ወገንን በነፃ ማገልገል ብሔራዊ ክብርና ኩራት የሚያሰጥ ትልቅ የክብር ምልክት ነው። መንገድ መሻገር ያቃታቸው አዛውንትን፣ አይነ ስውራንን እንዲሁም የተቸገሩ የማኅበረሰቡ ክፍሎችን በፍፁም ቅንነት ማገዝ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ብርቅ አይታይም። የቅንነትና የአክብሮት መገለጫ ነው። ይህን መሰሉን በጎነት በልዩ ልዩ አጋጣሚ በማኅበራዊ ሕይወታችን ውስጥ እናገኘዋለን።

በተቋም ደረጃ ብዙም የማይታየው ይህን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አሁን አሁን (በነፃ የማገልገል ስሜት) ተቋማዊ እንዲሆን ለማድረግ እየተሠራ ነው። ከባሕልና ልምድ ባሻገር ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖረውም መንግሥት በተለያየ ጊዜ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በበጎ ፍቃድ ማኅበረሰቡን የማገልገልና ለወገን በጎ አሻራን ትቶ የማለፍ ተቋማዊ ሥራ ውጤት እያመጣ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የዝግጅት ክፍላችንም በተቋማዊ አደረጃጀት ውስጥ ወጥ ቅርፅ ይዞ እየተሠራበት ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመዳሰስ ወድደናል። ለዚህም ወደ አዲስ አበባ የኅብረተሰብ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጎራ ብለናል።

የአዲስ አበባ የኅብረተሰበ በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብርሐም ታደሰ እንዳብራሩት፤ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በከተማዋ ሲጀመር በርካታ ተቋማት አቅም ቢኖራቸውም፣ የት ጋ ምን መሥራት እንደሚገባቸው ብዙም ግልጽ አልነበረም። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቋም ደረጃ በከተማዋ መሥራት ከተጀመረ 21 ዓመት ሞልቶታል፤ በወቅቱ የሚከናወኑ ተግባሮች ክረምትን ጠብቆ ተማሪዎችን ከዩኒቨርሰቲ በመጡ ተማሪዎች በነፃ ከማስተማር፣ አከባቢን ከማፅዳት፣ ችግኝ ከመትከልና አልፎ አልፎ ደም ከመለገስ ተግባሮች የዘለለ አልነበረም።

በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሲመሠረት ፕሮግራሞቹም እየበዙ መምጣታቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ በጎ ፈቃደኝነት ባሕል እንዲሆን በየተቋማቱ እየተሠራ ሲሆን፤ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ባሕል እየሆኑ እና ተጨባጭ ለውጥ እየመጡ ናቸው።

አሁን ያለው አሠራር እድገት አሳይቶ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጉዳይ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ መካተቱንም የማስተባበሪያው ትልቁ ስኬት መሆኑንም አቶ አብርሃም ጠቅሰዋል። ሲቲዘንሺፕ በሚባለው የትምህርት ዓይነት በጎ ፈቃደኝነት እንደ አንድ የትምህርት ክፍል ሆኖ ትምህርት መሰጠት ተጀምሯል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ይህም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተፅዕኖ እየፈጠረ መምጣቱን እንደሚያመለክት ተናግረዋል።

እንደ አቶ አብርሃም ገለፃ፤ በጎ ፈቃደኞች በበዙበት ከተማ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይጨምራል። በዚያው ልክ ደግሞ ምክንያታዊ ወጣቶች እየተፈጠሩ ይሄዳሉ። እነዚህም የማኅበረሰብን ችግር ከሩቅ የሚመለከቱ ሳይሆን ውስጡ ሆነው የሚፈቱ፣ በሀሳብ፣ በጉልበታቸው በአቅማቸው ችግር የሚፈቱ ይሆናሉ። በመሆኑም በጎ ፈቃድ ሥራ ለሀገር ግንባታ መሠረታዊ መሆኑን አመላክተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የበጎ ፈቃድ ተሳትፎው በከተማዋ ተቋማት በኩል እየሰፋ መምጣቱን ጠቁመው፣ የጤና ተቋማትም ነፃ ሕክምና በማድረግ በስፋት እየተሳተፉ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል። በማኅበራዊ ሚዲያው ያሉ የተቃርኖ ሀሳቦች መበራከትም በወጣቶች በነዋሪው የሚያስከትላቸው በርካታ አፍራሽ ተግባራት አሉ። አሁን ላይም ማኅበራዊ ሚዲያውን ለመልካም ተግባራት እና ዓላማ ለማዋል የበጎ ፈቃድ አካል ዓላማ ተደርጎ ሥልጠና እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በአዲስ ከተማ ከአውቶቡስ ተራ ጀርባ ያሉ ወጣቶች እና በአካባቢው ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ተሰባስበው ለአካባቢያቸው ሰዎች የዓይን ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ ዓይነት ሕክምናዎችን በግብዓት ጭምር ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በአብነት ጠቅሰው፣ በጎ ፈቃድ ላይ መሥራት ምን ያህል የሕሊና እርካታ እንዳለው ማኅበረሰቡ እየተረዳ እና ተሳትፎውንም እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚያው ልክ ለበጎ ፈቃድ የሚያደርገው ልግስና በትክክል ለሚመለከተው ሰው እንደሚደርስ ጠቅሰው፣ ይህንንም እየታየ ባለው የሰው ሕይወት መረዳት እንደሚቻል ገልጸዋል። የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችም እስከ ሰባተኛ ወለል ድረስ የሚደርሱ፣ በግብዓት የተሟሉ እና በገንዘብ ቢተመኑ ከፍተኛ ሀብት እና አቅም እየፈጠረ ነው። ይህ ሁሉ በሰው አስተሳሰብ ውስጥ የተፈጠረው የበጎ ፈቃድ ግንዛቤ በዚያው ልክ እያደገ መመጣቱን ያሳየ ነው ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕል እየሆነ መመጣቱን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ አጠቃላይ የበጎ ፈቃድ ተግባራቱ እየተፈጸሙ ያሉት በበጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ ከባለሀብቶች እየተሰበሰበ በሚገኝ ሀብት መሆኑን ተናግረዋል። በደም ልገሳም በወጣቶች ተሳተፎ የተገኘ ውጤት የላቀ መሆኑን አስታውሰዋል።

በየዓመቱ ያለው የበጎ ፈቃድ ተሳተፎ አያደገ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ ከ2011 ዓ.ም በፊት ይሳተፍ የነበረው የበጎ ፈቃደኛ ቁጥር ከ200 ሺህ የማይዘል ነበር ይላሉ። አሁን ግን በየፕሮግራሞቹ ባለው ድግግሞሽ ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጥ ቁጥር እየተሳተፈ ይገኛል ሲሉም ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚጠጋ ሀብት ብቻ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ሲከናወን ነበር። አሁን ላይ በአንድ ዓመት እስከ ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። ይህም በየዓመቱ በሚሰጠው አገልግሎትም፣ ባለው ተሳትፎ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት እየሰረጸ ከመምጣቱ አኳያ እድገት እንዳለው ማየት የሚያስችል ነው።

በየዓመቱ የነበረው የቤት እድሳት አፈፃፀም ሲታይም ቢዘያው ልክ ዕድገት ያለው ነው። ያለፈውን ክረምት ጨምሮ ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ውስጥ በየጊዜው ለውጥ ታይቷል። በ2011 አንድ ሺህ 75 ቤት ነው ተገንብቶ ለችግረኞች ተላልፎ የተሰጠው። ይህ አኃዝ በ2015 ግን ወደ ስድስት ሺ 415 ቤት ደርሷል። በአጠቃላይ ያለፈውን ክረምት ጨምሮ ወደ 24 ሺ 236 ቤቶች ግንባታ ተፈፅሟል። ከወጪም አንፃር በተመሳሳይ እያደገ መጥቷል።

ባለፈው ዓመት እነዚህን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ለማከናወን በታቀደው መሠረት ሁሉም ፕሮግራሞች መከናወናቸውን አቶ አብርሃም ገልጸው፣ አንዳንዶች ከእቅድ በላይ የተፈጸሙ እንደነበሩም ጠቅሰዋል። በከተማዋ በሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ውጤታማነት ከከተማ አስተዳደሩ ጀምሮ የበላይ አመራሩ እና በየደረጃው የሚገኘው የአስተባባሪ ኮሚቴ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። እነዚህ አካላት ከተሳትፎ በዘለለም ተግባራዊ እንቀስቃሴዎችን እያደረጉ ናቸው። በከተማዋም ሆነ በወረዳ የሚገኘው አመራርም ራሱ በበጎ ፈቃድ ከደመወዙ እየቆረጠ ይሳተፋል፤ በዚያው ልክ ደግሞ ኅብረተሰቡን ያስተባብራል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከዚህም ባሻገር ሴክተር ተቋማት ተጠሪ ተቋሞቻቸውንና ባለድርሻውን በማስተባበር ግንባታውን ያካሂዳሉ፣ ማዕድ ያጋራሉ። ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ደሞዝተኞችም ተቋሞቹ ባሉበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች የቤት እድሳት፣ ግንባታ፣ ማዕድ ማጋራት እና ሌሎችንም የበጎ ተግባራት ያከናውናሉ።

ከጥራት አንጻር ከተመለከትን በጣም የተሻሉ እና ከጊዜ ወደጊዜ አዳጊ የሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥም ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

አቶ አብርሃም እንዳስታወቁት፤ የቤት እድሳትን በተመለከተ አሁን ላይ የሚገነቡ ቤቶች ላይ ጥራት ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም። በአፈጻጸም ከ50 በመቶ በላይ ጥገና ካልተደረገላቸው ጥገና ተደርጓል ብለን አንይዝም። በጭቃ የምናካሂዳቸው ግንባታዎች የሉም በሚባል ደረጃ በጣም ጥቂት ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ቤቶች የሚሠሩት በብሎኬት በሲሚንቶ ግራውንድ ላይ የሚሠሩ እና ምንም ፎቅ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ በጥራት የሚሠሩ ናቸው፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ከሆኑ ደግሞ እቃ አሟልተንም ጭምር በመስጠት ወደቤቱ እንዲገቡበት ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች አንዱ ሰው ተኮር ተግባር መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፣ በቀጣይም ተቋማዊ አቅምን እያጠናከርን በመሄድ በአሠራር እና በአካሄድ የተደገፈ ቀጣይነቱን ሊያረጋግጥ የሚችል አሠራር ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ እንሠራለን ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በ2016 ዓ.ም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዓመቱን ሙሉ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት የበጋ በጎ ፍቃድ ተጀምሮ ወደ ሥራ ገብቷል። ክረምት ላይ በርካታ ወጣቶች እረፍት ላይ የሚሆኑበት ጊዜ ሲሆን ሌላው ደግሞ ብዙ ሰዎች ወደዚህ ተግባር ለመግባት ፍቃደኝነታቸው የሚጨምርበት ወቅት ነው። በመሆኑም የክረምት በጎ ፍቃድ ከግንቦት ወር ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ድረስ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ በስፋት ይሠራል።

ይህ ተግባር በበጋ ወቅት መቋረጥ የለበትም። ከዚህ ቀደም የነበረው በክረምት ወቅት ነበር ፤አሁን ግን 365 ቀን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዳይቋረጥ እንሠራለን ሲሉ ይገልጻሉ። ከኅዳር ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር ድረስ በምናካሂደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አንድ ሚሊዮን በጎ ፍቃደኞችን ለማሳተፍ ታቅዷል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በዚህም ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንሰጣለን፤ ወደ 700 ሺህ የሚጠጋ የከተማችን ነዋሪ ደግሞ ከነዚህ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የክህሎት ሥልጠናዎች፣ የልዩ ፍላጎት ሥልጠናዎች፣ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ፣ የደም ልገሳ፣ በጎነት በሆስፒታል ነፃ ሕክምና የኤች አይ ቪ መከላከል ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ የመንገድ ትራፊክ፣ የአካባቢ ሰላም፣ ኪነ-ጥበብ፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ድጋፍ እና “ሙያዬ ለሀገሬ” የሚሉ እና የአደጋ መከላከል በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በነዚህ መርሐግብሮች ተካተው የሚሰጡ ይሆናል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ራሱን የቻለ ተቋም ያለው አዲስ አበባ ብቻ ነው ያሉት አቶ አብርሐም፣ አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በፖሊሲ ለማስደገፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ነው ያስታወቁት። ፖሊሲው ከፀደቀ በሕግ ደረጃ ሲቋቋም የተሻለ አቅም ይፈጠራል ይላሉ።

በተቋማት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የውዴታ ግዴታ እንዲሆን፣ ተማሪዎች በሰፊው እንዲሳተፉ ቀጣይ በሰፊው የሚሠራ መሆኑን አመላከተዋል። የበጎ ፈቃድ ሥራ ተግባራቱ በኢኮኖሚ፣ በሀብት ክፍፍል የምናረጋግጥበት ነው፤ ባለሀብቱ አንድ ፎቅ ሠርቶ 60፣ 70 እና መቶ ሚሊዮን ብር ሲያወጣ ለሌላው ኅብረተሰብ እድል እየፈጠረ ነው። የሥራ እድልም ፈጠራል። ማኅበራዊ ችግር እንፈታለን ሲሉ ያብራራሉ።

ታዳጊዎችም ላይ የምንሠራው ሥራ አለ። በሕጻናት ላይ በምንሠራው ሥራ 400 ሕጻናት ደጋፊ እንዲያገኙ አድርገናል። ዛሬ በበቂ የሚመገቡት አግኝተው መማር ከቻሉ ለነገ ተስፋ መሆን ይችላሉ ማለት ነው። እነዚህ ሕጻናት ድጋፍ ያገኙት የክረምት በጎ ፍቃድ ላይ ሲሆን 100 የሚሆኑትን ሕጻናት አንድ ባለሀብት ሙሉ ለሙሉ ስፖንሰር አድርጓቸዋል። እንደነዚህ አይነት ሥራዎች በደንብ እየቀጠሉ ሲሄዱ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚመጣው የመደጋገፍ ልማድ እየጨመረ ይሄዳል። ዋናው አቅም የሚመጣው ከማኅበረሰብ ሲሆን እኛ በሪፖርት ውስጥ የምናካትተው እኛ የሠራነውን ነው። ነገር ግን የሚፈለገው ማኅበረሰቡ ልማድ እያደረገው ከሄደ ሥራው እየሰፋ ይሄዳል።

በሌሎች ሀገራት ለምሳሌ በስዊድን አስፓልት ቢበላሽ የሚጠግኑት የበጎ ፍቃድ ማኅበራት ሥራውን ይሠራሉ፤ የሆነ ቦታ ላይ አደጋ ቢከሰት በበጎ ፍቃድ ከቤታቸው ተነስተው የሚወጡ ሰዎች አሉ። ከዚያም የተፈጥሮ አደጋም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ ካጋጠመ ይህንን አገልግሎት ሰጥተው ይመለሳሉ። ይህ በገንዘብ አይሸፈንም፤ የሆነ ሰዓት ላይ በጣም ብዙ አቅም የሚጠይቅ ሰው ተቀጥሮ ሊሸፈን የማይችል ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ሲሆን በጎ ፍቃደኞች ያስፈልጋሉ።

በአደጋ መከላከል ላይ ከ450 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች አሰልጥነናል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በቀጣይ አደጋ ሲያጋጥም እነዚህ ልጆች ድጋፍ ይሰጣሉ ብለዋል። እነዚህ ነገሮች እያደጉ ሲሄዱ በጎ ፍቃደኝነት ይቀራል ማለት ሳይሆን ባሕሪው የሚፈልገው አገልግሎት እየሰፋ ይሄዳል። ማንም ሰው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት ይችላል፤ በገንዘብ በጉልበት ማገዝ ይችላል። ሲሉም አብራርተዋል።

በሐኪም ቤቶች ላይ የሚሠሩ በጎ ፍቃደኞች ከክልል ለሚመጡ ታካሚዎች የሚታዘዝላቸውን መድኃኒት ከተፈለገው ቦታ በመሄድ ይገዙላቸዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ሰዎች በመሆናችን የሆነ ጊዜ ላይ በተለያየ አደጋ ምክንያት በጎ ፍቃደኞች ሊያስፈልጉን ይችላሉ ይላሉ። ‹‹ሰዎች በመንገድ ላይ ሲወድቁ ሰዎች ይሸሻሉ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ግንዛቤ ላይ በሰፊው በመሥራት የሚረዳውም እርዳታ የሚያስፈልገውም ሰው እንዳይጎዳ እናደርጋለን ሲሉም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። ሁሉም ሰው የበጎ ፍቃድ ተሳትፎዎችን እንዲያጠናከርም መልዕክት አስተላለፈዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You