ለፕሮጀክት ማኔጅመንት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለያዩ መሠረታዊ ችግሮች ተተብትቦ ይገኛል። የግብዓት እጥረት፣ የአቅም ውስንነት፣ የሙስና መንሰራፋት፣ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ብቃት ማነስ፣ የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር ከዋና ዋናዎቹ የዘርፉ ችግሮች መካከል መሆናቸው ይጠቀሳል። በሀገሪቱ ለሚታየው የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች መጓተት፣ የጥራት ጉድለት፣ ከተያዘላቸው በጀት ውጭ ተጨማሪ በጀት መጠየቅ አንዱ ምክንያት ይሄው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር እንደሆነም እየተጠቆመ ነው።

የኢትዮጵያ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ደረጃ ከዓለም የፕሮጀክት ማኔጅመንት አምስት ደረጃዎች አኳያ ሲታይ ሀገሪቱ አንደኛ እና ሁለተኛ መካከል እንደምትገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግሥት ይህን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር በመፍታት ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማድረግ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። በአስር ዓመቱ መሪ እቅድ የፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅምን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ 80 በመቶ ላይ ለማድረስም ታቅዷል።

በኮንስትራክሽን ዘርፉ ካሉት ችግሮች አንዱና ቁልፉ ችግር እንደሆነ የሚገለጸው ብቁና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ተወዳዳሪ ባለሙያ እጥረት ነው። በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ፕሮጀክቶች የሚመሩ/ማኔጅ/ የሚያደርጉ ባለሙያዎች ከቻይና ከመሳሰሉት ሀገራት ስለሚመጡ ይህም ሀገሪቱ በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እያሳጣት መሆኑ እየተገለጸ ነው። የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት የሚመራበት መንገድ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ጥናቶችን እያጣቀሱ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

በመሆኑም ብቁና ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት ያላቸው የፕሮጀክት ማናጀሮችን ማፍራት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ታሞኖበታል። ይህን በማድረግ ፕሮጀክቶች ለተፈለገው ዓላማ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲደርሱ ማድረግ ላይ መሰራት ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ይህን ችግር የሚፈታ ዓለም አቀፍ ሥልጠናና ሰርተፊኬት መስጠት ወደ የሚያስችለው ሥራ ገብቷል።

ለዚህም በዓለም አሉ ከሚባሉት እና በፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ ሥልጠና ከሚሰጡት ተቋማት አንዱ የሆነው አንጋፋው ከአሜሪካ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያው ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የማሰልጠን እውቅና ተሰጥቶታል። ከሰሞኑም ከኦሮሚያ ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን፣ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን፣ ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተውጣጡ የፕሮጀክት ባለሙያዎችን ጨምሮ 43 ያህል ለሚሆኑ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለሙያዎች ለስድስት ቀናት የቆየ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

ኢንስቲትዩቱ ከአሜሪካው ፒኤምአይ የሥልጠና ሞጁሎችን በመግዛት ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን፣ ለሰለጠኑ ባለሙያዎችም ሞዴል ፈተናዎችን ያዘጋጃል። ባለሙያዎቹም ዋናውንና ዓለም አቀፍ ፈተናውን በቀጥታ/በኦንላይን/ በፒኤምአይ በኩል ይወስዳሉ።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር አፈወርቅ ንጉሴ የዚህ ሥልጠና ተሳታፊ ናቸው። በኮንስትራክሽን ዘርፉ ከአስር ዓመት በላይ ልምድ እንዳላቸው የሚናገሩት ኢንጂነሩ፣ በዚህ ስልጠና ያገኙት እውቀት ከወቅቱ እና ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የሚዛመድ እና የሚጣጣም መሆኑን ይገልጻሉ። አሁን ላይ በሀገሪቱ ፕሮጀክት እየተመራ ያለበትን ሁኔታ በመቀየር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ የሚመራበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ሥልጠናው በሀገሪቱ መስጠት መጀመሩ ትልቅ ለውጥ ነው። እስካሁን ባለው ሂደት ይህን ሥልጠና ለመውሰድ ባለሙያዎች ወደ ኬንያ፣ ዱባይ ወይም ደቡብ አፍሪካ መሄድ ይጠበቅባቸው ነበር። አሁን በሀገር ደረጃ የዚህ ሥልጠና መጀመር ብዙ ሥልጠናዎችን ለሌሎች ለመስጠት በር ይከፍታል። ሥልጠናው በትንሹ አንድ ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚደረግበት እንደነበር ጠቅሰው፣ ይህንን ከፍሎ ለመሠልጠን አንድ ባለሙያ ብዙ ተግዳሮት ሊያጋጥመው እንደሚችል፣ ሰርተፊኬቱንም ለማግኘት ሌላ ወጪ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል። ሥልጠናው በሀገር ውስጥ መካሄዱ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል።

ሥልጠናውን ሲከታተሉ የነበሩት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮንስትራክሽን ሴክተር ኃላፊ ሲቪል መሐንዲስ ኢንጂነር ሮቤል ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ሥልጠናው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ባለሙያዎችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። በመተባበርና በቡድን በመሥራት እንዲሁም ኃላፊነቶችን በመውሰድ ችግሮችን እየፈቱ ፕሮጀክቶችን መጨረስ እንደሚገባ ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል። ሥልጠናው በአሜሪካው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ በ2023 የወጣውን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ጭብጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በየጊዜው እያደገ እንደሚሄድ ጠቅሰው፣ ለኢንስቲትዩቱም ምስጋና አቅርበዋል።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለቴክኖሎጂ ብዙም ክፍት እንዳልነበረ አስታውሰው፣ አሁን ከኢኖቬሽን እና ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህም የግንባታ መረጃ ሞዴሊንግ (Building Information Modeling) ቴክኖሎጂን በአብነት ጠቅሰዋል። ይህም በጋራ በአንድ የግንባታ ሞዴል ላይ ለመሥራት እንደሚያስችል ተናግረዋል። ስትራክቸራል መሐንዲሱ፣ ኤሌክትሪካል መሐንዲሱ ሁሉም ተቀናጅተው በአንድ ሞዴል የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚፈጥርና ከፍተኛውን ቨርቹዋል ፕሮዳክት ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

ዲጂታል በሆነ መንገድ ኮምፒዩተር ላይ ፕሮጀክቱን ገንብተን ከጨረስን በኋላ ቁፋሮ የሚጀመርበት ነው ያሉት ኢንጂነር ሮቤል፣ በቅድሚያ ሞዴል ላይ መሥራቱ በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ጥፋት ያስቀራል፤ ይቀንሳል ይላሉ። ብዙ ጊዜም በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ፕሮጀክቶች በብክነት እና በአቅም ውስንነት እንደሚጠቁ ጠቁመው፣ ይሄንን ችግር ለመፍታት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ኮርፖሬሽንም ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምሮ ይህን ቢም ቴክኖሎጂ እያላመደ ነው ያሉት። ከ40 በላይ ባለሙያዎችም በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በኩል በቢም ቴክኖሎጂ ሰርቲፋይድ ሆነዋል። 3ዲ ቢም ብቻም ሳይሆን ፕላነሮች 4ዲ ቢም፣ ኮስት ኢንጂነሮች 5ዲ ቢም ላይ መሥራት የጀመሩ ሲሆን፣ በዚህም ብዙዎች ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

ኢንጂነር ሮቤል ቴክኖሎጂው ፕሮጀክቶችን በገንዘብም፣ በጥራትም፣ በጊዜም በኩል ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጨረስ እና ከሌሎች በርካታ ጉዳዮች አንፃርም ጠቀሜታው የጎላ ነው ይላሉ። እሳቸውም ዱባይ በነበሩበት ወቅት ያስተዋሉትን ዋቢ በማድረግ ሲያብራሩም፣ በዱባይ አንድ አማካሪ ቢምን ተግባራዊ ካላደረገ ከዱባይ ማዘጋጃ ቤት የሥራ ፍቃድ እንደማያገኝም አስረድተዋል። ተቋራጩም በዚያ ልክ ካልሰራ ከዱባይ አስተዳደር ጋር መሥራት አይችልም ሲሉም አሰራሩ አስገዳጅ መሆኑን ተናግረዋል። ይህንንም ኮንትራክተርም አማካሪ መሐንዲሱም በመቆጣጠር ተግባራዊ እንደሚደርጉም ኢንጂነሩ ገልጸዋል። እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠናም በማኔጅመንት ቡድኑ ላይ ያለውን ፈላጭ ቆራጭ የሆነ አሰራር ወደ መተባበር እና የጋራ አቅም ወደ መፍጠር እንደሚቀይረውም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለሙያ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅአለ፣ ይህን ሥልጠና ቀደም ሲል መውሰዳቸውን ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፍ ፈተናውን ካለፉት የመጀመሪያዎቹ ባለሙያዎች መካከል መሆናቸውን ይገልጸሉ። የፕሮጀክት ማኔጅመንት አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ለውጥ ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩት ኢንጂነሩ፣ ራሱን በሲስተም ወደ መምራት እያሸጋገረ መሆኑን ነው የገለጹት። የሀገሪቱንም ፕሮጀክቶች በሲስተም መምራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና በመሠረታዊነት ሀገር የምታቅዳቸው ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆኑ በሲስተም መመራት የሚችሉበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ፕሮጀክት ማኔጅመንት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጥ ሰርተፊኬት ሲሆን፣ የትም ሀገር ለመሥራት የሚያስችል ነው። ሥልጠናው ፕሮጀክቶችን ካሉባቸው ችግሮች ለማውጣት አቅም ይፈጥራል።

አንድ ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲሆን ተጨባጭ የስኬት አካላት ከሚባሉት አንዱ የአንድ ተቋም እና የአንድ ባለሙያ የፕሮጀክት ማኔጅመንት የእድገት ደረጃ (Maturity level) በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስት ደረጃዎች አላቸው። የሀገሪቱ የፕሮጀክት ማኔጅመንት የእውቀት አካላት ሲታዩ በጥቂቱ ብቻ ደረጃ ሁለት ላይ ነን ሲሉም የሚገልጹት ኢንጂነር ውብሸት፤ አብዛኛዎቹ ግን ደረጃ አንድ ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል። ይህም ከ100 ሲቆጠር ከ10 እስከ 35 አካባቢ ባለው ውስጥ ብቻ እየመራን /ማኔጅ እያደረግን/ ነው ብለዋል።

ይህም እንደ አንድ ችግር ታይቶ በ30 ዓመቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታ እና በ10 ዓመቱ የስትራቴጂክ ፕላን ከተለዩት ውስጥ የሀገሪቱን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ብስለት ደረጃ አሁን ካለበት ከአንድ እና ሁለት ወደ አራት ወይም ከ60 እስከ 80 ባለው ደረጃ ውስጥ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ይሄንን ለመምራትም ባለሙያዎች፣ ድርጅቶች፣ አማካሪዎች፣ እንዲሁም ኮንትራክተሮች የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሲስተሙን እንዲያውቁና ከዓለም አቀፉ ስታንዳርድ ጋር የተቀራረበ እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ እና በዚህም መምራትና ማስተዳደር እንዲችሉ ይህ ሰርተፊኬሽን አንዱ ግብዓት ይሆናል። መንግሥትም ለዚህ ትኩረት በመስጠት የውጭ ምንዛሪ መድቦ ሥልጠናውን እየሰጠ ነው። እስካሁንም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ከ300 በላይ ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ ተደርጓል፤ አሁን ግን ኢንስቲትዩቱ ራሱ ሥልጠናዎቹን እንዲሰጥ ፍቃድ ተሰጥቶታል። ይህ ሥልጠና ብዙ ወጪ በመቀነስ በራሳችን በሰፊው ለማሰልጠን የተዘጋጀንበት የሥልጠናው የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የግንባታ መረጃዎች ሞዴሊንግ አሰልጣኝ እና የፕሮጀክት ማኔጅመንት አሰልጣኝ ወይዘሮ ቅድስት ማሞ እንዳብራሩት፤ በወቅቱ ተጠናቀው ተገቢውን አገልግሎት ተደራሽ እያደረጉ ያሉት ፕሮጀክቶች ውስን ናቸው። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪያችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲቀረፉ ዘርፉን ተወዳዳሪ ማድረግ ይቻላል ያሉት ወይዘሮ ቅድስት፤ ኢንስቲትዩቱም ኢንዱስትሪው ብቃት ባለው የሀገር ውስጥ ባለሙያ እንዲመራ ለማገዝ እና ፕሮጀክቶች እንዴት መመራት እንደሚገባቸው በማስመልከት ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቅርቡም ኢንስቲትዩቱ በአሜሪካ ከሚገኘው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ፍቃድ ያለው የሥልጠና አቅራቢ መሆኑን አሳውቀዋል። ከሰሞኑ ለፕሮጀክት ማኔጅመንት ባለሙያዎች ሰርተፊኬሽን ላይ ያተኮረ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንስቲትዩቱ እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም በተቋሙ በተገኘው ፍቃድ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሥልጠና አንድ ባለሙያ ምን ምን ነገሮችን ማወቅ እንዳለበት በፈተና እንደሚለይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰርቲፋይድ ሲሆንም ባለሙያው የሚመዘነው ፕሮጀክትን ለመምራት ባለው ክህሎት እና እውቀት ነው ብለዋል። በእዚህ ሂደት ያለፉ ባለሙያዎች በተሻለ ደረጃ ፕሮጀክቶች ማስተዳደር እንደሚችሉም አስታውቀዋል። በሌላ በኩልም የፕሮጀክት አፈጻጸምን በማሻሻል ወደላቀ ደረጃ መሄድ ያስችላል ብለዋል።

ወይዘሮ ቅድስት እንደተናገሩት፤ በኢንስቲትዩቱ በኩል በሚሰጠው ሥልጠና ፕሮፌሽናሎቹ ወደ ተሻለ ደረጃ ሲያድጉ ከዩኒቨርሲቲ ለሚወጡት እንዲሁም ከታች ለሚመጡት የሥራ እድል እየፈጠረ ይሄዳል። ይህም የኮንስትራክሽን ዘርፉን በማሳደግና ዓለም አቀፍ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር ከማስቻሉም በላይ፣ የሀገሪቱን የግንባታ ደረጃ ለማሳደግ ያግዛል። በኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ዘንድ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች እንዲሰማሩ ያስችላል። ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሰማሩ ባለሙያዎችም ብቃት ያላቸው ይሆናሉ።

ሥልጠናውን ወስደው ሰርቲፋይድ የተደረጉ ባለሙያዎች ከሀገር ውስጥ አልፎም ወደ ውጭ ሄደው መሥራት የሚችሉበትን አቅም ያገኛሉ። ወደ ውጭ ሲሄዱም በተመሳሳይ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ደረጃ መቀጠር ይችላሉ። በዚህም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ይቻላል።

በሀገሪቱ እንደሚታየው ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ የሚገኙት ቻይናዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል። ከዚህ ቀደም የውጭ ድርጅቶች የሚይዙት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በየሰፈሩ የሚገኙ ግንባታዎችን መያዝ የጀመሩበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ። ይህም የሀገሪቱ የፕሮጀክት አስተዳደር /ማኔጀመንት/ ተወዳዳሪነት ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል። የዚሀ ዓይነት ሥልጠናዎች በሚሰጡበት ጊዜም ባለሙያው ብቃት ኖሮት በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ የሚሆንበት እድል ይፈጠራል ብለዋል።

ሥልጠናው ከውጭ አምጥተን በዶላር የምንከፍላቸውን ባለሙያዎች ወይም ኮንትራክተሮችን በሀገር ውስጥ ኮንትራክተር እና ባለሙያዎች ለመተካት የሚያስችል ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ መንግሥትም ትኩረት አድርጎ የሚሰራው በዚህ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሥልጠናውን በሀገሪቱ አሉ የሚባሉት አንጋፋ ተቋራጮች እና አማካሪዎች እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም አቅም ያለው ኮንትራክተር እና ኮንሰልታንት ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል። አንጋፋ ባለሙያዎች ያካበቱትን ልምድ እና ክህሎት ይዘው በሥልጠናው በመታገዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመሥራት እድል እንደሚያገኙም ገልጸዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You