የኢትዮጵያ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶችየብልጽግናዋ መሠረቶች ናቸው!

 ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ስንሄድ ያልተነኩ እምቅ ሀብቶች በስፋት የሚገኙባት ሀገር ነች። እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ከታወቁ እና ጥቅም ላይ መዋል ከቻሉም የኢትዮጵያ የብልጽግና መሠረትና የሕዝቦቿም የኑሮ መሠረቶች ይሆናሉ።

ከለውጡ ወዲህ መንግሥት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በማከናወንና ለቱሪዝም ዘርፉ መጠናከር የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። እንደ ሀገርም መንግሥት ኢኮኖሚውን ወደፊት ያሻግራሉ ብሎ ተስፋ ከጣለባቸው የግብርና፤ ኢንዱስትሪ፤ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ጋር በአንድነት የቱሪዝም ዘርፉን የመሪነት ሚና እንዲኖረው አድርጓል።

ይህንኑ ሀገራዊ ርዕይ መሠረት በማድረግም ሀገራዊ ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ዓ/ም ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማወቅ፤ በመለየት፤ በማልማትና በመጠቀም ረገድ እምርታዊ ለውጦች ታይተዋል። በአጠቃላይ ወቅቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ትንሳኤ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

የቱሪዝም ቦታዎችንና በማስፋትና በመንከባከብ እንዲሁም ለቅርሶች ተገቢውን እንክብካቤ በመደረጉ ምክንያት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን በቅታለች። ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት 13 ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር የነበረች ሲሆን በተለይ አዲሱ 2016 ዓ.ም ከገባ ወዲህ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክንና የጌዲኦ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መልክዓ ምድር በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች። ሰሞኑን ደግሞ የሸዋል ኢድ አከባበር ሥርዓትን በማስመዘግብ በዩኒስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መስህቦችን 16 በማድረስ በአፍሪካ ቀዳሚነቷን ማረጋገጥ ችላለች።

የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ኢትዮጵያ ብዝሀነት የሚንጸባረቅባት ሀገር መሆኗን ለዓለም ሕዝብ ለማሳየት ከማስቻሉም በላይ ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከርና አድማሱን እንዲያሰፋ የሚያደርግ ነው። ይህ ታሪካዊ ውሳኔም ሐረር ከተማን በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ እንድትሆንም ያደርጋታል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አፍላቂነት እና መሪነት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሚያበረታታ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሸገር፤ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚል ማዕቀፍ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ሥራ ተገብቷል። መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘናት ሀብቶችን በመለየትና በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በገበታ ለሸገር የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ የአንድነት፤ የወንድማማችነት እና የእንጦጦ ፓርኮች ለአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋታል። ለወትሮው በቱሪስት መተላለፊያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ የቱሪስቶች መቆያ የመሆን ዕድልም አግኝታለች። በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም የጎርጎራ፤ የኮይሻ እና የወንጪ የቱሪስት መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥረዋል።

በቅርቡም በደቡብ ምዕራብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የ ‹‹ገበታ ለትውልድ›› ውጥን አካል የሆነውን ‘የደንቢ ሐይቅ ሎጅ’ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ተግባር ተከናውኗል። ከዚሁ ጎን ለጎን የጅማ ከተማ በአዲሱ ገበታ ለትውልድ ከተመረጡ ቦታዎች ውስጥ አንዷ ሆናለች። የጅማ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የከተማውን ገጽታና የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ እንደሚለውጥም ታምኖበታል።

ሚዛን አማን ላይ የሚሠራው አዲስ ሪዞርትና ኮይሻ አካባቢ የሚሠራው ፕሮጀክት ከጅማ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ናቸው። እነዚህ ቦታዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ቆይታ ያማረ በማድረግ የአካባቢው ኅብረተሰብ ከዘርፉ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችሉም ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጅማና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶችን ሲጎበኙ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ሀገሩን ያላወቀና ሀብቱን በአግባቡ ያልተጠቀመ የባከነ ነው›› ሲሉ ተደም ጠዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ በማወቅ፣ በመጠቀምና በመጠበቅ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ሊሆን ይገባል። በየአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም የተረዳ ዜጋ ለመገፋፋትና ለመጣላት የሚሆን ጊዜ ስለማይኖረው ያለውን እምቅ ሀብት ሥራ ላይ አውሎ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ይገባዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ለቱሪዝም ዘርፉ እንቅፋት የሆነውን ጦርነትና ግጭት በማስወገድ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን እንድትጠቀም ማድረግ ተገቢ ነው።

አዲስ ዘመን ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You