ዛሬ ላይ ከዘመናዊነት ጋር ተያይዞም ይሁን በሌሎች አስገዳጅ ምክንያቶች በከተሞች አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል በእጅጉ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት፣ በመዲናችን አዲስ አበባ ሁሉም ሥራዎች ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው፡፡ በመኖሪያ ቤት ካሉ የማብሰያና መገልገያ እቃዎች እስከ ግዙፍ ፋብሪካዎች ድረስ የሚንቀሳቀሱት በኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡
የእንዳንዱ ህብረተሰብ ሕይወት ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ከመሆኑም አኳያ፤ ማህበረሰቡ ‹‹ዕራት እና መብራት አይንሳችሁ›› በሚለው ብሂሉ የመብራትን አስፈላጊነት ይገልጸዋል፡፡ ስለዚህም የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ለአፍታም እንዲቆራረጥበት አይሻም፡፡
ይሁን እንጂ በከተማ አስተዳደሩ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚታዩ ችግሮች ስለመኖራቸው ለማስረዳት እማኝ መጥቀስ አያሻም፡፡ በዚህም በሕዝብ ላይ ከሚያሳድረው ጫና ባሻገር፣ በሌሎች መሠረተ ልማቶች ጉዳት የሚያደርስበት አጋጣሚም የሰፋ ነው፡፡ በተለይም ክረምት በመጣ ቁጥር ከፍተኛ የሆነ መቆራረጥ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ሳቢያ የከተማዋ ነዋሪ በከፍተኛ ደረጃ ቅሬታውን ሲያሰማ ይደመጣል፡፡
እኛም ለዛሬው የተጠየቅ አምዳችን አገልግሎቱ በህብረተሰቡ የሚነሱ ኃይል መቆራረጥ ቅሬታዎች እና የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማዕከል በማድረግ፤ አገልግሎቱ ችግሩን ከመፍታት አኳያ መሠረተ ልማቱ እንዲዘምን የማድረግ ሂደትን፤ ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የሄደበትን ርቀት፤ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገበየሁ ሊካሳ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕዝብ ጥያቄንና ቅሬታን በሚመልስ መልኩ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅዳችሁ ምን ይዟል? ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር ገበየሁ፡- የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ሲታቀድ የ2015 በጀት አፈጻጸም የነበረውን ጉድለት ከመገምገም ይነሳል፡፡ ስለሆነም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመድረክ ተገምግመው ያሉ ድክመቶችን በማረም፣ በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በሚያስችል መልኩ የታቀደ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ዕቅድ የሚጀምረው ከኮርፖሬት ሲሆን፤ ይሄም እስከ ታችኛው አገልግሎት መስጫ ድረስ የሚወርድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሀምሌ 01/2015 ላይ ሁሉም የሥራ ክፍሎች ዕቅዶቻቸውን አውቀው ወደ ሥራ ገብተዋል። አተገባበሩም በየወሩ እየተገመገመ ሲሆን፤ ሂደቱም በተጨባጭም ለውጥ አምጥቷል። ለምሳሌ፣ ከግብዓት አቅርቦት አንጻር ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም በአብዛኛው የዕቃ ግብዓትን በተገቢው ሁኔታ ማሟላት ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ካለፈው ዓመት ድክመት በመነሳት እየተሠሩ ያሉና ሊጠቀሱ የሚችሉ ምን ተጨባጭ ሥራዎች አሉ?
ዶክተር ገበየሁ፡- ባለፈው በጀት ዓመት እንደ ድክመት የተገመገመው ችግር መካከል አንዱ የኃይል መቆራረጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የተለየው የአየር ንብረት ነበር፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ለኃይል ኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት ከሚሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ዛፎች ቀዳሚ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ ከሚቆራረጠው ኃይል ውስጥ 70 ከመቶው የሚሆነው ዋናው ኤሌክትሪክ ከመሬት ጋር ሲነካካ የሚከሰት ሲሆን፤ ይህን የሚያደርገው ባብዛኛው ዛፍ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይሄን መቆራረጥ የሚያስከትሉ ዛፎችን ለመቁረጥ ያለው ፈተና ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ዛፎች ይቆረጡ ሲባል ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጩኸት ይመጣል። ለምሳሌ፣ የከተማው አረንጓዴ ልማትና ውበት የሚባለው ተቋም ‘ዛፎችን አልምቶ ለደረሱበት ደረጃ ብዙ ዘመን ፈጅቶብናል፣ መቁረጥ አትችሉም’ ይላል፡፡ እናም እስካሁን ለኃይል መቆራረጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ጉዳይ ይህ ነው፡፡
ስለዚህ በዚህ በጀት ዓመት ችግሩን ለማረም ከአረንጓዴና ከተማ ውበት ጋርና ከሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር ምክክር እየተደረ ሲሆን፤ በተወሰኑ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም በየሳይቶች የሚከታተልና ትምህርት የሚሰጥ ባለሙያ ሰጥተው፣ አንዳንድ ቦታ ላይም ራሳቸው እንዲቆርጡ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ በመሆኑም በመሠረታዊነት ለውጥ የሚመጣው ዛፎችን በመቁረጥ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡
ይሄንን በመተግበር ረገድ፣ በመመሪያ ደረጃ በግራና በቀኝ በአምስት ሜትር ራዲየስ ውስጥ ዛፍ መኖር የለበትም። ይሄ ሲሆን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቱ አይጎዳም፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ላይ አጠቃላይ ወደ ሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር በከተማ አስተዳደሩ የኤሌክትሪክ መስመሮች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ሺህ 200 ኪሎ ሜትሩ ከፍተኛ መስመር የሚባለው ነው፡፡ በዛፎች እየተጎዳ ያለውም ይሄ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ከባለድርሻ አከካላት ጋር ዛፎችን በተገቢው ቦታ እንዲተከሉና በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ለማስቻል የጋራ እቅድ እየታቀደ ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ለውጥ እናመጣለን። ሆኖም ሌላውና አሁንም ፈታኝ የሆነው ችግር ግን ዝናብና ከፍተኛ ነፋስ ነው፡፡ ምክንያቱም ዝናብና ከፍተኛ ነፋስ ሲኖር የኃይል መቆራረጡ ይከሰታል።
አዲስ ዘመን፡- ባለድርሻ አካላት የሚባሉት እነማን ናቸው? ምን የጋራ አሠራርስ አላችሁ?
ዶክተር ገበየሁ፡– ባለድርሻ አካላት የሚባሉት መንገዶች ባለሥልጣን፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የከተማ አስተዳደሩ ናቸው፡፡ ችግሩን ከመገንዘብ እና በዘላቂነት እንዲፈታ ከማድረግ አኳያ ከሶስት ዙር በላይ በመከላከያና በከንቲባዋ ሰብሳቢነት በጋራ ታይቷል፡፡
በዚህም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቅበት ከዛፍ ውጭ እንከን የሚፈጥሩ እንደ ወሰን ማስከበር ያሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም በከተማዋ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል የኔትወርክ ዝርጋታ በአብዛኛው ከመሬት በላይ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከመሬት በታች የሚዘረጉ ኬብሎች በዝተዋል። በእነዚህ ኬብሎች ላይም ቢሆን ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በመሠረተ ልማት ገንቢ ተቋማት፤ በራሱ ጊዜና በተለያየ ምክንያት ሲሆን፤ ይህን ጉዳት ለመከላከል ተቋማት በትብብርና በቅንጅት የሚሠሩበት አግባብ ለመፍጠር እየተሠራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ችግር ሲያጋጥም ብልሽቱን በቀላሉ ለይቶ መጠገን የሚያስችል ሁኔታ ፈጥራችኋል?
ዶክተር ገበየሁ፡– ብልሽት ሲጋጥም መለየት የሚያስችል መሣሪያ አለን፡፡ ለምሳሌ፣ ከመሬት በታች ብለልሽት ማመልከቻ (underground fault locater) የሚባል አለ፡፡ ይሄ መሣሪያ የቱ ጋር ብልሽት እንዳጋጠመ የሚጠቁም መሣሪያ አለ፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው መሠሳሪያ በቂ ስላልነበር ለመጠገን ፈተና ነበር። በመሆኑም አሁን ላይ በቂ መሣሪያ ስላለ ባለሙያዎች ተገቢውን ሥልጠና በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡
ለምሳሌ፣ በዚህ መሣሪያ ትክከለኛ ቦታቸው የተለዩ 45 የሚደርሱ ቦታዎች ላይ ብልሽት አጋጥሟል፡፡ እነዚህ እስከ ጥር ድረስ ጥገና ይደረግላቸዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መሣሪያዎች በመጠቀም የኃይል መቆራረጡ ላይ የሚታይ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም የሆነው ከባለፈው በጀት ዓመት ድክመት በመነሳት ታቅዶ እየተሠራ ባለው ሥራ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በተከናወኑ ተግባራትም ብዙ የከተማዋ ክፍል ላይ የኃይል መቆራረጥ መሻሻል አሳይቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ አገልግሎት ከተማዋ የኃይል ፍላጎት አንጻር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ፍላጎትና አቅርቦትን ከማጣጣም አኳያስ ምን ተሠርቷል?
ዶክተር ገበየሁ፡- አቅርቦትና ፍላጎት ሲባል በዋናነት ከኃይል ማመንጫና ከተጠቃሚው ጋር ያለው ንጽጽር ነው። እንደ ሀገር የምናመነጨው አሁን ላይ አምስት ሺህ 300 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ከህዳሴው ግድብ ጋር ተዳምሮ ወደ 11 ሺ ሜጋ ዋት ይደርሳል፡፡ ያለው የኃይል ማመንጨት አቅም ትርፍ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ የሚጠቀመው ፒክ ሎድ ሁለት ነጥብ ሰባት ሜጋ ዋት አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ከፍላጎት አንጻር ሲታይ ያለው በቂ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለጎረቤት ሀገሮች መስጠት የተቻለው፡፡
ከዚህ አኳያ ችግሩ የኔትወርኩ ሁኔታ ነው። ለምሳሌ፣ 10 ሺህ 500 የማሰራጫ ትራንስፎርመር አለ። እነዚህ ትራንስፎርመሮች አቅማቸው ሲሞላ ፊውዝ ይቃጠላል። የትራንስርመሮችን አቅም ለመቀየር የአቅርቦት ፈተናዎች ያጋጥማሉ፡፡ በተመሳሳይ፣ ያረጁ ምሰሶዎች አሉ፤ እነዚህን ለመቀየር ጊዜና ገንዘብ ይፈልጋል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ በተለያየ ምክንያት ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ጥገኛ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ኔትወርኩ በህብረተሰቡ ፍላጎት ልክ ዕድሳት ተደርጎለት አላለቀም። ያለው ፈተናም ይህ ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባም በአቅርቦቱና በተጠቃሚው ማህበረሰብ መካከል ያለው ልዩነት የተፈጠረው በሰብ ስቴሽን አቅም ምክንያት ነው።
ለአብነትም፣ በከተማዋ ስድስት የሚደርሱ ሰብስቴሽኖች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ኮዬ አቦ የሚባል ቦታ ያለው ሰብስቴሽን 500 ሜጋ ዋት አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ፈተናው ኔትወርኩን አሻሽሎ በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለአገልግሎት ማብቃት ነው። ይህን ችግር ለማቃለልም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ በህብረተሰቡ ዘንድ እየፈጠረ ያለው ምሬት ችግሩን አንገብጋቢ ከማድረጉ ጋር ተይይዞ እየተሠራ ያለው ተጨባጭ ሥራ ምንድን ነው?
ዶክተር ገበየሁ፡- መንግሥት ለዘርፉ በስትራቴጅክ እቅዱ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ ለምሳሌ፣ በኃይል ማመንጫ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡ ይህም ምንጩ ከሌለ ቴክኖሎጂ ላይ ቢሠራ ትርጉም አልባ ስለሚሆን ነው፡፡ በተመሳሳይ የኃይል ማስተላለፊያ ላይ ተሠርቷል። ከተሞች ውስጥ ያለው የኃይል ማሠራጫ ጣቢያ የተጀመረውም በቅርቡ ነው፡፡ ምክንያቱም ኔትወርኩ ጥሩ ይዞታ ላይ አልነበረም።
ለምሳሌ፣ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሆነውን መስመር ለማዘመን ተግዳሮቶች አሉ። ምክንያቱም እነዚህን ለመቀየር ፋይናንስ ማፈላለግ ይጠይቃል፤ ጊዜም ይፈልጋል፡፡ የሚሠራው ከተማ ውስጥ እንደመሆኑም ሥራው አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንጻሩ፣ በገጠር አካባቢ አንድ የእንጨት ምሰሶን ወደ ኮንክሬት ለመቀየር ሌላ መንገድ ተይዞ ይሠራል፡፡
ከተማ ላይ ግን ያንኑ እያጠፋን ነው የሚቀየረው። አንድ መስመር አምስት ጊዜ ይጠፋል፡፡ ይህ ደግሞ ለመሠረተ ልማት ዝርጋታው ትልቅ ፈተና ነው። ምክንያቱም፣ የመብራት ዝርጋታ በየቦታው ፖል መትከልና ኔትወርክ መዘርጋትን ይጠይቃል፡፡ የመብራት ቴክኖሎጂውም ቢሆን ምንም አይነት ሽግግር አላደረገም። ቀድሞም የሆነ ጀነሬሽንና ማስተላለፊያ መስመር ይኖራል፤ ፖል ይተከካል፤ ከዛም ህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ አሁን ላይም ያለው ይሄው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ከማዘመንና በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ከማድረግ አኳያ ምን የታሰበ ነገር አለ?
ዶክተር ገበየሁ፡- የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማዘመንና ለማስተካከል በሁለት መልኩ እየተሠራ ነው። አንደኛው፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምሰሶዎችን የማዘመን ሥራ ነው። ምክንያቱም የኔትወርኩ አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይ ያረጀ ነው፡፡ እነዚህ ቢሆኑ መጀመሪያ የተዘረጉት ለትንሽ ደንበኛ ነው፡፡ እናም ደንበኞች እየጨመሩ ሲመጡ አቅሙ ከፍ ማለት አለበት፡፡
በተማዋ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የሕዝብ ቁጥር የሚጨምርበትና አገልግሎት ፈላጊው በየጊዜው እያደገ የመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህንን ደግሞ ኔትወርኩ ማስተናገድ አይችልም፡፡ ኔትወርኩ የተዘረጋው ደግሞ በእንጨት ምሰሶ በመሆኑ ከቆይታ በኋላ ያረጃል፡፡ ከተማ ሲሰፋና ማስተር ፕላኑ ላይ የማስተካከያ ሥራ ሲሠራ አንዳንድ ኔትወርክ የማንሳት ሥራ ይሠራል፡፡ ስለዚህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አይደለም ለዚህም ነባራዊ ሁኔታው ደካማ ነው፡፡
በመሆኑም ከ2010 በጀት ዓመት ወዲህ ስትራቴጂክ እቅድ ተቀርጾ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ሥራውም እየተሠራ ያለው በውጭ በተገኘ የፋይናንስ ምንጭ በመካከለኛ ቮልቴጅና በማሠራጫ ትራንስፎርመሮች ላይ ነው፡፡ ይሄም ‹‹ኤሊቪ›› የሚባል ወደ አራት ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ ከዚህ ወስጥ ሁለት ሺ ገደማ የሚሆነው መካከለኛ ቮልቴጅ ነው፡፡
አንድ መካከለኛ ቮልቴጅ 50 ትራንስፎርመሮች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ይህ መካከለኛ ቮልቴጅ ተበላሸ ማለት 50 ትራንስፎርመር ኃይል ያጣል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ትኩረት የተደረገው ሁለት ሺ 200 ኪሎ ሜትሩ መካከለኛ ቮልቴጅ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የአዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ማሻሻያ አደርጎ ለማጠናቀቅ የሚያስችል አራት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አራቱ ፕሮጀክቶች የሚባሉት የተኞቹ ናቸው? በምን ያህል ገንዘብ ነው የሚከናወነው?
ዶክተር ገበየሁ፡– የመጀመሪያው ስምንቱ ከተሞች የሚባሉት ናቸው፡፡ የፋይናንስ ምንጩ ዓለም ባንክና ኮፒክ የሚባሉ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ከስምንቱ ከተሞች አንዱ ነው፡፡ አብዛኛው አዲስ አበባ ውስጥ አለ። የክልል ዋና ከተሞች ላይ ከ2010 እስከ 2012 ተሰርቶ ተጠናቋል፡፡ በዚህም የክልል ከተሞች ከአዲስ አበባ የተሻለ የኔትወርክ ዝርጋታ አላቸው፡፡
ሁለተኛው፣ በቻይና ኤግዚን ባንክ ፋይናንስ የተደረገ ፕሮጀክት ነበር፡፡ በዚህም ሰባት መቶ ኪሎ ሜትር የሚሆን ኔትወርክ ዝርጋታ የመቀየር ሥራ ተሠርቷል። ሶስተኛው፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍ ሲሆን፤ በዚህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ናቸው እየተገነቡ ያሉት። ይሄ ቴክኖሎጂ አንድ ኃይል ሲቋረጥ መቋረጡን ማመላከት የሚችልና ወዲያውኑ ጥገና መስጠት እንዲቻል የሚያደርግ ነው፡፡
አራተኛው ፕሮጀክት፣ በዓለም ባንክ ከተገኘ የፋይናንስ ምንጭ የሚሠራ ሲሆን፤ አሁን ላይ ኮንትራክተሮች ተለይተው ወደ ተግባር ገብቷል። ተግባሩም በ2017 መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የአዲስ አበባን መካከለኛ ቮልቴጅ ኔትወርክ በሙሉ ያሻሽላሉ፡፡ የአራት ሺህ የማሰራጫ ትራንስፎርመሮችን አቅም ያሻሽላል። በድምር ውጤቱም የአዲስ አበባን የኃይል መቆራረጥ በተጨባጭ ለውጥ ያሳያል፡፡
ይህ የሚሻሻለውም በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። አንዱ፣ አካላዊ ኔትወርኩን በማሻሻል ሲሆን፤ በዚህም ካሉት 10 ሺ 500 ትራንስፎርመሮች አራት ሺህ የሚሆኑት አቅማቸው ይሻሻላል፡፡ ይህ ሲሆን ጫናው ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ኔትወርኩ በመሻሻሉና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሰው ተጠቀመ አልተጠቀመ የሚቃጠል ፊውዝ አይኖርም፡፡ አሁን በከተማዋ የሚታየው የኃይል መቆራረጥ 60 በመቶ የሚሆነው በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ምክንያቱም ፖል ለመትከልና ኔትወርክ ለመዘርጋት ሙሉቀን ማቋረጥን ይጠይቃል። ስለዚህ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዕቅድ የሚቋረጥበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእንጨት ፖሎችን በኮንክሪት ፖል የመቀር ሥራው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባብቶ ከመሥራት አኳያስ?
ዶክተር ገበየሁ፡- በአንድ ከተማ የመሠረተ ልማቶች መቀናጀት ወሳኝ ነው፡፡ በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በከተማ አስተዳደር ደረጃ የመሠረተ ልማት ቅንጅት የሚባል ተቋም ተቋቁሟል። ቅንጅቱ በምን ይገለጻል ቢባል በሚሠሩ መንገዶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም የ‹‹ዩቲሊቲ›› መስመሮች በሙሉ ተዘርግተዋል፡፡ ስለዚህ መንገድ ሲሠራ የዩቲሊቲ መስመሮች ጋር ኤሌክትሪክ መስመር መቅበር ሲፈልግ ያለምንም ችግር ኬብል መቅበር ወይም መዘርጋት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በዚህ ጊዜ ያለው ኔትወርክ ምንም እንከን የለሽ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ፣የኢምፔሪያልና የለቡ ማሳለጫ መንገድ ሲሠራ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይሄ የሆነው ከመሬት በታች የተቀበረ የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶ እያለ መንገድ የግድ መስፋት ስላለበት ይሄን በማድረግ ሂደት በተፈጠረ ጉዳት ነው፡፡ ይህ ቢቀናጅም ባይቀናጅም የሚቻል አይደለም፡፡
ምክንያቱም፣ ገመዱ መንገድ ማዕከል ውስጥ ይገባል። ይህን ለማስነሳት ጊዜ ይፈልጋል ብቻ ሳይሆን ኬብሉ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ለመዘርጋት ኮሪደር መገኘት አለበት። አብዛኛው ጉዳት የሚደርስበት ግዴታ በሆነ የመሠረተ ልማት ሥራ በመኖሩ ነው፡፡ ለቡ ላይ ከዓመት በላይ የወሰደ ችግር ገጥሟል፡፡ ስለዚህ በመሠረተ ልማቱ ላይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ የመንግሥት ተቋማት ጉዳት ያደርሳሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግለሰቦችም ሆነ በተቋማት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ሲደርስ ያለው ተጠያቂነት ምን ይመስላል?
ዶክተር ገበየሁ፡- ተያቂነት አለ፡፡ ለዚህም መደበኛ አካሄድና አሠራር አለው፡፡ ለደረሰው ውድመት ኬብሉን ከመተካት አንጻር ወጪውን ይሸፍናሉ፡፡ ነገር ግን ከተማው ላይ ብዙ ፈረሳና ግንባታዎች ስላሉ መቆጣጠር አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ ነዋሪዎች ከአገልግሎት አሠጣጡና ከኃይል መቆራረጥ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚያነሱትን ቅሬታ በተገቢው ጊዜ ምላሽ የመስጠቱ ሂደትን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ገበየሁ፡– ከኃይል መቆራረጥ ጋር የሚነሳው ቅሬታ ከአቅርቦትና ፍላጎት ጋር የሚያያዝ ነው። ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ሥራ ከፍተኛ መሻሻል አለ፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ከሚጨምረው የፍላጎት አቅም ጋር በቂ አይደለም፡፡ በተለይ፣ የሠራተኞች በጎ ምላሽ አለመኖርና በቶሎው ደርሶ ጥገና አለማድረግ፤ ያልተገባ ጥቅም መፈልግ አለ፡፡ አገልግሎት አቅራቢ ሲኮን ደግሞ ለዚህ ተጋላጭነቱ ይኖራል፡፡
በመሆኑም ይህን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በዚህም ተጨባጭ ውጤቶችም ተገኝተዋል። ለምሳሌ፣ በዚህ ላይ ክትትል ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከጂፒኤስ ጀምሮ አለ፡፡ በዚህም አዲስ ደንበኛ ከአመለከተበት ቀን ጀምሮ እስከሚገናኝበት ቀን ድረስ ያለውን ሂደት በማንኛውም ደረጃ፤ በትኛውም ቦታ ላይ ሆኖ መከታተል የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ኃይል ጠፋብኝ የሚል ቅሬታም ተመዝግቦ በጊዜው ጥገና ይደረጋል፡፡ ይህ በመሆኑ ሠራተኛው በጥንቃቄ ይሠራል።
ስለዚህ ርምጃ የሚወሰደው በጥርጣሬ ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው። ‘ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ’ የሚባል አሠራር ተግባራዊ መደረጉም ችግሮች እንዲቃለሉ እያደረገ ነው። አሠራሩ ከተጀመረ ሶስት ዓመትን አስቆጥሯል፡፡ አንድ ትራንስፎርመር የት እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህ በመሆኑም የሠራተኛው ሥነምግባር ላይ ለውጥ አምጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሠራሩ በመተግበሩ በተገልጋዩ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን መመለስ አስችሏል ለማለት ያስደፍራል?
ዶክተር ገበየሁ፡- ውጤታማ ነው ማለት አሁን ላይ ችግር የለም ማለት አይደለም፤ ችግሮች አሉ። 44 በመቶ የሚሆነው ሙስና አዳዲስ ደንበኞችን ከማስተናገድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ርምጃ የሚወሰድባቸው ከገማች እስከ ቆጣሪ ለጣፊ ድረስ ያሉ ሠራተኞች 44 ከመቶ የሚሆኑት ከአዲስ ደንበኛ ጋር የተገናኙ ናቸው። በሥነ ምግባር ማሻሻያ፤ በምክርና በሌሎች ክትትሎች መታረምና መመለስ ባልቻሉት ሠራተኞች ላይ ርምጃ ይወሰዳል፡፡
ለምሳሌ፣ በ2015 በጀት ዓመት 121 ሠራተኞች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ደሞዝ ማገድ የደረሰ አስተዳደራዊ ርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ በቀጣይ ህብረተሰቡ ብልሹ አሠራሮችን ጥቆማ የሚሰጥበት ዌብሳይት እየበለጸገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በህብረተሰቡ ዘንድ የክፍያ አለመጣጣም፤ ለምሳሌ፣ በአንድ ወር መቶ ሃያ ብር የከፈለ ተጠቃሚ በሚቀጥለው ወር 30 ሺ ብር ቆጠረ ተብሎ ከአቅም በላይ የሚጠየቅበት ሁኔታ አለ፤ ይሄ ከምን የመነጨ ነው? ችግሩስ በምን መልኩ ይፈታል?
ዶክተር ገበየሁ፡- ይህ ከኔትወርኩ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ቆጣሪ አንባቢ ሜትሮቹ ከተተከሉ ቆይተዋል፤ ሁሉንም አያነቡም። ክትትል የሚደረግባቸውም በሰው ነው፡፡ ከሜትሮቹ የተረፈው የሚነበበው በሰው ነው። ሌላ ሀገር ግን ሲታይ ስማርት ሜትር ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ለመቀየር እየተሠራ ነው፡፡
በስድስት ወር አንድ ጊዜ የሚያነቡ አሉ፡፡ አንድ ጊዜ ሲያነቡ በደንብ ያነባሉ፤ እስከ ሚቀጥለው ስድስት ወር በግምት ይነበባል፡፡ አገልግሎቱ ሰው መክፈል ያለበት የተጠቀመበትን እንዲሆን በየወሩ ቆጣሪ ያነባል።
ችግር እንዳይፈጠር በኤም አር አይ እና በጂፔኤስ ሠራተኞችን እንከታተላለን፡፡ አልፎ አልፎ ቤት ይዘጋል። በዚህ ወቅት ቆጣሪ አንባቢ ገብቶ ማንበብ አይችልም። ይህ ሲሆን ትንሽ ብር ብቻ የሚወጣበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሌላው ደግሞ ቆጣሪ አንባቢው ቤቱ ጋር ላይሄድ ይችላል፤ የተዘረጋው ሲስተም በብዛት የቀረፈ ቢሆንም ክትትሉ ሲበዛበት ቤቱ ድረስ ሄዶ ሳያነብ በግምት ይሞላል፡፡
አንዳድ ጊዜ ደግሞ የ‹‹ኢንኮዲንግ›› ስህተት ያጋጥማል፤ የተሳሳተ ቁጥር ሊሞላ ይችላል፡፡ ይህ ስህተት የሚጋጥማቸው ደንበኞች ከ2012 ጀምሮ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አንባቢው ቦታው ድረስ ሄዶ ማንበቡ ማስረጃ በሲኤምአርአይ ይመጣል፡፡ ሰው አቅሙ በላይ ከቆጠረበትና መክፈል የማይችል ከሆነ እስከ ስድስት ወርና አንድ ዓመት ጊዜ ወስዶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡
የተሳሳተ ነው ብሎ የሚያምን ከሆነ ቅሬታ አቅርቦ እንዲታረም ይደረጋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ አንድ ሚሊዮን ቆጣሪዎች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ደንበኛ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት አራት ወራት የግብዓት አቅርቦት ላይ በትኩረት እንደተሠራ ገልጸዋል፤ በየትኞቹ አቅርቦቶች ላይ በምን ያህል በጀት ነው የተሠራው?
ዶክተር ገበየሁ፡- ግብዓቶቹ ኮንክሪት ምሰሶ፤ የእንጨት ምሰሶ፤ የኃይል ማሰራጫ ትራንስፎርመርና ኮንዳክተሮች፤ ሽቦ፤ ቆጣሪ፤ ኬብሎችና የመሳሰሉት ናቸው። ይህን ግብዓት ለማሟላት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ስለሆነም ግብዓት አቅርቦት ላይ ሰርተናል ስንል ባለፈው በጀት ዓመት ላይ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ፈተናዎቹን በመለየት በመሠራቱ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት በተሠራው ሥራ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡
በዚህም አንድ ሺህ 600 ኮንክሬት ምሰሶ ውል ተወስዶ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ የማሰራጫ ትራንስፎርመር እስካሁን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከባዱ ፈተና ነበር፤ አሁን ላይ 291 ትራንስፎርመር ተገዝቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለኃይል መቆራረጥ 70 በመቶው ዛፎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፤ በዋናነት ከመልሶ ግንባታ ምሰሶዎችን ከመቀየርና ከዛፎች እንዲርቁ ከማድረግ አኳያ እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ገበየሁ፡- ቅድም ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን ገልጫለሁ፡፡ ዝቅተኛ መስመሩ አራት ሺህ 700 ኪሎ ሜትር በራስ አቅም ነው የሚሠራው፡፡ ለምሳሌ፣ ባለፈው በጀት ዓመት ሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት የሚባለውን አዲስ ክፍለ ከተማ ሙሉ በሙሉ ስድስት ሺህ የሚሆኑ የእንጨት ምሰሶዎችን ቀይሯል፡፡ የኮንክሪት ያልተደረገው ደግሞ በሲሚንቶ ዕጥረትና የዋጋ መናር ምክንያት ነው፡፡
የኮንክሪት ምሰሶ ዋጋ የእንጨት ምሰሶ ዋጋን አምስት እጥፍ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በኮንክሪት ብቻ ለማድረግ ብዙ ዓመታትን ይወስዳል፡፡ በዚህ ረገድ ፋይናንስ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የከተማው ማስተር ፕላን ኮንክሪት እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ነገ የሚፈርስ ሰፈር ይኖራል፤ ስለዚህ በዛ ሰፈር የኮንክሪት ምሰሶን መዘርጋት እጥፍ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ደንበኞች “ባንክ ላይ ሲስተም የለም በመባሉ ምክንያት መብራት ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንዲቋረጥብን እየተደረገ ነው፤” የሚል ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ዶክተር ገበየሁ፡- በጥቅምት ወር ባንክ ላይ በመሄድ የከፈሉ ደንበኞች 113 ሺህ 300፤ ሲቢኢ ብር በመጠቀም የከፈሉ 53፤ ቴሌ ብር በመጠቀም የከፈሉ 80 ሺህ፣ ሞባይል ባንኪንግ 161 ሺህ፣ ወደ ተቋሙ መጥተው የከፈሉ 12 ሺህ ሲሆኑ፤ በአጠቃላይ አራት መቶ 23 ሺ 947 ደንበኞች ከፍለዋል፡፡
ሆኖም ቴክኖሎጂ ሲሠራ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ በባንክ አካባቢ ሲስተም አለመኖር ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን መሰል ችግሮች በሁሉም ሳይሆን በውስን ደንበኞች ላይ የሚያጋጥም ነው፡፡ የአገልግቱ ሠራተኞች ሲስተም ስለሌለ ሳይሆን ይህ ደንበኛ አልከፈለም ብለው ነው የሚቆርጡት፡፡ ደንበኛው ባንክ ላይ ከፍሎም የሚቆረጥበት ሁኔታ አለ፡፡
ስለዚህ አንዳንድ ችግሮች ሲሰከቱ ለመፍታት አገልግሎቱ ቁርጠኛ ነው፡፡ እንደ አማራጭ ችግሩ ካጋጠመ መፍትሄ ለመስጠት የክፍያ ባለሙያዎች የካሽ ዴስክ አገልግሎት በየባንኩ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ሳይከፍል ሲቀር መቁረጥ፤ ሲከፍል መቀጠል ሥራ በጣም አሰልች ነው፡፡ ከዚህ አሠራር ለመውጣት ትኩረት እየተሠራ ነው። ይህን ለማስቀረት 600 ሺህ ቆጣሪ በዚህ በጀት ዓመት ወደ ስማርት ቆጣሪነት ይቀየራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ምክንያት የግለሰቦች መገልገያ የሆኑ እንደ ፍሪጅና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪዎች ይቃጠላሉ፡፡ ለዚህ ጉዳት ምላሽ ከመስጠት አንጻር አገልግለቱ ምን ያስቀመጠው አሠራር አለ?
ዶክተር ገበየሁ፡- በአጠቃላይ ይህንና መሰል ችግሮች የሚከሰቱበት ሁኔታ በጣም ውስን ነው፡፡ ኤሌክትሪክ የሚሠራበት ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎች አሉት። እያንዳንዱ መስመር የሚሠራው ዓለም አቀፍ ደረጃን መሠረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡ ስለዚህ በብዛት አያጋጥምም።
ካጋጠመም የሚጎዳ ተሽከርካሪ ማሽኖችና ሞተር ላይ ነው፡፡ አውቶማቲክ ጀነሬሽን መቆጣራጠሪያ የሚባል አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚፈጠረው አንዱ መስመር ተበጥሶ አንደኛው ኒውትራሉ ላይ ያርፋል፡፡ የሚያጋጥመውም በብዛት ሰፈር ላይ ነው፡፡ ስለሆነም መሰል ችግር ሲያጋጥም ማህበረሰቡ በ24 ሰዓት ውስጥ ሪፖርት ማድረግ አለበት። በዚህ መንገድ ልዩ ችግሮች ካልሆኑ ወደ እኔ መጥቶ አያውቅም፡፡ ደረሰኝ አገልግሎቱ ጠይቆ ያቀረበ ሲኖር የመተካት ሥራ ይሠራል፡፡
አንዳንዱ ከመሬት ተነስቶ አርባ ቴሌቪዥን ተቃጥሎብኛል ብሎ ሪፖርት የሚያቀርብ አለ። ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ትክክለኛ መረጃ በመያዝ ለተቃጠለበት ንብረት ደረሰኝ ይዞ እንዲመጣ ይደረጋል። ስለሆነም በአሠራር መልስ የሚሰጥበት አግባብ አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
ዶክተር ገበየሁ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም