የአየር ኃይል እግር ኳስ ቡድን ሲታወስ

 በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በሚሊተሪ ተቋማት የተመሰረቱ ክለቦች ትልቅ ድርሻ አላቸው። የጦሩ ቡድኖች በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም። ወደ ቀድሞ ስያሜው መቻል የተመለሰው መከላከያ በእግር ካሱም ይሁን በአትሌቲክሱ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ያኮሩ ስፖርተኞችን ሲያፈራ ኖሯል፣ አሁንም እያፈራ ይገኛል። በተመሳሳይ አንጋፋ ከሆኑ ክለቦች መካከል የአየር ኃይል ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ትልቅ ዐሻራ ማኖር የቻለ ነው።

አየር ኃይል አንጋፋውን የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮን ጀግናውን አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን ጨምሮ በርካታ አትሌቶችን አፍርቷል። በእግር ኳስ ስፖርትም አየር ኃይል ትልቅ ስም ያለው ክለብ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ወርቃማ ተብሎ በሚቆጠረው በ1970ዎቹ የአየር ኃይል ቡድን ገናና ስም ካላቸው ጠንካራ ክለቦች አንዱ እንደነበር ይታወቃል። እኛም ለዛሬ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰማንያ ስምንተኛ ዓመቱን እያከበረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ታሪካዊውን ክለብ ከብዙ በጥቂቱ እንዳስሳለን።

“ንብ” በሚል መጠሪያው ይበልጥ ዝነኛ የነበረውና በ1953 የኢትዮጵያ ዋንጫን የማንሳት ታሪክ ያለው የቢሾፍቱው ክለብ አየር ኃይል በመላው የአየር ኃይል ቤተሰቦች እንዲሁም በቢሾፍቱ እና አካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የብዙ ደጋፊዎች ባለቤት ሆኖ ይታወሳል። የአየር ኃይል ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመሳሰሉ ታላላቅ ክለቦች ጋር በተለይም በኢትዮጵያ ዋንጫ ያደርግ የነበረው ጠንካራ ፉክክር በታሪክ የተቀመጠ ነው። በመጨረሻው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ዋንጫ ጨዋታ በ1971 ዓ.ም በአሰልጣኙ ሀጎስ ደስታ ይመራ ከነበረው ቡድን ሰለሞን ቢተው፣ መኮንን ታደሰ፣ ግርማ ካሳ፣ ኃይሌ ቦሩ፣ ጥላሁን ጋሻው፣ አለምሸት ለገሰ፣ ጉልላት ቢልቻ፣ ሰለሞን በጋሻው፣ ታደሰ ቶላ፣ አብርሃም አበበ፣ ፋንታ በላይ (ሜ/ጀነራል)፣ ማሞ ወልዱ፣ እሸቱ ተስማማው፣ ግርማ ቶንካ፣ አሰፋ ተክለማርያምና ሌሎችም የሚታወሱ ኮከቦች ናቸው።

አየር ኃይል ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልኩ ከጀመረ በኋላ በ1998፣ 1999፣ 2000 እና 2004 ላይ የተሳተፈ ሲሆን 2004 ላይ በያኔው አጠራር ከብሔራዊ ሊግ ባደገበት ዓመት ተመልሶ ወርዶ ከአንድ ዓመት በኋላ በዛው እንደፈረሰ ይታወሳል። ወደ ከፍተኛ ሊግ በመውረዱ ምክንያት 2005 ላይ የፈረሰው አየር ኃይል ወይም ንብ ክለብ ለዓመታት ጉዳዩ ተዳፍኖ ቆይቷል።

2014 ላይ ግን ዳግም በከፍተኛ ሊጉ ተቋቁሞ ወደ ውድድር የሚመለስበት እድል አግኝተል። ይህም የመከላከያ ቢ ቡድን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጉን ተከትሎ የሁለቱ ክለቦች ኃላፊዎች ተነጋግረው በአየር ኃይል እግር ኳስ ክለብ በመተካት በ2015 ዳግም ለማቋቋም እና በከፍተኛ ሊግ የሚወዳደርበትን እድል ማግኘት ነበር። ለዚህም አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ከአስር ዓመት በኋላ ራሱን ዳግም ወደ እግር ኳሱ የተመለሰው አየር ኃይል ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ካለፈው 2015 ጀምሮ በመሳተፍ ጉዞውን ሲጀምር አሰልጣኝ ደምሰው በፍቃዱ በዋና አሰልጣኝነት መርተውታል። ንብ በሚል የቀድሞ ስያሜው በከፍተኛ ሊግ እየተወዳደረም ሁለተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል። በ2016 የከፍተኛ ሊጉ ፉክክር በምድብ ሀ የሚገኘው ንብ ከቀናት በፊት 5ኛ ሳምንት ጨዋታውን ከሲልጤ ወራቤ ጋር አድርጎ 1ለ1 በሆነ ውጤት መለያየቱ ይታወቃል። የፊታችን ማክሰኞም የውድድር ዓመቱ ስድስተኛ መርሃ ግብሩን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያደርጋል። በአምስት ጨዋታዎች የሰበሰባቸው ሰባት ነጥቦችም በምድቡ የደረጃ ሰንጠረዥ ስድስተኛ ላይ አስቀምጦታል። አንጋፋና ዝነኛው ክለብ ንብ በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ፉክክር አልፎ በአጭር ዓመት ውስጥ በትልቁ የፕሪሚየር ሊግ ፉክክር ለመቅረብም ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You