የአበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአትሌቶች አበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀል። ጉዳዩ ከቁጥጥሩ ውጪ እንደሆነና አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባም ፌዴሬሽኑ ከትላንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ኢትዮጵያ የአትሌቶች አበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ መመደቧን ተከትሎም ምን ይደረግ በሚል ከ20 በላይ ባለድርሻ አካላት ውይይት እንደሚያደርጉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፀረ-አበረታች መድኃኒቶች ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን በማከናወን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት ቢሆንም ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን ገልጿል። ችግሩ ከቁጥጥሩ በላይ በመሆኑም ጉዳዩን በበላይነት የሚመራ ሀገራዊ ኮሚቴ አንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል። አበረታች መድኃኒት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ስጋት ውስጥ የከተተ ጉዳይ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድና ከስሩ ነቅሎ ለመጣል የብዙ ባለድርሻ አካላት ርብርብን እንደሚጠይቅና ለዚህም በዛሬው ዕለት አስቸኳይ የባለድርሻ አካላት ስብሰባ መጠራቱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ይህ ስብሰባ የተጠራው ከወር በፊት ፌዴሬሽኑ ለባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ሲሆን ከብሔራዊ ፀረ አበረታች መድኃኒት ባለሥልጣን እንዲሁም ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ስብሰባዎች ከተካሄዱ በኋላ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ግርማ ለማ በመግለጫው እንደተናገሩት፣ በችግሩ ዙሪያ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሰፊ ዘመቻ ተደርጎ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተሰጠ ቢሆንም ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። ወንጀሉን ፈጽመው የሚያዙ ግለሰቦሕ ስፖርት ሚኒስቴር አስቸኳይ የባለድርሻ አካላት ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቀል። በዚህም ኦሊምፒክ ኮሚቴን፣ የፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲን፣ የፌደራል ፖሊስን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትንና የብዙኃን መገናኛን ጨምሮ 23 የሚደርሱ ባለድርሻዎች የሚሳተፉበት ስብሰባ ዛሬ ይካሄዳል።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ቡድን ኃላፊ ዶክተር አያሌው ጥላሁን በበኩላቸው፣ አትሌቲክስ በብዙ ትግልና በተለያዩ አካላት ፍላጎት የተጠመደ እንደሆነ ጠቁመው፤ ዘርፉ በርካታ ተዋናዮች የሚሳተፉበት በመሆኑ አትሌቲክሱ በተፅዕኖ ስር እንደወደቀ አስረድተዋል። በአትሌቲክስ የሚወሰዱና የሚከለከሉ ንጥረ ነገሮች ቢኖሩም መቼ፣ ማንና እንዴት የሚለው ጉዳይ አሳሳቢና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ካለው ችግር ጋር ጥንቃቄ እንዲደረግ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣትም አክለዋል። ‹‹ጉዳዩ እየሞቀና እየበረደ ስር ወደ መስደድ እየተጓዘ በመሆኑ ትክክለኛ ባለቤት ኖሮት እልባት ማግኘት ይኖርበታልም›› ብለዋል።

ተባብሶና አይኑን አፍጦ የመጣውን የአበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት እንዲባባስ የሚያደርጉ ብዙ ተዋናዮች ቢኖሩም ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው አይገኝም። በዚህም ውስጥ ለአትሌቶች ድጋፍ በመስጠት ሽፋን የአትሌቶች ተወካዮች፣ ከውጪ የሚመጡ አሠልጣኞች፣ ደላሎች ነገሩን እያባባሱና ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን እያደረጉ ነው። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ባለመሥራታቸው ችግሩ ሰፊና ስር እየሰደደ ሊመጣም ችሏል።

ለዚህም ማንም የውጪ ዜጋ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይጠይቅ መድኃኒቶችን ይዞ አትሌቶች ልምምድ በሚሠሩበት ስፍራ ድረስ ዒላማ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ሙያው ከሚፈቅደው ሕግ ውጪ አንዳንድ የመድኃኒት መደብሮችና የጤና ባለሙያዎች መድኃኒቱን እንደፈለጉ እያቀረቡ አትሌቶች የሚሠሩባቸውን ቦታዎች ለዚሁ ዓላማ የሚከፈቱ በመሆኑ የችግሩ ስፋት የከፋ ሆኗል። ይባስ ብሎ ኬንያ በዚህ ጉዳይ ነቅታ አትሌቲክሷን ከዚህ ለማላቀቅ በምታደርገው ጥረት ከሀገሯ ያባረረቻቸው ደላሎች፣ የአትሌት ተወካዮችና አሠልጣኝ ነን የሚሉ ግለሰቦች ኢትዮጵያን መሸሸጊያ አድርገው አትሌቲክሱን እየመረዙ ይገኛሉ።

ይሄ ጉዳይ ተባብሶ የቀጠለና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚጠረጠሩ አትሌቶች በመብዛታቸው ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድኃኒቶች ባለሥልጣን ኢትዮጵያን ለመቅጣት አሰፍስፎ እየጠበቀ እንደሚገኝ በመግለጫው ተጠቁማል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ መሆኗና ከአበረታች መድኃኒት ጋር በተያያዘ ጉዳይ የሚጠረጠሩና የሚያዙ አትሌቶች መከሰታቸውን ተከትሎ በጥርጣሬ ውስጥ መግባቷ ተጠቅሷል። በኤሽያና በተለያዩ ሀገራት የሚወዳደሩ አትሌቶች በጉዳዩ እየተጠረጠሩ በመሆኑ ኢትዮጵያ ስጋት እንዲደቀንባት አድርጓል። ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን ለውድድር ስለማይልክ በቱሪስት ቪዛና በንግድ ቪዛ እየወጡ ውድድራቸውን የሚያደርጉ አትሌቶችም ችግሩን እንዲባባስና ከቁጥጥር እንዲወጣ አድርገዋል።

ፌዴሬሽኑ መሄዳቸውን እንኳን የማያቅና ተወዳድረው ሲያዙ ብቻ የሚያውቅ በመሆኑ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር ለመፍትሔው ለመምከር እንደወሰነ ጠቁሟል። ችግሩን ለመቆጣጠር የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቢወጣም በአግባቡ ሥራ ላይ እንዳልዋለና ችግሩን መቅረፍ እንዳልቻለም ተጠቅሷል። ችግሩን ከሚያባብሱ አካላት ይልቅ የቅጣት እርምጃው አትሌቶች ላይ ብቻ የሚበረታ በመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ሆኖ እንዲቀጥል አስገድዷል።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ባለሙያ ቅድስት ታደሰ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በአበረታች መድኃኒቶች ስጋት የሚባል ደረጃ እንደ ደረሰና ችግሩን ዜሮ ለማድረግ እንደ ተነሱ ተናግረዋል። ነገሩ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የንጹሕ አትሌቲክስ ስም የሚያጠለሽ ስለሆነ ምንም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ የተባባሰው በጎዳና ውድድሮች በተለይም አሜሪካ፣ የአፍሪካ ሀገራት እና ኤሺያ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህም አጓጊ ሽልማቶችና ከጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ውጤታማ በመሆናቸው ከተጋላጭ ሀገራት ተርታ እንዳስገባቸው ባለሙያዋ አክለዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You