የዓለም አትሌቲክስ በየዓመቱ ድንቅ አቋም ያሳዩ አትሌቶችን አወዳድሮ በደማቅ ሥነሥርዓት ይሸልማል። ይህን ታላቅ ሽልማት ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እኤአ በ1999፤ ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እና በ2005፣ መሠረት ደፋር በ2007፣ ገንዘቤ ዲባባ በ2015 እንዲሁም አልማዝ አያና በ2016 ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። ከአልማዝ አያና በኋላ ግን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባለፉት ሰባት ዓመታት ሽልማቱን ማሸነፍ አልቻሉም። በነዚህ ዓመታት ለሽልማቱ የታጩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡
በውድድር ዓመቱ በአንድ የማራቶን ውድድር ብቻ ለማመን የሚከብድ ድንቅ ብቃት በማሳየት ክስተት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ትልቁን የዓለም አትሌቲክስ ሽልማት ከሰባት ዓመት በኋላ በማሸነፍ ሰባተኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት መሆን ችላለች። ትዕግስት በ2023 የውድድር ዘመን በማራቶን ያስመዘገበችው የላቀ ውጤት ለሽልማቱ አብቅቷታል። ባለፈው መስከረም የበርሊንን ማራቶን ያሸነፈችበት 2:11:53 አዲስ የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ሲሆን፣ ቀድሞ ከነበረው ክብረወሰን በ2 ደቂቃዎች ከ14 ሰከንዶች የተሻለና ሰፊ ልዩነት ያለው ነው። የሴቶችን ማራቶን የዓለም ክብረወሰን ያሻሻለች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት የሆነችው ትዕግስት ሽልማቱን ለማሸነፍ በአንድ ውድድር ብቻ ያሳየችው ለማመን የሚከብድ ብቃት በቂ ሆኗል፡፡
በተመሳሳይ ባለፈው ቅዳሜ የ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ የዓመቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። የዓለም አትሌቲክስ በየዓመቱ በሚያካሂደው ሽልማት አንዱ ዘርፍ የስፖርታዊ ጨዋነት ሲሆን ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ ለተሰንበት በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ሲያጠናቅቁ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወቃል፡፡
በዚያ ውድድር ወቅት በፉክክሩ መጨረሻ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ሜዳሊያ ለማጥለቅ ጥቂት ሲቀራት መውደቋ አይዘነጋም። በወቅቱ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ለተሰንበት ባገኘችው ውጤት ደስታዋን ከመግለፅ ይልቅ ወደ ወደቀችው ሲፈን በመሄድ እጇ ላይ የደረሰውን ጉዳት እየተመለከተች ስታፅናናትና ማዘኗን ስትገልፅላት ታይታለች። ይህም ድርጊቷ የዓመቱን የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት እንድታሸንፍ አድርጓታል።
የዓለም አትሌቲክስ ከትናንት በስቲያ ምሽት በፈረንሳይ ሞናኮ ባካሄደው የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ሽልማት ሥነሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የሽልማት ዘርፎቹን ዘርዘር አድርጎ ሸልሟል። የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ሽልማት የዓለም አትሌቲክስ ከዚህ ቀደም ከተለመደው የወንድ እና ሴት አትሌቶች ጥቅል አሸናፊነት የሽልማት አሰጣጥ ዘርፍ በብዙ መንገድ ባሻሻለው መሠረት የዘንድሮ አሸናፊዎች በመም፣ በሜዳ ተግባራት እና ከስታዲየም ውጭ ውድድሮች በሚሉ ዘርፎች ምርጥ አትሌቶችን ሸልሟል።
በዚህም መሰረት በመም ውድድሮች የዓለም ሻምዮኖቹ ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕየጎን እና አሜሪካዊው ኖሃ ሊልስ የዓመቱ ምርጥ ሲባሉ፣ ስዊድናዊው ሞንዶ ዱፕላንቲስ እና ቬንዙዌላዊቷ ዩሊማር ሮሃስ ደግሞ የዓመቱ ምርጥ የሜዳ ተግባራት ውድድሮች አሸናፊዎች ሆነዋል።
ልክ እንደ ትዕግስት አሰፋ ሁሉ የዓለም የማራቶን ክብረወሰንን ቺካጎ ላይ 02:00:3 በሆነ ሰዓት ያሻሻለው ኬንያዊው ኬልቪን ኪፕቱም በበኩሉ የዓመቱ ከስታዲየም ውጭ ውድድሮች ምርጡ ወንድ አትሌት ሽልማትን አሸንፏል።
ኢትዮጵያዊቷ መዲና ኢሳ የመጨረሻ እጩ ተወዳዳሪ በነበረችበት የዓመቱ ተስፋ የሚጣልባት ታዳጊ አትሌት የሽልማት ዘርፍ ኬንያዊቷ ፌይዝ ቼሮቲች ስታሸንፍ በወንዶች ዘርፍም የሀገሯ ልጅ የሆነው የ800 ሜትር ተወዳዳሪው ኢማኑኤል ዋኒዮኒ አሸናፊ ሆኗል።
ትዕግስትና ኬንያዊቷ የ1500 ሜትር የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮን አትሌት ፌይዝ ኪፕየጎን ይህን ሽልማት ሲያሸንፉ ከሰባት ዓመት በኋላ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን ሴት አትሌቶች ናቸው። ከፕዬጎን ይህን ሽልማት ስታሸንፍ የመጀመሪያዋ ኬንያዊት ሴት አትሌትም ነች።
በዚህ ሽልማት ላይ በውድድር ዓመቱ የዓለም ክብረወሰን በተለያዩ ርቀቶች ያሻሻሉ አትሌቶች በጃፓኑ ኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ‹‹TDK›› አማካኝነት እያንዳንዳቸው የመቶ ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ። የዓመቱ ምርጥ አትሌት በመባላቸውም ተጨማሪ ሰባ ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም