የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቅርቡ ባካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይም ይህንኑ ጉዳይ አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቶበታል፡፡ ነገር ግን ችግሩ አሁንም በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ በቀለ፤ በየክልሉ ዘመናዊ ስታዲየሞች መገንባታቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ ያለው የመም ቁጥር እያደገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ካለው የአትሌቶች ፍላጎትና ቁጥር አንጻር በቂ ካለመሆኑም ባለፈ በርካታ ክለቦችና አትሌቶች ከሚገኙባቸው ሥፍራዎች አንጻር ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት የመታወቋን ያህል ዓለምና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አይደለም አትሌቶቿ ልምምድ ሊያደርጉ የሚችሉበት በቂና ጥራት ያለው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ የላትም ሊባል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ከዓመታት በፊት ውድድሮችንና የአትሌቶች ልምምድን የሚያስተናግደው መም አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ብቻ ነበር። ነገር ግን ስታዲየም በእድሳት ምክንያት ለዓመታት ከአገልግሎት ውጪ በመሆኑ አትሌቶችና አሠልጣኞች በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡
በተለይ አዲስ የአበባ ስታዲየም ከእድሳት ጋር በተያያዘ ለዓመታት ሥራ ማቆሙን ተከትሎ በአማራጭነት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን መም ለልምምድና ውድድሮች መጠቀም ቢቻልም ካለበት ጫና አንጻር መጎዳቱ አልቀረም፡፡ በዚህም ምክንያት አትሌቶች ወደ ጎዳና በመውጣት ልምምድ ለመሥራት በመገደዳቸው ሕይወትን ሊያሳጣ ለሚችል አደጋ እየተጋለጡ መሆኑን ይታወቃል፡፡ ይሁንና የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ከድጋፍና ክትትል ውጪ ማዘውተሪያዎችን መገንባት ባለመሆኑ የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች ሊያስቡበት ይገባል፡፡
በሌላ በኩል የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በየክልሉ እየተገነቡ መሆኑ አበረታች ቢሆንም፤ የጥራታቸው ጉዳይ ግን አሁንም አነጋጋሪ ከመሆን ወደኋላ አላለም፡፡ ውድድሮች በሚካሄዱባቸው ወቅት አሊያም የባለሙያዎች ምልከታ በሚከናወንበት ወቅት ጉድለቶች መኖራቸው እንደሚደረስበትም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ መሞች ረጅም ዓመት እንዲያገለግሉ ቢጠበቅም ሁለት ዓመት ሳይሆናቸው ለብልሽት ይዳረጋሉ። ይኸውም ከግንባታ ጋር በተያያዘ በሚኖር የጥራት ጉድለት የሚከሰት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ ባለሙያ አሊያም ተቋም ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ችግሩን አስፍቶታል። ፌዴሬሽኑም በቻለው መጠን ግንባታዎች ሲከናወኑ ክትትል በማድረግ አስፈርሶ በአዲስ መልክ እንዲሠራ እስከማድረግ የሚደርስ ርምጃም ይወስዳል፡፡
በዚህም በእድሳት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየምም ከመም ግንባታው ጋር በተያያዘ አስተያየት እንዲሰጥ አስቀድሞ ፌዴሬሽኑን ማወያየቱን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ በቀጣይ በሚኖረው ሂደትም ፌዴሬሽኑ እድሳቱን ከሚያከናውነው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡ ኢትዮጵያ ከሀገር ውስጥ ባለፈ አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማዘጋጀት እንድትችል የዓለም አትሌቲክስ መስፈርቶችን ያሟላ መም ባለቤት መሆን ስለሚገባት ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴም እየተደረገ ነው፡፡ ይሁንና በሌሎች አካባቢዎች የሚገነቡ መሞች በባለሙያ እና ልምድ ባላቸው ተቋማት ካልተሠሩ ችግሩ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡
በተያዘው ዓመት የፓሪስ ኦሊምፒክ የሚካሄድ እንደመሆኑ አትሌቶች በአግባቡ ተዘጋጅተው ሀገራቸውን እንዲወክሉ ለማድረግ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች መኖር አስፈላጊነት አያጠያይቅም። በመሆኑም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በእድሳት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም መም ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ይደርሳል የሚል ተስፋን ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም ፌዴሬሽኑ ችግሩን ለመፍታት በእቅድ እየሠራ ሲሆን፤ በየክልሉ በመገንባት ላይ ላሉት ማዕከላት ክትትል ከማድረግ ባለፈ በራሱ አቅም ሸገር ከተማ ላይ የአሸዋ ትራክ ለመሥራት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በቀጣይም በሀገሪቷ ባሉት 7 የአትሌቲክስ ሥልጠና ማዕከላት በተጨማሪ የመሥራት እቅድ መኖሩን ተከትሎም እገዛውን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም