በኢንዱስትሪ መናኸሪያነታቸው ከሚታወቁት የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ‹‹የበረሃዋ ገነት›› ድሬዳዋ፣ የነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይነትና አስደናቂ ኅብር ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹና ተመራጭ ያደርጋታል። ድሬዳዋ በማምረቻ ዘርፍ (Manufacturing Sector) የተሻለ የኢንቨስትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታ አላት። የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ተከትላ የተቆረቆረችውና ‹‹የኢንዱስትሪ ኮሪደር›› በመባል የምትታወቀው ድሬዳዋ፣ በንግድ ማሳለጫነቷ ተጠቃሽ ከተማ የነበረች ቢሆንም፣ ይህ የንግድ መነኻሪያነቷ ተቀዛቅዞ ቆይቷል።
የድሬዳዋ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከተማዋ ቀደም ሲል ወደምትታወቅበት የንግድ መናኸሪያነቷ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። የዚህ ጥረቷ ማሳያ ከሆኑ ተግባራት መካከል አንዱ ደግሞ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ነው። ይህ እንቅስቃሴዋም ሰምሮላት ውጤት እያገኘችበት ነው። የከተማዋን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ችግሮችን በመፍታት የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ዘርፉ በቦርድ እንዲመራ ተደርጓል። ይህም ሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉዳዮች በቦርዱ እየታዩ የዘርፉ ችግሮችም ሆኑ የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈጣንና የተደራጀ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ የተወሰደ ርምጃ ነው።
ከተማዋ ባለፈው 2015 በጀት ዓመት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ጥሩ አፈፃፀም አሳይታለች። በበጀት ዓመቱ ለ450 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት ታቅዶ፣ 347 ባለሀብቶች (በአገልግሎት 206፣ በማምረቻ 104፣ በኮንስትራክሽን 22፣ በግብርና 15) ፈቃድ ወስደዋል። ባለሀብቶቹ ያስመዘገቡት የካፒታል መጠን ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ ከ21ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድሎችን የመፍጠር አቅም አላቸው።
ባለፈው የበጀት ዓመት ስኬታማ አፈፃፀም ያሳየው የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት፣ በ2016 የበጀት ዓመትም የተሻለ ስኬት እንዲያስመዘግብ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ጥናትና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አቶ አበራ መንግሥቱ ይገልፃሉ።
አቶ አበራ እንደሚሉት፣ በ2016 በጀት ዓመት ከ130 ቢሊዮን ብር በላይ ለሚያስመዘግቡ 500 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል። በዚህ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የከተማዋ ኢንቨስትመንት ዘርፍ መልካም አፈፃፀም ተመዝግቦበታል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሚያዘጋጀውና በየሦስት ወሩ በሚካሄደው የዘርፉ አስፈፃሚ አካላት ፎረም ላይም አፈፃፀሙ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተመስክሮለታል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ125 ባለሀብቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ 113 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲወስዱ ማድረግ ተችሏል። እነዚህ ባለሀብቶች ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ10ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጥናትና ፕሮሞሽን፣ የፈቃድ፣ የክትትልና ድጋፍ፣ ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት የተሰኙ የሥራ ክፍሎች ተቀናጅተው ባለሀብቶች በድሬዳዋ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ፤ ፈቃድ፣ ክትትልና ሌሎች የዘርፉን አገልግሎቶች እንዲያገኙ እያደረጉ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አበራ፣ የአገልግሎት አሠጣጡንና የመሠረተ ልማት አቅርቦቱን ቀልጣፋና የተሻለ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመርና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ውጤታማነት ለማሻሻል እየተሠራ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። የአገልግሎት አሠጣጥ ጥራትን ለማሻሻል በተደረጉ ጥረቶች አንዳንድ የኢንቨስትመንት ዘርፍ አገልግሎቶችን በኦንላይን (Online) መስጠት ተጀምሯል። የኢንቨስትመንት ፈቃድንም በኦንላይን ለመስጠት ጥረት ይደረጋል።
እንደሳቸው ገለፃ፣ በመሠረተ ልማት አቅርቦት ረገድም ከተማዋ የተሻለ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን እውን በማድረግ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር ጥረት እያደረገች ትገኛለች። 202 ሄክታር ስፋት ያለው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር የራሱ የኃይል ማከፋፈያ (ሰብስቴሽን) አለው። የኃይል ማከፋፈያው ከከተማው የኃይል አቅርቦት ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ የኃይል መቆራራጥ ስጋት የለበትም። ባለሀብቶችም ለዚህ አበረታች የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጥሩ ዕይታ እንዳላቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የኢንዱስትሪ መንደሩ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ በኢንቨስትመንት ተቋማት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያሳድር ለነበረው የኃይል አቅርቦት ችግር አስተማማኝ መፍትሄ የሰጠ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ነው።
የኢንዱስትሪ መንደሩ የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገድም በቀጣይ የሚሻሻሉ ክፍሎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንገዱ በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኝ ነው። በበጀት ዓመቱ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማትን ከሚመራው መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር የኢንዱስትሪ መንደሩን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ደረጃውን ለማሻሻል ታቅዷል። ድሬዳዋ እምቅ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ያላት በመሆኗ እንዲሁም ከከተማዋ የውሃ አቅርቦት ውስጥ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት የመደበው ውሃ በመኖሩ፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የውሃ አቅርቦት ችግር አያጋጥማቸውም።
በድሬዳዋ በኢንቨስትመንት ለሚሠማሩ ባለሀብቶች በጥናት የተለዩ 36 የፕሮጀክት ዘርፎች (Project Profiles) አሉ። ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ኮሪደር ትሆናለች ተብሎ ስለሚታሰብ በጥናት ከተለዩት ፕሮጀክቶች መካከል 19 የሚሆኑት የአምራች ዘርፍ ፕሮጀክቶች ናቸው። እነዚህን ዘርፎች ለባለሀብቶች የማስተዋወቅ ተግባራት ይከናወናሉ። ባለሀብቶች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዲታዩ ከተደረገ በኋላ ከ30 ደቂቃዎች ባልበለጠ ጊዜ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያገኙ ይደረጋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከከተማዋ የኢንቨስትመንት አቅምና ራዕይ አንፃር ብዙ ባለሀብቶች በማምረቻ ዘርፍ እንዲሰማሩ ፍላጎት አለው። ይሁን እንጂ ባለሀብቶቹ የእውቀት ደረጃቸው፣ የገንዘብ አቅማቸውና የሥራ ልምዳቸው ውጤታማ ሊያደርጋቸው በሚችለው ዘርፍ የመሠማራት ምርጫቸው የተጠበቀ ይሆናል።
‹‹መሬት ከወሰዱ በኋላ ፈጥነው ወደ ሥራ የማይገቡ ባለሀብቶች አሉ። በዚህም መሬት ወስደው ሥራ ያልጀመሩና አፈፃፀማቸው የተጓተተ 88 ባለሀብቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በበጀት ዓመቱ ሁለተኛ ሩብ ዓመት እነዚህን ባለሀብቶች ወደ ሥራ ማስገባት ከተቻለ ትልቅ እመርታ ማስመዝገብ ይቻላል። በባለሀብቶች በኩል የሚነሱ አንዳንድ የግብዓት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮችም አሉ›› በማለት ይገልፃሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህም መሠረት የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሬት ወስደው በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን ማከናወን ያልቻሉ ባለሀብቶች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሾችን በመስጠት እና ርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ የነበሩ የአፈፃፀም ክፍተቶችን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ባለሀብቶችን በማበረታታት ረገድ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጁትንና የሚተገበሩትን የማበረታቻ ማዕቀፎችን መሠረት በማድረግ መሬት ከሊዝ ነፃ የማቅረብ እንዲሁም ቀልጣፋ አሠራሮችን የማመቻቸት ተግባራትን ያከናውናል። ‹‹የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት ዋናው የትኩረት አቅጣጫ የማምረቻው ዘርፍ ነው። የከተማ አስተዳደሩም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለው በዚሁ ዘርፍ ላይ ነው። የኢንቨስትመንት አዋጁም (አዋጅ 1180/2012) ለማምረቻ ዘርፉ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም በአዋጁ መሠረት የተቃኘ ነው›› ይላሉ።
የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ የተጣለበት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና (Dire Dawa Free Trade Zone)፣ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ ይታወሳል።
አቶ አበራ እንደሚሉት፣ ድሬዳዋ በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የላቀ አፈፃፀም እንድታስመዘግብ ከሚያስችሏት መልካም እድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱና ዋናው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ነው። በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሀብቶች በነፃ የንግድ ቀጣናው ለመሠማራት ፍላጎት እያሳዩ ነው። ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የባለሀብቶች ፍሰት እየታየም ይገኛል። ነፃ የንግድ ቀጣናው ወደ ከተማዋ የሚገባውን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
‹‹ነፃ የንግድ ቀጣናው በሚዘጋጅለት ህጋዊ ማዕቀፍ መሠረት ወደ ሥራ ሲገባ በከተማው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይታሰባል። ብዙ ችግሮችን ይፈታል፤ ኢንቨስትመንትንም ያሳልጣል። በእርግጥ ነፃ የንግድ ቀጣናው የሚመራውና የሚተዳደረው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ነው። በአሁኑ ወቅትም ብዙ ባለሀብቶች ከውጭ እየመጡ ነፃ የንግድ ቀጣናውን እየጎበኙ ይገኛሉ፤ እኛንም መረጃ ይጠይቁናል›› በማለት ነፃ የንግድ ቀጣናው ለድሬዳዋ ኢንቨስትመንት ማደግ ስለሚኖረው አወንታዊ ሚና ያስረዳሉ።
‹‹የአንድ መስኮት አገልግሎት ባለሀብቶች ለፕሮጀክቶቻቸው አስፈላጊ የሆኑ የግብዓት ጥያቄዎችን በቀላሉ እንዲያቀርቡና በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል እንዲሁም የሀብት (የጊዜና የገንዘብ) ብክነትን ለማቃለል የሚረዳ ነው›› የሚሉት አቶ አበራ፣ ለባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እና መሬት በመስጠት እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ስራ እንዲጀምሩ በማስቻል የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሠራርን መዘርጋትና ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም፣ የኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት ለኢንቨስትመንት ስኬት ግብዓት የሆኑ ተግባራትን በእኩል ፍጥነትና ብቃት እንዲፈፅሙ ትኩረት መስጠት መዘንጋት እንደሌለበት ያስገነዝባሉ። በዚህም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለድርሻ ሆነው የሚንቀሳቀሱት ተቋማት እቅድን ከማስተዋወቅ ጀምሮ እየተናበቡ ለመሄድ ያደረጉት ጥረት ዘላቂ እንዲሆን አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ የሥራ ፍጥነትና ብቃት ሊኖር እንደሚገባ አቶ አበራ ይናገራሉ።
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ባለሀብቶችን ወደ ከተማዋ ሲያስገባ ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው። ማኅበረሰቡ ከኢንቨስትመንት ሥራዎች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ይጠበቃል። በዚህ ረገድ በከተማዋ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለከተማዋና አካባቢው ህብረተሰብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሏቸው አቶ አበራ ይገልፃሉ።
እሳቸው እንደሚያብራሩት፣ በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች በሚያከናውኗቸው የኢንቨስትመንት ተግባራት አማካኝነት የሥራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ፣ ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግና አቅመ ደካሞችን የማገዝ ተግባራት የዚህ ማሳያ ናቸው። የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችንም ይሠራሉ። ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን በሚሠሩባቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራትን ስለሚያከናውኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ በዚህ ተግባር በኩል ተጠቃሚ ይሆናል። ይህ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ማኅበረሰቡ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል።
በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ፣ ባለሀብቶች ከውጭ በሚያመጧቸው ባለሙያዎች የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ የተግባር ልምምድ የውጭ ዜጎችን ተክተው እንዲሠሩና የቴክኖሎጂ ሽግግሩ እውን እንዲሆን በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፤ በርካታ አምራቾች ይህን አሠራር ተከትለው የኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም